ከከንፈር መጠጣ ወደ ሁነኛ ካሳ (ከንግሥተ ሳባ)

ከንግሥተ ሳባ 
ሓምሌ 4 2012 ዓ ም

በቅድሚያ ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳኝ በየጊዜው በሚደርሰው የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመት ጋር በተገናኘ የሚደረገው አፀፋ ከከንፈር መጠጣና የሕሊና ፀሎት በዘለለ ወደሚቀጥለው ደረጃ ሽግግር እንዲደረግ ሃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡

በሰሞኑ እና ባለፈው በጥቅምት በተደረገው እጅግ አሰቃቂ እና አስነዋሪ ወንጀሎች ሕዝብ መሪር ሀዘኑን በመግለፅ ላይ ይገኛል፡፡ መንግሥትም ከበፊት ለስለስ ያለ ባህሪው ለየት ባለ መልኩ ፈጠን እና ቆፍጠን በማለት በቅርበትም ሆነ በርቀት ያሉ ተኳሽም ሆነ አስተኳሽም ለመያዝ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚህ ፈታኝ ሃገራዊ ወቅት ለዚህ ለደረስንበት ሁኔታ ጥፋትን እና ድክመትን ማደላደል ጥቅም የለውም፡፡ መንግሥትም፤ ተቃዋሚዎችም፤ ሌሎችም የሚመለከታቸው ሁሉ የሚወቀሱበትም የሚወደሱበትም ሰዓት ይመጣል፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡

በሰሞኑ በተካሄደው እንዲሁም በተለይ ባለፈው ጥቅምት አሰቃቂ እና ኢሰብአዊ ወንጀል ላይ የፀጥታ አካላት በተለይ የክልል ፖሊሶች ከዝምታ አንስቶ እስከ ወገናዊነት፤ ተባባሪነት እና አስተባባሪነት እንደተሳተፉ በግልፅ ህዝብም ታዝቧል፤ መንግሥትም አረጋግጧል፡፡ ይህ ማለት በወንጀል ድርጊቱ ግለሰቦች፤ ቡድኖችና የመንግሥት አካላትም መሳተፋቸው በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ይህ በፅኑ የተረጋገጠ እና ፀሐይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት መንግሥት የወሰዳቸውና እየወሰዳቸው ያሉት ተግባራት በግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ እንጂ በራሱ አካላት ላይ በግልጽ እየታየ አልነበረም፡፡ ይህ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው የሕግ መጣሱ መቀጠልና መሸርሸር አንዱ አካል በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ሊኮነን እና በፍጥነት ሊታረም ግድ ይላል፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት እየሰማናቸው እና እያየናቸው ያሉት ውሳኔዎች ትንሽ ተስፋን የሚሰጡ ናቸውና መንግሥት አበክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ለዜጎች የሚሰጠውን የደህንነት ህልውና በተደጋጋሚ ጊዜ ዋስትና ባለመስጠቱ እንዲሁም በራሱ መዋቅር ውስጥ ያሉ ቡድኖችና ግለሰቦች በወንጀል በቀጥታ ሲሳተፉ ለተደረጉት ጥፋቶች አግባብ ያለው ካሳ ሲያደርግ አይታይም፤አድርጎም ከሆነ በግልጽ አይታወቅም፡፡ ይህ በፍፁም መለወጥ ያለበት አስቸኳይ ጉዳይ ነው፡፡

ዜጎች ህልውናቸውን የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ እንዲያስከብሩ እና እንዲያረጋግጡ በሕግ መክሰስና ፍርድ ቤት ማቅረብ መጀመር አለባቸው፡፡ የሕግ የበላይነት ለሕግ አክባሪውም ሆነ ለአስከባሪው ወገን እኩል መሆን አለበት፡፡ በዚህም የተጎዱ ወገኖች፤ ወንጀልን በመከላከል ላይ የተሳተፉ የመንግሥት እና የክልል አካላትን ጨምሮ፤ አግባብ ያለው እና ተመጣጣኝ ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡ ከእንግዲህ ከከንፈር መጠጣና የህሊና ፀሎት ወደ ካሳ ክፍያ መዘዋወር በግድ ይላል፡፡

የሚቀጥለው ጥያቄ በዚህ ካሳ ክፍያ መንገድ ካሳውን ማን ይክፈል ይሆናል፡፡ የመጀመሪያውን ኃላፊነት መውሰድ ያለበት ድርጊቱ የተከሰተበት ክልል መሆን አለበት፡፡ ይህ አካሄድ ክልሎች በራሳቸው ስር ላለው መስተዳድር ሙሉ የፀጥታ ኃላፊነትና የነቃ እርምጃ እንዲወስዱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስገድዳቸዋል፡፡ የግለሰቦችን ሕይወት መጠበቅ እንዲሁም ሃብትና ንብረትን መተካት፤ መልሶ መገንባት እና ማቋቋም እንዲሁም ለተጎዱ ቤተሰቦች ካሳ መክፈል አደጋው የተከሰተበት ክልል ኃላፊነት መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ በተለይ የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን ነጥሎ የማጥቃት ድርጊት ክልሎችን ከፍተኛ ዋጋ ስለሚያስከፍል ጉዳዩን በጥብቅ እንዲመለከቱት እና እንዲከታተሉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያስገድዳል፡፡  

በዚህ ጉዳይ የፌደራል መንግስቱ የዚህ ወንጀሎች ተጠያቂ በመሆን የካሳው ተባባሪ ባለዕዳ መሆን  አለበት፡፡ 

ይህንን በተመለከተ በሕግ ዙሪያ የሚሰሩ በሃገርም ሆነ ከሃገር ውጪ ያሉ የፍትህ እና የሕግ ባለሙያዎች ይህንን ሃሳብ ወደፊት እንዲወስዱት ይገባል፡፡

One Response to "ከከንፈር መጠጣ ወደ ሁነኛ ካሳ (ከንግሥተ ሳባ)"

Leave a Reply

Your email address will not be published.