- Advertisement -spot_img
Wednesday, August 17, 2022
Home Blog

በትግራይ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ17 ሺህ ብር በላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

0
 ኩንታል ጤፍ

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀረው ጦርነት በተቀሰቀሰባትና መሰረተ ልማቶች በተቋረጡባት ትግራይ ውስጥ አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 17 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በክልሉ ውስጥ በእርዳታ አቅርቦት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ግለሰቦችም አንድ ኩንታል ጤፍ ከ15 እስከ 17 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሆነ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሠራተኞች እንዳሉት ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉት ባለሥልጣናት በጤፍ የመሸጫ ዋጋ ላይ ተመን ማውጣታቸው የዋጋ ጭማሪውን እንዳባባሰው ተናግረዋል።

የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ዳንኤል በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጾ፤ በተለይ የጤፍ ዋጋ ከሕብረተሰቡ አቅም በላይ ሆኗል ብሏል። ለቢቢሲ አስተያየተቸውን የሰጡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የግረሰ ሰናይ ድርጅቶች ሠራተኞች እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር በክልሉ የተጣለው የመሸጫ ዋጋ ተመን እጥረት እና የዋጋ መናርን ማስከተሉን ይናገራሉ።

“ጤፍ እጅግ በጣም ተወዷል። ነጋዴዎች በማኅበረሰቡ ላይ ጨክነዋል። የሕብረተሰቡን ሁኔታ ያላገናዘበ ተግባር ነው እየፈጸሙ ያሉት። ከባድ ሁኔታ ነው እያሳለፍን ያለነው። ብዙዎች እንጀራ መመገብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” በማለት ዳንኤል ያለውን ሁኔታ አስረድቷል።

ሌላኛው በርኽ የተባለ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ “ረሃብና ድርቅ አለ። ሕዝቡ ያለውን ተካፍሎ ለመኖር እየሞከረ ነው። ሰዎች ከትግራይ ውጪ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እንደምንም ብሎ የሚደርሳቸው ገንዘብ ምንም ነገር ሊገዙበት አልቻሉም። በተለይም የጤፍ ዋጋ የሚቀመስ አይደለም” ብሏል። በርኽ እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ ያለው የጤፍ ዋጋብቻ ሳይሆን የስንዴና የስንዴ ዱቄት ዋጋም ከሕብረተሰቡ የመግዛትአቅም ጋር በፍጹም የሚመጣጠን አይደለም።

“አንድ ሰው ሁለት እና ሦስት ሺህ ብር ከቤተሰብ ተልኮለት 25 ኪሎ ጤፍ እንኳን መግዛት የማይችልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። ሩብ ኩንታል ለመግዛት ከ4 ሺህ ብር በላይ ሊኖርህ ይገባል” ሲል ጨምሮ ገልጿል። በመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት በርኽ እና ዳንኤል እንደሚሉት በክልሉ የጤፍ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት የሆነው እጥረት በመኖሩ ሳይሆን፣ ነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ዋጋውን በማናራቸው ነው። “ነጋዴዎች የያዙትን ጤፍ ደብቀው በመያዝ፤ የለም በማለት እና በደላላዎች በኩል እያወጡ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ሕብረተሰቡን እየጎዱ ይገኛሉ። ባለሥልጣናት ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ቢገልጹም እስከ ዛሬ ግን የመጣ ለውጥ የለም” ብሏል በርኽ።

ዳንኤል በበኩሉ “ነጋዴዎች ‘እኛ በምንወስነው ዋጋ ነው የምንሸጠው’ እያሉ ስለሆነ ነው ችግሩ የተባባሰው” ሲል ያስረዳል። በአሁኑ ጊዜ በኩንታል ከ16 እስከ 17 ሺህ ብር በመክፈል የጤፍ እንጀራ መመገብ ያልቻሉ ሰዎች ከእርዳታ የሚገኘውን ስንዴ እና እንደ አቅማቸው ከሚገዙት ማሽላ እንጀራ ለማዘጋጀት ተገደዋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ነጋዴዎች ይፋዊ ባልሆነ መንገድ አዋሳኝ ከሆኑ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ነው ጤፍ ወደ ትግራይ ክልል የሚያስገቡት።

በቅርብ ቀናት የተወሰነ ጤፍ መግባቱን ተከትሎ በዋጋ ላይ መሻሻል የታየ ቢሆንም፤ ብዙ ሳይቆይ ወደነበረበት የማይቀመስ ዋጋ መመለሱን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ለመገንዘብ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ከጥቂት ቀናት በፊት የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ከመቀለ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል በርካቶች የጤፍ ዋጋ ጉዳይ በማንሳት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ድምጺ ወያነ ባስተላለፈው ዘገባ ከደብረጽዮን (ዶ/ር) ጋር ከተወያዩት ነዋሪዎች መካከል አንዲት እናት ለጤፍ ዋጋ መናር አመራሮችን እና ነጋዴዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

በዚሁ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ መሪ፤ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን እና ሕጋዊ ያልሆነ የንግድ እንቅስቃሴ መበራከቱን አረጋግጠዋል። “ሕጋዊ ያልሆኑ ነጋዴዎች ጥቂቶች ናቸው። በዝርዝር ይዘናቸዋል። ሕዝቡ ከነገረን ብቻ ሳይሆን ራሳችንም አጣርተናል። እርምጃ ወደ መውሰድም እንገባለን። መረጃ ስናገኝ ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ እናደርጋለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጤፍን ጨምሮ የሌሎች ሸቀጦች መቀለ ከደረሱ በኋላ ወደ ተቀረው የክልሉ ክፍል የሚከፋፈል መሆኑን በመጥቀስ፣ በተቀረው የትግራይ ክፍል የጤፍ ዋጋ መቀለ ከሚሸጠው በላይ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዳሉ። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የግረሰ ሰናይ ድርጅት ሠራተኞች ገንዘብ ያለው ጤፍ ልግዛ ቢል እንኳ በቀላሉ ማግኘት ሰለማይቻል በደላላ በኩል ማፈላለግ ግድ ነው። ይህም የአንድ ኩንታል ዋጋን ከ20 ሺህ ብር በላይ ያሻግረዋል ይላሉ።

በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ እንደ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ባንክን የመሳሰሉ መሠረታዊ አግልግሎቶች ተቋርጠው በሚገኙባት ትግራይ፤ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ6 አስከ 8 ሺህ ብር ሲሸጥ ነበር። ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ ድርጅቶች በክልሉ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲሉ ተደጋጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲያወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

የረድኤት ድርጅቶች ባለፉት ወራት እንደ ሰንዴ፣ በቆሎ እና አልሚ ምግቦችን ወደ ትግራይ ሲያደርሱ መቆየታቸው ይታወሳል። ምንም እንኳ ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት አይስማማ እንጂ ከሳምንታት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ አንዣቦ የነበረው የረሃብ አደጋ ስጋት ተቀልብሷል ብሎ ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊ ኤድሪያን ቫንዳክናብ ሐምሌ 08/2014 ዓ.ም. ለቢቢሲእንደተናገሩት፤ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ መቻሉን ገልጸው ነበር። የህወሓት አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ የረሃብ አደጋ ስጋቱ ተቀልብሷል ማለታቸውን ተችተውታል። ህወሓት ወደ ክልሉ የሚገባው እርዳታ መቆራረጥ እንደሚያጋጥመው እንዲሁም ያለውን እርዳታ ለተረጂዎች ለማድረስ የነዳጅ እጥረት መኖሩን ያመለክታሉ።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

«የውስጥ ችግራችን ለውጭ ተጋላጭነታችን ግብዓት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል» አቶ ሌንጮ ለታ – የኦነግ መስራች

0
አቶ ሌንጮ ለታ
አቶ ሌንጮ ለታ

ጀማል ሰይድ  
ቦርከና 

የውስጥ ችግር በሰፋ ቁጥር ለጠላቶች ሰፊ ዕድል ስለሚፈጥር ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ፖለቲከኛው አቶ ሌንጮ ለታ አመለከቱ።

አቶ ሌንጮ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ ሰሞኑን የአልሸባብ በተሳሳተ ስሌት ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሯ ምክንያት ራሷን መከላከል እንደማትችል በማሰብ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ብዙ ታጣቂዎችና ብዙ ጦር መሣሪያ በመያዝ ድንበር ጥሶ መግባቱ እንደ ቀላል የሚታይ ክስተት አይደለም።

ሱዳንም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተደረገውን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ለመግባት ሞክራለች ያሉት አቶ ሌንጮ፤ ከትንኮሳዎች ጀርባ ሌላ ፍላጎት መኖሩ እንዳለ ሆኖ የውስጣችን ችግር አስተዋጽኦ ማድረጉ አያጠያይቅም ብለዋል።

ያም ሆኖ ግን በተለይ በአልሸባብ ላይ የተወሰደው እርምጃ ቡድኑ የሃይማኖት አክራሪነትን ለማስፋትና ሌላውን በመጨፍለቅ ታላቋ ሶማሊያን ለመገንባት የሚደረገውን የቀን ቅዠቱን እንቅስቃሴ እርቃኑን ያስቀረና በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያን ጥንካሬ ያስመሰከረ አኩሪ ገድል ነው ያሉት አቶ ሌንጮ፣ ለዘላቂ ድል ግን ብሎም ጠላቶቻችንን ማፈናፈኛ ለማሳጣት ወደ ውስጥ በደንብ መመልከት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ዓለም እየተስተዋለ ያለው የሰላም እጦት አሳሳቢ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ በፊት የነበረው በጥርጣሬ የመተያየት ችግር እየሰፋ መጥቷል ያሉት አቶ ሌንጮ፣ በሱዳንም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የጸጥታ ችግር እያለ እንደገና በድንበር ሰበብ መጣላት የዚሁ አንዱ ማሳያ መሆኑንና መዘዙ ከባድ እንደሆነም አመላክተዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ግብጽና ሱዳን ሌሎች አገራት ኢትዮጵያን በጥርጣሬ እንዲያዩ አልፎም ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ በውስጥ ጉዳይዋ የሚያሴሩት የሴራ እንቅስቃሴ ቀላል እንዳልሆነ የጠቆሙት ፖለቲከኛው፣ ግድቡ ብዙ ዛቻዎችን በማለፍ ለፍሬ መብቃቱ የሕዝቡ አንድነት ውጤት ነው ብለዋል። በመሆኑም ከሁሉም በላይ የውስጥ አንድነት ማጠናከር ተቀዳሚ ተግባር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከሁሉም በላይ ግን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ በግድቡ ላይ የሚታቀድ ማንኛውም ሴራ ከኢትዮጵያ ይልቅ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት በእጅጉ ስለሚጎዳ ከዚህ በኋላ የግድቡ ደህንነት የጋራ ጉዳይ መሆኑ ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሌንጮ ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ በመልካ ምድር አቀማመጧ በቀይ ባህር አካባቢ ስለምትገኝ ጠላቶቿ ከግብጽና ከሱዳን በላይ ነው። የግድቡ ግንባታ ቢጠናቀቅ እንኳ የጠላቶች ሴራ አይቆምም። በእርግጥ ከዚህ በኋላ ለመኖር ሲሉ ለህዳሴ ግድብ ደህንነት የሚጨነቁ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ናቸው። ሆኖም አቅጣጫ በመቀየር ሴራዎችን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። የሕዝቡ አንድነት ከተጠናከረ የጠላቶች ሴራ ከንቱ ሆኖ ይቀራል።

የጠላቶችን ትልም ለማምከን ብሎም ኢትዮጵያን የልማትና የዴሞክራሲ ተምሳሌት ለማድረግ ብቸኛው አማራጭ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን ማስፈን መሆኑን ያላቸውን እምነት የተናገሩት አቶ ሌንጮ፣ ለእሳቸው ሌሎች አማራጮች አገሪቱን ወደ ለየለት ቀውስ የሚያመሩ ናቸው። ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ በጥቂት ግለሰቦች የሚወሰን ጉዳይ በመሆኑ የትኛው የመንግሥት አወቃቀር እንደሚያዋጣ ለሕዝብ ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ያልሆነው ሕብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም አገሪቱ ዛሬ ለገባችበት ችግር አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው ያሉት አቶ ሌንጮ፣ ከዚህ አንጻር የበላይነትን ለምደው እኩልነት የማይጥማቸው አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው ብለዋል። ሆኖም ብዙኃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ማገልገል ከተቻለ ቀሪውን በሂደት መቅረፍ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተለያዩ ሹመቶችን ሰጥተዋል። 

0
Ethiopian News _ Amhara region

በዚህም መሠረት 

1. አቶ ደጀኔ ልመንህ በዛብህ

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር 

2. ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው ተሰማ ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ

3. ረ/ኮሚሽነር ሠይድ አህመድ ሃምዛ ም/ኮሚሽነርና የአስተዳደር ልማት ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ

4. ረ/ኮሚሽነር እንዬው ዘዉዴ ከበደ ም/ኮሚሽነርና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ሆነው እንዲሰሩ ተሹመዋል።

መረጃው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ነው ፡፡

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ቦርከና እለታዊ ዜና ነሃሴ 10 , 2014 ዓ.ም.

0

ቦርከና

ቦርከና እለታዊ ዜና ነሃሴ 10 , 2014 ዓ.ም.

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ፡፡
__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

በኢትዮጵያ የተራቡ ዜጎችን ለመርዳት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ከዩክሬን የሸመተውን ስንዴ የጫነ መርከብ ከኦዴሳ ጉዞ ጀመረ

0
ስንዴ የጫነ መርከብ

ጀማል ሰይድ  
ቦርከና 

በኢትዮጵያ የተራቡ ዜጎችን ለመርዳት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ከዩክሬን የሸመተውን ስንዴ የጫነ መርከብ ከኦዴሳ ጉዞ ጀመረ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተከራየው እና የሊባኖስ ሰንደቅ የሚያውለበልበው ብሬቭ ኮማንደር የተባለ መርከብ ጉዞ መጀመሩ የተገለጸው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩን ባጣጣሉበት በትላንትናው ዕለት ነው። 

ከኦዴሳ አጠገብ ከሚገኘው ወደብ የተነሳው መርከብ በቱርክ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት ዩክሬን እና ሩሲያ ሥምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ እህል ለመጫን ወደ ቦታው ያቀና የመጀመሪያ መርከብ ነው። “ይኸ መርከብ በኢትዮጵያ ለተራቡ ሰዎች 23,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ በጅቡቲ ወደብ በኩል ያጓጉዛል” ሲሉ በዩክሬን የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ምክትል ዳይሬክተር ማርያነ ዋርድ ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትላንት እሁድ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ሲመረቅ ባደረጉት ንግግር ግን መንግሥታቸው ከዩክሬን ስንዴ እንዳልሸመተ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ በድርቅ ልትመታ ነው። ድርቅ ኢትዮጵያን ያጠቃታል የሚል ዜና በስፋት ይሰማል። ኢትዮጵያ ስንዴ ገዝታ፤ ስንዴዋ በጀልባ ተጭኗል። የሚል ዜናም ተሰምቷል” ያሉት ዐቢይ “ኢትዮጵያ ስንዴም አልገዛችም፤ ኢትዮጵያ ድርቅም አይመታትም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ዐቢይ በንግግራቸው ሁለቱን ጉዳዮች “ቀድሞ የማጥላላት ዘመቻ አካል” አድርገው አቅርበዋል። ዐቢይ በድሬዳዋ ባደረጉት ንግግር “ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን እያሉ ስንዴ ያስገባሉ፤ ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን እያሉ በድርቅ ተመቱ ለማለት እንዲያመቻቸው ነው” በማለት በስም ያልጠቀሷቸውን ወገኖች ከሰዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ይመረትበታል ያሉትን 127 ሺሕ ሔክታር ኩታ ገጠም የእርሻ ማሳ ጎብኝተው ነበር። ከጉብኝታቸው በኋላ በድሬዳዋ ከተማ ባደረጉት ንግግር ዐቢይ “ስንዴ ከጥቂት ወራት በኋላ ድርቅ ገባ እየተባለም ኤክስፖርት አድርገን ጠላት እናሳፍራለን። ኢትዮጵያውያንን እናስደስታለን” ሲሉ ተናግረዋል። 

ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የተከሰተው ድርቅ 19.4 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል። በድርጅቱ መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ 18.6 ሚሊዮን ሰዎች ብርቱ የምግብ ዋስትና እጦት እና እየጨመረ የሚሔድ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ገጥሟቸዋል። ይኸው ድርቅ በኢትዮጵያ ብቻ 7.4 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ለኃይለኛ የምግብ እጦት ዳርጓል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያ ድርቅም አይመታትም” ቢሉም በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተውን በንግግራቸው መልሰው ጠቅሰዋል። “ከዓመት በፊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ችግር ሲያጋጥም ´የዓለም ሚዲያ በሙሉ ከፍተኛ ድርቅ ስለሚያጋጥም ይኸ ድርቅን ተገን ያደረገ ውጊያ ነው እና አቁሙ` እንባል ነበር” ያሉት ዐቢይ “በወቅቱ እኛ ድርቅ በሰሜን ያገራችን ክፍል የለም፤ አይኖርም ብንልም ሰሚ አልነበረንም” ሲሉ ተደምጠዋል።   ጠቅላይ ምኒስትሩ “በሰሜን ድርቅ ያጋጥማችኋል ብለው በስፋት ሲናገሩ የነበሩ ኃይሎች ሶማሌ እና ቦረና ሲጠቃ እንኳን ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ቀርቶ ከአምስት ስድስት ዓመት በፊት፤ ከአስር ዓመት በፊት ያደረጉትን ድጋፍ ማድረግ አልቻሉም” ሲሉ ከሰዋል።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተና ማስፈፀሚያ መመሪያ ፀደቀ

0
የከፍተኛ ትምህርት

ጀማል ሰይድ  
ቦርከና  

የከፍተኛ ትምህርትን አገራዊ ቅድመ ምረቃ የመውጫ ፈተናን በአግባቡ ለመምራትና ለማስተዳደር የተዘጋጀው የከፍተኛ ትምህርት መውጫ ፈተና ማስፈፀሚያ መመሪያ ፀድቋል።

መመሪያው በፍትህ ሚኒስቴር ተመዝግቦ እና ፀድቆ ለትግበራም ይፉ ሆኗል። መመሪያው በመውጫ ፈተና ዝግጅት ሊካተቱ ስለሚገባቸው ሃገራዊ ዝቅተኛ የትምህርት ብቃት መመዘኛዎችን ፣ የሙያ ሥነምግባር ደምቦችን እና ተቋማት ሊከተሏቸው የሚገቡ  የአሠራር ስነ- ስርዓቶችን አካቷል ።

መመሪያው የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ሀገሪቱ የምትፈልገውን የሠለጠነ የሠው ሀይል ለማፍራት ከሚደረጉ ማስፈፀሚያ ስልቶች አንዱ  ነው። በመመሪያው ዝግጅት ሂደት ውስጥ በስርዓተ ትምህርት እና ፈተና ዝግጅት ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን፣የሙያ ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ግብአት ሰጥተውበታል ።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

አካባቢያዊ ምርጫን ማከናወን የሚያስችል ውይይት እየተካሄደ ነው  

0

ጀማል ሰይድ  
ቦርከና  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አካባቢያዊ ምርጫን ለማከናወን የሚያስችለውን ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ነው ።  

በኢትዮጵያ ለአምስተኛ ጊዜ በሚደረገው አካባቢያዊ ምርጫ ለሚደረገው ዝግጅት ቦርዱ ያስጠናውን ጥናት ተከትሎ ነው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎችም 160 የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ የሆኑበት ውይይት እየተካሄደ ያለው። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ አካባቢያዊ ምርጫ አስፈላጊቱ እጅግ ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል። 

አካባቢያዊ ምርጫን ለማከናወን እና ትክክለኛ ልምምድን ከአዳጊ ሀገራት ለመማር ውይይቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ምርጫውን በየክልሎቹ ለማስፈፀም ፣ የሚገጥሙ ችግሮች እና ሊኖሩ የሚችሉ የህግ ማሻሻያዎች ለውይይቱ ግብዓት እንዲሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል። 

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገው አካባቢያዊ ምርጫ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ወረዳ እና ዞን ድረስ ዜጎች ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚያዳብሩበት ነው  ብለዋል። በአካባቢያዊ ምርጫ እና አካባቢያዊ የመንግስት አስተዳደርን በተመለከተም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም ጥናት ማዕከል ጥናት በዶክተር ዘመላክ አየለ ቀርቧል። 

 በዚህ ወቅትም አካባያዊ ምርጫ ውክልናን ለማስፋት እና በፖለቲካ ሂደት ውስጥ ምህዳሩን ለማስፋት እና ውድድርን ለመፍጠር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚረዳ የሀገራትን ተሞክሮ በማቅረብ አስረድተዋል።

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ባልደራስ ፕሬዝዳንቱ እስክንድር ነጋ “የመታፈን አደጋ ደርሶባቸዋል” የሚል እምነት እንደሌለው አስታወቀ   

0
ባልደራስ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት


ጀማል ሰይድ
  
ቦርከና                                                                                                      

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 9/2014 በጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ በቅርቡ ከፓርቲው ፕሬዝዳንትነት መልቀቃቸውን ያሳወቁት አቶ እስክንድር ነጋን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል። 

የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኛው፤  የፓርቲው አመራሮች አቶ እስክንድር ስላሉበት ሁኔታ ከእርሳቸው በቀጥታ መረዳት ባይችሉም፤ “የመታፈን አደጋ ደርሶባቸዋል” የሚል እምነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል። 

“ባልደራስ እስክንድርን ከድቷል ወይስ እስክንድር ነው ባልደራስን የከዳው?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ በሰጡት ምላሽ፤ “እስክንድርን ሊከዳ የሚችል ፓርቲ አይኖረንም። የተሰበሰብነውም እስክንድር ብለን ነው” ብለዋል። “እስክንድርን ያህል የጽናት ተምሳሌት፤ ባለበት የፖለቲካ ጫና ምክንያት ከፖለቲካ ትግሉ ገሸሽ አለ ማለት፤ ፖለቲካው ላይ ያለው ተጽዕኖ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መረዳት [የሚያስችል ነው]” ሲሉም ተናግረዋል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።  

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ በደቡብ ክልል አደረጃጀት ጉዳይ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው

0
አቶ አገኘሁ ተሻገር የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው በተሾሙበት እለት በመንግስት መገናኛ ብዙሃን የተለቀቀ


ጀማል ሰይድ

ቦርከና

መደበኛው ጉባኤውን ከአንድ ወር በፊት ያደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ በደቡብ ክልል አደረጃጀት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 11፤ 2014 ለሚደረገው ለዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ እንደተደረገላቸው ነገሩኝ ያላቸውን ሁለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ጠቅሶ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘግቧል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ፤ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባውን በመጪው ረቡዕ እንደሚያካሂድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። አቶ ተረፈ ምክር ቤቱ “ከደቡብ ክልል ጋር ተያይዞ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ይኖራሉ” ሲሉ ስብሰባው የተጠራበትን ምክንያት ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል የሚገኙ አስር ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች፤ በሁለት የተለያዩ ክልሎች የመደራጀት ጥያቄያቸውን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 28፤ 2014 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት አስገብተዋል። ጥያቄዎቹን የያዙ ሰነዶች ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ “የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥያቄው ላይ ውይይት አካሄዶ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ወስኖ የሚያሳውቅ ይሆናል” ብለው ነበር።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ቦርከና እለታዊ ዜና ነሃሴ 7 , 2014 ዓ.ም.

0

ቦርከና

ቦርከና እለታዊ ዜና ነሃሴ 7 , 2014 ዓ.ም.

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ፡፡
__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena