ምርጫ ማለት ሂድት ነው፤ ሁነት አይደለም። የምርጫው ቀን የሚደረገው ድምጽ የመስጠት እንቅስቃሴ እና ድምጽ የመቁጠሩ ስራ የሂደቱ የመጨረሻዎቹ ክፍሎች እንጂ ፤ በራሳቸው ሙሉ በሙሉ የምርጫው ሂደት መለኪያዎች ሊሆኑ አይችሉም።
የምርጫ ቅስቀሳ እና የሚወዳደሩበትን የፓለቲካ ፋይዳ ለመራጭ ማሳወቅ የምርጫ ሂደቱ ዋነኛ አካል ነው ብሎ ማለት ይቻላል። በዚህ አንጻር የተስተዋለው ነገር ምንድን ነው? ትላንት ከትላንት ወዲያ ከሰማነው ብንነሳ የአረና ፓርቲ በቅስቀሳ ሂደት ላይ ድብደባ እንደደረሰበት ( ባለፈው ምርጫ አባል በጩቤ ተወግቶ ተገደለብን እንዳሉ አስታውሳለሁ) ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ዘገባ ሰምተናል። የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ አባላትም እንዲሁ ወከባ እንደደረሰባቸው ሰምተናል።
መኢአድስ ምን ሆነ? አመራሩ (ማሙሸት አማረ) የወሮበላ አፈና በሚመስል ሁኔታ ከመንገድ ታፍኖ እንደታሰረ እንኳን የታወቀው ከቀናት በኋላ ነው። ሌሎች ብዙ የመኢአድ አባላት በመላው ኢትዮጵያ የደረሰባቸውን ድብደባ እና ግድያ ጭምር ሰምተናል።
ትንሽ የማይባሉ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እንዲሁ ወከባ እስር እና እንግልት ደርሶባቸዋል።
የወራቶች እድሜ ወደ ኋላ መለስ ስንል ገና የምርጫው ቅስቀሳ ሳይጀመር ፤ የተቃዋሚ ፓርቲነቱን ይዞታውን ስሙን ተቀምቶ ለወያኔ የፖለቲካ ገረድ የተሰጠበት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲም አለ። እንደተቋም የምርጫ ቦርድን ሚና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ልብ ይሏል!
ይሄው ተቋም የስርዓቱ ራሱን የቻለ የማጥቂያ መሳሪያ እንጂ ፈጽሞ በገለልተኛነት ሂሳብ ሊያዝ የማይችል አካል እንደሆን አያሻማም። በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ገለልተኛነት ስለሚካሄደው ምርጫ ፍትሃዊነት እና ኢፍትሃዊነት በመለኪያነት ሊቀመጥ ሁሉ የሚችል እጂግ አስፈላጊ ግብዓት ነው ።
ኢህአዲግ እንደፓርቲ የፓርቲነት አቅሙን መሰረት አድርጎ ተወዳድሯል ማለትም አይቻልም። ለይስሙላ የተደረገውንም ነገር እንኳን በመንግስትነት አቅም ነው ያደረገው።
የድምጽ አሰጣጥ ስርዓት ሳይጀመር፤ ድምጽ ሳይቆጠር ፤ የምርጫው ውጤት ከወዲሁ ታውቋል። የውጭ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ መንግስት (ወያኔ እንደሆነ ልብ ይሏል!) ውጤቱን ጥርግርግ አድርጎ እንደሚወስድ (ላንድስላይድ) መተንበይ የቻሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል።
ምርጫው አንዳንዶች እንደሚገምቱት የተወሰነ ቁጥር ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪ ለፓለቲካ ዲኮሬሽንነት ፋይዳ ወደ ፓርላማ ይመልስ ይሆናል።
ከዚያ ውጭ ከዚህ ምርጫ እንደ ወያኔ ያሸነፈ የለም ከወንበርም ባሻገር!
የወያኔን ማንነት አሳይተንበታል የሚባለው ነገር እንደኔ እንደኔ ብዙም ትርጉም ያለው ነገር አይደለም። ከምርጫ ጋር በተያያዘ ከሆነ ፤ ቢያንስ ያለፉት ሁለት ምርጫዎች ያሳዮት ከበቂ በላይ ነው። ሙሉ በሙሉ የተሸነፈበትን ምርጫ እንዳሸናፊ ሲወስድ አይተናል፤ የባለፈን ደሞ በሙሉ “አሸናፊነት”ም ሂሳብ ሲወስድ አይተናል።
ሃገር ቤት ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በብዙ ወከባ መካከል ድካማቸው እና ምኞታቸው ክብርም፤ ምስጋናም ይገባዋል። መሬት ላይ ስንወርድ እና በውጤት ስንሰፍር ግን እንደ ከዚህ በፊቱ እነሱ በምርጫ ከተጠቀሙት የበለጠ ወያኔ ተጠቅሞበታል። እርግጥ ነው በምርጫ ባይወዳደሩ ኖሮ የፓርቲዎቹን ህጋዊ ሰውነት ወያኔ ከጥቅም ውጭ አድርጎ መተንፈስም እንዳይችሉ ያደርጋቸው ይችል ይሆን ነበር። ወያኔ ተቃዋሚዎች በምርጫ በመወዳደራቸው ቢጠቀምም ፤ አንወዳደርም ቢሉ ኖሮ ይጎዳል ማለት አይደለም። የፖለቲካ ገረድ ይቀጥር ነበር።
ለማጠቃለል። ምርጫው አልቋል። ነገር ውጤቱ በቁጥር ደረጃ በምንም መልኩ ቢቀርብም ፤ የውጤቱ መሰረታዊ ተፈጥሮ ከዚህ በፊቱ የተለየ ሊሆን አይችልም። ሰላማዊ ትግል የሚገባውን ህጋዊ ዋስትና እና ተቀባይነት ባላገኘበት ሁኔታ ፤ የምርጫ ውጤት በሚታወቅበት ሁኔታ ፤ ምርጫ እንዴት ትርጉም ይኖረዋል? ወያኔ በሰማላዊ ምርጫ ስልጣን ለህዝብ እንደማይመልስ እየታወቀ ፤ ምርጫ ምን ትርጉም ይኖረዋል? #Ethiopia #EthioElection2015
ከድሜጥሮስ ብርቁ