spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትኢህአዴግ ሆይ ነቄ ነን ተቀየስ! - ርዕዮት አለሙ- ከቃሊቲ እስርቤት

ኢህአዴግ ሆይ ነቄ ነን ተቀየስ! – ርዕዮት አለሙ- ከቃሊቲ እስርቤት

ሚያዚያ 14 ፤ 2007 ዓ ም
#EthioElection2015 #Ethiopia
ኢህአዴግ ሆይ ነቄ ነን ተቀየስ!

አራት ሆነን ወደምንኖርበት የአሁኑ የማግለያ ክፍል ከመግባቴ በፊት በርካታ እስረኞች በተለምዶ የአራድኛ ቃላት የሚባሉትን በመጠቀም ሲነጋገሩ የመስማት እድል ነበረኝ፡፡ ለርዕሴ የመረጥኳቸው ቃላትንም ያገኘሁት ከነሱው መሆኑን መግለፅ ይኖርብኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፤

አንዳንድ እስረኞች የሚፈልጉትን አንዳች ነገር ለማግኘት በጉልበታቸው ወይም ጤፍ በሚቆላ ምላሳቸው ይጠቀማሉ፡፡ ሀይልን በመጠቀም ያስገድዳሉ ወይም ያታልላሉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነቶቹ እስረኞች እንደለመዱት ለማድረግ ሲሞክሩ አንዳንዴ ደፋርና የማይታለሉ እስረኞች ላይ ይወድቃሉ፡፡ እናም ለማታለል ወይ ለማስገደድ የሞከረች ባለጌ የሚጠብቃት መልስ “ነቄ ነን እባክሽ! ተቀየሽ! ንኪው!”የሚል ይሆናል፡፡ እኛን ማታለልም ሆነ ማስፈራራት ስለማትችይ ይቅርብሽ፡፡ ዞርበይልን እንደማለት ነው፡፡

ኢህአዴግም እያደረጋቸው ያለው የማታለል ሙከራዎችና ተገቢ ያልሆኑ የሀይል እርምጃዎች ተመሳሳይ ምላሽ ሊያሰጡት እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ የዘንድሮውን ምርጫ ለማለፍ ከወትሮው በከፋ ሁኔታ እየሄደባቸው ያሉት እነዚህ ሁለት ጠማማ መንገዶች መጨረሻቸው አውዳሚ ነው፡፡ በመሆኑም “ኢህአዴግ ሆይ ነቄ ነን ተቀየስ!” በማለት እኛና ሀገራችንን ይዞ ወደጥፋት እያደረገ ያለውን ግስጋሴ መግታት ይገባል፡፡

ጠማማ መንገድ አንድ

የፈሪ ዱላውን የመዘዘው ኢህአዴግ

ኢህአዴግ የተቃዉሞ ድምፆችን በሰማበት አቅጣጫ ሁሉ ዱላውን ይዞ የሚሮጥና ያለሀሳብ የፈሪ ምቱን የሚያሳርፍ ደንባራ መሆኑን በተደጋጋሚ በተግባር አይተናል፡፡ በሰሜን አፍሪካ አመፅ ተቀሰቀሰ ሲባል ለአመፅ ምክንያት የሚሆኑ ድክመቶቹንና ጥፋቶቹን ከማስወገድ ይልቅ ነቅተው ሊያነቁብኝ ይችላሉ ብሎ የጠረጠረንን ጋዜጠኞችንና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ለእስር መዳረጉ ከቅርብ ጊዜ ተዝታዎቻችን ውስጥ ይጠቀሳል፡፡ የሩቁን ብንተወው እንኳ ማለት ነው፡፡

በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ እንኳ ሳይቀር ገብቶ ያለአግባብ ያሰራቸው የሙስሊም ሀይማኖት መሪዎችና አማኞች የማደናበሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ካለፈው አመት ጀምሮ የምርጫውን ዝግጅት ማድረግ የጀመረው እንደለመደው ከሱ የተለየ ሀሳብ የሚያንፀባርቁ ጋዜጦችንና መፅሔቶችን በመዝጋትና፣ ጋዜጠኞችንና ፖለቲከኞችን በማሰርና በመደብደብ ነበር፡፡ በምሳሌነት የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንና የሶስቱን ጋዜጠኞች ጉዳይ ማንሳት ይቻላል፡፡

ዘንድሮ ደግሞ ኢህአዴግን በድፍረት በመሄስ የሚታወቀውን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ ምርጫ ቦርድን በመጠቀም ያለአግባብ ከፓርቲያቸው እንዲገለሉ ያደረጋቸውን የአንድነት ፓርቲ አባላትን በግፍ ማሰሩን ተያይዞታል፡፡ በተመሰረቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢህአዴግ ፈተና የሆኑበት ደፋሮቹ የሰማያዊ ወጣቶችም የኢህአዴግ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ የየትኛውም ፓርቲ አባላት ያልሆኑና ቅሬታቸውን በተለያዩ መድረኮች ያሰሙ በርካታ ግለሰቦችም ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸዋል፡፡

ኢህአዴግ ይሄን ሁሉ የፈሪ ዱላውን እያዘነበ የሚገኘው በሚወስዳቸው እርምጃዎች ከተቃዉሞ ድምፆችና እንቅስቃሴ የሚገላገል እየመሰለው ነው፡፡ እንደተሳሳተ ማን ቢነግረው ይሻል ይሆን? የራሱን ዜጎች ማክበር ስለማይሆንለት የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንድትነግርልን ብናደርግ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለማንኛውም የሚኒስትሯን ጉዳይ ለጊዜው እንተወውና በሀገራችን ዴሞክራሲ ሰፍኖ ለማየት የቆረጥን እኛ ግን ከትግላችን ለሰከንድም ቢሆን እንደማናፈገፍግና በዚህም ምክንያት የሚደርስብንን ሁሉ ለመቀበል ፍቃደኞች እንደሆንን ልንነግረው ያስፈልጋል፡፡ “ኢህአዴግ ሆይ እየበዛኸው ያለኸው ግፍና በደል ይበልጥ ጠንካሮች ያደርገናል እንጂ አንተ እንደፈለከው አያንበረክከንም ነቄ ነን ተቀየስ” ልንለውና ጥንካሬያችንንም በተግባር ልናሳየው ይገባል

ጠማማ መንገድ ሁለት

“አይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛቹ” ማለትን የሚወደው ኢህአዴግ

ኢህአዴግ እንደጠቀስኳቸው አይነቶችና ሌሎች የሀይል እርምጃዎችን በአብዛኛው የሚወስደው ሊያሞኛቸው እንደማይችል በተረዳው በነቁ ሰዎች ላይ ነው፡፡ እንዳልነቅ የገመታቸውን ደግሞ እንደጨለመባቸው እንዲቀሩ የሚያደርግ የሚመስለውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ያዘጋጅላቸዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታዲያ ይሄ ግምቱ ግቡን መምታቱ ይቀርና እንደሚያታልላቸው እርግጠኛ በሆነባቸው ዘንድ ሳይቀር መሳቂያ ሲያደርገው ይስተዋላል፡፡ ሌሎቹን ትቼ ለምርጫው ካዘጋጃቸው ማታለያዎቹ ውስጥ እጅግ በጣም ጥቂቶቹን ላንሳ፡፡

2.1 ተቃዋሚዎች አማራጭ የላቸውም፡፡

በተለይ በዘንድሮው ምርጫ ጆሮአችን እስኪያንገሸግሸው ድረስ ኢህአዴግ ሊግተን ከሞከራቸው ሀሳቦች ውስጥ “ተቃዋሚዎች አማራጭ የላቸውም” የሚለው ዋነኛው ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ በእውነተኛና ጠንካራ ተቃዋሚዎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ደባ የሚያውቅ ሁሉ ይሄ ሀሳብ በውስጡ በርካታ ሴራዎችን የያዘ መሆኑን ይረዳል፡፡ እንዴት ማለት ጥሩ! ኢህአዴግ ሰራኋቸው ብሎ የሚመፃደቅባቸውን ስራዎች በሙሉ ከነድክመቶቻቸውም ቢሆን መስራት የጀመረው ባለፉት አስርት አመታት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዕድሜ ለ1997ዓ.ም የተቃዋሚዎች ድንቅ አማራጭና እንቅስቃሴ! ከዚያ በፊትማ ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ነበር፡፡ በዚያ የምርጫ ወቅት ከተቃዋሚዎች ጋር ባደገረው ክርክሮች ባዶነቱ የታየበት ኢህአዴግ ራቁቱን ከመሸፈን ይልቅ ተቃዋሚዎችን መግፈፍ መፍትሔ አድርጎ ወሰደ፡፡ ያለፉትን አስር አመታት ሙሉ ጠንካራ አማራጭ ያላቸውንና በሀሳብ የተገዳደሩትን ፓርቲዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የማፍረስ፣መሪዎችን የማሰርና የማሳደድ እርምጃዉን ገፋበት፡፡ በዚህ ድርጊቱም በርካታ ጠንካራ ፖለቲከኞችን ከጫዋታ ዉጪ አደረጋቸው፡፡ ባደረሰባቸው ከባድ ኩርኩም ተቃዋሚዎችን ድንክ እንዳደረጋቸው እርግጠኝነት የተሰማው ገዢው ፓርቲ “ተቃዋሚዎች አማራጭ የላቸውም” ብሎ ለመፎከር በቃ፡፡ ድሮስ በራሱ የማይተማመን ሰው ሁሌም ትልቅ ለመምሰል የሚሞክረው ጠንካሮችን በማስወገድና በደካሞች ራሱን በመክበብ አይደል? የተቃዉሞው ሰፈር በየቀኑ ከኢህአዴግ በሚሰነዘርበት የሀይል ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም ዛሬም ቢሆን የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጉንጫቸው እስኪቀላ ድረስ የሚገዳደሩና መልስ የሚያሳጡ ሰዎች አላጣንም፡፡ የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ እንዲሉ ኢህአዴጎች ግን “ተቃዋሚዎች አማራጭ የላቸውም” የሚለዉን ነጠላ ዜማቸውን ለማቆም አልፈለጉም፡፡ ጠንካራ አማራጭ ያላቸውን ከጎዳናው ላይ በማስወገድ ብቸኛ ባለአማራጭ ሆነው ለመታየት በተግባር የሚያደርጉትን ሙከራ ማጀቢያ ሙዚቃ መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም “ኢህአዴጎች ሆይ ነቄ ነን ተቀነሱ!” ብለን ልናስቆማቸው ይገባል፡፡

2.2 በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ

ይሄ ምርጫ አልፎ ከመስማት ልገላገላቸው ከምፈልገው ሸፍጥ የተሞላባቸው የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳዎች አንዱ “የምርጫ ቅስቀሳውና ክርክሩ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ ለማካሄድ እንደረዳቸው የእንትን ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ” የሚለው ይገኝበታል፡፡ አስቀድሜ እንደገለፅኩት ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎች አማራጭ እንደሌላቸው ደጋግሞ ነግሮናል፡፡ እንግዲህ በዚህ ስሌት መሰረት ከሄድን እየተፎካከሩ ያሉት ባለአማራጭ ኢህአዴግና አማራጭ የሌላቸው ተቃዋሚዎች ናቸው ማለት ነው፡፡ ከውድድሩ ሜዳ ላይ ሊገዳደሩት የሚችሉትን ሁሉ ለማስወገድ የሞከረው ኢህአዴግ በሱ ቤት ብቸኛና ምርጥ ቀስቃሽ የሆነ መስሎታል፡፡ “በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ” እያለ የሚያደረቁረንም ለዚህ ነው፡፡

አይ ኢህአዴግ! በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲካሄድ እንደማይፈልግ ተግባሩ እንደሚመሰከርበት እንኳ አይታየውም፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በገዢው ፓርቲ የሚሽከረከሩ የሚዲያ ተቋማት የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ ሳያስተናግዱ የቀሩባቸው ግዜያት ነበሩ፡፡ ህገመንግስቱ ገለልተኛ መሆናቸውን የገለፀውን ተቋማት ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ይዘት ያለው ቅስቀሳ ነው በሚል፡ አሳዛኝና አስቂኝ ምክንያት! እንደምርጫ ቦርድ፣ ፍርድቤትና የመሳሰሉት ያሉትን ገለልተኛ መሆን የሚገባቸውና በተግባር ግን ሆነው ያልተገኙ ተቋማትን መሞገት እንኳን የማይችል ተቃዋሚ መፈለግ ምን የሚሉት አምባገነንነት ነው? ሁሉም ነገር በአንድ በእርሱ የተበላሸ መስመር እንዲሄድ የሚፈልግና የተለዩ ሀሳቦችን ለማስተናገድ ያልፈቀደ ፓርቲ የሚያካሂደው ምን አይነት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንደሚሆን አይገባኝም፡፡

ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ እንዲሉ በመጀመሪያ ደረጃ ለውጥ የምንፈልግበት ምክንያት በዋናነት ያን ያህል ምሁራዊ ንድፈሀሳቦችን የሚጠይቅና የተወሳሰበም አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ሆይ አይደለህም እንጂ ጎበዝ ተከራካሪ ብትሆን እንኳ እንደሰውና እንደዜጋ የመኖር መብታችንን የገፈፍክ አምባገነን ሆነህ ሳለ አፈጮሌ ስለሆንክ ብቻ እንድታስተዳድር የምንፈልግ ጅሎች መስለንህ ከሆነ ተሳስተሀል፡፡ ነቄ ነን አልንህ እኮ!

2.3 ከ “የህዝቡን ድምፅ መቀበል” እስከ “አስፈላጊው እርምጃ”

የምርጫውን መቅረብ ተከትሎ ኢህአዴግ እየነገረን ያለው ሌላው ጉዳይ የህዝቡን ድምፅ መቀበል እንደሚገባ ነው፡፡ ድምፄ ይከበርልኝ ብሎ አደባባይ የወጣን ህዝብ በመግደል ስልጣኑን በደም ያራዘመው ኢህአዴግ ይሄን ለማለት ምን የሞራል መሰረት አለው? ፈፅሞ ሊኖረው አይችልም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ኢህአዴግ አጭበርብሮም ሆነ በስልጣን ለመሰንበት ማንኛቸውንም ጉዳይ ፈፅሞ ካበቃ በኋላ በምርጫ ቦርድ “አሸናፊነቱ” ሲታወጅለት የህዝቡ ድምፅ እንደሆነ ተቆጥሮ እንዲወሰድለት ይፈልጋል፡፡ ስቴድየም “ድሉን” ምክንያት በማድረግ በሚያዘጋጀው ዝግጅት ላይም “መሾምና መሻር ለሚችለው የህዝቡ ሉአላዊ ስልጣን ” እጅ ለመንሳትም በእጅጉ ቋምጧል፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትሪያችን እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኮፍያቸውን አንስተውና ከወገባቸው ዝቅ ብለው ላልመረጣቸው ህዝብ “የእንኳን መረጥከን” ምስጋና ሲያቀርቡ እንደምናይ ለመገመት እደፍራለሁ፡፡ ይሄንን ድርጊት ለማሰናከል የሞከረ ሰው ደግሞ “አስፈላጊዉ እርምጃ” እንደሚወሰድበት አንዴ ኮሚሽነር፣ ሌላ ጊዜ ምክትል ኮሚሽነር ሲያሻው ደግሞ በርካታ ኮማንደሮችን ዋቢ እያደረገ ሰሞኑን ኢብኮ ሊያስጠነቅቀን ሞክሯል፡፡ ከፍተኛ መኮንኖቹም በቂ ትጥቅ እንዳሟሉና ከ2006ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅት ሲያደርጉ እንደከረሙ በኩራት ሊነግሩን ሞክረዋል፡፡ ዝግጅታቸው ለእውነተኛ የሀገር ጠላትና አሸባሪ ቢሆን ኖሮ ኩራታቸው ኩራታችን ይሆን ነበር፡፡ ግን ዝግጅታቸው ለኢህአዴግ ተቀናቃኞች መሆኑን በሚገባ ስለምናውቅ ስሜታቸውን ልንጋራቸው አልቻልንም፡፡ ኢብኮ ከመኮንኖቹ ንግግር መሀል እያስገባ ሲያሳየን የነበረው የታጣቂና የትጥቅ ብዛትም የ “አርፋቹ ተቀመጡ” መልዕክትን ያዘለ ነው፡፡ በእኔ በኩል ለውጥ ያለፅናት ሊታሰብ እንደማይችልና ቦግ ድርግም በሚል አይነት ትግል ድል እንደማይገኝ ስለማምን ሁሌም በመስመሬ ላይ ነኝ፡፡ በትግሉ ውስጥ ያሉትን ሁሉ የምመክረውም ይሄንኑ ነው፡፡ ይሄ አቋማችን ህይወታችንን እስከመስጠት የሚያደርስ መስዕዋትነት ሊጠይቀን እንደሚችል አሳምሬ አውቃለሁ፡፡ ለሀገራችንና ለህዝቡ መልካም ለውጥ ለማምጣት እስከሆነ ድረስ ይሁን፡፡ ነገር ግን በትግሉ ውስጥ ያላችሁትን ሁሉ ትግሉን ወደፊት ሊያራምድ ከማይችልና ኢህአዴግን የበለጠ ስልጣን ላይ እንዲደላደል ከሚያደርግ አጉል መስዕዋትነት እንድትቆጠቡ አደራ እላለሁ፡፡ የምታደርጉት እንቅስቃሴ የተጠና፣ የለውጥ ሀይሎችን በሙሉ በአንድነት ያሰባሰበ፣ ቀጣይነት ያለውና በተቻለ መጠን አደጋን የሚቀንስ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን በማድረግ ትግሉን ሊያስቆም ወይም ደግሞ የጅምላ እስርን ሊፈፅምና ሀገራችንን በደም አበላ ሊነክር የተዘጋጀውን ኢህአዴግ የትኛውም ፍላጎቱ ቢሆን እንዲሳካ ባለመፍቀድ “ነቄ ነን ተቀየስ! ” ልትሉት ይገባል፡፡

በመጨረሻም

ኢህአዴግን “ነቄ ነን ተቀየስ” ልንልባቸው የሚገቡንና ሌሎችንም እንዲነቁበት ማድረግ የሚገባን በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ያለሁበት ሁኔታ ብዙ ለመፃፍም ሆነ እናንተጋ እንዲደርስ ለማድረግ ፈፅሞ አመቺ አይደለም፡፡ አሁን አሁንማ የምርጫውን መቃረብ አስመልክቶ የሚፈትሹኝ፣ የሚያጅቡኝ ሆነ ቤተሰብ የሚያገናኙኝ በሙሉ የህወሓት ሰዎች ብቻ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ራሱን የብሔረሰቦች መብት አስከባሪ አድርጎ የሚያቀርበው ገዢው ፓርቲ ምነው እኔን ለመፈተሽና ለመጠበቅ እንኳ ሌሎቹን ብሔረሰቦች ማመን አቃተው?የፖለቲካ እስረኛ የሆኑ ወገኖችም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚፈፀም ይገባኛል፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ከሚያደርግበት በርካታ ምክንያቶች አንዱ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል የትግራይ ወገኖቹ ላይ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲያድርበት ለማድረግ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ የትግራይ ህዝብ ሌላው ብሔረሰብ በጥሩ አይን አያየኝም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረውና ሳይወድ በግዱ የህወሓት ባርያ ሆኖ እንዲቀር መሆኑ ነው፡፡ አይ ኢህአዴግ! ፓርቲና ህዝብ መለየት የምንችል ነቄዎች መሆናችንን ረሳኸው እንዴ? የትግራይ ልጆችም ቢሆኑ ሴራህ ገብቷቸው አብረውን እየታገሉህ በመሆናቸውና ያልነቁትንም እያነቁ በመሆናቸው የሚሳካልህ አይመስለኝም፡፡

እንደው እንደው ግን እናንተዬ ከላይ የጠቀስኩት ከፋፋይ ባህርይው ብቻ እንኳን ኢህአዴግን ለመታገል ከበቂም በላይ ምክንያት አይሆንም? ይሆናል እንደምትሉኝ አውቃለሁ፡፡ በመሆኑም ይሄን በዜጎች መሀከል ጥላቻን ለመዝራት የሚሞክር መርዘኛ መንግስት ከትከሻችን ላይ አሽቀንጥሮ ለመጣልና ነፃነታችንን ለማወጅ በአንድ ላይ እንቆም ዘንድ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ምንጭ ዞን ዘጠኝ ፌስ ቡክ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here