የተኛ ትውልድ እና የተረገጠ ትውልድ ትርጉሙ ለየቅል መሰለኝ። እንዳይሞት እንዳይድን ሆኖ ተረግጦ የተኛ ከሚነቃበት እድል እኩል ወይንም ከዚያበላይ በዚያው የሚያሸልብበት እድል አለ።
ትውልዱ እየተረገጠ ያለው በዱላ እና በእስር ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘዴዎችም ነው። በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው ጉዳዮ ገብቷቸው በየጊዜው ስጋታቸውን የሚገልጹት። እነሰይፉ ያሳስቃሉ፤ ሌላው በሌላ መንገድ ያዘናጋል ፤ የኢትዮጵያን “አከርካሪ” ሰብረናል ( ለ”እስክታ የሚሆን ብቻ ነው የተውንላት”) የሚሉት ደሞ በእነሱ እግር ለሚተኩት ሁሉን ነገር ለማዘጋጀት እንቅልፍ የላቸውም። “እናንተ አውሩ እኛ ስራ ላይ ነን” የሚያስብሉት ግን አከርካሪውን ሰብረነዋል የሚሉትን ወገን ነው።
መስፍን አበበ የሚባለው ዘፋኝ በዚሁ በተረገመ ሰይፉ ሾው ቀርቦ በአብዮቱ አካባቢ ስለነበረው ትውልድ ሲናገር ፤ “ያኔ ሰው ክፉ እና ኮስታራ ነው ፤ አይስቅም” እንዳለ ሰይፉ የሚያስገለፍጠው ትውልድ እዛው በግልፈጣው ቀጠለ። ልዮነቱ እና አንደምታው እንኳ አልገባውም። ምክንያት ተቀጥቅጦ ስለተኛ። የሚያሳስቀው ግን በሚያሳስቅበት መንገድ እያሳሳቀ ነው። ወያኔዎቹ ራሳቸው በነሱ ላይ የሚቀለደው ነገር ብዙም ቁብ አላሉትም፤ ‘ቀልዶ ገልፍጦ ካለፈ ምን ጨነቀን’ ይመስላል ነገሩ። ይሄ ሁሉ ግፍ እና በደል እየተፈጸመ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓውያኑ (ከሞላላቸው) እኩል ቀልድ በገፍ የሚያምረን ከሆነ እና ቀልድ የኑሮ ዘየ ከሆነ አሁንም ስለ ንቃት እና ዘመናዊነት ሳይሆን የሚያሳብቀው ስለመደንዘዝ እና ስለመተኛት ነው የሚያሳብቀው። ሁለት ሞት።
ከያ ትውልድ ወደዚህ መራራ ትግል ደብዛው አልጠፋም ማለት አይቻልም ። እርግጥ በጣም ጥቂቶች አሉ። በቅርቡም ሳሙኤል አወቀ የከፈለው መስዋዕትነት ከጥቂቶቹ አንዱ ነው። ላመነበት ነገር ህይወት ሰጥቷል። ሽንፈትን የሚያሳይ ነገር አይደለም። ብልህ ትውልድ ፤ የሰውነት እና የሃገር ትርጉም የገባው ሰው ሳሙኤል ያሳየውን ቁርጠኝነት ወደ ሌላ ምዕራፍ በማሸጋገር እምቢተኝነቱ ከወያኔ መዳፍ እና ጭካኔ እንዲወጣ ያደርጋል። የእኛ ትውልድ ግን ብዙም ሳይቆይ ወደ ግልፈጣው ተመለሰ። እየተቆመረ ያለው ግን በሚመጣውም ትውልድ ነው።
ድሜጥሮስ ብርቁ