ጎንደር ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ተደረገ

ሐምሌ 24 2008 ዓ.ም.

ዛሬ ጎንደር በ97 ዓመተ ምህረት ከተደረገው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወደዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልታየ ጀግንነት እና አርቆ አስተዋይነት የተንጸባረቀበት ታላቅ ሰልፍ ተደረገ። ምንም እንኳን በስልጣን ላይ ያለው ቡድን አካላት ሰልፉ እንዳይደረግ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት አልፈው በጎንደር ሰራዊት ቢያሰማሩም ህዝቡ ከምንም ሳይጎጥራቸው በታላቅ ጀግንነት ፤ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በነቂስ ወጥቶ ከወልቃይት ጠገዴ በተጨማሪ ሃገራዊ የፍትህ እና የለውጥ ጥያቄ ሲያስተጋባ ውሏል።

“የወልቃይት ጉዳይ መልስ ይሰጠው” ፤ “መንግስት በኦሮሞ ወገኖቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያ እንቃወማለን” ፤ “ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእስር ይፈቱ” “የሙስሊም ኮሚቴ አፈላላጊዎች ይፈቱ” የሚሉት ከተስተጋቡት መፈክሮች ጥቂቶቹ ናቸው።

ከመቶ ሺ በላይ የተገመተው ሰልፈኛ ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ባንዲራ በማንገብ ኢትዮጵያዊ ኩራቱንም ሲያንጸባርቅ ዉሏል።

የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት አካባቢ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ኢትዮጵያን እንዳዲስ ከማካለሉ በፊት የወልቃይት መሬት የጎንደር አካል ፤ የራያ መሬት የወሎ አካል እንደነበረ የሚታወቅ ነው።

የጎንደር እንቅስቃሴ ከእለት ወደ እለት እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን መንግስህ ህገመንግስታዊ ጥያቄዎቹን በሰላም መመለስ ካልፈለገ ጉዳዮ ወደ ኃይል ፍጥጫ ሊያመራ እንደሚችል የሚጠቁሙ ሁኔታዎች አሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.