አንተነህ መንግስቱ
ሐምሌ 26 2008 ዓ.ም
1. ህዝብ በአንድነት ከተነሳ፣ ሊያቆመው የሚችል አንዳችም ምድራዊ ሃይል የለም።
2. “ገለን ቀብረነዋል” የተባለው የአማራ ህዝብ ዳግም አንሰራርቷል።
3. አንድን ህዝብ ለማንቋሸሽ፣ ለማሳነስ፣ 25 አመታት ሙሉ የተሰራበት የጥላቻ ፖለቲካ ጭራሽ ያንን ህዝብ አጠንክሮታል። በአደባባይ “ንፍጣም” “ትምክተኛ” “ነፍጠኛ” ሲባል የኖረ ህዝብ ትዕግስቱ ተሟጧል።
4. ህዝብ ከመንግስቱ ንቃተ ህሊና ልቆ ሄዷል። ሰላማዊውን የህዝብ የማንነት ጥያቄ አንድ ብሄር ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርጎ ለማሳየት የተደከመበትን ፕሮፓጋንዳ የጎንደር ህዝብ በግልጽ “ጠላታችን ህውሃት እንጅ የትግራይ ህዝብ አይደለም” ሲል በማወጅ ውሃ ከልሶበታል።
5. በህውሃት እጅ ግፍና ግድያ እየተፈጸመብት ከሚገኘው የኦሮሞ ህዝብ ጋር በመቆም የአማራና የኦሮሞ ህዝብ ወንድማማች ህዝቦች እንጅ ታሪካዊ ጠላቶች እንዳልሆኑ ጎንደር ዳግም አስመስክሯል። ከሁለቱ ታላቅ ህዝቦች መጣመር በላይ የህውሃት እራስ ምታት የሚጨምር ምንም ነገር የለም።
6. የወልቃይትም ሆነ የሌሎች ህዝቦች የማንነት፣ የዲሞክራሲ፣ እራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሽ እስካላገኙ ድረስ ይህን መሰል ህዝባዊ ንቅናቄዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ እንጅ በተራ ማስፈራራትና ውንብድና የሚቆም እንዳልሆነ ይሄ ጥሩ ማሳያ ይሆነናል።
7. በመጨረሻም፣ የህውሃት ባለስልጣናት ከመቸውም ጊዜ በላይ ህዝብ ሊበላቸው ጫፍ መድረሱን አውቀው፣ ከትዕቢትና ከማን አለብኝነት ወተው፣ በሰከነ አዕምሮ ስለራሳቸውም ሆነ ስለቤተሰቦቸቸው እንዲሁም ቆመንለታል ስለሚሉት ህዝብ ማሰብ የሚገባቸው ውቅት አሁን መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል።
ማን አለብኝነትና ትዕቢት መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ከፈርዖኖች እንኳን ባይሆን እነሱ ጥለውት ከመጡት ደርግ ይማሩ።