ለሰላማዊ ተቃውሞ በወጣው ህዝብ ላይ መንግስት ጦርነት ከፈተ

ሐምሌ 30 2008 ዓ.ም

Gonder Genocide
ባለፈው ሳምንት በጎንደር የተካሄደውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ለዚህ ሳምንት መገባደጃ ቅዳሜ እና እሁድ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ክፍል የሚያካልል ሰላማዊ ተቃውሞ ለማሰማት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ፤ እንደተገመተው በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ሰላማዊ ሰልፎቹ ላይ ጦርነት የሚመስል ዘመቻ እንደከፈተ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ፤ በባሌ፤ በአርሲ ፤ በሃረር ከተሞች እና በናዝሬት ሰልፍ የተደረገ ሲሆን መንግስ አጋዚ እየተባለ የሚጠራውን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ታማኝ ሰራዊት በሰላማዊ ሰልፈኖቹ ላይ አሰማርቷል። ሚኒሶታ የሚገኝ የኦሮሚያ ሜዲያ ኔት ወርክ እንደዘገበው ከሰላማዊ ተቃውሞው ጋር በተያያዘ በነቀምቴ በኦሮሚያ ፖሊስ እና በአጋዚ ሰራዊት በተነሳ ግጭት አንድ የኦሮሚያ ፖሊስ ተገድሏል። ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም ከላይ በተጠቀሱት የኢትዮጵያ አካባቢዎች በደረሰው የአጋዚ ጥቃት በርካታ ሰዎች እንደሞቱ ይነገራል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በአዲስ አበባም ዛሬ ጧት የተቃውሞ ሰልፍ የነበረ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ እንደበተነው ከሮይተርስ የዜና ወኪል የተገኘ ቪዲዮ ያመለክታል።

በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ደብረታቦር ላይ ተመሳሳይ ሰላማው ተቃውሞ የነበረ ቢሆንም ፤ በህዝቡ ላይ ከባድ ጦርነት ተከፍቶበታል። ዛሬ እና ትላንት በጎንደር በደረሰው እልቂት የሞተውን ሰው ቁጥር አንዳንዶች ሰላሳ ያደርሱታል።

ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ እጂግ አሳሳቢ ቢሆንም ፤ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ነገሩን ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲገባ የኃይል ርምጃ ላይ ትኩረት ሰቶ እየሰራ ነው።

ከወልቃይት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በጎንደር በተነሳው ተቃውሞ ሳቢያ የበቀል የሚመስል ኢሰብአዊ የጭካኔ ርምጃ በመውሰድ ላይ እንደሆነ ከአካባቢው መልዕክት የሚያስተላልፉ ሰዎች ይናገራሉ። አልሞ ተኳሾች በጎንደር እና በኦሮሚያ አካባቢዎች ተሰማርተው እንደነበርም ተጠቁሟል።

ቦርከና

Leave a Reply

Your email address will not be published.