ነሃሴ 9 2008 ዓ ም

በቶሮንቶ እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ከሰዓት በኋላ በኦንታሪኦ ፓርላማ ፊት ለፊት ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ እያደረሰ ያለውን አሰቃቂ የጂምላ ግዲያ አውግዘው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መንግስ አገዛዝ ማክተም አለበት ሲሉ በመፈክር መልክ አሰምተዋል።
የካናዳን መንግስት በሚመለከት ከኢትዮጵያ ጋር አለው ያሉትን የኢንቬስትመንት ፤ የንግድ እና የእርዳታ ግንኙነት አውስተው ፤ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ተጨማሪ እልቂት እንዳያደርስና እና ኢትዮጵያን በርዋንዳ ታይቶ እንደነበረው አይነት የዘር ፍጂት እንዳይወስዳት ተጽዕኖ ካናዳ ያላትን የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ አቅም በመጠቀም በአገዛዝ ስርዓቱ ላይ ተጽዕኖ እንድታሳድር ሰልፈኖቹ በቶሮንቶ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አማካኝነት በተዘጋጀ ደብዳቤ ጠይቀዋል።
ሰልፉን ያስተባበረው በቶሮንቶ የኢትዮጵያውያን ማህበር ነው። የድርጂቱ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ የሺሃረግ ወርቁ በሰልፉ ላይ ባደረገችው ንግግር ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እጂግ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጻ ፤ የፖለቲካ ልዮነቶቻችንን ወደጎን በማድረግ በኢትዮጵያዊነታችን ስለ ኢትዮጵያ ስንል ድምጻችንን እንድናሰማ ጥሪ አስተላልፋለች። በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችንን እየገደለ ያለው ስርዓት ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው በቶሮንቶ በሚያንቀሳቅሳቸው ንግዶች (ከኢትዮጵያ የሚላከውን እንጀራ ጨምሮ) ላይ ኢትዮጵያውያን ማዕቀብ መጣል አለብን ስትል እልህ እና ወኔ በተቀላቀለበት ሁኔታ ተናግራለች።
ቦርከና
___
ካነበቡ በኋላ ሼር በማድረግ ፤ የፌስ ቡክ ገጻችንን ላይክ በማድረግ ይተባበሩ።