spot_img
Monday, November 27, 2023
Homeነፃ አስተያየትራስዎን ከጎሰኝነትና ከዘረኝነት ይጠብቁ!!!!!! እንዴት?

ራስዎን ከጎሰኝነትና ከዘረኝነት ይጠብቁ!!!!!! እንዴት?

advertisement

ኤፍሬም እሸቴ 
አደባባይ

ነሃሴ 18 2008 ዓ ም

አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ተረት ባስታውሳችሁ ለውይይታችን የበለጠ ይረዳናል። አንድ መንገደኛ ሰው ይመሽበትና ከአንድ መንደር ለማደር «የእግዜር እንግዳ፤ አሳድሩኝ» እያለ ይለምናል። የሚያድርበት ቦታ ቢፈልግም በልቡ አንድ ነገር ሰግቷል። የዛ አገር ሰዎች «ቡዶች ናቸው» ሲባል ስለሰማ ቀርጥፈው እንዳይበሉት ፈርቷል። ይሁንና «ቤት የግዚሐር ነው» ያለ ገበሬ በሩን ይከፍትለትና ያስተናግደዋል። የሰውየው ልጆች እግሩን ሲያጥቡት፣ ባለቤቱ ራት በሰፌድ፣ ጠላ በሽክና ታቀርብለታለች። እስካሁን በተደረገለት ሁሉ እጅግ የተደሰተው እንግዳ ዘና ማለት ሲጀምር በልቡ የቋጠራትን ጥያቄ ያወጣል። «ለመሆኑ የቡዶቹ መንደር የት ነው?» ይላል። የቤቱ ባለቤትም ሲመልስለት «እዚያ ማዶ ያሉት ሰዎች እኛን ይላሉ፣ እኛም እነርሱን እንላለን» ሲል ይመልስለታል። የጎሰኝነቱም እንደዚያው ነው። ሁላችንም ጣት እንደተጠቋቆምን አለን። አዳሜ ሁሏም ጥቂት ጥቂት ጎሰኝነት እና መንደርተኝነት አታጣም።

«ዘረኝነት» መጥፎ መሆኑን ሁላችንም ብናምንም በዚህ ዘመን የተለያየ ጎሳ እና ብሔረሰብ ስላለን ያንን ተያይዞ የሚመጣው ችግር፤ ማለትም ጎሰኝነት፤ አጥቅቶናል። የእርሱን ዘረኝነት ዘረኝነት ባይለውም ዘረኛውም ሰውዬ ጭምር ዘረኝነትን ሲቃወም ልንሰማው እንችላለን። በርግጥ አገራችን ውስጥ ያለው ችግር «ዘረኝነት» ሳይሆን «ጎሰኝነት» መሆኑን ፕ/ር መስፍንን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ይናገራሉ። ሁላችንም ዘራችን እና ቀለማችን ጥቁር ስለሆነ የተለያየን አይደለንም።በአገራችን ጉዳይ የሚጻፉ ጽሑፎች ግን ሁለቱን ቃላት በተለዋዋጭነት ይጠቀሙበታል። ለጊዜው ዘረኝነት ስንል ጎሰኝነት ማለታችን እንጂ እንደ ጥቁሮች እና ነጮች ችግር ያለ አለመሆኑ ከግንዛቤ ይግባና ሁላችንም ዘረኝነት የምንቃወም ነገር ግን ጥቂት ጥቂትም ቢሆን ዘረኝነት የሚያጠቃን መሆናችንን እንገንዘብ።

እዚህ ላይ ግን አንድ መሠረታዊ ጉዳይ ግን ማንሣት ያስፈልጋል። በአገራችን ጎሳን እና ጎጥን፣ ወንዝንና መንደርን መሠረት አድርጎ መጠቃቀም የነበረ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በዚህ ዘመን ግን ልዩ የሆነውና አገራችንን የበጠበጠበት ምክንያትና ነገሩን ያከፋው በዘመነ ሕወሐት ያለው ጎሰኝነት ግለሰባዊ ብቻ ሳይሆን «ተቋማዊ ጎሰኝነት» (Institutional racism) መሆኑ ነው። ኢሕአዴግ መልሶ መላልሶ እንደሚናገረው «ችግሩ የመልካም አስተዳደር ችግር»፣ የተወሰኑ አባሎቹ ያመጡት የተሳሳተ አሠራር ሳይሆን የፓርቲው ተቋማዊ ጎሰኝነት ያመጣው ችግር ነው። ጎሰኝነት የፓርቲው ፖሊሲ ነው።

ተቋማዊ ጎሰኝነት ማለት በተቋም ደረጃ ሰውን በብሔረሰቡ ማንነት ላይ ተመርኩዞ መጥቀም ወይም መጉዳት ማለት ነው። የትኛውንም አገልግሎት ለማግኘት ቅድሚያ ማግኘት ማለት ነው። የገዢው ፓርቲ ወገን የሆኑ ብዙ ሰዎች የማይረዱት ነገር ይህ ነው። ከትግራይ የተወለዱ እና የዚህ ጎሰኝነት ተቋዳሽ ያልሆኑ ሰዎችን በመጥቀስ ለመከራከር የሚሞክሩት የጎሰኝነቱን መሠረታዊ ምንጭ ካለመገንዘብ ይመስላል። ጎሰኝነቱ ግለሰባዊ ሳይሆን ተቋማዊ «ኢኒስቲቲዩሽናል ትራይባሊዝም/ Institutional racism» መሆኑ ላይ መግባባት ይጠይቃል። ተቋማዊ ጎሰኝነት ያመጣው ጭቆና ደግሞ ተቋማዊ ጭቆና («institutional discrimination») ነው። አንድ ሰው ከትግራይ በመወለዱ ከሌላው ብሔረሰብ በላይ የመጠቀም ዕድሉ ከፍ ያለ ሲሆን አንዳንዱ ደግሞ ከሌላ ብሔረሰብ በመወለዱ ብቻ ለጉዳት ሊጋለጥ የሚችልበት ዕድል ከፍ ያለ ነው፤ ይህም በተግባር ታይቷል።

እንዲህ ያለው ተቋማዊ ጎሰኝነት በሚሰለጥንበት ወቅት ሌሎች ጎሳዎችም ለዚያ አፀፋ ወደሚሰጡበት ሌላ ጥግ ተገፍተው ይኼዳሉ። እነርሱም በራሳቸው ጎሳ ዙሪያ የመደራጀት፣ የጨቋኙን ጎሳ አባላት በጅምላ የመጥላት እና በተቋማዊ ጎሰኝነት ያጡትን ጥቅም የዚያን ጎሳ አባላት በማጥቃት ለመበቀል ወደመፈለግ ሊሄዱ ይችላሉ። አንዳንዱ ቂም ተጸንሶ ሳይወለድ ይመክናል። አንዳንዱ ግን በሐሳብ የተጸነሰው በተግባር ተለውጦ ብዙ ችግር ሊፈጥር ይችላል። «ለማንኛውም ድርጊት ተመጣጣኝ የሆነ ተቃራኒ ድርጊት አለ – For every actionthere is an equal and opposite reaction» የሚለው የፊዚክስ ሕግ (Newton’s third law) መቸም በዚህም ይሠራል ቢባል ብዙም ስሐተት አይሆንም። ይሁንና ጎሰኝነት በጎሰኝነት አይፈወስም። ተቋማዊ ጎሰኝነትን ለማጥፋት ሌላ ተቋማዊ ጎሰኝነትን መመሥረት ወይም ለመመሥረት መታገል መፍትሔ አይሆንም።

ከዚህ አንጻር ስንመለከተው የሕወሐትን ተቋማዊ ጎሰኝነት ለመለወጥ የሚደረግ ማንኛውም ተቃውሞ በኅሊናዊ ዳኝነትም ሆነ በሥነ ምግባራዊ ደንብ ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬ አምናለኹ። ለውጡ ደግሞ የቀለም ቅብ በማድረግ የሚሻሻል አይሆንም። መሠረታዊ ለውጥ ይፈልጋል። መሠረታዊ የሆነ የሕግ ለውጥን የሚጠይቅ እንጂ ጉልቻ በመለዋወጥ የሚፈታ አይደለም። ኢሕአዴግን በመምከር የሚመጣ ለውጥ የለም። ፈረንጆቹ እንደሚሉት«አሳማን ሊፒስቲክ መቀባት:: To put “lipstick on a pig”» ይሆናል። ሊፒስቲክ አሳማን ውብ አያደርጋትም። ለውጥ ሲባልም የሕወሐትን ጎሰኝነት በአማራ ወይም በኦሮሞ ተቋማዊ ጎሰኝነት መለወጥ አይደለም። ሙሉ በሙሉ ፍትሐዊ የሆነ ተቋማዊ አሠራርን ለመመሥረት ያለመ መሆን አለበት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ጎሰኝነቱን ለመቃወም በሚደረግ ጥረት አስቀድሞ ያልነበሩ ጎሰኝነቶች ሊያቆጠቁጡ እና የችግሩ ሰለባ ያልሆኑ አካላትን ሊጎዱ የሚችሉበትን ዕድል አብሮ መቃወም ያስፈልጋል። የሕወሐትን ጎሰኝነት ለመቃወም የሚደረገው ተቃውሞ ሰላማዊ ዜጎችን በሥነልቡናም ይሁን በአካል ሊጎዳ እንዳይችል ኃላፊነት የሚወድቅበት ጎሰኝነቱን በሚቃወመው ወገን ላይ ነው። ከዚህ በፊት እንደተለመደው ሁሉ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች የሚኖሩ የትግራይ ልጆች የዕለትተዕለት ኑሯቸው እንደማይነካ በቃልም በተግባርም ማሳየት ያስፈልጋል። ከሕወሐት በኩል በየቀኑ የሚነዛባቸውን የሽብር ማዕበል እንዲቋቋሙ ማገዝ ያስፈልጋል። «ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው» ነውና በመንግሥታዊው ጎሰኛ ድርጅት ተጠልፈው ከቀሪው ወገናቸው ተለይተው እንዳይቀሩ ማገዝ ያስፈልጋል። ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ይህንን ያደርጋል፣ እስካሁንም የተደረገው በርግጥ ይኼው ነው። ለዘጠኝ ወራት በዘለቀው የኦሮሚያ ተቃውሞ የትግራይ ሰዎች ዒላማ አልተደረጉም። በአማራ ክልል በተቀጣጠለው እምቢተኝነት ትግራዋዩን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እንዳልተፈጸመ የአማራ ክልል መንግሥት ጭምር ተናግረውበታል። በላባቸው ንብረት ያፈሩ፣ የሰው ደም በእጃቸው ላይ የሌለ፣ የጎሰኝነቱ የቀጥታ ተጠቃሚዎች ያልሆኑ ወገኖች ምንም አይሰጉም። ኮረኔል መንግሥቱ እንዳሉት (ያለፈ ሥርዓት ናፋቂ እንዳይሉኝ እንጂ) «ብታምኑም ባታምኑም፣ ወደዳችሁም፣ ጠላችሁም፣ ይህ ሕዝብ የምትነዱትን መኪና፣ የምትኖሩትን ሕይወት …. በደንብ ያውቃል»። ማን በዘረፋ እንዳገኘ፣ ማን በላቡ እንዳገኘ ሕዝብ ያውቃል። የተቋማዊው ጎሰኝነት ተጠቃሚዎች በርግጥም ቢፈሩ አይፈረድባቸውም። ሰላማዊው ሕዝብ ግን በምን ጦሱ ይስጋ?

በመጨረሻ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሊያውቃቸው የሚገቡ ሦስት ነጥቦችን በመጠቀስ ሐሳባችንን እንቋጭ። 1ኛ. ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦች አገር እንደመሆኗ ከራሳችን ጎሳ ውጪ ስላለው ወገን ለማወቅ ሙከራ ማድረግ ያስፈልጋል። ከ80 በላይ ቋንቋ በሚነገርባት አገር፣ የሁሉንም ታሪክና ባህል ለማወቅ መሞከር አባይን በጭልፋ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹን ብሔረሰቦች ማንነት አለማወቅ ግን አዋቂነት አይሆንም። ሕወሐት የአዲስ አበባን ሕዝብ ለማስፈራራት እና እንዳያምጽበት ለማድረግ ተጠቅሞበታል ከሚባለው ማስፈራሪያ አንዱ «ኦሮሞ ይመጣባችኋል» መሆኑን ስሰማ እጅጉን ማዘኔን አስታውሳለኹ። ኦሮሞ በአንድ የአገሪቱ ጥግ ያለ ትንሽ ብሔረሰብ አይደለም። ለምሳሌ እንደ ሐመር ወይም ሙርሲ ከአዲስ አበባ የራቀ አይደለም። በአዲስ አበባና በአካባቢው ያለው ኦሮሞ ነው። በሕዝብ ብዛት ትልቁ ኦሮሞ ነው። ታዲያ የአዲስ አበባ ሰው «ኦሮሞ መጣብህ» በመል ማስፈራሪያ እንዴት ሊሰጋ ይችላል? ሕወሐት የአዲስ አበባን ሰው እንዴት ቢንቀው ነው በኦሮሞ የሚያስፈራራው?» የሚል ሐሳብ ማጫሩ አይቀርም።

በዚህ ረገድ አንዳችን ስለሌላችን ብሔረሰብ ታሪክ «የመጽሐፍ መግቢያ ላይ ያለ ትንሽ ሐሳብ ያህል» እንኳን ለማወቅ ለራሳችን የቤት ሥራ መውሰድ ይኖርብናል። ምሁራንም በዚህ በኩል ከዕውቀታቸው በማካፈል መርዳት አለባቸው። አንድ ስለ ኢትዮጵያ ምንም የማያውቅ ሰው መጠነኛ ግንዛቤ እንዲኖረው ከምን መጀመር አለበት? ምን ማንበብ አለበት? አማራው ስለ ኦሮሞው ወይም ትግሬው፣ ትግሬው ስለ ኦሮሞው ወይም አማራው ሊያውቀው የሚገባው ምንድነው? ባለማወቅ ከሚመጣ መፈራራት ትውልዱን እንዴት መታደግ ይቻላል? ከኢሕአዴግ በፊት በነበረው የትምህርት ሥርዓት ለመማር ዕድል የገጠመን ሰዎች የዚህን ነገር አስፈላጊነት ላንገነዘበው እንችላለን። 60% ዜጋችን ኢሕአዴግ ከመጣ የተወለደ ወጣት መሆኑን እና ያገኘውም ዕውቀት ሕወሐት በሚፈልገው መልክ የተቀመመ መሆኑን ስንረዳ ዕውቀትን በዕውቀት ማለት እንዳለብን እንገነዘባለን። ጤናማ ታሪክን ማወቅ ከብዙ አገራዊ ደዌ ይታደገናል።

በሁለተኛ ደረጃ አገራችን ውስጥ ተቋማዊ ጎሰኝነት እና ግለሰባዊ ጎሰኝነት ተንሰራፍቷል ካልን የዚህን ችግር ከየትመጣ (the evolutionary root of tribalism) ለማወቅ መጣር አለብን። ሕወሐትን በጅምላ በማውገዝና በመስደብ ሳይሆን በሰከነ መንገድ የነገሩን ጅማሮ በመረዳት ወደ መፍትሔው ለመድረስ መጣር ይገባናል። በጉዳዩ ላይ ዕውቀት ያላቸው ምሁራን ምንጩን በመጠቆም መርዳት አለባቸው። በርግጥ በጉዳዩ ላይ በሰፊው የተጻፈ ከመሆኑ አንጻር ለተጠቃሚ በሚመች መልክ ማደራጀት ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ነገር ለማወቅ የሚፈልግ ወጣኒ/ጀማሪ/ ዜጋ ከየት ይጀምር? የትኛውን መጽሐፍ ያንብብ? ማንን ይጠይቅ? ወዘተ

ሦስተኛም የመፍትሔው አካል ለመሆን ራሳችንን እናዘጋጅ። «ጨለማን በማውገዝ» የሚገኝ ብርሃን እንደሌለው ይልቁንም «አንድ ሻማ ማብራት» እንደሚሻለው ሁሉ ጎሰኝነትን አምርረን ከመቃወም ጎን ለጎን ይህንን በሽታ ልናጠፋ የምንችልበትን መፍትሔ መፈለግ፣ መፍትሔ ነው ለሚባለው መድኃኒት ተባባሪና አጋዥ ለመሆን መጣር ያስፈልጋል። በግላችን ራሳችንን ከጎሰኛና ዘረኛ አባባሎች እንቆጥብ። በንግግርም፣ በጽሑፍም፣ በቀልድም፣ በቁምነገርም ጎሰኝነትን የሚያስፋፉ ሰዎችን በቀጥተኝነት መንፈስ እናርም። የሌላውን ብሔረሰብ ጎሰኝነት እየተቃወምን የራሳችን ሲሆን እያየን እንዳላየን አንለፍ። ለራሳችን ሰዎች ጎሰኛ አመለካከቶች ማስተባበያ መፈለግ የለብንም። «አካፋን አካፋ» እንበል። ያልዘራነው አይበቅልም፣ ያልኮተኮትነው አያድግም። የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳን።

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here