ከሊሻን ደበበ
ነሃሴ 21 2008 ዓ.ም
አማራ በልዩ ሁኔታ በህወሓት ለመጥፋት የተፈረደበት ህዝብ መሆኑ በሰፊው ይታወቃል። ይህ አይነቱ አደጋ በሌሎቹ ብሔሮች (ብሔረሰቦች) ላይ ስለሌለ ጥያቄውን የተለዬና ህልውናን የማትረፍ ትግል ያደርገዋል። ለህልውና (ራስን ለማትረፍ) የሚደረግ ትግል ደግሞ ለፖለቲካዊ እኩልነት፣ ለኢኮኖሚያዊ እኩልነትና ለነፃነት ከሚደረግ ትግል በጣም ይለያል። አንድ የራሱን ነገዳዊ ህልውና ለማትረፍ የሚታገል ህዝብ ስለዴሞክራሲ፣ ስለኢኮኖሚያዊ እኩልነትና ስለፍትህ ከማሰቡ በፊት ህልውናን ለማትረፍ ማሰቡን እንዲያስቀም ይገደዳል።
አማራው ህልውናውን ለማትረፍ ደግሞ በአማራነቱ ብቻ አንድ ሆኖ ከመቆምና የሞት ሽረት ትግል ከማድረግ ሌላ አማራጭ ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም የአማራው በአማራነት መታገል ተገዶ እንደገባበት እንጂ እንደ ተራ ፅንፈኛ የዘረኝነት ትግል ሊታይ አይችልም ማለት ነው ። ነገር ግን የአማራውን መደራጀት የሚቃወሙ አማሮች ነን ባይ የዋሃን (ግን ከኛ በላይ አዋቂ ላሳር ባዮች) የማይገባቸው፣ ወይም እያወቁ በሸፍጠኝነት ለመቀበል የማይፈልጉ፣ ወይም ስለአማራ ቁብ የማይሰጠውን ድርጅታቸውን ለመከላከል ብለው በኢትዮጵያዊነት ጭምብል ተጠቅመው የአማራውን ትግል ለማዳከም የሚጥሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ይህን ከላይ ባጭሩ ለመግለፅ የሞከርኩትን አመክንዮ ሊያጣጥሉት ይሞክራሉ።
ህወሓት ከሌሎቹ ብሔረሰቦች ጋር ያለው ግጭት በጥቅም ላይ የተመሰረተ ችግር እንጂ በማንነታቸው ላይ የተነጣጠረ አለመሆኑ ግልፅ ነው።
አማራው ህልውናውን ለማትረፍ ከፈለገ ራሱን በአማራነት ብቻ ማደራጀትና መሪዎቹን መርጦ ትግል ማካሄድ ይጠበቅበታል። ለ[ዚ]ህም የራሱ ምክንያቶች አሉት፤
1) አማሮች በማንነታቸው ተለይተው የጥቃት ሰለባዎች መሆናቸውን ስለሚረዱ ልዩ ቁጭት፣ ቆራጥነትና ፅናት ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል፤
2) አማራዎች ትግላቸውን ስኬታማ ለማድረግና በመሃላቸው መተማመንን ለመፍጠር ሲሉ ድርጅታቸውን አማራ ካልሆኑ ሰርጎ ገቦች ራሳቸውን ማፅዳት ግዴታ ይሆንባቸዋል። አማርኛ መናገርና ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ብቻቸውን መስፈርት የሆኑባቸው ትግሎች አማራውን ከጥፋት እንዳልተከላከሉለት ባለፉት ሃያ አምስት አመታት አይተናል።
አማራው ህልውናውን ለማረጋገጥ ደግሞ ህወሓትን ከማስወገ ሌላ ምንም አማራጭ አይኖረውም። አማራው ለህልውናው ሲል ህወሓትን ለማጥፋት የሚያደርገው ትግልና ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህና ለነፃነት ብለው የሚያደርጉት ትግል ህወሓትን በማስወገድ ላይ ያነጣጠረ እስከሆነ ድረስ [ማለትም ለጥገናዊ ለውጥ (for a regime refirm) እስካልሆነ ድረስ] ትግሎቹ ተፃራሪ አይሆኑም። በአንፃሩ ግን ህወሓትን የሚያካትት ጥገናዊ የለውጥ ትግል ከሚያራምዱ ወይም ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆኑ አካላት ጋር አብሮ መራመድ አይቻልም። ከዚህ አንፃር የአማራው የህልውና ትግልና የሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ትግል በተደጋጋፊነት ሊራመዱ ይችላሉ። ይህ ሲሆን ግን የአማራውን ትግል ማንነታዊነት ማክበርና እንደ ተራ ዘውጋዊ ትግል አለመመልከት እንዲሁም መሰናክል አለመሆን በጣም አስፈላጊ ነው። በመሆኑም አማራው ህልውናውን እንዲያተርፍ የሚፈልጉ ሁሉ ይህን መሠረታዊ ሃቅ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።
አማራው ከፈፅሞ ጥፋት ራሱን ያድናል!
አመሰግናለሁ።