ቦርከና
ነሃሴ 27 2008 ዓ ም
የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መንግስት ደጋፊ እና ውስጥ አዋቂ ሚዲያ ተቋማት በመባል ከሚታወቁት አንዱ ፋና ብሮድካስቲንግ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከተቃሚ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሊነጋገሩ እንደሆነ ትላንት በድረ ገጽ የኢትዮጰያ ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ ባወጣው ዜና አስታውቋል።
እንደዘገባው ንግግሩ ይደረጋል የተባለው ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር ነው። እንደ ፋና ዘገባ ንግግሩን ያነሳሳው የፓርቲዎች የጋር ምክር ቤት ይመስላል።
ንግግሩ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ ጥገናዊ ለውጥ የሚመስል አጀንዳ ይዞ እንደቀረበም ከዘገባው መረዳት ይቻላል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማንሳት በአዋጆች ፤ ደንቦች እና መመሪያዎች ላይ የማሻሻያ ሃሳቦች እንደሚያቀርብ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉ እና ሃሳብ በመስጠት የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ዜናውን በተለያየ መልክ ተንትነውታል።
ካነሳሱ ጀምሮ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የቀረበ መስሎ ቢታይም ፤ አዋጂ ለማሻሻል ሳሃብ የሚያቀርብ ንግግር የማነሳሳት አቅም እንደሌላቸው እና ይልቁንም የህወሓት መንግስት ራሱ የጋራ ምክር ቤቱን ተጠቅሞ የፓለቲካ ጥገናዊ ለውጥ በማድረግ ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት ያደረገው ሙከራ እንደሆነ የሚያስቡ ጥቂቶች አይደሉም።
ህወሓት ከኦሮሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በለዘብተኛ አቀራረብ ከአዲስ አበባ ጋር በተያያዘ የተነሱትን ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ በመመለስ ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምዝገባ ህግ በማሻሻል በህገወጥነት የፈረጃቸውን እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ያሉ ድርጂቶችን በማባባል የመንግስት አካል እስከማድረግ ድረስ ሊሄድ ይችላል የሚሉ ወገኖችም አልጠፉም። ሆኖም ኦነግ ካለፈው ተሞክሮው በመነሳት እና ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በኦሮሞ እንቅስቃሴ ምክንያት በተገደሉ ከሺ በላይ በሚሆኑ ኦሮሞዎች ደም ቆምሮ ለመውደቅ ከደረሰው የህወሓት መንግስት ጋር ተደራድሮ ነብስ ይዘራበታል ለማለት ያስቸግራል። ከቅርብ ግዜ ወደዚህ የኦሮሞ እንቅስቃሴ ብስለት እያሳየ ፤ በጥላቻ ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ወደ ጎን በማድረግ ከአማራ ህዝብ ትግል ጋር ትብብር እያሳየ መጥቷል።
———
ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ። ካነበቡ በኋላ ያጋሩ!