spot_img
Monday, December 4, 2023
Homeነፃ አስተያየትአድሏዊ ሐዘኔታ (Selective Sympathy) ምንድነው?

አድሏዊ ሐዘኔታ (Selective Sympathy) ምንድነው?

advertisement

Ephrem Esheteከኤፍሬም እሸቴ
ነሃሴ 27 2008 ዓ ም

አድሏዊ ሐዘኔታ (Selective Sympathy) ማለት ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው ሁለት ወገኖች ቢኖሩ፣ ለአንዱ አዝኖ ለሌላኛው አለማዘን፣ ወይም ለአንዱ የበለጠ አዝኖ ለሌላኛው የነካነካ ሐዘን፣ አላዘኑም ላለመባል፣ ዕንባ ሳይመጣ «ወይኔ ወይኔ» ብሎ እንደሚለቀሰው ወጉን ለማድረስ የሚደረግ ጥረት ዓይነት ነው።

ይብዛም ይነስም ሁሉም ሰው ለአንድ ጉዳይ እኩል አያዝንም። በተለይም ዓለማችን የመከራ መአት በሚወርድባት በዚህ ዘመን፣ በዓለም ላይ ያለው መከራ ሁሉ እኩል ዋጋ አያገኝም፣ ሞትም ሁሉ እኩል ትኩረት አይሰጠውም። ሁሉም ነገር አድሏዊነት ያለበት በሚመስል መልኩ በግልጽ የሚታይ ነገር ነው።

እያሉ ምርር ብለው ይጠይቃሉ።

ወደ አገራችን እንኳን ብንመጣ፣ ለረዥም ዓመታት ብዙ መከራ በሕዝቡ ላይ ሲወርድ ከርሟል። አንዳንድ ሰዎች ግን መከራው ከጆሯቸው አልፎ ውስጣቸውን አይኮረኩረውም። ሰዎቹ ክፉ ሰዎች እንዳልሆኑ እናውቃለን። ነግር ግን ኃዘኔታው ከልባቸው ሳጥን ተፈልቅቆ ያልወጣበት ምክንያት ምንድነው? በሌላ ጊዜ ግን እነዚሁ ሰዎች ተወልደው ባደጉበት፣ ዘመድ ወዳጆቻቸው በሚኖሩበት አካባቢ ያው ችግር መከሰት ሲጀምረ ስሜታቸው ይቀየራል። የሰዎቹ ችግር እጅጉን ውስጣቸውን ሰብሮ ይገባል። ለሌሎቹ አላዘኑም ለነዚህኞቹ ግን አዝነዋል። ለምን?

1ኛ. አንድ ሰው ለሌላው ያለው ኃዘኔታ ቶሎ እንዲሰማው የቅርብም ይሁን የሩቅ የደም ትስስር ብዙ ወጋ አለው። አውሮፓ ውስጥ ለተከሰተው አደጋ አሜሪካኖች ቶሎ ምላሽ ሰጥተው ነገር ግን የመካከለኛ ምስራቁ ላይ ፍንክች የማይሉት አንድም ከአውሮፓውያን ጋር ባላቸው የደም ትስስር ምክንያት ነው።

አሜሪካ የሁሉም አውሮፓ አገሮች ዝርያዎች ድብልቅ ናት። በፈረንሳይ ለሚደርሰው አደጋ ፈረንሳውያን-አሜሪካውያን ቶሎ ቢያዝኑ ወይም ቤልጅየም ዝርያ ያላቸው አሜሪካውያን ቶሎ አጋርነታቸውን ቢያሳዩ አይደንቅም ማለት ነው። የሰው ልጅ እንዲህ ነው።

በቤተ ክርስቲያን የሚዜመው የጥር ሥላሴ «ነግሥ» (ነግሥ ዘጥር ሥላሴ)
«ሠለስቱ ነገሥት ይለብሱ ነደ፣
ወይዐጸፉ በረደ፣
አሐዱሰ ወልድ ሶበ እማርያም ተወልደ፣
በለቢሰ ሥጋ ኮነነ ዘመደ፣
ወአስተርአየ እምህቡዕ ገሃደ።» ይላል።

«በለቢሰ ሥጋ ኮነነ ዘመደ» በምትለዋ «ሥጋ በመልበሱ (ስለለበሰ ወይም ሰው ስለሆነ) ዘመዳችን ሆነ» ሲል ስለ ክርስቶስ የተናገረውን ነው ማንሣት የፈለግኹት። እኛን መሰለ ያለበትን። ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ነው በተለየ አካሉ ወደዚህች ምድር የመጣው። እናም ሊቁ «ዘመዳችን ሆነ» አለው። ያገራችን ሰው «ትንሽ ሥጋ እንደመርፌ ትወጋ» እንደሚለው ማለት ነው። ሰው ሆኖ ለራስ ወገን ማድላት የሰው ጠባይ ነው። ይህንን ጠባይ የሚያሸንፍ ሰው በርግጥም ታላቅ ሰው ነው።

ኃዘኔታችን የሚቀሰቀስበት 2ኛው ምክንያት እነርሱ የገጠማቸው ዓይነት ችግር ገጥሞን ከነበረ ችግራቸውና ኃዘናቸው እኛንም ቶሎ ሊሰማን ይችላል። ያልተራበ ያልተጠማ ሰው ስለመራብ እና ስለመጠማት እንደማያውቀው ሁሉ ያልተቸገረ ሰውም ስለ ችግረኛ ሊገባው አይችልም። ኃዘንም ሊሰማው አይችልም። አንዱ ባለቅኔ እንዲህ አለ።

«አብን ተዉትና ንገሩት ለወልድ፣
ተገርፏል ተሰቅሏል እርሱ ያውቃል ፍርድ።»

ከፍ ብለን ከሦስቱ አካላት መካከል በተለየ አካሉ ሰው የሆነው ክርስቶስ ነው እንዳልነው ሁሉ ሰው ሆኖ ብቻ ሳይቀር ስለ እኛ የተገረፈው፣ የተቸነከረው እና በመስቀል ላይ የተሰቀለው በተለየ አካሉ እግዚአብሔር ወልድ ስለሆነ ባለቅኔው ይህንን ሐሳብ አኳሽቶ ያቀርበዋል። በነገረ ሃይማኖት አብና መንፈስ ቅዱስ ከወልድ የተለዩ እንዳልሆነ የሚያውቀው ባለቅኔው መከራን የሚያውቃት መከራን የተቀበለ መሆኑን ለማሳየት ወልድን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ለይቶ «ለወልድ ብቻ ንገሩት» ይለናል። ሰሙ ሳይሆን ወርቁን ስለምንረዳ ትርጉሙ ይከሰትልናል። ያልተነካ ግልግል ያውቃል አለ ያገራችን ሰው።

በሦስተኛ ደረጃ የአይዲዎሎጂም ሆነ የሃይማኖት አንድነት አንዱ ሰው ለሌላው ለማዘን ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ከተለያዩ አጋጣሚዎች መገንዘብ እንችላለን። አጼ ካሌብ በናግራን (በየመን) ያሉ ክርስቲያኖች መከራ እየደረሰባቸው እንደሆነ ሲሰማ መከራቸው ተሰምቶት ጦሩን ጭኖ፣ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ የመን ሄዷል። ጠላቶቻቸውንም ተበቅሎላቸዋል። በግብጽ ያሉ ክርስቲያኖች በአረማውያን ሲገደሉ በኢትዮጵያ ያለን ክርስቲያኖች ሁል ጊዜም እናዝናለን። በሌላውም እምነት እንደዚያው ነው።

ብዙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አሉ። የቱርኩ መሪ በቅርቡ የተደረገበት መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እጅጉን ያሳሰባቸው፣ ኋላ የተገኘው ውጤትም ያስደሰታቸው ሙስሊም ወንድሞቻችን በሰፊው ሲወያዩበት እንደነበር ከፌስቡክ ተከታትለናል። በወቅቱ «የቱርኩ መሪ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲህ ታዋቂ መሆኑን አላውቅም ነበር?» ላልኩት ሐሳብ አንድ ሙስሊም ወንድም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቶኝ አመስግኜዋለኹ።

በተጨማሪም አይዲዎሎጂ ከእምነት ባልተናነሰ የደስታም ሆነ የኃዘን ተጋሪ ሊያደርግ ይችላል። በዘመነ ሶሺያሊዝም አገራችን በሶማሊያ በተወረረች ጊዜ በዓለማቀፋዊ ወንድማማችነት መርሕ መሠረት ኩባውያን ደማቸውን አፍስሰውልናል። ኮሪያዎችና ሶቪየቶች ከጎናችን ቆመዋል። ያው ኀዘናችንን ተካፍለዋል ማለት ነው።

በአራተኛ ደረጃ፤ የጥቅም ትስስርም የአንዱ ኃዘን የሌላውም ኃዘን እንዲሆን ያደርገዋል። አልቃሽ «ማን ይመግበኝ፣ ማን አይዞህ ይበለኝ» እያለ ቢያለቅስ አንድም የሞተው ሰው ምን ያህል ደግ እንደነበር እያወሳ ነው፤ አንድም የሱንም የወደፊት ጉዳት እየነገረን ነው። አይጠቅም-አይጎዳ ዓይነት ለሆነ ሰው የሚታዘነውና፤ ሰብሳቢ፣ ረጂ፣ የክፉ ቀን ደራሽ ለሆነ የሚታዘነው መቼም አንድ አይደለም። ሰው እንደዚህ አውቆትም ይሁን ሳያውቀው ጥቅሙን ተከትሎ ይደሰታል፤ ጥቅሙን ተከትሎ ያዝናል።

ከዚህ ሁሉ ባሻገር ደግሞ፣ ዘመኑ የፈጠራቸው ሚዲያዎች በሚሰጡት እና በሚነሱት ትኩረት ምክንያት አንድ ችግር ሞቅ ያለ ኃዘኔታ ወይንም የቀዘቀዘ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል። በሰማነው መጠን እናዝናለን፣ ባልሰማነው መጠን አናዝንም። የ1977 ዓ.ምሕረቱ ኢትዮጵያ ረሃብና ችጋር መላውን ዓለም ያንቀሳቀሰውና የኃዘኔታ ጎርፍ ያወረደልን ሚዲያው ትልቅ ትኩረት ስለሰጠው ነበር።

ሰው እንደመሆናችን ከላይ በዘረዘርናቸው በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያት ለአንዱ አዝነን ለሌላው ላናዝን ንችላለን። ይሁን እንጂ ለተጎዳ ሁሉ፣ ኃዘኔታ ለሚያስፈልገው ሁሉ ያለ አድልዎ ማዘን የትልቅ ሰውነት ምልክት ነው። ፊት አይቶ አለማድላት/አለማዳላት እና የሰው ዘር በመሆኑ ብቻ፣ ቀረብ ካደረግነውም ወገናችን ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ ችግሩን እንደራስ ችግር ወስዶ ማዘን ትልቅነት ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ የመከራ መአት በሚወርድባት በዚህ ዘመን ማንንም ከማን ሳንለይ ለሁሉም ወገናችን ማዘንን፣ በችግራቸው ጊዜ መድረስ፣ ቁስላቸውን መጠገንን፣ ዕንባቸውን ማበስን ልንተገብር የሚገባበት የቁርጥ ቀን ነው። ኃዘናችን ግን ጊዜያዊ ነጥብ ለማስቆጠር ሳይሆን ከእውነት ይሁን። በምንም ይሁን በምን ምክንያት ለሚሰቃየው ወገን ያለ ምንም ልዩነት እንዘንለት። ይህ የችግር ጊዜ አልፎፐ በሰላም ለመኖር ያቺን የሰላም ቀን እንመኝ።

ይቆየን

ኤፍሬም እሸቴ በተለያየ መንገድ በማህበራዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ለአንባብያን በርካታ ቁምነገር አዘል ጽሁፎችን በማቅረብ ይታወቃል። በ በአደባባይ የጡመራ ገጽ ላይም ይጽፋል። ኤፍሬም እሸቴን በፌስ ቡክ ለማግኘት ይሄንን ይጫኑ
____
ካነበቡ በኋላ ያካፍሉ ፤ የቦርከናን ፌስ ቡክ ገጽ “ላይክ” ያድርጉ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here