ጳጉሜ 1 2008 ዓ ም
“የኢትዮጵያ አርበኞች አንድነት ግንባር የጦር ክንፍ ዋና አዛዠ ቶውት ፖል ቾይ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በመቀበል ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመስራት ተስማማ” በሚል ዛሬ የህወሃት መንግስት ዛሬ በቴሌቭዥን እንዳሰራጨ ይታወቃል። ጉዳዮን ከበድ አድርጎ ለማቅረብም
ቶውት ፖል ቾይ አስው ስለተባለው ሰራዊት ፤ ተደረገ ስለተባለው ድርድር እና ስለ ፖለቲካ ማንነቱ ቦርከና ከታማኝ ምንጭ ያገኘው ዜና አለ።
ከፖለቲካ ታሪኩ ለመጀመር ያህል ቶውት ፖል ቾይ በደርግ መንግስት የጋምቤላ የኢሰፖ አንደኛ ጸሃፊ ሆኖ የሰራ ፤ ቀደም ሲልም በደህንነት ውስጥ የሰራ ሰው ነው። ከደርግ መንግስት ውድቀት በኋላ በኬኒያ በስደት የቆየ ሲሆን ፤ እዚያ በነበረበት ወቅት ቀደም ሲል “ጥቁር አንበሳ” በሚል ሰራዊት ለማደራጀት ከተደረገ ሙከራ ጋር በተያያዘ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ኢትዮጵያውያንን በጉዳዮ ሲያናግር እና ሎጂስቲክ ሲያሰባስብ የቆየ ሰው ቢሆንም ፤ ብዙ ሰዎችን ተስፋ ያስቆረጠ ወደ አጭበርባሪነት ወሰድ የሚያደርገው የፖለቲካ ባህሪ እንደነበረው ከሰውየው ጋር ትውውቅ የነበራቸው ታማኝ የቦርከና ምንጮች ይናገራሉ። በኬኒያ የስደተኞች መንደር የሳሙና ፋብሪካ ነገር ተቋቁሞ ፖል ሲመራው ብዙ ሳይቆይ ከጥቅም ውጭ ሆኗል።
ከዚያም በኋላ የቦርከና ምንጭ ስሙን በትክክል ካላስታወሰው አንድ የኦሮሞ ጄኔራል ጋር ጦር ተደራጂቶ ፤ ባልታወቀ ሁኔታ መረጃ ሾልኮ በወያኔ ተከበው ጥቃት እንደደረሰባቸው እና ቶውት ፖል ቾይ ከከበባው ባልታወቀው ሁኔታ አምልጦ ወደ ናይሮቢ ተመልሶ እንደነበርም የቦርከና ምንጭ ጨምሮ ገልጿል።
ከዛ በኋላ የአርበኞች አንድነት ግንባር አደራጃለሁ በሚል ቢሞክርም ፤ የረባ ነገር ማድረግ ሳይችል በወሬ ብቻ እያስወራ በኬኒያ ሩይሩ እንደኖረም ታውቋል። የሚቆጠር እና ቦታ የያዘ የራሱ ሰራዊት እንዳልነበረውም የዚህ ዜና ምንጭ ያብራራል። ይልቁንም ቶውት ፖል ቾይ ወያኔ ከሚደግፈው የደቡብ ሱዳን አንጃ ጋር ግንኙነት እንደነበረው ፤ ምናልባትም ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ሰራዊት ማሳየት ቢኖርበት እንኳ ከዚያ ከደቡብ ሱዳን አንጃ ውጭ ሊያሳይ የሚችለው ነገር እንደሌለ ነው።
ህወሓት በዚህ ቀውጢ የፖለቲካ ቀውስ ወቅት ቶውት ፖል ቾይን ወደላይ ሰቅሎ ከግዙፍ የታጠቀ የፖለቲካ ኃይል ጋር ተደራድሮ እንዳሳመነት አድርጎ ለማሳየት ቢሞክርም ፤ ከዚህ በፊት ሰውየው ቢያንስ ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ሄዶ እንደነበር እና ወያኔ ይልቁንም ንቆ ትቶት እንደነበረ የዚህ ዜና ምንጭ ስለጉዳዮ በቅርበት የሚያውቁ ሰዎችን በስም ጠቅሶ ያስረዳል። በቅርቡ ቶውት ፖል ቾይን እና በቪዲዮው ከጀርባ የሚታየውን ሰው ( ጌታነህ ዘለቀ ይባላል) በሆቴል ውስጥ እንዳስቀመጣቸውም ታውቋል።
ጌታነህ ዘለቀ የሚባለውም በደርግ ዘመን ገራፊ የነበረ እና በኋላም በናይሮቢ ኬኒያ የቤት ሰራተኛ እና ቤት የሚያፈላልግ ደላላ ሆኖ እንደሰራ ለማወቅ ተችሏል።
ቶውት ፖል ቾይን አለው የተባለው አርበኛ ድርጂት በኤርትራ መሽጎ እየተፋለመ ካለው የአርበኞች ግንባር ሰራዊት እና የፖለቲካ ኃይል ጋር ምንም የሚያገኛው ነገር የለም።
በጉዳዮ ላይ ተጨማሪ ዜና እንደተጠናቀረ ይቀርባል።
—————
ቦርከና፤ በፌስ ቡክ ላይክ ማድረግ አይርሱ! ያጋሩ።