spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትተዋት ፖልና ኢአአግ ማን ናቸው? ዓለማየሁ መላኩ

ተዋት ፖልና ኢአአግ ማን ናቸው? ዓለማየሁ መላኩ

ዓለማየሁ መላኩ ከአውስትራሊያ

ጳጉሜ 3 ፤ 2008 ዓ ም

ተዋት ፖል ከአንድ የጋምቤላ ባላአባት እና ዳኛ የሚወለድ እና የንጉስ ኃይለሥላሌ ዘመን የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት አባል እና ወንጀል መርማሪ ግለሰብ ነበር።

የ1966 የካቲት አብዮት ትምህርትና ልማት ባልተዳረሰባቸው አካባቢ የሚገኙ ብሄረሰቦችን በአብዮቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከየብሄረሰቡ ትንሽ የተማሩ ልጆችን ፈልጎ ንቃት በመስጠት የአካባቢውን ሕዝብ እንዲረዱ ባለው ዓላማ መሠረት በ1973 ዓ ም የደርግ መንግስት ከኢሉባቦር ኢሠፓአኮ ኮሚቴ ተመርጦ ወደ የካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት እንዲመጣ ተደርጎ የተሰጠውን መደበኛ የኢሠፓአኮ የመጀመሪያ ካድሬነት ኮርስ አጠናቆ ከተመረቀ በኋላ ወደ ኢሉባቦር ክ/ሀገር ተመለሰ።

ከዚያም እዚያው እየሰራ ቆይቶ በ1980 ዓ ም ጓድ ፀጋየ ጋቢሣ የጋምቤላ ኢሠፓ ኮሚቴ 1ኛ ጸሃፊ የካቲት 66 የፖለቲካ ትምህርት ቤት ዲፕሎማ ኮርስ ለመካፈል ከቦታው ሲነሳ ተዋት የጋምቤላ አውራጃ ኢሠፖ ኮሚቴ 1ኛ ጸሃፊ ሆኖ ተመደበ። ከዚያም ታህሳስ19 ቀን 1981 የሃገሪቱ አስተዳደራዊ መዋቅር በ5 ራስ ገዝ እና በ25 ክልሎች ሲዋቀር ጋምቤላ የክፍለ ሀገር ደረጃ በመሰጠቱ እሱም ከአውራጃ 1ኛ ጸሃፊነት ወደ ክልል ኢሠፓ አንደኛ ጸሃፊነት ተሹሞ እስከ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ ም ድረስ ቆየ። በ1983 በደቡብ ሱዳን SPLA ይዞታ ሥር ከቆየ በኋላ በ1985 ዓ ም ወደ ኬኒያ መጣ። ከዚያም በወቅቱ በኬኒያ የሚገኙ ከ20 በላይ የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ከ5 በላይ ጄኔራሎ መኮንኖች ለሃገሪቱ መጻዒ ዕድል ማሰብ ትተው ለራሳቸው የወደፊት ኑሮ እየተሯሯጡ ባሉበት ወቅት በአጭር ታጥቆ ወያኔዎችን ለመዋጋት ቆርጦ በመነሳት ፤ ለዚህ ደግሞ የሚያበቃ ምንም መፍትሄ በማጣቱ በቀጥታ ወደ ዚምባቡዌ በመሄድ የቀድሞ የኢትዮጵያን ፕሬዝደንት መንግስቱ ኃይለማርያምን በማግኘት ፤ ሌሎችም ውጭ ካሉት እና ከእርሳቸው ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ግለሰቦች በመገናኘት በ1986 ዓ ም መንግስቱን የድርጂቱ ሊቀመንበር በማድረግ ኢአአግ የተባለ ድርጂትን ለመመሥረት ከሌሎችም አባላት ጋር ተንቀሳቀሰ። በወቅቱ ስለሁኔታው ግንዛቤ ያላቸውንና በገንዘብም የሚረዱ ሰዎችን በመፈለግ ድርጂቱ ተጨባጭ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ታግሏል።

በዚህም መሰረት ከዮጋንዳ አቶ ኢያሱ ሲራክ የተባሉ ባለሃብና ቀደም ሲል ኢዲሐቅ ባሰባሰባቸው የጦር አባላት መካከል የኢዲሐቅ እንቅስቃሴ በመዳከሙ ሌላ የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ሲፈልግ የነበረውን ዘለቀ ጀበሮ የተባለ ግለሰብ እንዲቀላቀላቸው ከፕሬዝዳንት መግስቱ በተሰጠው መመሪያ መሠረት ወደ ካምፖላ መጥቶ በመገናኘት ወደ ናይሮቢ ተመለሰ ፤ የካምፓላ ኮሚቴ ሁኔታዎችን መልክ ባለው መንገድ በማዘጋጀት

ሀ) የድርጂቱን ፕሮግራም በማርቀቅ
ለ)መሳሪያ የሚገኝበትን ሃገር በማፈላለግ
ሐ)አባላትን በመመልመል ሰፊ ሥራ ከተሰራ በኋላ ፤ በአስተማማኝ ዝግጂት እና በከፍተኛ ሚስጥር የጉዞ እንግስቃሴ እንዲጀመር ተወስኖ በ1987 ዓ ም የዛሬው ሳልቫኪር በሰጠው መሳሪያ ትግሉን ለመጀመርና ከውጭ የተገዛው መሳሪያ ከኋላ እንዲከተል ሆኖ ፤ ከ270 ምርጥ አባላት መካከል 59 አባላትን ይዞ ጉዞ ወደ ደቡብ ሱዳን ከፓይታ ግንባር አቀኑ። በዚህም ጉዞ ቱዋትፖል ቻይ የግንባሩ ጦር አዛዥ እና የደህንነት ኃላፊ ሆነ።

ዘለቀው ጀበሮ የግንባሩ ም/ጦር አዛዥ እና የፖለቲካ ኃላፊ ፤ ሌሎች መኮንኖች የመረጃ ፤ ስልጠናና የአዛዥነት ቦታ ተመድበው ተዋቀሩ።

በዚህ መካከል ጦሩን ከፖይታ ለማንቀሳቀስ ተሽከርካሪ እየጠበቁ እያለ አንድ ድንገተኛ የሆነ ክስተት ተፈጠረ ይላል ለጊዜው ስሙን ለመግለጽ ያልፈለገ በጊዜው ከቡድኑ አንዱ የነበረ ከፍተኛ የጦር መሆንን። ይኸውም ከኮሚኒዝም ውድቀት ማግስት የአሜሪካንን ህልውና የሚፈታተን የእስላሚክ ፋንዳሜንታሊዝም በሩቅ ምስራቅ ፤ በመካከለኛ ምስራቅ አልፎም በአፍሪካ ሱዳን ሪፑብሊክ ላይ የሚያርፍ የሃሳብ መስመር ስለተሰመረ እና ሆሳማ ቢንላደን የሚባል የአሜሪካ ጠላትም ካርቱም በመኖሩ አንድ የኬሚካል ፋብሪካም እየተገነባ መሆኑን CIA ስለደረሰበት በቀጥታ በወቅቱ አዲስ ትውልድ (new breeds) ያሏቸውን የኢትዮጵያ ፤የኤርትራ ፤ እና የዮጋንዳ መሪዎችን በማስተባባር ከየኢ-ጂባ ፤ በኩምሩክ ዳማዚንና በከሰላ ግንባር ዮጋንዳ ፤ መለስ እና ኢሳያስ ከፍተኛ የውጊያ ግንባር እንዲከፍቱ በመወሰኑ ጋራንግ ወደ አዲስ አበባ ተጠርቶ በሄደበት ቦታ ለሳልቫኪር ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሄደውን የመንግስቱ ኃይለማርያም ጦር በአስቸኳይ በሁለት ቀን ውስጥ እንድትመልሰው ተብሎ ይነገረዋል። በተሰጠው የጦር ሜዳ ትዕዛዝ መሰረት ጦሩ ተጭኖ በውድቅት ሌሊት ካኩማ የስደተኞች ካምፕ ኬኒያ ይወረወራል።

ከዚያም የጦሩ ሞራል በመሰበሩ እና እነ አቶ እያሱም ከዚህ ድርጂት ራሳቸውን ወደ ሌላ ግንባር ስላዞሩ ክፉኛ የመበታተን አደጋ ቢኖርም ትግሉን እንደገና በማቀናጀት እነ ዘለቀ ጀበሮ በካምፓላ ፤ ቱዋት ፖል በናይሮቢና በካኩማ እንደገና አዋቅረው ከሰሜን ሱዳን መንግስት ጋር ከሆስኒ ሙባረክ የግድያ ሙከራ ጋር በተያያዘ የሱዳን እና የኢትዮጵያ መንግስት መካከል የተፈጠረውን ክፍተት በመጠቀም ኢድሐቅ ከሌሎች ጋር ግንባር ለመፍጠር ፤ የኢትዮጵያ አንድነት ግንባር “ኢአግ” ፤ “ኢአአግ” ከከፋኝ አንድ ቡድን እና ከጎሹ ወልዴ መድህን ጋር በመዋሃድ “የህብረት ግንባር” የሚል ድርጂት በመመስረት ካርቱም ላይ ትግል ጀመሩ።

ይሁን እንጂ ትግሉን ሁለት አደጋዎች ገጠሙት ፤

1) ጀኔራል ኃይለ መለስ በሥራ ክፍፍል ወቅት የራሳቸው የአካባቢ ልጂ የነበረውን መ/አ ሞላ አባተን ከፍተኛ ቦታ በመስት ቱዋት ፖልን ገፍትረው ያልረባ የስራ ድርሻ ይሰጡታል

2) የሻቢያና ወያኔ (የኢትዮ-ኤርትራ) ጦርነት ይፈነዳል። በእነዚህ ቅራኔ ምክንያት ቱዋት አኩርፎ ባለበት ሁኔታ ኃይሌ መለስበወያኔ ትዕዛዝ ተይዞ ይታሰራል። ድርጂቱም ስራውን እንዲያቆም ሲታዘዝ ፤ ቱዋት አጋጣሚውን በመጠቀም እና ኮ/ል ጋልዋክ የተባለ የወቅቱ የሱዳን ምክትል የደህንነት ሚኒስተር የኑዌር ተወላጂ በመሆኑ ለቱዋት በሰጠው ሽፋን ቱዋት የተወሰኑ የራሱን አባላት ከአዘጋጀ በኋላ ከዛሬ ጀምሮ መንግስቱ ኃይለማርያምን እና ካሣ ከበደን ከድርጂቱ አባረናል የሚል መግለጫ ይበትናል። እነ ካሣ ከበደም በወቅቱ “የነጻ ሬዲዮ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ” በተባለ ራዲዮ አንድ ተከታይ ብቻ ያለው ግለሰብ ሰለሆነ ጦሩ ሳይሸበር ራሱን በማደራጀት ተከታታይ ትዕዛዝ እንዲጠብቅ መመሪያ ተላለፈ።

ቱዋትም ከካርቱም ወደ ናይሮቢ በመምጣት የተወሰኑ አባላቱን ወደ ኤርትራ ይዞ በመግባት የዛሬውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ፈጠረ። ካምፓላ የቀሩትም ከሌሎች ድርጂቶች ጋር በመዳበል ከኢንጂነር ቅጣው እጂጉ ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ግንባር አቋቋሙ። ቱዋትም ከአስመራ አርበኞች ግንባር ተባሮ ወደ ናይሮቢ ተመለሰ ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአስመራውም ተጠናክሮ ከግንቦት 7 ጋር የካምፓላውም በሌላ መንገድ በመታገል የቆዮ ሲሆን ቱዋት በየትኛው፣ አካል ትግል ውስጥ የሌለ ፤ በሪያክ ማቻር አካባቢ ያደራጀው ሁለት የመቶ ጦርም በወያኔ ተመቶ ከጫዋታ ውጭ ሆኖ ቤተሰቡን በሞላ ወደ አውስትራሊያ በመላክ እርሱ በሌላ የኑሮ ዲል ውስጥ የቆየ ነው።

ጫካ ያሉ አባላት ከሞቱና ከተበታተኑ በኋላ እርሱ ወደ ሌላ ትርፍ ማግኛ ስፍራ ተዛወረ። በዚህም መሰረት JARCH capital እና JMG ከመሳሰሉ የነዳጂ ፍለጋ እና ቁፋሮ ካምፖኒዎች ጋር በመቆላለፍ በወር $10,000 በላይ በማግኘት እና በአሜሪካ የመኖሪያ ፈቃድ በማግኘት ከአፍሪካ አሜሪካ በመመላለስ ኑሮውን በአየር ላይ የሆነ ግለሰብ ከመሆኑም በላይ ላለፉት 11 ዓመታት ከትግሉ ከተሰናበተ ቆይቷል። ይህም ብቻ ሳይሆን ከሱ ከተገነጠሉ እና በርትተው ለመታገል የቆረጡትን ታጋዮችና ድርጂቱን በማስመታት ለወያኔ ከፍተኛ ዋጋ ያስገኘ ሰው ነው።

ዛሬ ግን የኢአግ ጦር ጠቅላይ መምሪያ የሚል ደብዳቤ /letter head/ የት ያለ እና ምን ያህል የጦር ኃይል ያቀፈ እንደሆነ ያስቃል። የእሱን ያለፍት 11 ዓመት የትግል ሁኔታና የድሎት ኑሮ ለማወቅ ፤ ያለ ሰራዊት ጄኔራል ማዕረግ መሾሙን Duncan Clarke “Africa Crude Continent ; The struggle for Africa’s oil Prize” በሚል ከጻፈው መጽሃፍ ከገጽ 504-508ን ብቻ ማንበብ ይበቃል።

የአቶ ቱዋት ፖል የትግል ሁኔታ ይኽ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ወደ ግራ ወይንም ወደ ቀኝ ዞር እላለሁ ቢሎ ከፍተኛ የጦር ወንጀሎች የሚከተሉ መሆኑ አቅቀው ለወያኔዎች የሸቀጡት የውሸት ጦርና ሁለት ጓዶቹን አስረክቦ ወደ ምሽጋቸው ወደ አሜሪካ እንዲያቀኑ እንመክራለን።

ሀቀኛ ትግልና ሀቀኛ ታጋዮች ያሸንፋሉ!

—————
ካነበቡ በኋላ ያጋሩ ፤ በፌስ ቡክ ገጻችን ላይ ላይክ ያድርጉን
ጽሁፍ መላክ ከፈለጉ በeditor@borkena.com መላክ ይቻላል።

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here