በመስከረም አበራ
መስከረም 2 2009 ዓ ም
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ መባቻ ከዘመነ መሳፍንት ማክተም ጋር የሚቆራኝ ነው፡፡የሃገራችንን የቀደመ ግርማ አኮስሶ፣ የጦር አለቆች የረብሻ ምድር አድሮጓት የኖረው፣ በታሪክ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የሚታወቀው ወቅት የቆየበት ጊዜ ዘለግ ያለ በመሆኑ ተክሎት ያለፈው ችግር ስርም ጠለቀ ያለ ነበር፡፡በተለይ ከዘመነ መሳፍንት በፊት የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት በታላቅ ሃገር ላይ ታላቅ መሪ የመሆን አልፎም ቀይባህርን ተሻግሮ የማስገበር የታላቅነት ምኞት በትንንሽ መንደሮች ትንሽ አለቃ ለመሆን ወደ መቃተት የንዑስነት ምኞት አንሶ ነበር፡፡ ይህ የንዑስነት ዘመን መንደርተኛነት በሃገራዊነት ላይ የገነነበት፣ መነጣጠል አብሮነትን የረታበት፣የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሰለለበት ዘመን ነበር፡፡ ይህ የድቀት ዘመን ያከተመው ከወደ ጎንደር በተነሳ የቀደመ ታላቅነትን የመናፈቅ ሃሳብ ነበር፡፡ስር የሰደደው የዘመነ መሳፍንት ዘመን የንዑስነት ምኞት እና የመከፋፈል አባዜ በቋራው ካሣ ታላቅነት የመናፈቅ ከፍ ያለ እሳቦት ፍፃሜውን አገኘ፡፡የካሣን ውድ ህይወት ቢነጥቅም በዘመነ መሳፍንት የመንደርተኝነት ዝንባሌ እልም ስልም ሲል የባጀው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ወደ ህዝብ ልቦና ተመለሰ፡፡
ሆኖም ከዘመነ መሳፍነት ማክተም ብዙ ዘመን በኋላ ኢትዮጵያዊነት ሌላ ፈተና ገጠመው፡፡በተለይ ከኢህአዴግ ወደ ወንበር መምጣት በኋላ ኢትየጵያዊነትን የማቀንቀን ፖለቲካዊ አቋም፣ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ቱርፋቶች መስበክ፣ ስለኢትዮጵያዊ ወንድማማች/እህትማማችነት ማውራት እንደ መርገም ጨርቅ ያለ ነገር ሆኖ ኖረ፡፡የመርገም ጨርቁ ስም ደግሞ “ትምክህተኛ አማራነት” ነው፡፡የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠቅመው ለአማራው ብቻ ባለመሆኑ ኢህአዴግ አማራ ከሚላቸው ሰዎች ሌላም በሁሉም የሃገራችን ጥግ ለኢትዮጵያዊነት የሚቃትቱ ኢትዮጵያዊያን በብዛት አሉ፡፡ኢህአዴግ ለእነዚህም ስም አለው – “የአማራ ተላላኪዎች” ሲል አንድ ሰው ስለ ሃገሩ ህልውና እና የሃገር ባለቤትነት ጥቅም በራሱ ጭንቅላት አስቦ ይረዳ ዘንድ የማይቻል አስመስሎት ቁጭ ይላል፡፡ እውነታው ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ትልቅ ስፍራ ያለው ነው፡፡ አከራካሪው ነገር ኢትዮጵያ እንዴት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሆነች እናት ትሁን በሚለው ታሪክ ከማቃለል ይልቅ እያከማቸው በመጣው የቤት ስራ ላይ ይመስለኛል፡፡ከእውነት ጋር ብዙ የማይስማማው ኢህአዴግ ታዲያ ይህን የታሪክ ክፍተት ለተፈጠረበት ኢትዮጵያዊነትን የማደብዘዝ እኩይ አላማ በደንብ ተጠቀመበት፡፡ አገዛዙ በቆይታው ስኬታማ የሆነበት ዋናው ጉዳይ ይህን አኩይ አላማ ከግብ ለማድረስ የሮጠው ሩጫ ይመስለኛል፡፡
ህወሃት አስራ ሰባት አመት ጭንጫ ገደሉን ረግጨ ቧጥጬ የታገልኩት ለብሄር ብሄረሰቦች መብት ስል ነው ባይ ነው፡፡ይህን ያስመሰክር የነበረው ደግሞ የአማራ ህዝብን ቅስም የሚሰብሩ ንግግሮች፣ ድርጊቶች በማድረግ ነው፡፡ ህወሃት ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊትም ሆነ ከመጣ በኋላ የፖለቲካ ግንዛቤው ጥግ የአማራን ህዝብ ማጥላላት፣ ያልሆነ ስም መለጠፍ፣ማሰር፣ማፈናቀል፣መግደል፣ ሰድቦ ለተሳዳቢ መስጠት ይመስለው ነበር፡፡ ለሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች መብት መቆሙን የሚያስመሰክረውም የጠየቁትን፣ራሱም በህገመንግስቱ የፃፈውን እስከ መገንጠል የዘለቀውን መብት በመተግበር ሳይሆን የአማራን ህዝብ በአደባባይ በማበሻቀጥ፣ ‘የድሮ በዳያቸውን’ (አማራን መሆኑ ነው) የማጥፋቱን ታዳጊነት ገድል በመተረክ ነው፡፡ የድሮው ይቅርና በቅርቡ የአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝን ወደ ስልጣን መምጣት አስመልክቶ አዛውንትነታቸውን የሚመጥን የንግግር ጭዋነት የሚያጥራቸው አዛውንቱ ስብሃት ነጋ ‘ሰውየውን መሾማችን አማራን እና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይን ከስልጣን አጥረገጥ የማጥፋታችን ምልክት ነው’ ሲሉ ጫካ የለከፋቸው የጥላቻ ክፉ ደዌ እያደር የሚብስ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ይህን ክፉ ጥላቻ ያረገዙት ህወሃትዎች የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን ለብቻቸው አንቀው መያዛቸው፣በመገናኛ ብዙሃን ይህንኑ የጥላቻ ስብከት ለማጧጧፍ እፍረትም ሆነ ሃላፊነት የማይሞክራቸው መሆኑ ደግሞ የነገሩን ውጤት በተለይ በአማራው ህዝብ ላይ ክፉ አድርጎት ኖሯል፡፡ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ከኢህአዴግ በኋላ ያለችውን ኢትዮጵያ እጣፋንታ አጨልመው የሚያቀርቡትም ከዚህ እውነታ ጋር በተያያዘ ነው፡፡የሰራውን የሚያውቀው ኢህአዴግ ደግሞ በዚህ ሃላፊነት በጎደለው ስራው ሊያፍር ሲገባው ይኩራራል፣ ‘ከሌለሁ ወዮላት ለኢትዮጵያ’ ሲል ያስፈራራል፡፡በሃገሪቱ ሌላ ፍጥረት ያልተፈጠረ ይመስል የእልቂቱ ተዋናዮች፣የሃገሪቱ እጣፋንታ ወሳኞች የአማራ አና የኦሮሞ ህዝብ እንደሚሆኑ ይተነብያል፡፡የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ለመገዳደል ብቻ የሚፈላለጉ ታሪካዊ ባላንጣዎች አድርጎ ውሸትን እጅግ ደጋግሞ እውነት ሊያስመስል ምንም አልቀረውም ነበር፡፡
ከንቱው ልፋት
የስሌት አውዳችን ጎሳን ማዕከል ያደረገ ከሆነ ህወሃት ወጣሁበት የሚለው የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ንዑስ ቁጥር ካላቸው ጎሳዎች ወገን ነው፡፡ እንደ እውነቱ ቢሆን የጎሳ ፖለቲካ መሲህ ነኝ የሚለው ህወሃት የሰፈሩን ልጆች ጠርቶ የወረረውን የፖለቲካ ስልጣን ለተላላቆቹ ኦሮሞ እና አማራ ጎሳዎች መልቀቅ ነበረበት፡፡ ይህን እንደማያደርግ ልቦናው የሚያውቀው ንዑሱ ህወሃት ታዲያ እንደ አማራጭ ያየው ስልጣኑ ለሚገባቸው ጎሳዎች እርስበርስ የመናቆር፣አይን እና ናጫ የመሆን የቤት ስራ መስጠት ነው፡፡ ለኦሮሞዎች የተበዳይነት ሙዚቃ ከፍቶ ሲያስቆዝም ለአማራው እንደጉተና የከበደ የበዳይነት ሸክም ጫነው፡፡ አማራው በተነፈሰ ቁጥር በእብሪተኛነት፣በጭካኔ፣በትምክህተኛነት እየፈረጀ ሁለተኛ ወደ ስልጣን ዝር ማለት የሌለበት እኩይ አድርጎ ያቀርባል፡፡
በትዝታ እንዲቆዝም የተደረገው ኦሮሞ ታዲያ አሁን ሊቀመጥበት የሚችለውን የፖለቲካ ስልጣን ወንበር ጥያቄ ረስቶ ቀና ብለው “አቤት” የማይሉትን አፄ ምኒልክን በመርገም፣በመውቀስ እንዲጠመድ ተደርጓል፡፡አፄ ምኒልክም መላውን አማራ ወክለው የሞቱ ይመስል ለእርሳቸው በተነሳው የጭቃ ጅራፍ አማራ የተባለው ሁሉ ይገረፍ ያዘ፣ ለምኒልክ የተከፈተ የበደል ሙዚቃ ለአማራ ሁሉ የሚበቃ የጥላቻ ስንቅ አስቋጥሮ በጎሪጥ ሲያስተያይ፣ አፍንጫ ሲመታ አይን እንዳያለቅስ እንባ አድርቆ ኖሯል፡፡ አማራውም በፊናው በዋናነት በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሌሎች ክልሎችም ለፍቶ ያፈራውን ንብረት ለቆ እንዲወጣ ሲደረግ ይህን ያደረገው ማን እንደሆነ ስለሚያውቅ በተዋለደው እና አብሮ በኖረው ህዝብ ላይ አፉን አላላቀቀም፡፡አማራነቱ ብቻ በደል ሆኖ ተቆጥሮ የሚገረፍበትን በትር ብርታት ስላወቀ አድርጎት የማያውቀውን አንገቱን መድፋት ተማረ፣ቅዝምዝምን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ ተሽሎት ወገኖቹ ሲታሰሩ፣ሲገደሉ፣ ከምድር ዳርቻ ሲሳደዱ አዝኖ እንዳላዘነ ሆኖ አለፈው፡፡ሽሽት የማያውቀው ህዝብ ሽሽት ለመደ፡፡ይሄኔ ነው እነ ስብሃት ነጋ፣ሳሞራ የኑስ እና መለስ ዜናዊን የመሰሉ የጥላቻ ሰባኪዎች ‘አማራን እንዳይነሳ አድርገን ቀበርነው’ ያሉት፡፡
ሰፊውን የአማራ ህዝብ ብቻቸውን ገድሎ ለመቅበር የንዑስነት አቅማቸው እንደማይፈቅድ የተረዱት ህወሃቶች ባለግርማውን የኦሮሞ ህዝብ መጠለያ ማድረግን መረጡ፡፡ ‘ከየት አመጣችሁት?’ ተብለው የሚጠየቁበት መድረክ የለምና የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ በኖረ የመረረ፣ የከረረ ጠላትነት እንዳላቸው ብቻቸውን በያዙት መገናኛ ብዙሃን ሲያላዝኑ ኖሩ፡፡ በሃሰት የተለወሰ የፈጠራ እና የጥላቻ መርዛቸውን መድሃኒት አስመስለው የሚያቀርቡበትን ስብከት ስለሚያረክስባቸው በሳይንሳዊ መረጃ ላይ የቆሙ የታሪክ ድርሳናትን አጣጣሉ፡፡እውነትን ለመፈለግ በየዋሻው የተሻጡ ‘ኦርጅናል’ የታሪክ መዛግብትን የሚያስሱ ኢትዮጵያ-በቀል የታሪክ ተመራማሪዎችን ፈተናቸውን አብዝተው ከሃገር አሰደዱ፡፡ ሰሞኑን በፕ/ሮ ፍቅሬ ቶሎሳ አዲስ መፅሃፍ ሽያጭ ላይ የተዘመተው ዘመቻ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ (ወደ ሚቀጥለው ገጽ ዞሯል፤ ከታች ገጽ 2ን ይጫኑ)