spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeአበይት ዜናበጎንደር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ቃጠሎ ሊያደርሱ ነበር የተባሉ ሰዎች ተያዙ

በጎንደር ከተማ በተለያዩ ቦታዎች ቃጠሎ ሊያደርሱ ነበር የተባሉ ሰዎች ተያዙ

ኢሳት
መስከረም 12 2009 ዓ ም

gonder-fire-plot-suspect

ላለፉት 4 ቀናት የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ላይ በምትገኘው ጎንደር ከተማ ትናንትና ዛሬ የገበያ ቦታዎችን፣ የንግድ ድርጅቶችን እንዲሁም መስሪያ ቤቶችን ሊያቃጥሉ ነበር የተባሉ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። ግለሰቦቹ በህወሃት የተላኩ መሆናቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ከትግራይ ክልል እንዲሁም ከመከላከያ ሰራዊት የይለፍ ወረቀት እንዳላቸው የአይን እማኞች ተናግረዋል።

የአንዲት ሴትና የአንድ ወንድ ወጣት መያዛቸውን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞውን ገልጿል።

በከተማው የተሰማሩት ወታደሮች ድረሰው ሁለቱንም ወጣቶች ወደ ፖሊስ ጣቢያ የወሰዱዋቸው ሲሆን፣ መርማራዎች ጉዳዩን በተመለከተ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ መግለጫ አልሰጡም።

ሴቷ ቤንዚንና ክብሪት ይዛ መገኘቷን የአይን እማኞች ይናገራሉ።

ለኢሳት የደረሱት የቪዲዮ እና የፎቶ ማስረጃዎችም ይህንኑ ያሳያሉ። ትናንት 4 ሰዎች መያዛቸውን ኢሳት መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ከ50 በላይ የሚሆኑ በህወሃት የደህንነት አባላት የሰለጠኑ ሰዎች ባህርዳር፣ ጎንደርና ደብረታቦር መግባታቸውን የተያዙት ሰዎች መናገራቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ህወሃት እንዲህ አይነት በህዝብ ውስጥ ጥርጣሬና ግጭት የሚፈጥር እርምጃ በመውሰድ ሊያገኝ የሚፈልገው የፖለቲካ ትርፍ ግልጽ አይደለም ሲሉ ያነጋገርናቸው ሰዎች ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሃት ኢህአዴግን አገዛዝ በመቃወም የሚደረገውን ህዝባዊ ትግል የብሄር ግጭት አድርጎ ለማቅረብ ሰሞኑን ነባር የህወሃት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ መግለጫዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል። ይህ አደገኛ አካሄድ የህወሃት ባለስልጣናቱ በአደባባይ በመገኛ ብዙሃን የተናገሩትን እውነትነት ለማረጋገጥ በሚል የተቀነባበረ ሳይሆን እንደማይቀር አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ግን የስራ ማቆም አድማው በጎንደር፣ ባህርዳር አዲስ ዘመን ለ4ኛ ቀን እንዲሁም በጎጃም በጅጋ ከተማ ለሁለተኛ ቀን በመካሄድ ላይ ነው።

በወረታ እና ደብረታቦር ተመሳሳይ የስራ ማቆም አድማ ትናንት የተጀመረ ቢሆንም፣ ወታደሮች ነጋዴዎችን ይዘው በማሰር ድርጅቶቻቸውን እንዲከፈቱ አስገድደዋቸዋል። አሁንም ድረስ አንከፍትም ያሉ ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸው እንደታሸጉባቸውና የንግድ ፈቃዳቻውን እንደሚነጡ የሚያስገድድ የማስጠንቀቂያ ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

በተለይ በወረታ ከተማ ፖሊሶች በአድማው ምክንያት የቆሙ ባጃጆችን ታርጋ እየፈቱ መውሰዳቸው አልበቃ ብሎ፣ ዛሬ ደግሞ ወንበሮችን በመፍታት በመኪና እየጫኑ ወስደዋል ።

በባህርዳር ከተማም እንዲሁም በርካታ አስገዳጅ ሁኔታዎች ቢኖሩም ህብረተሰቡ በአላማው ጸንቶ አድማውን ቀጥሎአል፡፡

በተለምዶ አዴት ተራ በተባለው የንግድ ስፍራ ከሚሰሩ ከፍተኛ ነጋዴዎች መካከል አምስቱን ማክሰኞ ጠዋት በማሰር ‹‹ ወደ ስራ ለምን አልገባችሁም? ›› የሚል ማስፈራሪያ አዘል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ነጋዴዎችም ‹‹ ለምን ያለጥፋታቸው ታስራላችሁ? ››በማለት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ከአንድ ቀን እስር በኋላ ትላንት 10 ሰዓት ላይ ተፈተዋል፡፡

አብዛኛውን ነጋዴ በሱቁ በራፍ ላይ በሚገኘው የንግድ መለያ(ታፔላ) ላይ የጻፈውን የስልክ ቁጥር ተመልክተው በመደወል ‹‹እኛ እንወዳችኋለን፡፡አሁን ለቆመው መንግስት ድጋፍ ብትሰጡ መልካም ነው፡፡ስለዚህ የንግድ ቤታችሁን እንድትከፍቱ እንጠይቃለን ›› በማለት የገዥው መንግስት አመራሮች ወደ እያንዳንዱ ነጋዴ ስልክ በመደወል ልመና እያሰሙ ነው፡፡

ልመናው አላዋጣ ሲል የንግድ ድርጅቶቻችሁን አልከፈታችሁም የሚል ማስጠንቀቂያ በንግድ ድርጅቶቻቸው ላይ እየተለጠፉ ነው።

ገነት አስማማው በምትባል ግለሰብ ለአንድ ነጋዴ በተጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ላይ “ ድርጅትዎን በመዝጋትዎ ምክንያት ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ ተነግሮዎት እና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያም ተሰጥቶዎት አሁንም ቢሆን ድርጅትዎን ከፍተው እያገለገሉ ባለመሆንዎና ከስህተትዎ ሊታረሙ ባለመቻሉዎ የተሰጠዎት የንግድ ፈቃድ ከ11/01/2009ዓም ጀምሮ እስከ 17/01/2009 ዓም ድረስ ፈቃድዎ ለ7 ቀናት የታገደ ሲሆን፣ ፈቃድዎ ታግዶ ከፍተው ሲሰሩ ቢገኙ በአዋጁ መሰረት ቀጣይ እርምጃ የምንወስድ መሆኑን በጥብቅ እንገልጻለን” የሚል ትእዛዝ ሰፍሮበታል።

በስራ ማቆም አድማ ላይ ያሉ የአባይ ማዶ ገበያ ነጋዴዎች ደግሞ ‹‹ ንብረታችንን እንደ ጎንደር ቅዳሜ ገበያ ሊያቃጥሉብን ይችላሉ ››በማለት ንብረታቸውን ሲያወጡ ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተጋጭተዋል፡፡በባህር ዳር ማህል ከተማ ትልቁ የቅዳሜ ገበያ የሚሰሩ ነጋዴዎችም ተመሳሳይ ስጋት እንዳላቸው እየተናገሩ ሲሆን፣ በአድማው የተበሳጨው የህውሃት መንግስት ገበያውን ሊያቃጥለው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

የክልሉ መሪዎች የህዝቡን አድማ ለማስቆም የሚወስዱት እርምጃ ለማክሸፍ አለመቻላቸው ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ውስጥ እንዲገቡ አድርጎዋቸዋል። ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ የተጋቡት ወታደሮች ኳስ የሚጫወቱ ወጣቶችን ሳይቀር እየያዙ ለማሰር እየሞከሩ ነው። ትናንት ቀበሌ ሰባት አካባቢ ኳስ ሲጫወቱ የነበሩትን ወጣቶች ለምን ተሰባሰባችሁ በማለት ሁሉንም አፍሰው ወደ በላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ለማሰር ሲዎስዷቸው የተመለከቱ እናቶች በጩኸት ህዝቡን በመሰብሰባቸው የአካባቢ ነዋሪ በነቂስ ወጥተው ‹‹ ምንም ሳያጠፉ ልታስሯቸው አትችሉም!! ›› በማለት ወጣቶችን ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተከራክሮ ፖሊስ ጣቢያ ካደረሱ በኋላ በህዝብ ጫና ሊያስፈታቸው ችለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ንጋት ላይም የመኪና ፍሰት በማይበዛባቸው መንገዶች ላይ ኳስ የሚጫወቱት ወጣቶችን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሰሩ ጎልማሶችን ‹‹ ለምን መንገድ ትዘጋላችሁ ?›› በማለት ሲያንገራግሩና እናስራለን በማለት ችግር ሲፈጥሩ አርፍደዋል፡፡

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here