መሐመድ አሊ መሐመድ
መስከረም 18 2009 ዓ ም
የህዝብ ንቅናቄ ጥሩ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር መንግሥትን ነቅንቆ ከእንቅልፉ ሊያባንነው ይችላል፡፡ ሰሞኑን እንደምናየው የወያኔ ሥርዓት እንደዋዛ ተንፈላስሶ ከተኛበት የህዝብ ንቅናቄ አባንኖት ተነስቶ ሲደናበር እያየን ነው፡፡ ሥርዓቱ ምቾትና እርጅና በተጫጫነው አኳኋን ከሸለብታው በደንብ ሳይነቃና የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በአግባቡ ሳይረዳ ተነስቶ ለመቆም እየተንገዳገደ ነው፡፡ ባንድ በኩል አርጅቻለሁ፣ በስብሻለሁ፣ እያለ በሌላ በኩል እታደሳለሁ ይለናል፡፡ በዚህ ሁኔታው ተጠናክሮ የመቆምና ወደፊት የመራመድ ዕድሉ በህዝቡ ንቅናቄ መጠንና ግፊት የሚወሰን ይሆናል፡፡
የህዝብ ንቅናቄ መንግሥትን ከማባነን ባለፈ ከተሰቀለበት የሥልጣን ማማ ላይ ነቅንቆ ሊጥለውም ይችላል፡፡ ይህም በዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች የሩቅና የቅርብ ተሞክሮዎች ተረጋግጧል፡፡ በሀገራችንም ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየውን ንጉሳዊ ሥርዓት ከሥሩ መንግሎ የጣለው የ1966ቱ ህዝባዊ ንቅናቄ ለአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይሁን እንጅ የአገዛዝ ሥርዓቶች የተንጠላጠሉበት የሥልጣን ማማ ሲወድቅ እንጅ ለመውደቅ ዘመም ሲል አይሰማቸውም፡፡
በሌላ በኩል የህዝብ ንቅናቄ የአገዛዝ ሥርዓትን ነቅንቆ የሚጥል መሆኑ የማያጠራጥር ቢሆንም መዳረሻ ግቡ ግን በግልፅ አይታወቅም፡፡ በርግጥ ከህዝቡ ምሬትና የለውጥ ፍላጎት አንፃር የሥርዓቱ መውደቅ በራሱ እንደ ትልቅ ግብ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከዚህ ይበልጥ ግን አሳሳቢውና አነጋጋሪው ጉዳይ ከአገዛዝ ሥርዓቱ ውድቀት በኋላ ምን ሊፈጠር ይችላል? የሚለው አብይ ጉዳይ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የወያኔ አገዛዝ በውጫዊ ግፊትም ሆነ በራሱ ውስጣዊ ችግር የመውደቁ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እንኳን ህዝብ አንቅሮ የተፋው የወያኔ አገዛዝ ይቅርና ማንም ምድራዊ ኃይል የሚነቀንቃቸው የማይመስሉ የዓለማችን ኃያላን አይቀሬውን የውድቀት ፅዋ ተጎንጭተዋል፡፡
ከዚህ በመነሳት የወያኔ አገዛዝም የውድቀቱን አይቀሬነት መቀበልና አወዳደቁን ማሳመር ያለበት ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል የህዝቡን የለውጥ እንቅስቃሴ ሥርዓት ባለው መንገድ ሊመራና ኃላፊነት ሊወስድ የሚችል የተደራጀ ኃይል አስፈላጊ ነው፡፡ የሚመጣው ለውጥም ግብታዊ ሳይሆን የታቀደና የት ሊያደርሰን እንደሚችል የሚታወቅ መሆን ይኖርበታል፡፡ መዳረሻ ግቡን በግልፅ የሚያውቅን የለውጥ ኃይልና እንቅስቃሴን ደግሞ ማንም ምድራዊ ኃይል ሊያቆመው አይችልም፡፡ ስለሆነም ሰፊና ጠንካራ ህዝባዊ መሠረት፣ እንዲሁም ግልፅ የትግል አጀንዳና ስትራቴጂ ያለው የፖለቲካ ድርጅት አሁኑኑ!!!
ጸሃፊው መሐመድ አሊ መሐመድን በፌስ ቡክ ላይ ማግኘት ይቻላል። እዚህ ይጫኑ።
___
ከነበቡ በኋላ ያጋሩ ፤ ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ።