መስከረም 23 2009 ዓ ም

በኦሮሞ ሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ መንግስት ባስነሳው ቀውስ እና በወሰደው ርምጃ ምክንያት የብዙ ኢትዮጵያውያን ህይወት መጥፋቱ በተለያየ መገናኛ ብዙሃን የተዘገበ እና ህዝባዊ ቁጣም የቀሰቀሰ እንደሆነ ይታወቃል።
ሆኖም ዜጎች ስለተገደሉበት ሁኔታ እና ህይወታቸውን ስላጡ ሰዎች ቁጥር የተለያየ መረጃ ሲዘዋወር ቆይቷል። ዓለም አቀፍ ሜዲያዎች በአብዛኛው የሃምሳ ሰዎች ህይወት እንደጠፋ እና አሟሟታቸውንም በሚመለከት በመረጋገጥ በማለት ዘግበውታል። ዘገባቸው የሕወሓት መንግስት ካቀረበው መረጃ ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሆኖም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ያጠናቀረውን መረጃ ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ600 በላይ እንደሆነ አመልክቷል። አሟሟታቸውን በሚመለከት በጭስ ጋዝ፤ በጥይት እና በመረጋገጥ እንደሆነም አክሎ ገልጧል። ማምሻውን የወጣ መረጃ የሟቾችን ቁጥር 678 አድርሶታል።
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደሚሉት ህወሓት በኦፖዲኦ አማካኝነት የሬቻን በዓል በፖለቲካ ስራ ሊጠቀምበት ፈልጎ ዝግጂት ሲያደርግ እንደነበረ እና በበዓሉ እለትም በተናጋሪነት የተጋበዙ ሰው ለመናገር በሚሰናዱበት ጊዜ ተቃውሞ እንደተቀሰቀሰ እና የአጋዚ ሰራዊት በአስለቃሽ ጭስ እና የተኩስ ሩምታ ከፍቶ እንደነበር በአካባቢው የነበሩ ሰዎች የተገኘውን መረጃ በማጣቀስ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የህወሓት መንግስት የጦር ሄሊኮፕተር በማሰማራት የጭስ ጋር ከሰማይ በትኗል ፤ ብዙዎች ወደ ጥልቅ ጉድጓድ በመግባት ህይወታቸው አልፏል።
ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ በዓሉ መሰረዙ ይታወቃል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ሀዘነተኞች ሆነዋል። በዚሁም ምክንያት ኢትዮጵያውያንም አዝነዋል።
የህወሓት መንግስት ችግሩ የተፈጠረው “በጸረ ሰላም ኃይሎች ነው” ይላል። ሆኖም በዓሉ ሊጀመር በነበረበት ሰዓትም ሆነ በዓሉ እንዲሰረዝ ከሆነ በኋላ ከሰላማዊ ተቃውሞ በሰተቀር ህዝቡ የፈጠረው ምንም አይነት ሁከት አልነበረው። እጂን በማጣመር “ወያኔን አንፈልግም ከማለት በስተቀር”
ተሰማርቶ ከነበሩት መትረየስ የተጠመደባቸው ተሽከርካሪዎች ፤ በቦታው ከአንድ ቀን በፊት እንዲያድር ከተደረገው መከላከያ ሰራዊት እና በሄሊኮፕተር የታገዘ ጥቃት ከመሰንዘሩ አንጻር ህወሓት የፈጠረውን ነገር ለመፍጠር ዝግጂት ማድረጉን የሚጠቁሙ ፍንጮች ናቸው የሚሉት ጥቂት አይደሉም።
ቦርከና
ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ፤ ያነበቡትን ያጋሩ።