ኢሳት
መስከረም 27 ፥ 2009
በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ የአርሲ ነገሌ ከተማ ከንቲባና በከተማዋ የቀበሌ 01 ሊቀመንበር አስተባባሪነት በኦሮሞዎችና በአማሮች መካከል ግጭት ለመፍጠር የተጠናከረ እንቅስቃሴ መደረጉን በዚህም ሂደትም ጉዳት መከተሉን የአይን ምስክሮች ለኢሳት ገለጹ።
ዛሬ አርብ ከስፍራው ለኢሳት በደረሰው መረጃ መሰረት ባለፉት ሁለት ቀናት ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ 70 ያህል ሰዎች በአጋዚ የተገደሉ ሲሆን፣ ከተማዋ በአጋዚ ኮማንዶ ቁጥጥር ስር ወድቃለች።
በከተማው ውስጥ የተካሄደውን ግድያ ተከትሎ በገጠር የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በከፍተኛ ቁጥር ወደ ከተማ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ፣ አማራን ለማጥቃት እየመጡ ነው በሚል አማሮችን ከኦሮሞዎች ጋር ለማጋጨት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይህንንም የሚመሩት በአካባቢው ከሰፈረው የአጋዚ ሃይል አዛዦች መመሪያ ወስደው የሚያስፈጽሙት ሚልኪሳ የተባሉት የከተማዋ ከንቲባ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።
በህዝብ ውስጥ ሰርገው የገቡ ታጣቂዎችና በካድሬዎች አቀናባሪነት የተጀመረውን ግጭት ለማስቆም የአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ታውቋል። የአርሲ ነገሌ ምንጮች እንደሚናገሩት አሁን መቀዝቀዝ የጀመረውን ግጭት ለማባባስ ታዋቂ የኦሮሞ ወይንም የአማራ ተወላጆችን ለመግደል እቅድ ስለመኖሩ የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
______
ካነበቡ በኋላ ያጋሩ።