spot_img
Wednesday, March 22, 2023
Homeነፃ አስተያየትሕገ-አራዊት-ተጀመረ ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈቀደው «ነጻ ርምጃ»ና ጭካኔን ነው (ኤፍሬም እሸቴ)

ሕገ-አራዊት-ተጀመረ ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፈቀደው «ነጻ ርምጃ»ና ጭካኔን ነው (ኤፍሬም እሸቴ)

- Advertisement -

(ኤፍሬም እሸቴ)
ጥቅምት 4 2009 ዓ ም

የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረ እንደመሆኑ ጭካኔ፣ ሰቆቃ መፈፀም እና በሰው ላይ ግፍ መዋል የባሕርይው አይደለም። የሰው ልጅ «ሰው» ነውና እግዚአብሔር በኅሊናው ውስጥ ክፉውንና ደጉን የሚለይበት መዳልው (ሚዛን) ፈጥሮለታል። ከማንም ባይማረው እንኳን በኅሊናው ክፉውን እና ደጉን የመለየት ሥጦታ አለው። ይህ ክፉንና ደጉን የመለየት ሥጦታ በሥነ ምግባር እና በትምህርት የበለጠ ይዳብራል፤ ያድጋል፣ ይጎለምሳል።

ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ኅሊናው ክፉና ደጉን በመለየት መካከል ፈራጅ ሆኖ የተቀመጠለት ቢሆንም ክፉውን እየተወ ደጉን እንዲከተል «ሥነ ምግባር» ብሎም «ሕግ» የሚባል አጥር ይበጅለታል። በነጻነት የተፈጠረ እና ነጻ ፈቃድ ያለው ቢሆንም በነጻ ፈቃዱ ተጠቅሞ ለሚሠራው ሥራ ደግሞ ተጠያቂነት አለበት። ያ ተጠያቂነት ነጻ ፈቃዱን በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርገዋል። ለሰው ልጅ ሰማያዊ ሕግ እንዳለው ሁሉ ምድራዊ መተዳደሪያ ሕግም አለው። ለሰማያዊው ሕግ ብሎ መልካም ባይሠራ ስንኳ ምድራዊውን ቅጣት ፈርቶ ከክፉው ይልቅ በጎውን ይመርጣል። በእርግጥ በምድራዊው ሕግ ጥሩ የተባለ ነገር ሁሉ በሰማያዊው ሕግ ጥሩ የማይባል ሊሆን ቢችልም በዚህ ዓለም ላይ አንዱ ከአንዱ ተከባብሮ ለመኖር ግን ይጠቅመዋል። ያ ባይሆን ኖሮ ለሃይማኖት ደንታ የሌላቸው ነገር ግን በሥርዓት የሚኖሩት ሕዝቦች እርስበርሳቸው በተበላሉ ነበር።

ሰው ልጅ ሰማያዊ ሕግም ምድራዊ ሕግም የማይገዛው ሲሆን ከእንስሳትና ከአውሬዎች ያልተሻለ ጨካኝና አረመኔ ይሆናል። ወንጀል እና ጭካኔ የዕለት ተዕለት ተግባሩ ይሆናሉ። በሌላ ዘመን እና በሌላ ጊዜ ቢሆን እንኳን ሊፈጽማቸው ሊያስባቸው እንኳን የማይችላቸውን ነገሮች መፈፀም ይጀምራል። ስለዚህ የሕግ አጥር እንዳይጣስ እና ሰው ከሰዋዊነት (ሰብዓዊነት) ድንበር ወጥቶ የአውሬዎችን ጠባይ እንዳይላበስ (በሕገ አራዊት እንዳይመራ) ትልቅ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ይህንን በማድረግ ረገድ የሥነ ምግባር ሚዛን ያላቸው የእምነት ተቋማት እና ምድራዊ የሕግ ሚዛን ያላቸው መንግሥታትና መንግሥታዊ ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። እነዚህ ሁለቱ ተቋማት (ማለትም ሃይማኖት እና መንግሥት) ይህንን ሚዛናቸውን የጣሉ ቀን የሰው ልጅ ከሰውነት ተርታ ወጥቶ ወደ አራዊትነት እንዲገባ በሩ ተከፈተለት ማለት ነው።

«የእግዚአብሔር አገር፣ የሃይማኖተኞች አገር» በምትባለው በአገራችን በኢትዮጵያ ሰዎች ከሰውነት ወደ አውሬነት የተቀየሩበትን የቀይ ሽብር/የነጭ ሽብር ዘመን ማንሣት የግድ ነው። ወገን ወገኑን የጨፈጨፈበት፣ ወንድም እህቱን፣ እህት ወንድሙን አሳልፎ የሰጠበት፣ ለሳንቲም ድቃቂ፣ ለጨርቅ እላቂ ሲባል ሰው ከሰው የተከዳዳበት፣ ሚስቱን ለመድፈር ሲባል ያለ ወንጀሉ ባል የተገደለበት ዘመን ታሪክ የተጻፈበት ቀለም ገና አልደረቀም። በወጣነታቸው ሮጠው ያልጠገቡ ያገራችን ልጆች በፖለቲካ አመለካከት ተለያይተው የተጫረሱበት፣ እርበርስ የተከዳዱበት፣ ዘግናኝ ጭካኔ የተፈጻጸሙበት ዘመን ትናንት እንጂ ጥንት አይደለም። የዚያ ዘመን የጭካኔ ተሳታፊዎች አሁንም በመካከላችን አሉ። ከመካከላቸው ጥቂቶቹ በቃላቸው እየነገሩን፣ በጽሑፋቸው ያንን ታሪክ እንዳንደግም እየመከሩን፣ ዘመነ ንስሐቸውን በደግ ነገር ለማሳለፍ እየጣሩ እኛም ወደዚያ አይነት ዘመን እንዳንመለስ እያስጠነቀቁን ቢሆንም አልሰማናቸውም። አሁንም አገራችን በአስቸኳይ አዋጅ ሰበብ «ነጻ ርምጃ»ን ድጋሚ አውጃ ያንን ዘመን ለመድገም አፋፍ ላይ ደርሳለች።

1. ከአዲስ አበባና ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት መብራት በማጥፋትና በየቤቱ በመግባት መዝረፍ ተጀምሯል። ይህንን የሚያደርገው ወንጀል መፈፀም እንደሚችል የተፈቀደለት ብረት አንጋቢ ወታደር ነው።

2. መንገድ ላይ ሰዎችን እያሰቆሙ በመፈተሽ ንብረታቸውን መውሰድ ተጀምሯል።

3. ተጠርጣሪ የተባለ ሰው በገፍ እየታሰረ ነው። ከታሳሪዎች መካከል አንዳንዱን በአደባባይ መግደል ተጀምሯል።

ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የንብረት ዘረፋው ስስት ጋብ ሲል ሴቶችን መድፈር መሆኑን ከዘመነ ቀይ ሽብር ታሪክ መማር የግድ ነው። በቂም በበቀል ያለ ምንም ወንጀላቸው የሚገደሉ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል። ጎረቤት ከጎረቤቱ መበቃቀያ ጊዜ ያገኘ ይመስለዋል። በዲላና በአካካዊዋ ምን እየሆነ ነው? የሰው ልጅ የሥነ ምግባር እና የሥነ ሕግ ሚዛኑ ሲነሳለት የማያደርገው ነገር የማይፈጽመው ወንጀል አይኖርም።

ይህ ሁሉ እንዳይመጣ የሃይማኖት አባቶች እና የሃይማኖት መሪዎች ትልቅ ኃላፊነት ነበረባቸው። ምን እያደረጉ እንደሆነ በይፋ ስለምናውቅ ከእነርሱ አንዳች መፍትሔ መጠበቅ የዋህነት ነው። ይሁን እንጂ በሥልጣን ላይ ባይኖሩም መንፈሳዊ ሥልጣኑ ያላቸው የሃይማኖት አባቶች በግላቸው ይህንን ኃላፊነት መሸከም አለባቸው። በወታደርነት ለሚያገለግል ማንኛውም ዜጋ መንገር አለባቸው። ከሰውነት ወጥተው ወደ አውሬነት እየገቡ መሆናቸውን፣ ያንን ድንበር ካለፉ በኋላ ወደ ሰውነት መመለስ እንደማይኖር ሊመክሯቸው ይገባል። በደም የሰከሩት የሕወሐት ሰዎች ወደ ኅሊናቸው ይመለሳሉ ብሎ መገመት መቸም የዋህነት ነው። ሌላው ጀሌ ግን ጊዜና ተስፋ አለው። አሁንም ኅሊናውን ቢያዳምጥ ተስፋ አለው። ቀሪ ዘመኑን በጸጸት እሳት ሲቃጠል ከሚኖር አሁን ምርጫውን ቢያስተካክል ይበጀዋል። ይህ የፖለቲካ ምርጫ አይደለም። ሰው የመሆንና ሰው ያለመሆን ምርጫ ነው።

ሌላው ይህ ጥሪ የሚመለከታቸው በስማቸው የሚነገደው የትግራይ ወገኖቻችን ናቸው። አገራችን ከምድረ ሰብዕ ወደ ምድረ አራዊት፣ ሕጋችን ከሕገ ሰብዕ ወደ ሕገ አራዊት እየተንሸራተተች መሆኗን ተረድተው የመጨረሻ የመፍትሔ ርምጃቸውን መውሰድ አለባቸው። ይህ ደም መፋሰስ ማቆሚያ አይኖረውም። ጭካኔ ጭካኔን ይወልዳል። ጭካኔ ቂምን ይወልዳል። ደም ማፍሰስ ደም ማፍሰስን ያስከትላል። አሁንም ኅሊና ላላቸው፣ በጎ ኅሊና ላላቸው በሙሉ እንጮኻለን፣ ጆራቸው ሳይሆን ኅሊናቸው እንዲሰማን።
ይቆየን

ጸሃፊው ኤፍሬም እሼቴ አደባባይ ብሎግ ላይ ይጦምራል። የፌስ ቡክ ገጹ ላይ ለማግኘት ይሄንን ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,440FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here