spot_img
Sunday, March 3, 2024
Homeነፃ አስተያየትኢትዮጵያን የሚጠቅማት ”እኛ” እና “እነሱ” ሳይሆን “እኛ” ብቻ ነዉ (ኤፍሬም ማዴቦ)

ኢትዮጵያን የሚጠቅማት ”እኛ” እና “እነሱ” ሳይሆን “እኛ” ብቻ ነዉ (ኤፍሬም ማዴቦ)

ኤፍሬም ማዴቦ
ህዳር 4 ፤ 2009 ዓ ም

እንደኔ አንዴ ሲቆጥቡት አንዴ ሲደብቁት በድንገት ዕድሜያቸዉ ወደ ሃምሳዎቹ የገባ ሰዎች አንድ የምንጋራዉ እምነት አለ- እሱም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አንድ ነገር መጀመር እንጂ መጨረስ አያዉቁበትም የሚል እምነት ነዉ። በፍጹም ሊፈረድብን አይገባም። ከልጅነት ወደ አዋቂነት የደረስነዉ ጥንስስ ሲጠነሰስ እንጂ እንጄራዉን ሳናይ ነዉ። ፓርቲ ሲፈጠር እንጂ ዉጤቱን ሳናይ ነዉ። የፖለቲካ ህብረቶች ተፈጥረዉ ፈረሱ ሲባል ነዉ እንጂ እንዲህ አደረጉ ሲባል ሰምተንም አይተንም አናዉቅም። ባጠቃላይ የፖለቲካ ትግል ሲባል ነዉ እንጂ ድል ሲባል ሰምተን አናዉቅም። ድል የረጂም ግዜ ትግል ዉጤት እንደሆነ ይገባናል፥ ሆኖም ግን ዛሬ የሚረግጡን ሰዎች በረሃ ገብተዉ አዲስ አበባን እሲኪቆጣጠሩ ድረስ የወሰደባቸዉን ግዜ ሁላችንም የምናስታዉሰዉ ይመስለኛል። እኔ ይህንን ሁሉ ጉድ በአይኑ እያየ ያደገ ትዉልድ አካል ነኝ። ግን ይህንን ዕድሜ ልኬን ሲደጋገም ያየሁትን የአገሬን በሽታ መድሐኒት እፈልግለታለሁ እንጂ “ከመሳሳት እራሴን ላድናት” እኔን ምን አገባኝ የ”እነሱ” ጉዳይ ነው ብዬ እጆቼን አጣጥፌ አልቀመጥም። ጉዳዩ የኔ ነዉ . . .. ጉዳዩ የኛ ነዉ። “እነሱም” “እኛም” አንድ ላይ “እኛ” ነን። ሰዉ የመሆኔ ትልቁ ሚስጢር የሚነግረኝ በአካባቢዬ ካሉ ሰዎች ዉጭ መኖር የማልችል ማህበራዊ ፍጡር መሆኔን ነዉ። አንዳንዶቻችን መሳሳትን እንደ ጦር እንፈራለን፥ መሳሳትን ፈርተን እጃችንን አጣጥፈን ከምንቀመጥ እየተሳሳትንና ከስህተታችን እየተማርን የምንሰራዉ ስራ ነዉ አገራችንን ነጻ የሚያወጣት። ስለዚህ በእኔ እምነት ምንም ይሁን ምን ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚጠበቅ ምንም ነገር የለም ብለን እጅና እግራችንን አጣጥፈን መቀመጡ የበሽታ ምልክት ነዉ እንጂ የጤንነት አይመስለኝም።

እኔ ይህ የኔ ትዉልድ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት ያለበት የአደራ ትዉልድ ነዉ ብዬ የማምን ሰዉ ነኝ። ግን እንዴት ነዉ እኛ የኢትዮጵያ ልጆች በዘር፥በቋንቋና በሀይማኖት ሳንከፋፈል አንድ ላይ ቆመን ኢትዮጵያን አንድነቷ የተጠበቀ የፍትህ፥ የነጻነት፥ የእኩልነትና የዲሞክራሲ አገር የምናደርጋት? እንዴትና መቼ ነዉ ሁሉንም ያቀፈ ስብስብ ፈጥረንና በአንድ ጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጠን የአገራችንን ችግሮች በዉይይት የምንፈታዉ? መቼ ነዉ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ማዶ ለማዶ ለያይቶ ካስጮኸንና ካጨቃጨቀን ማለቂያ የሌለዉ የባዶ ቃላት ጫጫታ ተላቅቀን ሞት አፋፍ ላይ የደረሰችዉን አገራችንን ከሞት የምንታደጋት? መቼ ነዉ ማንም ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊነት ሳይሰማዉ በኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚመለከታቸዉና ከሚያገባቸዉ ወገኖች ሁሉ ጋር ተቀምጠን ስለአገራችን ችግሮች የምንወያየዉና መፍትሄ የምንፈልገዉ? መቼ ነዉ በቋንቋ ብንለያይም፥ በሀይማኖት ብንለያይም፥ በሀሳብና በፖለቲካ አመለካከት ብንለያይም የጋራ የሆነዉ የአገራችን ጉዳይ አገናኝቶን በሰለጠነ ቋንቋ ተነጋግረን አዲስቷን ኢትዮጵያ አምጠን የምንወልዳት?

አብረነዉ ከቆምን፥ከተባበርነዉ፥ ከረዳነዉና ግዜና ሀሳብ ከሰጠነዉ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል አካል ጥንስስ ባለፈዉ ወር አሜሪካ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ ዉስጥ መጀመሩን ብዙዎቻችን ኢሳት በለቀቀዉ ሰበር ዜና የሰማን ይመስለኛል። አገር ዉስጥ የሚደረገዉ ትግል ማዕከላዊ አመራር በሚፈልግበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ኢትዮጵያዊያንን ማሰባሰብ የሚችል ድረጅት መፈጠሩ ሁላችንንም ሊያስደስት የሚገባ መልካም ዜና ነዉ። እኔም ይህንን መልካም ዜና እንደሰማሁ ቁርሴን በላሁና ፌስቡኩ፥ድረገጹና ቲዉተሩ የሚሉትን ለመስማት Internet ፍለጋ ወጣሁ። Internet ቤት ደርሼ አይፎኔን ገና ስክፍተዉ ዜናዉ ሁሉ የሚያወራዉ አዲስ ስለተፈጠረዉ አገር አድን ንቅናቄ ነበር። ለምን እንደሆነ አላዉቅም እኔን ያጋጠመኝ ዜና ግን አዲሱን አገር አድን ንቅናቄ ገና ከመወለዱ “አትደግ” እያለ የሚራገም ዜና ነበር። በፍጹም አልገረመኝም! ምክንያቱም እንዲህ አይነት ከፈረሱ ጋሪዉ የቀደመ ትችት እየሰማሁ ነዋ ያደኩት። ስለዚህ በትዕግስት ማንበቤን ቀጠልኩ። ቆየት ብዬ ነገሮችን በስፋት እያዩና በጥልቀት እያሰቡ የሚጽፉ ሰዎችን ሀሳብ ሳነብ አንድ ነገር ተረዳሁ። በአገር አድን ንቅናቄዉ ስብሰባ ላይ የተነገረዉ ንግግር በሙሉ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ነበር፥ ከእያንዳንዱ ድርጅት ተወካይ አፍ ይወጣ የነበረዉ ቃል የወደፊቷ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን መሆን አለባት የሚል ተስፋ የሞላበት ቃል ነበር፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የስብሰባዉ መንፈስና የአገር አድን ንቅናቄዉ የተፈጠረበት ዋነኛ አላማ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት አደጋ እናድናት የሚል ነበር። እነዚያ ከሀሳባቸዉ ብዕራቸዉ የቀደመ ወገኖቼ የተመለከቱት ግን የጋራ ንቅናቄዉን ይዘትና ይዟቸዉ የተነሳዉን ግቦች ሳይሆን ላይ ላዩን የሚታየዉን የአገር አድን ንቅናቄዉን ቅርጽ ብቻ ነበር። በተለይ አብዛኛዉ ሰዉ የተቸዉ ሶስቱ ድርጅቶች በብሄር የተደራጁ ድርጅቶች የመሆናቸዉን ጉዳይ ነበር። እርግጠኛ ነኝ አሁንም ይህ ስለዚህ ጥንስስ የሚያወራዉ ጽሁፌ ብዙ ጩኸት ይዞብኝ እንደሚመጣ አዉቃለሁ። የሚያወሩ ሰዎች ያዉሩ የሚሉም ሰዎች የሚሉትን ሁሉ ይበሉ – እኔ ግን አንድ የማረጋግጥላቸዉ ነገር አለ – እሱም ድምጽ ፈርቼ ኢትዮጵያን ከአደጋ የሚያድን ሀሳብ ከማፍለቅና ከመናገር በጭራሽ ወደ ኋላ ከማይሉ ኢትዮጵያዊያን ዉስጥ አንዱ መሆኔን ነዉ። “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነዉ” የሚል አባባል እየሰማሁ ነዉ ያደኩት። ዛሬ ይህንን አባባል ሙሉ ለሙሉ አልቀበለዉም። ያገኘዉን አጋጣሚ አይጠቀምበትም እንጂ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ብቻ ሳይሆን እጁ ላይ ነዉ ያለዉ።

ይህንን መጣጥፍ የሚያነብ አብዛኛዉ ሰዉ ተወልዶ ያደገዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉና ሁሉም ኢትዮጵያን እንዳቅሙ ያዉቃል የሚል እምነት አለኝ። አገራችን ኢትዮጵያ የረጂም ግዜ ታሪክ ያላት አገር ናት። ታሪካችን እንደማንኛዉም አገር ታሪክ መራራና ጣፋጭ ምዕራፎች አሉት። ግን ወደድንም ጠላን መራራዉም ታሪክ ጣፋጩም ታሪክ የኛ ታሪክ ነዉ። ሁለቱንም የታሪክ ምዕራፎቻችንን እንደ ታሪክ መቀበል ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችን ማስተማር አለብን። ኢትዮጵያ ለአዉሮፓ ኢምፔሪያሊዝም እጄን አልሰጥም ብላ የራሷ ብቻ ሳይሆን የአለም ጥቁር ህዝብ የነጻነት ምልክት ሆና የቆየች አገር ናት። ይህ ከምንወደዉና በኩራት ከምንናገረዉ ታሪካችን ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ የበደለዉ ወይም ያገለለዉ ህዝብ አለ ብዬ በፍጹም አላምንም። የተለያዩ የኢትዮጵያ ገዢ መደቦች ግን አንዱን ከፍ ሌላዉን ዝቅ አድርገዉ ህዝብን ከህዝብ መለያየታቸዉንና በህዝብ ላይ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የማይችል እጅግ በጣም ከፍተኛ በደልና ሰቆቃ መፈጸማቸዉን ለአንድም ደቂቃ ቢሆን መርሳት የለብንም። ይህ ደግሞ የመራራዉ ታሪካችን አንዱ ክፍል ነዉ። ይህም ታሪካችን በፍጹም ልንክደዉ የማንችለዉ የረጂሙ ግዜ ታሪካችን አካል ነዉና አንገታችንን ቀና አድርገን በግልጽ ልንናገረዉ የሚገባ ታሪክ ነዉ። ከፋም ለማ ልንማርበት የሚገባ ታሪክ እንጂ የምናፍርበትና ከሌላዉ አለም ህዝብ የተለየ ታሪክ የለንም። እንደ አንድ አገር ህዝብ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን ወደፊት መጓዝ የምንችለዉ ባለፈዉ ታሪካችን ላይ ተመስርተን በዳይና ተበዳይ እየተባባልን ስንካሰስ ሳይሆን የበደለም የተበደለም እንዳለ ተማምነን ይህንን መራራ የሆነዉን የታሪክ ምዕራፍ ላለመድገም ስንማማል ብቻ ነዉ። በታሪክ ነግዶ ብቻዉ ያተረፈ ማንም የለም፥ ብቻዉን የከሰረም የለም። የታሪክ ንግድ ትርፉ ያለፈዉን ስህተት መድገም ብቻ ነዉ። ይህ ደግሞ ማህበረሰባዊ ኪሳራ ነዉ። ዛሬ የሁላችንም አይን አተኩሮ መመልከት የሚገባዉ የትናንቱን በደልና ጭቆና ሳይሆን የነገዉን ብሩህ ዘመን ነዉ። እኛ ማድረግ የምንችለዉ የትናንቱን ስህተት ማረም ሳይሆን ከትናንቱ ስህተት ተምረን ነገን አስተካክሎ መቅረጽ ነዉ። ብዙ ሰዉ ለአገሩ ለኢትዮጵያ ስለሚሳሳ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ በጣም ያስጨንቀዋል። እኔ ተጨንቄም አላውቅ! ተፋቅረን፥ ተስማምተንና ተግባብተን አንድ ላይ ከሰራን የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዳይ እኛ እጅ ላይ እንደሆነ በሚገባ አዉቃለሁ። ታዲያ እጄ ላይ ላለ ነገር ለምን እጨነቃለሁ? ይልቅ እኔን የሚያስጨንቀኝና እንቅልፍ የሚነሳኝ አለመተባበራችንና የምንፈለገዉን ነገር ለማግኘት አንድ ላይ አለመስራታችን ብቻ ነዉ። (ገጽ 2 ላይ ዞሯል)

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here