ኢሳት (ኅዳር 14 ፥ 2009)
ሃምሌ 5 ፥ 2008 ጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉ እየተሰማ ሲሆን፣ በአርማጭሆ ሳንጃ ወረዳ ረቡዕ ዕለት አንድ መኪና በተወሰደበት ዕርምጃ መቃጠሉንም የአይን ዕማኞች ገልጸዋል።
በተበታተነ መልኩ ሲካሄዱ የነበሩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በአንድ ዕዝ በተቀናጀ መንገድ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱንም፣ በበረሃ የሚገኙት ታጣቂዎች ከኢሳት ጋር ባካሄዱት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በተለይም በሰሜን ጎንደር በየአካባቢው ተደራጅተው በጎበዝ አለቆች ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሃይሎች በጋራና በአንድ ዕዝ ስር ለመታገል መወሰናቸውንና በቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃል መሃላ መፈጸማቸውን ለኢሳት ገልጸዋል።
ሰኞ ህዳር 12 ፥ 2009 ዓም በአንድነት በጋራ ዕዝ ስር ለመታገል የወሰኑት በቁጥር 450 የሚቆጠሩት ታጣቂዎች ኢትዮጵያ ነጻነቷን እስከምታገኝ እንደሚታገሉ ገልጸዋል።
ሰሚን ጎንደር ኢትዮጵያና ደቡብ ጎንደር ቴዎድሮስ በሚል በሁለት ቡድን የተከፈሉት የታጠቁ ሃይሎች ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም የእንቅስቃሴው መሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል። ከአርበኞች ግንቦት 7 የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሰሜን ኢትዮጵያ የቀጠለው በመሳሪያ የተደገፈ እንቅስቃሴ በአብደራፊ፣ ቃብትያና፣ ሁመራ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚገልጹት የአይን ምስክሮች፣ የታጠቁ ሃይሎች ረቡዕ ዕለት በሳንጃ ወረዳ በሰነዘሩት ጥቃት የዳሽን ቢራ የጫነ መኪና መቃጠሉን ገልጸዋል።
በዚህም ጥቃት ሳቢያ መንገድ በመዘጋቱ በርካታ መኪኖች ከእንቅስቃሴ መገታታቸው ታውቋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ በአብደራፊ በቃፍቲያ ወታደራዊ ግጭቶች መቀጠላቸው የተሰማ ሲሆን፣ በርካታ የታጠቁና ያልታጠቁ ሃይሎች ወደ ትግል መውጣት መጀመራቸው ተመልክቷል።