spot_img
Sunday, May 28, 2023
Homeነፃ አስተያየትታጥቦ ጭቃ! የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት የፖለቲካ ትርምስ (ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ)

ታጥቦ ጭቃ! የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት የፖለቲካ ትርምስ (ከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ)

- Advertisement -

tibebe-samuelከጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ
ኅዳር 28 : 2009

“በእኔ አመለካከት፤ሁልጊዜም በጦርነት ላይ ያለ መንግስት፤በተለይም ሰላም ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ፤ጦርነት የሚቀጥል መንግስት፤ብቃትና ችሎታ የሌለው (መንግስት) በመሆኑ (ከስልጣን) መልቀቅ አለበት”። (ቅንፍና መስመር የተጨመረ)። ክርስቲና ኤንጌላ የተባሉ ጸሃፊ።

በተደጋጋሚ እንዳየነው፤ የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት፤ እንኳን ኢትዮጵያን የሚያክል ትልቅ ሃገር ይቅርና፤ የራሱን ድርጅት በብቃት መመራት የሚችል አይደለም። ብዙዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ያየናቸው ለውጦች፤ በሕዝቡ ጥረት፤ እንዲሁም የአለማችን የፖለቲካ ስርዓት ለውጥ፤ ያስከተላቸው ውጤቶች ናቸው። በእኔ እምነት፤ የኢሕአዲግ ፖሊሲ፤ ለሃገራችን ፍትሃዊና ፈጣን እድገት ማነቆ የሆነ፤ የተሻለ ነገር መስራት ስንችል፤ በተሳሳተ የዘር ፖለቲካ፤ የተዛባ የመሬት ፖሊሲ፤ ፍትሃዊ ያልሆነ የግብር ሕግ፤ ትውልድ ገዳይ በሆነ የትምህርት ፖሊሲ፤እንዲሁም ስርዓቱ በፈጠረው አላስፈለጊ የግጭት አዙሪት፤ የሰው ሃይል፤ ሕይወትና፤ የሃገሪቱ አንጡራ ሃብት እንዲባክን በመደረጉ፤ ሃገራችን፤ ለጥቂት ሰዎች ገነት፤ ለብዙሃኑ ደግሞ ሲኦል ሆናለች።

በዚህ ፀሃፊ እምነት፤ የኢሕአዲግ መራሹ መንግሥት፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት የጀመረው፤ ገና ስልጣን ከጨበጠበት ከ25 ተኩል ዓመታት በፊት ጀምሮ፤ እራሱን በገዥነት ከሰየመ በኋላ ነው። አቶ መለስ ዜናዊ፤ በለስ የቀናቸው መሪ ቢሆኑ ኖሮ፤ የመጀመሪያው “ማንዴላ” መሆን በቻሉ ነበር። ሻዕብያ፤ ኦነግና፤ የኢሕአዲግ መራሹ ቡድን፤ ደርግ ለ17 ዓመታት በደም የተነከረበትን በትረ ሥልጣን ሲረከቡ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ እርቅ እንዲወርድ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገው ቢሆንና፤ ብሔራዊ እርቅ መሪ አጀንዳ ሆኖ ቢተገበር ኖሮ፤ ኢትዮጵያችንም ሆነች፤ ዛሬ የጎረቤት ሃገር የሆነችው ኤርትራ፤ በኢኮኖሚ፤ በማህበራዊ ኑሮ እድገትና ዲምክራሲያዊ ስልተ ስርአትን በመግንባት፤ለዓለም ተምሳሌት የሆኑ ሃገራት በሆኑ ነበር። ነገር ግን፤ ባለመታደል፤ ገዥዎቻችን በቂምና በጥላቻ የተበከለው ሕሊናቸው የፈቀደላችው በሕዝብ ላይ ጦርነት ማወጅን ሆነና፤ ይኽው ላለፉት 25 ዓመታት “በጦርነት እንዳክራለን”።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ምክትል ፐሬዝዳንት የነበሩት ሌ/ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ፤ በቅርቡ ለንባብ ባብቁት መጽሐፋቸው ያስቀመጡት መሪ ሃሳብ፤ ዛሬ እንኳን ያስተዋለው ሰው ቢኖርና በተግባር ቢውል፤ ከገባንበት የጨለማ ጉዞ እራሳችንን ባወጣን ነበር። በመኤሶን ብልህነት፤ በደርግ ሃገር ወዳድነት፤ በኢሕአፓ ቁርጠኝነት፤ አንድ ላይ ብንሰራ ኖሮ የት በደረስን ነበር ሲሉ በቁጭት ጽፈዋል። ይህ አባባላቸው የዘገየ ቢሆንም፤ ዛሬም፤ ኢትዮጵያውያን ያለንን እውቀት፤ ጉልበት፤ እንዲሁም የገንዘብ ሃይል ብናሰተባብር ወሰናችን የሚሆነው ሰማዩ ነው። ይህ ተራ መላ ምት አይደለም፤ ከረጅም ዓመታት ጀምሮ፤ ለሱዳን ኢኮኖም መንቀሳቀስ፤ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዛሬም አሻራው ይታያል። ዩጋንዳን፤ ኬንያን፤ ደቡብ አፍሪካን፤ እንዲሁም በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸውን፤ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት፤ የአውሮፓና፤ የአሜሪካን ከተሞችን ስናይ፤የኢትዮጵያውያን ስኬት ጎልቶ ይታያል። እድል አጋጥሞኝ በተሳተፍኩባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች ላይ፤ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን የውጭ ሃገራት ድርጅቶችን ወክለው በስብሰባ ሲገኙ ማየት የሚያኮራ ቢሆንም፤ እነዚህ ብርቅዬ ዜጎች ሃገራቸው ውስጥ በነጻነት የመስራት እድሉ ቢኖራቸው ኖሮ ሊያበርክቱት የሚችሉትን ነገር ሳስብ ልቤ ይደማል።

የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት፤ ከጭንቅላቱ ጀምሮ መበስበሱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከተነገረን እነሆ መጪው መጋቢት 2017፤16ኛ ዓመቱን ይይዛል። በዙውን ጊዜም ኢሕአዲግ በግምገማና በታሃድሶ ስም ተለውጫለሁ ቢለንም፤ ሁሌም የምናየው ነገር ታጥቦ ጭቃ መሆኑን ነው። በሃገሪቱ ውስጥ ያለው ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና፤ ማህበራዊ ችግር፤ ፈጦ እየታየ፤ የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት ግን ‘ችግሩ የፖሊሲ ሳይሆን፤ አፈፃፀም ላይ ነው’ በሚል አሳዛኝና አሰቃቂ ቀልድ፤ ወደ 26ኛ ዓመት የስልጣን ልደቱ እየተጓዘ ይገኛል። ከቅርብ ዓመት በፊት፤ ሃይለማርያም ደስአለኝን “ደፋር” ያሰኛቸውን የፓርላማ ንግግር ላዳመጠና፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማእረግ የተሾሙት ደመቀ መኮንን፤ ከጋዜጠኛ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ ስለተፈፀመው ግፍ ተቆርቋሪ ሆነው ሲናገሩ ስንሰማ፤ ‘እነዚህ ሰዎች ወደ ልባቸው እየተመለሱ ነው እንዴ’ ብለው በኢሕአዴግ ላይ ያላቸውን አቋም ለመለወጥ ያመነቱ ጥቂት አልነበሩም። የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በሙስና ተዘፍቀዋል፤ በሃገራችን የመልካም መስተዳድር ጉድለት አለ፤ ዘረኝነትና የዘር መድልዎ በከፋ መልኩ ተንሰራፍቷል ያሉን ሃይለማርያም፤ በነዚህ ሙሰኛና በዳይ ባለስልጣናት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ጣታቸውን ሲያነሱ አላየንም። የአቶ ደመቀም አስተያየት ጉንጭ አልፋ ሆኖ ቀረ እንጂ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ ግፍ የፈጸሙት ሲከሰሱም አላየንም። እንደውም ይባስ ተብሎ፤ እንደ ሽፈራው ሽጉጤ ያሉ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍ የፈጸሙ ሰዎች፤ ለተሻለ ስልጣን፤ ክክልል ወደ ፌደራል ሥልጣን ሲዛወሩ ተመለከትን። በቁስል ላይ ጨው መነስነስ ይህ ነው።

የሕዝብ ብሶት፤ ተጥዶ፤ በስሎና ተንተክትኮ፤ ከገነፈለና በድጋሚ በህዳር 2015 በኦሮምያ ክልል ሕዝባዊ አመጽ ከተነሳ በኋላ፤ ኦሮምያን ተከትሎም፤ በአማራ ክልልና በቆንሶ የሕዝብ አመጽ መቀሰቀሱ፤ በአዲስ አበባም ብልጭ ድርግም የሚል እምቢተኝነት መታየቱ፤ የኢሕአዴግ መራሹን መንግስት የበለጠ ጨካኝና አረመኔ ቢያደረገውም፤እንደ እነ ጄነራል አበበ ተክለሃይማኖትና፤ እንደነ ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ያሉ፤ የቀድሞው ባለስልጣናት፤ የመንግስትን የተሳሳት አቅጣጫ መጠቆም መጀመራቸውና፤ በመላ ዓለም የሚገኘው ኢትዮጵያዊም፤ የኢሕአዴግ መራሹን መንግስት ግፍና በደል በመቃወምና በማውገዝ፤ በአለም መድረኮች ይህን ኢስብዓዊ ግፍ በማጋለጣቸው፤የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ፤በሕዝብ ፊት ምሎ ተገዝቶ እታደሳለሁ አለ። ኢሕአዲግ ከዚህ በፊት ተሃድሶ አድርጊያለሁ ብሎ አልነበረም ወይ እንደገና ለምን መታደስ አስፈለገው ተብሎ ሲጠየቅ፤ አቶ አባዱላ ገመዳ፤ ሰሚውን ባሰደመመ ምላሻቸው፤ ‘እንታደሳለን አልን እንጂ መቼ ደግመን አንበሰብስም አልን’ ሲሉ ተደመጡ። ኢሕአዲግ ታጥቦ ጭቃ እንደሆነም ከዚህ የተሻለ ምስክር አይገኝም። በኦሮምያ ክልል በአማራ ክልልና ሌሎች አካባቢዎች የተንሳውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ፤ የኢሕአዲግ አመራር ስብሰባ አድርጎ እራሴን ገምግምያለሁ ብሎ ነሐሴ 22፣ 2016 ለሕዝብ ይፋ ባደረገው መግለጫ፤ አንባቢውን በሚያሰገርም መልኩ፤ “የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴና እንደገና የመታደስ ጥረት ለላቀ ፍሬ እንዲበቃ መላ የአገራችን ህዝቦች ሰላማዊና ህጋዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።” ሲል አስነበበን። እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ፤ የአስፈጻሚው ኮሚቴ ያለው፤ ሕዝቡ ያነሳው ጥያቄና የትግል እንቅስቃሴው ተገቢ ነው የሚልና፤ እንዳውም አጠናክራችሁ ቀጥሉ ብሎ ጥሪ ያስተላለፈ ነው። ታድያ ትግሉ ትክክልና አስፈላጊ ከሆነ፤ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ሕዝቡን ለምን ያስሩታል ለምንስ ይገድሉታል?

ይህ ታጥቦ ጭቃ የሆነ መንግስት፤የጭቃ ጅራፉ እርስ በእርሱ በሚጣረዝ መግለጫና ድርጊት አላበቃም። ለይምሰል ብሎ፤ ሹም ሽር አደረገና፤ እነ ሙክታር ከድር የመልካም አስተዳደር ጉድለት በማሳየታቸው ከክልል ስልጣናቸው ተነስተዋል ባለን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ፤ ሙክታር ከድር፤ የፌደራል መንግስት የመልካም አስተዳድር ዘርፍ ሃላፊ ሆነው መሾማቸውን ደግሞ ሲያበስረን፤ ገዥው ፓርቲ ከተነከረበት የጭቃ ባኞ ውስጥ ጸድቶ ለመውጣት የማይችል መሆኑን አረጋገጠልን። መከራችን በዚህ ብቻ አላበቃም፤ በሕዝብ ላይ ከ25 ዓመት ተኩል ጀምሮ ጦር የሰበቀው ስርዓት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚል መተተ ጦርነቱን አቀጣጥሎ፤ ላለፉት 25 ተኩል ዓመታት፤ የሰላም ችቦ ይዘው ስለብሔራዊ እርቅ የሚማጸኑትን፤ እንደ ዶ/ር መረራ ጉዲና ያሉ የሰላም ታጋዮችን ደግሞ ማሰሩን ቀጠለበት። በተለያየ ጊዜያት፤ይህ ስርዓት እየተከተለ ያለውን አደገኛ አቅጣጫ እንዲያስተካክል፤ የተቹትን፤ የተሻለ አቅጣጫ የጠቁሙትን፤የመከሩትን፤በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ያሉትን፤ ስርአቱ ጽፎ ያጸደቀው ሕገ መንግስት እንዲከበር እና በስራ እንዲውል ጥያቄ ያቀረቡትን ሁሉ፤ ማሰርና መግደሉን ተያይዞታል። እነዚህ ታሳሪዎችና መስዋዕት የሆኑ ጀግኖች፤ኢሕአዴግ ስለራሱ ከሚለው የተለየ ያሉት ነገር የለም። እነዚህ ቅን ኢትዮጵያውያን፤ በተደጋጋሚ ያሉት፤ ስርዓቱ በስብሷል፤ በሙስና ተጨማልቋል፤የአንድ ዘር የበላይነት እየገነነ ነው፤ መልካም አስተዳደር በሃገሪቱ የለም ነው። ይህንን የሚሉት ደግሞ ያለችውን የሰላማዊ መንገድ እየተጠቀሙ ነው። ስርዓቱ ግን በሕዝብ ላይ ግፍና በደል እየፈፀመ፤ የማይወጣው ጋሬጣ ሲያጋጥምው፤ ሁሌም የሚመዛት፤ የተሃድሶን ካርዱ ነው። ሰልተሃድሶ ከማውራት ውጭ ግን ስር ነቀል ለውጥ ለማድረግና አቅጣጫውን ለማስተካከል የተገበረው ነገር የለም። ዛሬም ከጭቃዬ ታጥብያለሁ ብሎ ሲዳክር የምናየው ግን ጭቃ ውስጥ እየተንከባለለ ነው። ስርዓቱ ሊገነዘብ ያልቻለው፤ ሰላማዊ ትግልን ባፈን ቁጥርና የሰላማዊ ትግል አርበኞችን ባሰረ፤ በገደለና ባሳደደ ቁጥር፤ ‘ካለ ትጥቅ ትግል ለውጥ ሊመጣ አይችልም’ የሚሉትን ዜጎች የሚያጠናክር እንደሆነ ነው።

የሚያሳዝነው፤ የስርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች ከራሳቸው ታሪክ የማይማሩ ያስተሳሰብ ደኩማኖች መሆናቸው ነው። ስርዓቱ ከታሪክ ያልተማረ በመሆኑ፤ ሌ/ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ፤ ዘመን ካለፈባቸው በኋላ፤ በቁጭት የተናገሩት፤ በዚህ ስርዓት እንደሚደገም ምንም ጥርጥር የለኝም። ብዙ ጥፋት ከጠፋ በኋላ ቁጭት ለውጥ አያመጣም። ጀርመናዊው ፈላስፋ ፍሬድሪክ ሔግል እንዳለው ከታሪክ የምንማረው ነገር፤ ከታሪክ እንዳልተማርን ነው። የኢሕአዲግ መራሹ ስርዓት፤ ሃገራችንን ከገባችበት የጦርነት አዙሪት እንዳትወጣ፤ በሰላማዊው ሕዝብ ላይ የሚያካሂደውን ጦርነት ቀጥሏል፤ በሕዝብ ስም፤ የሕዝብን ልጆች እየገደለ ነው። ይህን “ተሃድሶ” ደግመን ደጋግመን አይተነዋል፤ ውጤት አልባነቱንም አስመስክሯል። የብዙዎቻችን ድምዳሜ ስርዓቱ ታጥቦ የማይፀዳ ነው የሚል ሆኗል። ሰለዚህም፤ እኔም ልክ ክርስቲና ኤንግላ እንዳሉት፤ ሰላም ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ፤ጦርነት የሚቀጥል መንግስት፤ብቃትና ችሎታ የሌለው መንግስት በመሆኑ፤ የኢሕአዲግ መራሹ መንግስት ከስልጣን መልቀቅ አለበት እላለሁ። ኢሕአዲግ ብቃትና ችሎታ በሌላቸው፤የሕዝብና አደራ በበሉ፤ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የከፈሉትን መስዋዕትነት ያራከሰ፤ አደገኛና ብቃት የለሽ ስርዓት ለመሆኑ፤ ከራሱ በላይ ሌላ ማንም ምስክር የለም። ዲሞክራሲያዊት እና ፍትሃዊ ስርአት ያለባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት የሕይወት ዋጋ የከፈሉ ወጣቶች፤ ለአንድ ደቂቃ ቀና ብለው፤ የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ቢያዩ፤ በስርዓቱ ምን ያክል ባፈሩ። ኢሕአዲግ ስልጣኑን ለሕዝብ ካላስረከበ የሚያጋጥመው ምን እንደሆነ፤ የቀድሞ የትግል ጓዳቸው ሜጀር ጄነራል አበበ ተክለሃይማኖት ያሉትን በጥሞና እንዲያገናዝቡ እጠይቃለሁ።

“ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ በጠበበ ቁጥር የዜጎች ተስፋ እተሟጠጠ ስጋታቸው እና ፍርሃታቸው እየጨመረ ከቁጥጥር ውጪ የመሆኑ እድል ይሰፋል፡፡ ይህን መሰል ሁኔታም ከውስጥም ከውጪም ሊነሱ ለሚችሉ ፅንፈኛ ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር አገሪትዋን ወደአላስፈላጊ መንገድ ሊመራ ይችላል፡፡ ፍትህ ተራ ፍርድ የማግኘት ጉዳይ አይደለም፡፡ ፍትህ የማህበራዊ ተቛም የመጀመርያ ፀጋው ነው ይላል ጆን ራዉልስ፡ ሙስናና መልካም ያልሆነ አስተዳደርም ሃገርን ሊበትን የሚችል፤እየታየ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ገደል የመክተት አቅም ያላቸው ስርዓታዊ በሽታዎች ናቸው፡፡የሶስቱም እናት ደግሞ የጠበበ ወይም የኮሰመነ የዲሞክራሲ ምህዳር ነው፡፡” ይላሉ ጄነራሉ።

ሃገራችንን ወደተሻለ አቅጣጫ ለመምራት ዛሬም እድሉ አለ። ይህ ጸሃፍ እንደበርካታ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን፤ የብሔራዊ እርቅን አስፈላጊነት ለረጅም ዓመታት ሲያሳስብ ቆይቷል። የኢሕአዲግ አመራርና አባላት፤ ከተጠናወታቸው የግብዝንት በሽታና “የድርጅት ፍቅር” እራሳቸውን አላቀው፤ ትልቁን የሃገር ሰእል በማየት፤ ሃገራችን የብሔራዊ እርቅ አቅጣጫ እንድትከተል፤ በኢሕአዴግ መራሹ መንግስት ላይ የበኩላቸውን ግፊት እንዲያደርጉ በድጋሚ ጥሪ አቀርባለሁ። የብሄራዊ እርቅ አጀንዳ መንገድ እንዲይዝ፤በፍርደ ገምድል ስርዓትና ዳኞች የተፈረደባቸውና፤ እንዲሁም ያለምንምፍርድ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን ስርዓቱ ባስቸኳይ ይፍታ።

ጥበበ ሣሙኤል ፈረንጂ “የባለታክሲው የመጨረሻ ደንበኛ” መጽሃፍ ደራሲ ናቸው። ጸሃፊውን በ ibebesamuel@yahoo.com ማግኘት ይቻላል።

————————

ቦርከናን በፌስ ቡክ “ላይክ” ለማድረግ ይሄንን ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,856FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here