ከዘዉዴ ጉደታ ሙለታ
ታህሳስ 11 2009 ዓ ም
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ድህረ-ገጾችና እንደ ፌስቡክ ባሉ የማህበራዊ መገናኛ መድረኮች አማካይነት የሚሰራጩ አንዳንድ መልዕክቶች እየተካሄደ ላለዉ ፀረ-ወያኔ ትግል ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ የሚያስከትሉት ጉዳት የሚያመዝን ይመስላል፡፡ በተለይም በ1960ዎቹና 1970ዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ዉስጥ በአንድ ወይንም በሌላ መልኩ ተሣታፊ የነበሩና ዛሬም ድረስ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ ሙሉ በሙሉ ያልተለዩ ወይም በጣም ያልራቁ አንጋፋ ወገኖቻችን የሚያነሷቸዉን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ እየተሠራጩ ያሉት አንዳንድ አስተያየቶች የታቃዉሞ ትግላችንን በጣም የሚጎዱ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ አንጋፋ ወገኖቻችን በተግባር ካለፉባቸዉና ዛሬም ከሚታዘቧቸዉ ነገሮች ተነስተዉ አገራችን ከወያኔ አገዛዝ ነፃ የምትወጣበትንና ወደ እዉነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት የምትሸጋገርበትን መንገድ በማመላከቱ ረገድ የጎላ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸዉ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዶቹ ምክንያታዊ ያልሆኑ ትችቶችንና አላስፈላጊ ተራ ስድቦችን የመቋቋም ችሎታና ንቆ የማለፍ ትዕግሥት የሌላቸዉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት የየትኛዉም የፖለቲካ ድርጅት አባል ሳይሆኑ ስለአገራቸዉና ስለሕዝባቸዉ የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር ዕረፍት ስለሚነሣቸዉና ኢትዮጵያዊነታቸዉ ስለሚያስገድዳቸዉ ብቻ የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚሞክሩት ወገኖቻችን በየድህረ ገጾችም ሆነ በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች በተለይም በፌስቡክ ገጾች ላይ በሚተላለፉት ልቅና ስሜታዊ አስተያየቶች ብሎም ስድቦች ምክንያት ተስፋ ቆርጠዉ ራሣቸዉን ከአገራቸዉ ጉዳይ ለማራቅ ይገደዱ ይሆን? ብዬ እሰጋለሁ፡፡ ይህችን አጭር መልዕክት በዚህ ርዕስ ሥር ለመጻፍ ያነሣሣኝም ይኸዉ ስጋቴ ነዉ፡፡
በመሠረቱ አንዳንዶቻችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ያለንበት ነፃ ዓለም ስለተመቹንና አንዳንድ መሠሎቻችንና የፌስቡክ ተከታዮቻችን ደግሞ የሃሳቦቻችንን ጥልቀትም ሆነ ጎጂ ጎን ሣይረዱ ወይም ሣያገናዝቡ በስሜታዊነት በመነሣሣት ብቻ አድናቆታቸዉን ወይንም የድህረ-ገጽ ላይ ድጋፋቸዉን ስለቸሩን “ከእኔ በላይ አዋቂ የለም” ብለን የደመደምን እንመስላለን፡፡ በመሆኑም ሃሳብን በሃሳብ ከመሞገትና የምናራምደዉን ሃሳብ ለማሣመን ከመሞከር ይልቅ ከሃሳባችን ጋር ያልተስማሙትን ወገኖች ሁሉ የትናንት ፖለቲካዊ ተሣትፎአቸዉን በማጣቀስ ወይንም ደግሞ በአንዳንድ መድረኮች ለይ ያነሷቸዉን ሃሳቦች ሃሳቦቹ ከተነሱበት/ከተነገሩበት ይዘት ዉጭ (out of context) በመዉሰድ መስደብን፣ ማዋረድን፣ ብሎም ማሸማቀቅን የዘወትር ተግባራችን ያደረግን እንመስላለን፡፡ ይህ ደግሞ እናካሄዳለን ለምንለዉ የነፃነት ትግል ምንም የሚጠቅመዉ ነገር የለም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጠለቅ ያሉና ብዙዎች ለማንሣት የማይደፍሩትን አንዳንድ አከራካሪ ሃሳቦች በድፍረት በማቅረብ የሚታወቁ ጥቂት ኢትዮጵያዉያንን ያለፈ የፖለቲካ ተሣትፏቸዉን፣ ዕድሜያቸዉን ብሎም ከየትኛዉ ብሔረሰብ እንደሆኑ በመጥቀስ (አመለካከታቸዉን ከብሄረሰባቸዉ ወይም ከዕድሜያቸዉ ጋር በማጣመር) ለመተቸተ መሞከር እናካሄዳለን ለምንለዉ የነፃነት ትግል ምን ሊጠቅም እንደሚችል አይገባኝም፡፡ የዚህ ዓይነቱ እጅግ ተራ የሆነ አቀራረብ የሚጠቅመዉ መግባባታችንን የማይፈልገዉን ወያኔንና ወያኔን ብቻ ነዉ፡፡ ገዢዉን ሥርዓት እንቃወማለን ለምንለዉ ወገኖች ጠቃሚ ሊሆን የሚችለዉ እነዚህን አንጋፋ ወገኖቻችንን በተገኘዉ መንገድ ሁሉ ቀርበናቸዉ ወይንም አቅርበናቸዉ ከሃሳቦቻቸዉ ወይም ከአመለካከቶቻቸዉ ያልገባንን እንዲያስረዱን መጠየቅ፣ ከተሞክሮዎቻቸዉ መማር፣ ልምዳቸዉን እንዲያካፍሉን ማድረግና ለዛሬዉ ዉስብስብ የአገራችን ችግሮች መፍትሔ ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በተግባራዊ ልምድ ላይ የተመሠረተ ምክራቸዉን እንዲለግሱን በአክብሮትና በትህትና መጠየቅ ነዉ፡፡
የፖለቲካ ተሣትፎ የሚያደርጉ ግለሰቦች (Political Activists) ብቻም ሣይሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንም ቢሆኑ እነዚህን ከዕድሜ፣ ከፖለቲካ ተሣትፎ፣ ከሕይወት ተሞክሮና ከተግባራዊ የሥራ ልምድ የተገኘ ሰፊ ዕዉቀት ባለቤት የሆኑትን ወገኖቻችንን አመቺ በሆነዉ መንገድ ሁሉ ቢቀርቧቸዉና ሌላዉ ቢቀር በአማካሪነት እንኳ ቢጠቀሙባቸዉ ለሥራቸዉ መቃናት በጣም ይረዳቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ረገድ በቅርቡ የተቋቋመዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (ኢአን) በአርዓያነት ሊታይ የሚችል እንቅስቃሴ ለማድረግ ያለመ ይመስላል፡፡ ኢአን ምሥረታዉን ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ “የአማካሪዎች ምክር ቤት” (Consultative Council) የሚባል አካል እንደሚኖረዉ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ንቅናቄዉ በሚያቋቁመዉ የአማካሪዎች ምክር ቤት ዉስጥ በሁሉም መስኮች ሰፊ ልምድ ያካበቱና ተግባራዊ ተሞክሮ ያላቸዉን ኢትዮጵያዉያን ያካትታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የአማካሪዎች ምክር ቤቱ ከተለያዩ የሙያ መስኮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የዕምነት ተቋማት፣ ወዘተ የተዉጣጡ በሳልና ሰፊ ልምድ ያካበቱና ከሁሉም የአገራችን ሕዝቦች የተገኙ ኢትዮጵያዉያን የሚካተቱበት እንዲሆን ቢደረግ ለንቅናቄዉ ዓላማዎች ግብ መምታት የሚጠቅሙ ሃሳቦችን የሚያመነጭና ብዙ ጥሩ ሥራዎችን የሚሠራ የአገራዊ ንቅናቄዉ በጣም ጠቃሚ ክንፍ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ይህ ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በፌስቡክ ከምናየዉ አንጋፋዎቻችንን የመስደብ፣ የማዋረድና የማሣነስ ተግባር የተለየ ስለሚሆን የአገራችንን ወቅታዊ ፖለቲካ ትንሽ ለየት ባለና እስከአሁን ብዙም ባልተለመደ መልኩ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሰ አድርጎ ወደፊት ለማራመድ ይጠቅማል፡፡ ያ ብቻም ሣይሆን ባለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት የወያኔ ተቃዉሞ እንቅስቃሴዎች ዉስጥ ደጋግመን የታዘብነዉንና በጣም አሣፋሪ የሆነዉን በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሚመሠረቱ ትብብሮችን/ህብረቶችን በተመሠረቱ ማግሥት የማፍረስ ችግር ኢአንን እንዳያጋጥመዉ ለማድረግም ይረዳል፡፡ በተጨማሪም የዚህ ዓይነት አካል ማቋቋሙ ልምዱም፣ ችሎታዉም፣ ፍላጎቱም፣ ዕዉቀቱም ሣይጎላቸዉ ወያኔ በጠመንጃ ኃይል ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ዉሉ የጠፋዉ የአገራችን ፖለቲካ አስጠልቷቸዉና ተስፋም አስቆርጧቸዉ በየቤታቸዉ ገብተዉ ለመቀመጥ የተገደዱትን በርካታ ኢትዮጵያዉያን በቀጥታ እንኳን ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ወደትግሉ ጎራ እንዲመጡ ያደርጋቸዉ ይሆናል፡፡
እንደሚታወቀዉ ከስመ-ጥሩዉ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደቶች ዉስጥ የጎላ ሚና የነበራቸዉ ብርቅዬ ወገኖቻችን በዕድሜም ሆነ በሌሎች የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰዉ-ሠራሽ ጫናዎች ምክንያት ከጊዜ ወደጊዜ እየተለዩንና በቁጥር እየተመናመኑ ሄደዋል፡፡ ስለሆነም የሕይወት ዉጣ-ዉረዶችን ሁሉ አልፈዉ በሕይወት ለመቆየት የታደሉት አንጋፋ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን መከበርና በስስት ዓይን መታየት ያለባቸዉ ዕንቁዎቻችን እንጂ መሰደብና መዋረድ ያለባቸዉ ባላንጣዎቻችን አይደሉም፡፡ ለዚህም ነዉ እነዚህን ጠቃሚ ዜጎች በአማካሪ ምክር ቤቱ አማካይነት በኢአን በጎና ተስፋ ሰጪ ጅምር ዉስጥ ማሣተፍ ንቅናቄዉን እስከአሁን ከተፈጠሩት የፖለቲካ ደርጅቶች ትብብሮችና ህብረቶች የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል ብዬ የማምነዉ፡፡
እንደዛሬዉ የብሔር-ብሔረሰብ አጥር ሣይከልላቸዉ የሚያምኑበትን ዓላማ ብቻ መሠረት በማድረግ ትክክለኛ እና ለአገር ጠቃሚ ናቸዉ ብለዉ ባመኑባቸዉ የትግል መስመሮችና የፖለቲካ ድርጅቶች ሥር ተሰባስበዉ ብዙ ጠቃሚ አስተዋፅኦዎችን ያበረከቱት ወገኖቻችን ብዙዎቻችን አገራችንንና ሕዝቦቻችንን በተመለከተ ለምናንፀባርቃቸዉ የዛሬዎቹ አመለካከቶቻችን መሠረቶች ናቸዉ፡፡ ስለሆነም ከተሞክሮዎቻቸዉ የምንማራቸዉ ብዙ በጣም ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ስለመኖራቸዉ ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም፡፡ በበኩሌ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አንዳንዶቹን በአካል የማግኘትና በጣም በመቅረብም አብሬያቸዉ የመሥራት ዕድል ስላገኘሁ ስለአገሬና ስለወገኖቼ ከመደበኛ ትምህርትም ሆነ ከንባብ ያላገኘሁትን በርካታ ጠቃሚ ዕዉቀቶችን ከእነዚህ ወገኖቼ ለመማር ችያለሁ፡፡ ስለሆነም በዚች ጽሑፍ አማካይነት ለሌሎች ኢትዮጵያዉያን ወንድሞቼና እህቶቼ በተለይም በዕድሜ ታናናሾቼ ለሆኑትና ከምንም በላይ የፌስ-ቡክ ተጠቃሚ ለሚመስሉ የአሁኖቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ንቁ ተሣታፊዎች (Facebook-based Ethiopian political activists of the current time) ለማስተላለፍ የምሞክረዉ ይህ መልዕክት ከይሆናልና ከባዶ ሜዳ በመነሣት የምፅፈዉ ሣይሆን በተጨባጭ ያየሁትን የግል ተሞክሮ መሠረት ያደረገ እንደሆነ ላሰምርበት እወዳለሁ፡፡
አለመታደል ሆኖ እንጂ ከእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ጀምሮ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች ይዘዉት ተነስተዉ የነበረዉ ሕዝባዊና አገራዊ ዓላማ ተሣክቶላቸዉ ቢሆን ኖሮ አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ብሎም በዕድገትና ሥልጣኔ የዳበረችና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ልዩ ምሳሌ መሆን በቻለች ነበር፡፡ በግል ኑሯቸዉ ምንም ሣይጎልባቸዉ ሕዝብን ከችግር ለማላቀቅ ወደትግል የገቡት ቀደምቶቻችን ያለሙት አገርን የማሻሻልና ሕዝብን ከችግር ነፃ የማድረግ ትልም ሙሉ በሙሉ ባይሳካላቸዉም ብዙ ጥሩ ሥራዎችን ሠርተዉ እንዳለፉና ለዛሬዉ አስተሳሰባችንና አመለካከታችን መሠረት የሆኑ ጠቃሚ አስተዋፅኦዎችን እንዳደረጉ ግን መካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በሌላ አባባል ከራሣቸዉ ምቾት፣ ጥቅምና ዝና ይልቅ ለአገራቸዉና ለሕዝባቸዉ ቅድሚያ በመስጠት ሁሉንም ዓይነት ተፅዕኖዎች በመቋቋም የታገሉት እነዚህ አንጋፋዎቻችን በርካታ ጠቃሚ አስተዋፅኦዎችን አበርክተዉልናል፡፡ቢያንስ “እኔን ከተመቸኝ ወይንም እኔ በግል ካልተነካሁ የሌላዉ ጉዳይ ምኔ ነዉ?” የሚል ራስ-ተኮር (self-centered) አመለካከት እንዳይኖረን በማድረጉ ረገድ ያበረከቱልን አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡
ስመ-ጥሩ ከሆነዉ የኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ተሣታፊነት ጀምረዉ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ መንግሥት በጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከተተካም በኋላ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ሥር በመሰባሰብ ለአገራቸዉና ለሕዝባቸዉ ጠቃሚ ሥራዎችን ለመሥራት ሞክረዉ ያልተሣካለቸዉ ወገኖቻችን ተገቢ ክብርና ልዩ እንክብካቤ የሚገባቸዉ ናቸዉ ብል “አይ አይደሉም አጋነንክ” የሚለኝ አንባቢ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ በማይችለዉ የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህላችን ምክንያት በመንግሥት ኃይሎች ከተፈጁትና እርስበርስም ከተፋጁት ምርጥ ኢትዮጵያዉያን መካከል በእግዚአብሔር ተዓምር ተርፈዉ ዛሬም ድረስ ከአገራቸዉ የፖለቲካ መድረኮች ራሳቸዉን ያላገለሉት ወይንም ተስፋ ቆርጠዉ የተቀመጡት እነዚህ ብርቅዬ ወገኖቻችን አሁንም ብዙ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ አጠያያቂ አይደለምና የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ በአግባቡ ሊጠቀምባቸዉ ይገባል እላለሁ፡፡ ከምንም በላይ አንዳንዶቹን ተንቀሣቃሽ ቤተ-መጻሕፍት (walking library) እንድንላቸዉ የሚያደርገንን ተዝቆ የማያልቀዉን ከመደበኛ ትምህርት፣ ከሥራ ልምድ፣ ከዓመታት የሕይወት ተሞክሮ እና ከሰፊ የንባብ ባህል የተገኘ ዕዉቀታቸዉን፣ ያለፈ ትዝታቸዉንና ተግባራዊ ተሞክሮዎቻቸዉን መስማት በራሱ እጅግ በጣም ጠቃሚ ብቻ ሣይሆን አስፈላጊም ነዉና የነገዎቹ አገር ተረካቢ ወጣት ኢትዮጵያዉያን ከጊዜ አመጣሹ የድህረ-ገፅ በተለይም የፌስቡክ ስድብና አንዱ ሌላዉን የማዋረድ አሣፋሪ ተግባር ወጥተዉ ከአንጋፋዎቻችን ጠቃሚ ትምህርት እንዲቀስሙ በማድረጉ ረገድ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ብዙ ሊሠራ የሚችል ይመስለኛል፡፡ (ወደ ገጽ 2 ዞሯል)