spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትወዴት እየሄድን ነዉ? የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (ኢአን)፣አንጋፋዎቻችን እና ፌስቡክ

ወዴት እየሄድን ነዉ? የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (ኢአን)፣አንጋፋዎቻችን እና ፌስቡክ

ስማቸዉን ዘርዝረን የማንዘልቃቸዉ በሕይወት የሌሉና ዛሬም ድረስ በሕይወት ያሉ እነዚህ ወገኖቻችን ለአገራችንና ለሕዝቦቻችን የሚበጁ የትልልቅ ራዕዮች ባለቤቶች እንደነበሩና እንደሆኑ መካድ አይቻልም፡፡ አንዳንዶች ይህችን አጭር ፅሑፍ ሲያነቡ በየግል ቀረቤታዎቻቸዉና ግንኙነቶቻቸዉ ምክንያት የሚያዉቋቸዉን አንዳንድ አንጋፋ ኢትዮጵያዉያን ያስባሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (ኢአን) ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነትና ወንድማማችነት የሰፈነባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የእነዚህን በሕይወት የሌሉና ዛሬም ድረስ በሕይወት ቆይተዉ ከትግሉ ሜዳ ሙሉ በሙሉ ያልተለዩ ብርቅዬ ኢትዮጵያዉያን ራዕይ ዕዉን ለማድረግ ይሠራል ተብሎ ይገመታል፡፡ መጠፋፋትና በየምክንያቱ መጠላለፍ ጎልቶ የሚታይበትን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደት ከመሠረቱ መለወጥ ከሚቻልባቸዉ መንገዶች አንዱም አንጋፋዎቻችንን በማግለልና በማዉገዝ ሣይሆን በተለያዩ መንገዶች የትግሉ ተሣታፊዎችና ጠቃሚ አጋሮች የማድረግን ዓይነት ከአሁን በፊት ብዙም ጎልተዉ ያልታዩና ያልተለመዱ ለየት ያሉ ነገር ግን ፀረ-ወያኔ ትግሉን ዉጤታማ ለማድረግ በጣም ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ አካሄዶችን በመከተል ነዉ ብል የተሣሣትኩ አይመስለኝም፡፡

በሣልና አንጋፋ ፖለቲከኞቻችን አንድን ሃሳብ ሲያቀርቡ ያነሱት ሃሳብ ትክክለኛ መስሎ ካልታየን ወይም እኛ የማንቀበለዉና የማናምንበት ከሆነ ትህትናና አክብሮት ባልተለየዉ መንገድ መቃወምና ሃሳብን በሃሳብ መሞገት ብሎም ያላቸዉን ልምድ፣ ተሞክሮና ዕዉቀት መሠረት አድርገዉ ሊያበረክቱ የሚችሉትን ሁሉ እንዲያበረክቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና በተቻለ መጠን ደግሞ ከእያንዳንዳቸዉ ጠቃሚ ቁም ነገሮችን ለመቅሰም መሞከር ይገባናል እንጂ ፌስቡክና ሌላዉም የመገናኛ ቴክኖሎጂ ስለተመቸን ብቻ የትናንት ተሞክሮዎቻቸዉን አንስተን ማዉገዝ፣ ማዋረድ፣ ማሸማቀቅና ማሣነስ ተገቢ አየደለም፡፡ ከዚያም አልፎ ብዙዎቻችን ፌስ-ቡክንም ሆነ ሌሎች የማህበራዊ መገናኛዎችን የምናዘወትር ኢትዮጵያዉያን በዕድሜ፣ በትምህርትም ሆነ በተግባራዊ የሥራ ልምድና በሕይወት ተሞክሯችን ከብዙዎቹ የ1960 እና 1970ዎቹ ፖለቲከኞችና አንጋፋ ምሁራን የምናንስ ስለሆንን የአገራችንን፣ የአህጉራችንንና የዓለማችንን ያለፉ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እዉነታዎች በተመለከተ ያለንን የዕዉቀት ዉስንነት ተረድተን ከእነዚህ አንጋፋዎቻችን ለመማር መሞክር በራሱ አዋቂነት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

አንዳንዶች ሲያደርጉ እንደታዘብነዉ እኛ በየራሣችን ምክንያቶች ሃሳባቸዉን የማንደግፈዉን እነሱ ግን ለአገራቸዉ በራሣቸዉ መንገድ ጠቃሚ አስተዋፅኦ ለማድረግ የሚሞክሩትን አንጋፋ ኢትዮጵያዉያን በጭፍን ስሜትና በችኮላ ወደማዉገዝ፣ ከዚያም አልፈን የዘር ሀረጋቸዉን ሣይቀር እንደምሳሌ ወስደን ጥላሸት ለመቀባትና ለማሸማቀቅ ወደመሞከር፣ ትናንት በሠሩት የፖለቲካ ሥራዎች ምክንያት ለመተቸት ብሎም ለማዋረድ መቸኮል ፍፁም ተገቢ አይደለም፡፡ በግልፅ እንነጋገር ከተባለ በድህረ ገፆች ወይም በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች አማካይነት አንዳንድ ነገሮችን ጽፈን መበተን ስለቻልንና የእድሜ፣ የዕዉቀትና የአስተሣሰብ መሰሎቻችን አድናቆታቸዉን ስለቸሩን ከአቅማችን በላይ ራሳችንን ከፍ ከፍ አድርገን የማየቱ ስሜታዊ አቀራረብ የትም አያደርሰንም፡፡ እዉነቱን እንነጋገር ከተባለ እርስ በእርስ የሚያነጋግረንና የሚያነታርከን ዋነኛ ጉዳይ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያዉያን ነፃነት ጉዳይ መሆኑን የምናምን እስከሆነ ድረስ የእኛ የሆኑትን የጋራ እሴቶቻችንን የምንረሣዉ ለምንድነዉ?

ታላላቆቻችንን ማክበር ከቆየዉ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አንዱ (among the old Ethiopian values) መካከል የመሆኑን እዉነታ የማያዉቅ የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ያለ አይመስለኝም፡፡ ባለበት እየረገጠና ወደፊት አልራመድ እያለ የተፈታተነን የተቃዉሞ ፖለቲካችን ራሱ ከታለመለት ግብ ሊደርስ የሚችለዉ የራሣችን የሆኑ አንዳንድ ጠቃሚ እሴቶችን ስንጨምርበት ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም መለስ ብለን በማየት (ፈረንጆች “back to roots” እንደሚሉት ማለቴ ነዉ) ምን ምን ጠቃሚ እሴቶቻችንን ብንጠቀም ዉጤታማ ልንሆን እንደምንችል ማሰብ አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ በዕድሜ፣ በትምህርት፣ በተግባራዊ የሥራ ልምድ እና ለህብረተሰቡ ባበረከቱት አስተዋፅኦ ታላላቆቻችን የሆኑትን ወገኖቻችንን ማክበርና ከእነሱም ለመማር መሞከር ደግሞ ከቆዩት ባህላዊ እሴቶቻችን የሚደመር በጎ ተግባር እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህ ሥልጣኔ ወይም አዋቂነት መስሎን ሃሳባቸዉ የማይስማማንን ሁሉ ለማዋረድና ለማሣነስ መጣደፉ የትም እንደማያደርሰን ተረድተን ኢትዮጵያዊ ወደሆነዉ የመከባበር ባህላችን የመመለሱ አስፈላጊነት ቀጠሮ የሚሰጠዉ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ አንጋፋዎቻችንም ቢሆኑ ትናንት ዛሬን ሊሆን አይችልምና የአሁኑን በአብዛኛዉ ቴክኖሎጂ-መራሽ የሆነዉን የዓለማችንን፣ የአህጉራችንንና የአገራችንን ተጨባጭ እዉነታ ተረድተዉ የዕድሜም ሆነ የዕዉቀት እንዲሁም የልምድና የሕይወት ተሞክሮ ታናናሾቻቸዉን ስሜት፣ ምኞትና ስጋት ለመጋራት መሞከር ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢአን እንግዲህ በሚያቋቀመዉ ሰፊ መሠረት ያለዉ የአማካሪዎች ምክር ቤት (broad-based Consultative Council) አማካይነት በትዉልዶች መካከል ጎልቶ መታየት የጀመረዉን ክፍተት ለመሙላት መሥራት እንዳለበት ይሰማኛል፤ ይሠራልም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ብዙዎቻችን ወደምንመኘዉ የአብሮነትና የጋራችን የሆነች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ የመገንባት አኩሪ ደረጃ ላይ መድረስ የምንችለዉ ስንዋደድ፣ ስንከባበር፣ ስንተሳሰብና እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ለመራመድ ስንችል እንደሆነ ለአፍታ እንኳን መዘንጋት የለብንም፡፡ ይህ የመተባበር፣ የመቀራረብ፣ የመከባበር፣ የመተባበርና የመፈቃቀር መንገድ ደግሞ አገር ቤት ባለዉና የወያኔ-ሠራሽ ችግሮች ሁሉ ገፈት ቀማሽ በሆነዉ ሕዝባችን በተለይም በሁለቱ ታላላቅ የአገራችን ብሔሮች ማለትም በአማራና በኦሮሞ መካከል በጣም በሚያበረታታና ተስፋ ሰጪ በሆነ መንገድ የተጀመረ መሆኑን በተግባር አይተናል ወይም ሰምተናል፡፡ ይህ ደግሞ ላለፉት ለሃያ-አምስት ዓመታት ሕዝብን ከሕዝብ አለያይቶ ለማጋጨት የተሠራዉ ጭፍን የወያኔ ሥራ ተመልሶ ሊያንሠራራ በማይችልበት ሁኔታ የከሸፈ መሆኑ በተግባር የታየበት ነዉ፡፡ የእኛ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተበትነን የስደት ኑሮን ለመግፋት የተገደድን ወይንም የመረጥን ኢትዮጵያዉያን ድርሻ መሆን ያለበት እንግዲህ ለሕዝቦቻችን ጥረቶች አጋር መሆን የሚያስችሉንን መንገዶች በመከተል ተባብረንና ተከባብረን የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ነዉ፡፡ ይህን ወያኔ ያመጣብንን እጅግ ፈታኝና ክፉ ጊዜ በአሸናፊነት ለማለፍና የዛሬዉን መጥፎ ሁኔታ ወደበጎ ለመለወጥ የምንችለዉ ሕዝባችን በአገር ዉስጥ እያደረገ እንዳለዉ ሁሉ እኛም በየአገሩ ተበትነን ያለነዉ ኢትዮጵያዉያን ተባብረን፣ ተከባብረንና ከምንጊዜዉም በላይ እጅ ለእጅ ተያይዘን አብረን መሥራት ስንችል ብቻ ነዉ፡፡

አንዳንዶቹ የቅናት በሚመስል መንገድ “ሣይወለድ ሞተ” የሚሉት የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ያን ማድረግ የሚያስችለን ብዙዎቻችን የምንመካበት ኢትዮጵያዊ ስብስብ ሊሆን ይችላል? በቅርቡ የሚታይ ይሆናል!!

ጸሃፊው አቶ ዘውዴ ጉደታን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል ፤ zewdieg@gmail.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here