spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ እና የአገር አንድነትን “ያገቱት” ሦስት ተፃራሪ ኃይሎች (ዘዉዴ ጉደታ...

የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ እና የአገር አንድነትን “ያገቱት” ሦስት ተፃራሪ ኃይሎች (ዘዉዴ ጉደታ ሙለታ)

ከዘዉዴ ጉደታ ሙለታ
ታህሳስ 26 ፤ 2009 ዓ ም

ብዙዎቻችን በየቆምንበት ማዕዘን ላይ ሆነን ስለአገራችን ኢትዮጵያ ትክክለኛ የመሰለንን ሁሉ እንናገራለን፤ የዛሬ ችግሮቻችን ናቸዉ ለምንላቸዉ ጉዳዮችም ትክክለኛ መስለዉ የታዩንን የመፍትሔ ሃሳቦች ለማቅረብ እንሞክራለን:: ጥቂቶች ደግሞ የሚያምኑባቸዉን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ አመቺ ሆነዉ ያገኟቸዉን መድረኮች ተጠቅመዉና ጊዜያቸዉንም ሰዉተዉ ማራኪ፣ አስተማሪና አሣማኝ የሆኑ ጽሑፎችን ለአንባቢያን በማቅረብ ጠቃሚ ዉይይቶችን ያስነሳሉ፤ በሚያቀርቧቸዉ ጽሑፎች አማካይነትም አንባቢዎቻቸዉን ያስተምራሉ፤ ከአንባቢዎቻቸዉም ይማራሉ፡፡ ከዚያ ከፍ ባለ ደረጃ የተሰለፉት አገሬን፣ ወገኔንና ነፃነቴን ያሉ ኢትዮጵያዉያን ደግሞ የሚያምኑበትን ዓላማ በሚያራምዱ (እናራምዳለን በሚሉ) የፖለቲካ ድርጅቶች ጥላ ሥር ተሰባስበዉ የየበኩላቸዉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ይፍጨረጨራሉ፡፡ ቆራጥ የሆኑት ጥቂቶቹ ደግሞ የተመቻቸ ኑሯቸዉንና የሚወዱትን ቤተሰባቸዉን ትተዉ ትግሉ የሚጠይቀዉን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል በመወሰን በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈዉ ታግለዉ በማታገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምርጥ ኢትዮጵያዉያን ያሉባቸዉን አላስፈላጊ ጫናዎችና ተፅዕኖዎች ሁሉ ተቋቁመዉ የነፃነት ትግሉን በሕዝባዊ ድል ለመደምደም በሚያስችል ደረጃ ለማራመድ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰዱም ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ወያኔን በመቃወም የሚደረገዉ ትግል ለሚፈለገዉ ዉጤት ሊበቃ አልቻለም፡፡

በመሠረቱ ሃያ-አምስት ዓመታትን ያስቆጠረዉ ወያኔ-መራሹን መንግሥት በመቃወም በየአቅጣጫዉ የሚደረግ ትግል ለምን የተፈለገዉን ግብ መምታት ወይንም ለምን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጉጉት የሚጠብቁትን ዉጤት ማስገኘት እንዳልቻለ ለማወቅ ራሱን የቻለ ሣይንሳዊ ጥናት በቂ ዕዉቀት፣ ጊዜ፣ ልምድ፣ ችሎታና የተሟላ ፍላጎት ባላቸዉ የማህበራዊ ሣይንስ ባለሙያዎች መደረግ ይኖርበታል፡፡ ከሣይንሳዊ ጥናት በመለስ ግን በግልፅ የሚታዩና ብዙዎች በቀላሉ የሚረዷቸዉን ምክንያቶች ማየት ተገቢ ነዉ፡፡ የዚህ ፅሑፍ ዓላማ እነዚህን ነጥቦች በማንሣት “ለገንቢ ዉይይት” መነሻ ሊሆን የሚችል ሃሳብ በግልፅነት፣ በቅንነትና በድፍረት ለማቅረብ መሞከር ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ “ገንቢ ዉይይት” ለሚለዉ ሃሣብ (ነጥብ) አንባቢያን ተገቢዉን ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም መከባበር ሣይሆን መናናቅ፣ ፍቅር ሣይሆን ጥላቻ፣ እኛ/ለእኛ ሣይሆን እኔ/ለእኔ፣ መቀራረብ ሣይሆን መራራቅ፣ መተባበር ሣይሆን መበታተን፣ መግባባት ሣይሆን መቃቃር፣ መመሰጋገን ሣይሆን መወቃቀስ፣ ወዘተ ጎልተዉ በሚታዩበት የወያኔ ተቃዋሚ ወገኖች የፖለቲካ መስክ በሚገባ ያልታሰበባቸዉን አፍራሽ ሃሳቦች በስሜታዊነት መወርወርና እኛ የማናምንበትን ሃሳብ ይዞ የተነሣን ወገን ማሳነስ፣ ማዋረድና ማሸማቀቅ እየተለመደ የመጣ የዘወትር ተግባር ስለሆነ ነዉ፡፡ ይህ ድምዳሜ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየድህረ-ገጹም ሆነ በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች፣ በተለይም በፌስ-ቡክ የሚወጡ ጽሑፎችንና በጽሑፎች ላይ የሚሰጡ የአንባቢያን አስተያየቶችን ማየት ይበቃል፡፡ ስለሆነም የሕዝቦቻችን መከራና ስቃይ አሁን በደረሰበት ደረጃ ላይ ሆነን ስናስብ በተለያዩ አገሮች ከምንገኘዉ ኢትዮጵያዉያን መካከል አብዛኞቻችን የሚፈለግብንን፣ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የዕዉቀት፣ የሞራል፣ ወዘተ አስተዋፅኦዎችን ማበርከታችን ሣይቀር፤ አገር ቤት ያሉት ወገኖቻችን ደግሞ ማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ከጨካኝ የወያኔ የአንድ ወገን ሠራዊት ፊት ባዶ እጃቸዉን በድፍረትና በጀግንነት ቆመዉ የአካል፣ የደም ብሎም የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸዉ ሳይቀር “የፀረ-ወያኔ ተቃዉሞ ትግላችን

ዉጤታማ ያልሆነዉ ለምንድነዉ?” ብለን በግልፅ አለመጠያየቁ ወያኔ-ሠራሽ መከራችንን አርዝሞታል፤ አሁንም ይህንን ጥያቄ ለመጠያየቅ ድፍረቱና ፍላጎቱ ከሌለን የእስከዛሬዉ ዉጤት-አልባ አካሄዳችን መከራችንን የበለጠ ያረዝመዋል፡፡

የፀረ-ወያኔ ትግላችን የሚፈለገዉን ዉጤት አለማስገኘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ሁሉም የወያኔ ታቃዋሚ ኃይሎች ስለ ሁለት ጉዳዮች ደግመዉ
ደጋግመዉ ያነሣሉ፡-
1. ስለኢትዮጵያ አንድነት – (አንድነትን በመደገፍም በመቃወምም የሚታገሉ ወገኖች መኖራቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ)
2. ስለወገኖቻችን በወያኔ አገዛዝ ሥር የስቃይ ኑሮን ለመምራት መገደድና ከዚህ አስከፊ ኑሮ ነፃ ለመዉጣት መታገል አስፈላጊ ስለመሆኑ፡፡
እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ዕዉነትም የሚያነጋግሩና ትኩረት ሊሰጣቸዉ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸዉ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ለጥያቄዎቹ እስከአሁን አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ያልተቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ አለመሞከር ለወደፊቱም ወያኔ-ሠራሽ መከራችንን እንደሚያረዝመዉ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም ነገ ሣይሆን ዛሬ፣ በመሸፋፈንና በማድበስበስ ሣይሆን በግልፅነት፣ በሚያራርቅና በሚያቃቅር መንገድ ሣይሆን በሚያቀራርብና በሚያግባባ መንገድ፣ ለጥርጣሬ በር በሚከፍት መንገድ ሣይሆን መተማመንን መፍጠር በሚያስችል መልኩ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በድፍረት አንስተን ልንወያይባቸዉ ይገባል፡፡ ይህን ካደረግን ወያኔን ተባብረን መጣልና ከወያኔ ዉድቀትም በኋላ አገራችንን ለሁላችንም ልትስማማና ሁላችንንም እንደልጆቿ በእኩልነት ልታቅፈን በምትችልበት መንገድ የመገንባቱ ሥራ ከባድ አይሆንም፡፡

በዚህ ረገድ በቅርቡ የተመሠረተዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (Ethiopian National Movement) እስከአሁን በተቃዉሞዉ ጎራ ሲታዩ የነበሩትን ድክመቶች አስወግዶ፣ ችግሮችን በተቻለ መጠን ፈትቶና ካለፉት ስህተቶች ትምህርት ወስዶ ለሁሉም ልጆቿ የምትመች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ላይ እንደአዲስ ለመመሥረት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሕብረ-ብሔራዊ በሆነና ብሔር-ብሔረሰቦችን መሠረት አድርገዉ በተደራጁ አራት የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ ስምምነት የተመሠረተዉና ሌሎች ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችንም ለማካተት በሩ ክፍት መሆኑን በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጦ ሥራዉን በይፋ የጀመረዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ሕዝቦች የነፃነት ትግል ከፍ ወዳለ ደረጃ ላይ ለማድረስና በተበታተነ መንገድ እየተካሄደ ያለዉን የነፃነት ትግል አቀናጅቶ በሕዝባዊ ድል ለመደምደም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በሚያስችለዉ ጎዳና ላይ ለመራመድ ወስኖ ለመነሣቱ የንቅናቄዉ መሪዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ ከሰጧቸዉ ይፋዊ መግለጫዎች በተጨማሪ በግልፅ ቋንቋ የተቀመጠዉ የንቅናቄዉ መጠሪያ ስም ራሱ በቂ ምስክር ነዉ፡፡ ስሙ በግልፅ እንደሚያመለክተዉ ንቅናቄዉ “አገራዊ”ነዉ፤ ያቺ አገር ደግሞ ወደድንም ጠላንም የሁላችንም የጋራ ቤት የሆነችዉ “ኢትዮጵያ”ናት፡፡ ስለሆነም ራሣቸዉን “የአንድነት ኃይሎች” ብለዉ የሚጠሩ ወገኖች ጧት ማታ እንደዋነኛ የመታገያ አጀንዳቸዉ አድርገዉ የሚያቀርቡትና ለብሔር-ብሔረሰቦች መብት መከበር እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችንና ልሂቃንን በአገር አፍራሽነት ወይንም በፀረ-አንድነት የሚከሱበት “የአገር አንድነት”ጉዳይ የሁሉም ሕዝቦች መሠረታዊ የዲሞክራሲ መብቶች ሣይሸራረፉ እስከተከበሩ ድረስ በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ መሥራቾች ዘንድ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉደይ አይደለም፡፡ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎት ከግምት ዉስጥ ገብቶ ያልተሸራረፈ የዲሞክራሲ መብትን ዕዉን ማድረግ እስከተቻለ ድረስ“የአገር አንድነት”ጉዳይ አሣሣቢ አይሆንም የሚል ጠንካራ እምነት ባይኖር ኖሮ ከመጀመሪያዉም አገራዊ ንቅናቄዉ ባልተመሠረተ ነበር፡፡

የኢትየጵያ አገራዊ ንቅናቄ መሥራቾች ስለንቅናቄዉ ምሥረታዉ ይፋ ባደረጉበት ሰነድ (declaration) ላይ በግልፅ እንዳስቀመጡት የንቅናቄዉ “ራዕይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት፤ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች መብት ሳይሸራረፍ የሚከበርበት፤ ባህላቸዉ፣ ታሪካቸዉና ማህበራዊ እሴቶቻቸዉ የሚንፀባረቁበት፤ ሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች በዜግነታቸዉ ተከብረዉ በህግ ፊት በእኩልነት የሚስተናገዱበት እና ዕድገትና ብልፅግና የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት ነዉ፡፡ … የንቅናቄዉ ተልዕኮ ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አስተባብሮ በአንድ አገራዊ ዓላማ ሥር በማሰባሰብ ከሕዝቦች ፍላጎት ዉጭ በጠመንጃ ኃይል የያዘዉን ሥልጣን በመጠቀም የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ተቋማት በበላይነትና በብቸኝነት የተቆጣጠረዉን አምባገነን ሥርዓት በተባበረ ሕዝባዊና ነፍጥ-አልባ ትግል አስወግዶ ዕዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት የሚለዉን የአገራዊ ንቅናቄዉን ራዕይ ከግብ ማድረስ ይሆናል፡፡” እንግዲህ ከዚህ ራዕይና ተልዕኮ በግልፅ የምንረዳዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የተመሠረተዉ በወያኔ መዳፍ ሥር ያለችዉን የዛሬዋን ኢትዮጵያ በተባበረ ትግል ከወያኔ የጭቆናና የአፈና ቀንበር የማላቀቅ ፍላጎትና ዓላማ ብቻ ባላቸዉ ደርጅቶች ሣይሆን የነገዋ ድህረ-ወያኔ ኢትዮጵያ ህልዉናም በጣም በሚያሣሰባቸዉ ኃይሎች የመሆኑን እዉነታ ነዉ፡፡

በመሠረቱ ስለኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮች ስናስብ እና ሕዝባችን ብሶቱ ገንፍሎ እስከአፍንጫዉ ድረስ የታጠቀዉን የወያኔ ሠራዊት በባዶ እጁ መጋፈጡንና ጥሎም እየወደቀ መሆኑን ስናይ አሣሣቢዉ ነገር የወያኔ መዉደቅ አይደለም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነዉ እንጂ አምባገነኑ የወያኔ ሥርዓት በሕዝቦች የተቀናጀ ትግልና በተከተለዉ የጥፋት መንገድ ምክንያት አንድ ቀን መዉደቁ አይቀሬ ነዉ፡፡ ሊታሰብበት የሚገባዉና የሁሉንም ባለድርሻ ወገኖች ትኩረት (the serious attention of all stakeholders) የሚሻዉ ዋና ጥያቄ “ከወያኔ መዉደቅ በኋላ የምትኖረዉ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ኢትዮጵያ ትሆናለች?”የሚለዉ ነዉ፡፡ ያቺ የነገዪቷ ድህረ-ወያኔ ኢትዮጵያ እንደ ቅድመ-ወያኔዋና በወያኔ የግፍ፣ የጭካኔ፣ የመሃይምነትና የራስ ወዳድነት ጫማ ሥር ስትረገጥ እንደነበረችዋ ኢትዮጵያ ለጥቂቶች ተንከባካቢ እናት፤ ለአብዛኛዎቹ ልጆቿ ግን ከጨካኝ የእንጀራ እናትም የባሰች ጨካኝ ሆና ትቀጥላለች? በሌላ አባባል ድህረ-ወያኔ እንደ አዲስ የምትገነባዉ ኢትዮጵያ በየትም ብለዉ ሥልጣን ለመያዝ የቻሉ ጥቂት ወገኖች ከመጠን በላይ ተደስተዉና ተንደላቀዉ የሚኖሩባት፤ ወያኔዎች ሲያደርጉት እንደነበረዉና አሁንም እያደረጉ እንዳሉት ጥቂት ባለጊዜዎች ብቻ እንደልባቸዉ የሚዘርፏት ፣ አብዛኞቹ የአገሪቱ ዜጎች ግን የሚራቡባት፣ የሚታረዙባት፣ ለጥቂቶች ብልፅግና ሲባል ብዙሃን ቤትና ንብረት አልባ የሚደረጉባት፣ ከዚያም አልፎ ሰላማዊ ዜጎቿ በሰላም ወጥተዉ ስለመግባታቸዉ እርግጠኞች የማይሆኑባት የችግርና የስቃይ ተምሳሌት እንደሆነች ትቀጥላለች? እነዚህ ጥያቄዎች ፍትህን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትንና ያልተሸራረፈ የዲሞክራሲ መብት መከበርን በሚፈልግ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መመለስ ያለባቸዉ ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጣቸዉ መልሶች የእስከዛሬ አካሄዶቻችንን ዞር ብለን እንድናይ ሊያደርጉን ስለሚችሉና ስህተቶች ከነበሩም ከስህተቶቻችን እንድንማር ስለሚያደርጉን የተቃዉሞ ትግሉን ወደፊት ለማራመድ መንገድ ከፋች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስለሆነም በወያኔ የግፍ አገዛዝ ሥር ያለችዉ የዛሬዋ ኢትዮጵያና የሚፈልጉትን ዓይነት መንግሥታዊ ሥርዓት ለማግኘት ያልታደሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁኔታ የሚያስብ አዕምሮ ያለዉን ታዛቢ በጣም የሚያሣዝኑ ከመሆንም አልፈዉ የሕዝቦቻችንና የአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እጅግ አሣሣቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ እስከአሁን ያየናቸዉ የወያኔ ሥርዓት ቁንጮዎች የፈፀሟቸዉና ዛሬም የሚፈፅሟቸዉ የግፍ ድርጊቶች እንኳንስ በመንግሥትነት ስም እናስተዳድረዋለን በሚሉት የራስ ሕዝብ ላይ ቀርቶ በወራሪነት በተቆጣጠሩት ባዕድ ሕዝብ ላይ እንኳን ተፈፅመዋል ሲባል የሰማናቸዉ አይደሉም፡፡ በዚህ ረገድ አገራችንን በግፍ ወርሮ የነበረዉና በቀደምት አባቶቻችን የአንገዛም ባይነት ትግል የሃፍረት ማቅ ተከናንቦ የተባረረዉ የሞሶሎኒ ፋሺስት መንግሥት እንኳን የዛሬዎቹ የሕወሐት ገዢዎች ያደረጉትንና የሚያደርጉትን ዓይነት ለሰሚ ጆሮ የሚዘገንን ግፍ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ አልፈፀመም፡፡

የህወሐት ገዢ ቡድን ወላጅ እናትን በጭካኔ በገደለዉ ልጇ ሬሣ ላይ አስቀምጦ ለሌሎች እናቶች መቀጣጫ እንድትሆን ያደረገ፣ በተለያዩ የፈጠራ ወንጀሎች አሳብቦ በቁጥጥሩ ሥር ያዋላቸዉን ሰዎች በጥይት ፈጅቶ ለማስመሰል የታጎሩበትን እስር ቤት በዉስጡ ካሉት እስረኞች ጋር በእሳት ያቃጠለ፣ ባዶ እጁን የዕምነት በዓሉን ለማክበር የተሰበሰበንና ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃዉሞዉን ለመግለፅ የሞከረን ሕዝብ በምድር እስከአፍንጫዉ በታጠቀ የወታደር ኃይል ከሰማይ ደግሞ የመርዝ ጭስ በሚረጩ የጦር ሄሊኮፕተሮች አስገድዶ/አፍኖ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ገደል ዉስጥ ገብተዉ እንዲያልቁ ያደረገ ለግፈኛነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የወሮበሎች ቡድን ነዉ፡፡ የሥርዓቱ ተቃዋሚ የሆንን ወገኖች ደግሞ የሕወሐት ገዢ ቡድን ይህን ሁሉ ግፍ በሕዝባችን ላይ ማድረሱንና አሁንም እያደረሰ መሆኑን እያየንና እየሰማን ተባብረን ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ እንዲወርድ ለማድረግ የሚያስችለንን ትግል እንደማጠናከር ለጥቃቅን ልዩነቶች ቅድሚያ በመስጠት ዕዉነተኛዉን ጠላት ረስተን እርስ በርሳችን በጠላትነት መተያየትን የዘወትር ተግባራችን አድርገነዋል፡፡

ተባብሮ ፋይዳ ያለዉ ሥራ መሥራት የማይችለዉን የተቃዋሚ ጎራ ከምንጊዜዉም በላይ የናቀዉ የሕወሐት ቡድን በሕዝቡ ላይ የሚወስደዉን የግፍና የንቀት እርምጃ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀያየረ “እስቲ ምን ታመጣላችሁ?” እያለን ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሰሞኑ የንቀት ድርጊቱ የበለጠ ማረጋገጫ የለም፡፡ ሰሞኑን ከራሱ የዜና አዉታሮች እንደሰማነዉ “የኢትዮጵያ መንግሥት” ተብዬዉ ሕወሐት-መራሽ የጥቂቶች ቡድን በጭካኔ በትር አንቀጥቅጦ ከሚገዛቸዉ የአገሪቱ ዜጎች መካከል በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩትን በእስረኝነት ስም አፍኖ በየማጎሪያ ማዕከላቱ ሲያሰቃይ (torture ሲያደርግ) ከከረመና አንዳንዶቹንም አካለ ጎደሎ ካደረገ በኋላ ሲለቃቸዉ ነፃ የእስኮላርሺፕ ዕድል በመስጠት ዩኒቨርሲቲ አስገብቶ በማስተማር ያስመረቃቸዉ ይመስል “ሥልጠና ሰጥቼ አስመርቄያለሁ” ብሎ በማወጅ በግፍ አንቀጥቅጦ በሚገዛቸዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ መቀለዱን ታዝበናል፡፡ ይሉኝታ ቢሱ የወያኔ መንግሥት ተብዬ ቡድን በእንደዚህ ዓይነቱ የማላገጥ ተግባር በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የማይገኝለት “ልዩ ልማታዊ መንግሥት” መሆኑንም አስመስክሯል፡፡ እዉነታዉ ግን እነዚህ መብታቸዉን በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ ከመሞከር ዉጭ ምንም ወንጀል ያልሠሩ ንፁሃን ዜጎች ታስረዉ በቆዩበት ወቅት ከበቂ በላይ ግፍ የተፈፀመባቸዉና ለሌሎች ተረኛ ታፋኞች ቦታ እንዲለቁ ለማድረግ ታስቦ ከጠባቡ እስር ቤት ወጥተዉ ሰፊ ወደሆነዉ የወያኔ እስር ቤት መዛወራቸዉ ነዉ፡፡ ምክንያቱም በወያኔ አገዛዝ ሥር ያለችዉ አገራችን ኢትዮጵያ የመቃወም፣ የመደራጀት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ ወዘተ መብቶች የሌሉባት ሰፊ እስር ቤት ናትና፡፡ ስለሆነም ይህ እስረኞች የነበሩ ዜጎችን “የተሃድሶ ሥልጠና ሰጥቼ አስመርቄያለሁ” የሚለዉ የወያኔ ዜና ቡድኑ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለዉን ወደር የለሽ ንቀት በድጋሚ ያረጋገጠበት ነዉ ከማለት ዉጭ ሌላ ትርጉም የሚሰጠዉ አይደለም፡፡

እነዚህን “የተሰጣቸዉን ሥልጠና ጨርሰዉ የተመረቁ” የግፍ ታሣሪዎችን በተመለከተ “የኢትዮጵያ ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬሽን (EBC)”
በሚባለዉ የሥርዓቱ የዉሸት ዜናዎች ማምረቻ ተቋም አማካይነት በተሠራጨዉ ዜና ዉስጥ የሚከተለዉ ይገኝበታል፡-

“በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት አፈፃፀም መመሪያ መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳቸው በቀጣይ ህዝብን ለመካስ ዕድል እንደሚሰጣቸው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡በተሳሳተ መረጃ እንዲሁም በስሜት ተገፋፍተው በሁከት የተሳተፉ ወጣቶች ወደቀድሞ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ የተሰጠው ስልጠና ጠቃሚ ነበር፡፡ በተሃድሶው የተሳተፉት ስልጣኞች በእጅጉ መፀፀታቸው አይደገምም የሚል መፈክር በማንገብ ድርጊቱን አጥብቀው ማውገዛቸውን ገልጿል፡፡ በኮማንድ ፖስት የአፈጻጸም መመሪያ መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ዜጎች እንደ ወንጀላቸው ተለይተው ቀለል ያለ ወንጀል የፈጸሙት ስልጠና ወስደው ሲለቀቁ ከባድ ወንጀል ፈጽመው የተገኙት ደግሞ በህግ አግባብ እንደሚጠየቁም ገልጿል።

ጽህፈት ቤቱ በሃገሪቱ በተወሰኑ አካባቢዎች በተፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦች የተነሳ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ዜጎች መካከል 9ሺህ 800 ያህሉ የተሃድሶ ስልጠና አጠናቀው እና ተመርቀው ሰሞኑን ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን አስታውሷል። አብዛኛዎቹ የሁከቱ ተሳታፊዎች ወጣቶች መሆናቸው የጠቀሰው መግለጫው በተቀነባበረ ቅስቀሳ እና በተሳሳተ መረጃ እንዲሁም በስሜት ተገፋፍተው ወደ ሁከት መግባታቸውን እንስተዋል። ወጣቶቹ ወደቀድሞው ሰላማዊ ህይወታቸው በመመለስ የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ስልጠና ወስደው መመረቃቸው አስፈላጊና ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን መንግሥት ያምናል ብሏል መግለጫው።”

እንደዚህ የሚያላግጥብንን የአረመኔዎች ሥርዓት እንቃወማለን የምንል ወገኖች ይህ ሁሉ ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ ግፍ በሕዝቦቻችን ላይ ተፈፅሞ እያየንና እየሰማን ተባብረን በየአቅጣጫዉ በተለያዩ መንገዶች እየተካሄዱ ያሉትን የአልገዛም ባይነት እንቅስቃሴዎች በሚገባ አጠናክረን አገራችንንና ሕዝቦቻችንን ከዚህ የኢትዮጵያዉያን ደመኛ ጠላት ከሆነ ቡድን እጅ እንዴት ነፃ ልናወጣ እንደምንችል በቅንነት፣ በንፁህ ልቦና እና በግልፅነት እንደመመካከር ጎራ ለይተን መናከስን የዘወትር ተግባራችን አድርገናል፡፡ አሁን አሁንማ የለየለት ጠላታችን የሆነዉ የሕወሐት የገዢ ቡድን ተረስቶ አንዳንዶቻችን በየጽሑፎቻችንም ሆነ በየንግግሮቻችን ዘወትር የምናወግዘዉ የአንዳንድ ፖለቲካ ድርጅቶችን መሪዎችና በወያኔ ተቃዋሚነት የሚታወቁ ግለሰቦችን ሆኗል፡፡

እንደዚህ የሚያላግጥብንን የአረመኔዎች ሥርዓት እንቃወማለን የምንል ወገኖች ይህ ሁሉ ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ ግፍ በሕዝቦቻችን ላይ ተፈፅሞ እያየንና እየሰማን ተባብረን በየአቅጣጫዉ በተለያዩ መንገዶች እየተካሄዱ ያሉትን የአልገዛም ባይነት እንቅስቃሴዎች በሚገባ አጠናክረን አገራችንንና ሕዝቦቻችንን ከዚህ የኢትዮጵያዉያን ደመኛ ጠላት ከሆነ ቡድን እጅ እንዴት ነፃ ልናወጣ እንደምንችል በቅንነት፣ በንፁህ ልቦና እና በግልፅነት እንደመመካከር ጎራ ለይተን መናከስን የዘወትር ተግባራችን አድርገናል፡፡ አሁን አሁንማ የለየለት ጠላታችን የሆነዉ የሕወሐት የገዢ ቡድን ተረስቶ አንዳንዶቻችን በየጽሑፎቻችንም ሆነ በየንግግሮቻችን ዘወትር የምናወግዘዉ የአንዳንድ ፖለቲካ ድርጅቶችን መሪዎችና በወያኔ ተቃዋሚነት የሚታወቁ ግለሰቦችን ሆኗል፡፡

በተለይም የእስከዛሬዉ የተናጠል የተቃዉሞ ትግል የምንፈልገዉን ዉጤት አላመጣምና ተባብረን የጋራ አገራችንንና ሕዝቦቻችንን ከሕወሐት አገዛዝ ነፃ እናዉጣ ብለዉ በድፍረት የተነሱትንና የጋራ የሆነ አገራዊ ንቅናቄ መመሥረታቸዉን ይፋ ያደረጉ ድርጅቶችን ታዋቂ፣ ደፋርና ቆራጥ መሪዎች መወንጀል፣ ማንቋሸሽ፣ ባልተጣራ ጥፋት መወንጀል፣ በአጠቃላይ በቀና ጥረቶቻቸዉ ላይ ለጊዜዉም ቢሆን ዕንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ የቃላት ጋሬጣዎችን ማስቀመጥን የዘወትር ተግባራችን አድርገናል፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ ያንኑ የተለመደዉንና ከዓመት ወደዓመት የማይቀየረዉን በአንድ በኩል “አንድነት አንድነት” በሌላዉ ወገን ደግሞ “መገንጠል መገንጠል” የሚሉና ቅንጣት ያህል እንኳን ወደፊት ለመራመድ የማያስችሉ ባዶ መፈክሮቻችንን አንግበን በየራሣችን ሙዚቃዎች ብቻችንን ወይንም ጥቂት መሰሎቻችንን አስከትለን የመደነሱን ዉጤት-አልባ ተግባራት ተያይዘናል፡፡

እዚህ ላይ በመካከላችን ያለዉ የብሔረሰብ ልዩነት ሣያግደን ከቅርብ ጓደኛዬ ጋር (ጓደኛዬ የአማራ ብሔር ተወላጅ ነዉ) ወቅታዊዉን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንስተን በግልፅነትና በመግባባት መንፈስ ስንነጋገር ጓደኛዬ ያነሣዉን ነጥብ እና እኔም ከልብ የማምንበትን እዉነታ ለዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ለማካፈል እወዳለሁ፡፡ በዚህ ጓደኛዬ አባባል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቀት የገመገመ ሰዉ በቀላሉ የሚረዳዉ ዕዉነታ የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ በሦስት ተፃራሪ ኃይሎች ዕገታ ሥር ያለ መሆኑን ነዉ፡፡ እነሱም፡-
1. ራሣቸዉን “የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች” ብለዉ የሚጠሩ
2. የመገንጠል አጀንዳን የሚያራምዱ
3. የሕወሐት ገዢ ቡድን ናቸዉ፡፡

(ወደ ገጽ 2 ዞሯል)

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here