spot_img
Friday, June 21, 2024
Homeአበይት ዜናየጦር መሳሪያ ዋጋ አሻቀበ፤ ክላሽንኮቭ እስከ 60 ሺህ ብር ይሸጣል፣ መሳሪያ ቁልፍ...

የጦር መሳሪያ ዋጋ አሻቀበ፤ ክላሽንኮቭ እስከ 60 ሺህ ብር ይሸጣል፣ መሳሪያ ቁልፍ ሃብት ሆኗል!

የካቲት 14 2009 ዓ ም

Ethiopian Highland fighter

.ሱዳንና ህወሃት የመሳሪያ ዝውውርን ለመግታት ተስማሙ
.ትግራይ ክልል ኢትዮጵያን ወክሎ ከሱዳን ጋር ስምምነት አደረገ

ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተቀሰቀሰዉ አመጽ ማህበራዊ መሰረቱን እያሰፋ በጎንደርና በጎጃም የተለያዩ ዞኖችን፣ ወረዳዎችን፣ የከተማ አስተዳደሮችና የገጠር ከተሞችን ያዳረሰ ህዝባዊ እምቢተኝነት ለመሆን በቅቷል። ይኸው ህዝባዊ እምቢተኝነት በጦር መሳሪያ የታጀበ መሆኑ ደግሞ ከሌሎች የተለየ አድርጎታል። በተለያዩ ማህበራዊ ገጾች፣ የሚዲያ ውጤቶች እንዲሁም “የአማራ ተጋድሎ” በሚል ስያሜ የሚታወቁት ክፍሎች ባቋቋሟቸው መገናኛ መንገዶች በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው የሚወድቁ ብቻ ሳይሆን የሚጥሉ የተጋድሎ ሃይሎች እየተበራከቱ ነው። አንዳንዴም የድል ብስራት ያውጃሉ። ትንቅንቁም ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሲያምጽ በምን ያህል መጠን ሊቆጣና ጨቋኙን መደብ ያለ ርህራሄ ሊቀጣ እንደሚችል ቀደምት ኩነቶች ማረጋገጫ ቢሆኑም ህወሃት ግን “ጦርነት ሰሪ ነኝ” በሚል ትዕቢት ገሃዱን እውነት ለመቀበል ተስኖት እስካሁን ቆይቷል። በአገሪቱ የተቀሰቀሰውና ዳር እስከዳር ያዳረሰው የህዝብ አመጽ አሁን አሁን ባህሪውን ቀይሮ በብረት የተደገፈ ሆኗል።

ይህ ብረትን መፍትሄ ያደረገው ትግል መጨረሻው በገሃድ የተቀመጠ ባይሆንም፣ የመረረና የከረረ ስለመሆኑ ጉዳዩን የሚከታተሉ የዓለም መገናኛዎች እየመሰከሩለት ነው። ራሱ ህወሃትም ቢሆን ስጋት እንዳራደው በሚያሳብቅበት መልኩ የሰላም ዜማ እያዜመና የማያውቅበትን አንድነትና ዕርቅ እየሰበከ ነው።
ይህ ህዝባዊ እምቢተኝነት መዋቅራዊ ድጋፍ ያለዉ በሚመስል መልኩ በጦር መሳሪያ መታጀቡ ማዕከላዊ መንግስቱን በበላይነት የተቆጣጠሩትን የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ይበልጥ በማሸበሩ የድርድር፣ የእርቅ፣ የሃብት እኩል ተጠቃሚነት፣ የስልጣን ሽግሽግ፣ የካቢኔ ሹም ሽር፣ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ካድሬዎችን እስከማባረር፣ ህገ መንግስት እስከማሻሻል የሚደርስ የተሃድሶ ዘመቻ ለማካሄድ ቃል እስከመግባት አድርሶታል።

በኦሮሚያ ክልል ከተፈጠረዉ ህዝባዊ አመጽ ጋር እየተመጋገበ ህወሃትን ያራደዉ ህዝባዊ እምቢተኝነት ለማፈን ወታደራዊ ኃይልን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመጠቀሙ በከፋ ደረጃ ደም ያቃባው ህወሃት/ኢህአዴግ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅም ነገሮች ባሰበው መልኩ ባለመሄዳቸው፣ የኮማንድ ፖስቱን ዕድሜ እንደሚያራዝም ከወዲሁ ይፋ እያደረገ ይገኛል። አገሪቱ በወታደራዊ ቀንበር ስር እንደምትቀጥል ሳያቅማማ ማረጋገጫ ሰጥቷል።

ከአዋጁ ጋር በተያያዘ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ በረድ ያለ ቢመስልም የለየለት የጦርነት ዜናዎች መስማት፣ ይህንኑ የጦርነት ዜና ተከትሎ የስርዓት መዛነፍ፣ የመዋቅር መፍረስ፣ የአስተዳደር አካላትና የበታች መዋቅሮች የመናድ ጉምጉምታ ማድመጥ ከተለመደ ወራት ተቆጥረዋል። እነዚህ አማጺ የሚባሉት ኃይሎች በጎበዝ አለቃ ተደራጅተው ህግና ፍርድን በእጃቸዉ የጨበጡበትም አጋጣሚዎች መኖራቸውም እንዲሁ ስምና ቦታ እየተጠቀሰ ተጠቁሟል። አሁንም እየተጠቆመ ነው። በከባድ መሳሪያ የታጀበ ኃይል በከበባ ሊያጠቃቸው ሲነሳ ከበባውን በመመከት ድል እንደተቀዳጁ ብስራቱን እስከማወጅ ደርሰዋል። ልክ እንደ ህወሃት የበረሃ ተሞክሮ የነጻነት ታጋዮቹ ብረታቸውን ሲያሻቸው እያነሱ እርምጃ ሲወሰዱ በሚሸሽጋቸው ህዝብ ውስጥ መሆናቸው ደግሞ ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው ከህወሃት አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች ያሳብቃሉ። ይህ አካሄድ ታሪካቸው የጀመረበትና ገዢ የሆኑበት ጥንስስ በመሆኑም ይህንኑ ስጋት ለማስወገድ አገሪቱን በወታደራዊ አገዛዝ ስር አውለው ከላይ ታች በማለት ላይ ይገኛሉ።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል አስቸጋሪ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያላቸዉን ስፍራዎች በተለይም ታች አርማጭሆ፣ ምዕራብ አርማጭሆ፣ ጠገዴ፣ መተማ፣ ወገራ፣ ምዕራብና ምስራቅ በለሳ ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በዋናነት የእምቢተኛነቱ እምብርት እንደሆኑ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በዝርዝር ባይገለጽም ጎጃም አንዳንድ አካባቢዎችና ሰሜን ሸዋ የኅቡዕ ጥቃት እንደሚፈጸም ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። በሰሜኑ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍል በሚገኙ ወረዳዎች ከአርሶ አደሮች መሰብሰብ የነበረበት የ2008 ዓ.ም የመሬት ግብር እና የማዳበሪያ ዕዳ እስካሁን ሊሰበሰብ አለመቻሉ ትልቁ የመዋቅር መሰበር አመላካች ተደርጎ መወሰዱን የጎልጉል የአካባቢው መረጃ አቀባይ አስታውቋል። መረጃ አቀባዩ እንዳለው ራቅ ባሉ የገጠር ቀበሌዎች የማህበራዊ ተቋማት (ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የግብርና ጣቢያዎች) ወደ ቀድሞ መደበኛ ሥራቸዉ መመለስ አልተቻላቸውም።

ለዚህም ይመሰላል ከጸረ-ሽብር ግብረ ኃይል ቡድን፣ ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ሰራዊት የተዉጣጣዉ የኮማንድ ፖስቱ ወታደራዊ ክንፍ ከላይ በተጠቀሱት ወረዳዎች በተለይ በገጠር ቀበሌዎች በነጻነት መንቀሳቀስ እንዳልቻለ ሪፖርት እየቀረበ ያለው። እንደ መረጃ አቀባዩ በዚህ መነሻ ነው እንግዲህ የጅምላ እስር፣ የጅምላ ውንጀላ፣ የጅምላ ግፍ በወረዳዎች ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው።

በወገራ በታጋይ መሳፍንት፣ በታች አርማጭሆና ምዕራብ አርማጭሆ በታጋይ ጎቤ አበራ፣ በጠገዴና አካባቢዉ በታጋይ ደጀኔ ማሩና ወንድሞቹ መሪነት፣ በበለሳና አካባቢዉ በእነ ታጋይ አደራጀዉ ታደሠ የሚካሄደዉ የደፈጣ ዉጊያ በኮማንድ ፖስቱ ወታደራዊ ክንፍ ሊሰበር ያልቻለዉ ህዝባዊ መሰረት ያለዉ የትግል አቅጣጫ በመነደፉ እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ለጎልጉል የአካባቢው መረጃ አቀባይ ነግረውታል። በዚህ ዙሪያ በርካታ መረጃዎች ያሉ ሲሆን ለጥንቃቄ በሚል ይፋ ከመደረግ ታልፈዋል፡፡

በዚህ መነሻ በሰሜኑም ሆነ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ግብይቱ ከወትሮዉ በተለየ መልኩ ፍጥነቱን ጨምሯል። በቀደሙት ጊዜያት በገጠር ቀበሌዎች እልፍ ሲል ደግሞ በወረዳ ከተሞች ይደረግ የነበረዉ የጦር መሳሪያ ግብይት ከህዝባዊ አመጹ መቀስቀስ በኋላ የጦር መሳሪያ ግብይቱ የተለያዩ የአገሪቱን ክፍሎች እያዳረሰ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። እንደ ዘጋቢያችን ገለጻ ከሆነ የጦር መሳሪያ ባለቤት መሆን አሁን አሁን የአየር ያህል ቁልፍ ጉዳይ ሆኗል።

አሁን ባለዉ የጦር መሳሪያ ግብይት ዋጋ መሰረት AK-47 ታጣፊ ክላሽ ከአርባ እስከ ሃምሳ አምስት ሺህ ብር፤ ስታር ሽጉጥ ከአስራ ስምንት እስከ ሃያ አምስት ሺህ ብር፤ ማካሮፍ ከሃያ እስከ ሰላሳ ሺህ ብር፤ የእጅ ቦምብ ከሦስት መቶ እስከ ስድስት መቶ ብር፤ F-one ቦምብ ከአንድ ሺህ እስከ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። ሲፈለግ ማንኛውም ዓይነት የከባድ መሳሪያ ማቅረብ የሚችሉ ኃይሎች እንዳሉ የገለጹት ክፍሎች “ጊዜው የወሬ ባለመሆኑ ወገን ባለው መዋቅርና የግንኙነት መሠረት ድጋፉን ይስጥ” ሲሉ የጥሪ ይዘት ያለው ጥቆማቸውን አሰምተዋል።

ኤርትራ የከተመውና ዕድሜውን የፈጀው ኦነግ የሚፈይደው ነገር የለም በሚል አሁን አዲስ አደረጃጀት የጀመሩ ክፍሎችም በኦሮሚያ ተመሳሳይ የትጥቅ ትግል ለመጀመር፣ የተበታተነውን የኦነግ ሃይል ወደ አንድ በማምጣት ኃይላቸውን ለማጠናከር፣ ደጋፊዎችም ለጦር መሳሪያ ግዢና አቅርቦት አስፈላጊውን እንዲያደርጉ ጥሪ እየቀረበ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ በቦረና፣ በጉጂ፣ እንዲሁም በሞያሌ አካባቢ በብረት የታገዘ ትግል አልፎ አልፎ እየተካሄደና ከኢህአዴግ ወገን ነፍጠኞች እየተገደሉ መሆኑንን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በተደጋጋሚ እየዘገበ ነው። በተለይም በምዕራብና በምስራቅ ሐረርጌ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ድንበር የኦሮሞ ተወላጆች ብረት አንስተው ለተከፈተባቸው ጥቃት ምላሽ መስጠታቸው በጀርመን፣ አሜሪካ ሬዲዮና በተለያዩ የሚዲያ መስመሮች መገለጹ አይዘነጋም።

ኦህዴድ ህዝቡን ሲሰበስብ “አስታጥቁን” የሚል ጥያቄ እንደቀረበለት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ይፋ አድርጓል። ፋና በበኩሉ የኦህዴድን አመራሮች ጠቅሶ በተጠቀሰው አካባቢ ችግር መኖሩን አትሟል። ሃይለማሪያም ደሳለኝም “ግጭቱ እንዲቆም” ሲል ማዘዙን ፋና አክሎ አስታውቋል።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተነሳው ተቃውሞ ያሳሰበው ህወሃት “የኢትዮ ሱዳን የጋራ ድንበር ልማት ኮሚሽን በፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች የጀመሩትን የትብብር ግንኙነት አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ” በሚል ላለፉት ሁለት ቀናት በመቀሌ የተካሄደውን ስብሰባ ውጤት ይፋ ተደርጓል። ፋና እንደዘገበው ለሁለት ቀናት በመቀሌ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 18ኛው የኢትዮ ሱዳን የጋራ ድንበር ልማት ኮሚሽን ጉባኤ የተለያዩ ስምምነቶችን በማፅደቅ ተጠናቋል፡፡ በፖለቲካና ፀጥታ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት በድንበር አካባቢ የሚካሄድ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የወንጀል ድርጊቶችና ወንጀለኞችን መከላከል ላይ ተባብረው ለመስራትም ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የፋና ዘገባ ያስረዳል። በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ምክንያት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር በጋራ ለመከላከል በሚቻልበት አግባብ ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ፋና አክሎ ገልጿል። ለስምምንቱ ተፈፃሚነት ኢትዮጵያን በመወከል

የትግራይ ክልል ሊቀመንበር አባይ ወልዱ፥ በሱዳን በኩል ደግሞ ሚስተር ሚርቀኒ ሳልሕ የገዳሪፍ ክልል አስተዳዳሪና የሱዳን ልዑክ ቡድን መሪ ፈርመዋል፡፡ ይህ በመሳሪያ ዝውውር ላይ የተደረሰው ስምምነት ከላይ የተባለውን ስጋት ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።

በሌላ ዜና ሱዳን ትሪቢውን የሱዳን ባለስልጣናት የድንበር ማካለሉንና የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የወሰዱትን መሬት ስለሚመልሱበት ሁኔታ ንግግር መደረጉን ስብሰባውን የተሳተፉትን በመጥቀስ ዘግቧል። መሬቱ ለሱዳን ከተሰጠ በኋላ ወደፊት የትግራይ ተወላጆች መልሰው በሊዝ እንደሚወስዱት ስለሚነገርለት ይህ አከራካሪ የመሬት ጉዳይ የሱዳን ትሪቢውን ይህን ቢልም የኢህአዴግ ንብረት የሆኑ ሚዲያ ውጤቶች ስለድንበር ማካለልና መሬት ስለመመለስ ውይይት መደረጉን አልተነፈሱም። ከቪኦኤ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት ሃገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ መለስ አለም “ይህ ጥሩ ድርሰት ነው” ሲል ነው ያስተባበለው።

ህወሃትና ሱዳን ውስጥ ውስጡን እያደረጉ ያለው የትራንስፖርት፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የቀረጥ ነጻ ንግድ ስምምነት፣ ረጅም የባቡር መስመር መዘርጋት …. በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በጤና የማይታይ፣ የወደፊቱን “የታላቋ ትግራይ” ምስረታ መንገድ ጠራጊ ሂደቶች ተደርገው ነው የሚታዩት። ከዚህ ጋር በተያያዘ ከአራት ቀን በፊት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት “በትግራይ ክልል 160 ሺህ ሄክታር የሚሸፍን የደን ሃብት በመንግስት ጥብቅ ደን እንዲከለል እየተሰራ” መሆኑን ዘግቧል፡፡ በጋምቤላና በሌሎች የአገሪቱ ቦታዎች የተፈጥሮ ደን “የመንግሥት ጥበቃ” ሊደረግለት ሲገባ በኢንቨስትመንት ስም በተለይ ለትግራይ ተወላጆች መሬቱ እየተቸበቸበ በተጨፈጨፉት ዛፎች ምትክ ሳይደረግ ለጊዜያዊ ትርፍ ከሰል እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ይህ ዓይነት ፍትሐዊነት የሌለው አሠራር በኢትዮጵያ ኪሣራ “ታላቂቱን ትግራይ” ከመመሥረቱ ዓላማ ጋር የሚታይ መሆኑን ዜናውን ያነበቡ በሰጡት አስተያየት አመልክተዋል፡፡

ለዘመናት ከሱዳን ጋር የሚዋሰነው አሁን “የአማራ ክልል” ተብሎ የሚጠራ ሆኖ ሳለ የትግራይ ሱዳን አዋሳኝነት ገና ሳይለይለት ትግራይ እንደ አገር ከሱዳን ጋር ይህንን መሰሉ ስምምነት ማድረጓ የክልሉን ተስፋፊነትና የወደፊት ዕቅድ አመላካች ነው ተብሎለታል፡፡ (ፎቶው ለማሳያ የቀረበ ሲሆን የተገኘው እዚህ ላይ ነው)

ምንጭ ጎልጉል

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here