መጋቢት 1 2009 ዓ ም
. ከደቡብ ምሥራቅ ወደ ገዳሙ ቅዱሳን ጫካ (ምዕራብ) እየተቀጣጠለ ነው
. የወረዳው አስተዳደር እና ሕዝብ ከገዳሙ ማኅበረሰብ ጋራ እየተጋገዘ ነው
. ቃጠሎውን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ርዳታና ድጋፍ እየተጠየቀ ነው
በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ የደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ዙሪያ፣ ዛሬ፣ መጋቢት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ የእሳት ቃጠሎ ተቀሰቀሰ፡፡
ከቀኑ 9፡00 ገደማ፣ በገዳሙ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ ከርቀት የተቀሰቀሰው እሳት፣ ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ሰዓት፣ የቅዱሳን ጫካ/ከተማ እየተባለ ወደሚጠራው ምዕራባዊ አቅጣጫ፣ በከፍተኛ ኃይል እየተቀጣጠለ መኾኑን የገዳሙ አባቶች ተናግረዋል፡፡
ቃጠሎው የተቀሰቀሰበት አካባቢ፥ “ከርቀት ታች የተራራው ጫፍ ላይ ነው፤ ከገዳሙ ከ7 እስከ 9 ኪ.ሜ ይኾናል፤” ያሉት ገዳማውያኑ፣ እሳቱን ለማጥፋት ቢረባረቡም፣ ማምሻውን ከዐቅም በላይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
“የቅዱሳን ጫካ የምንለው አለ፤ በአዱላላ በኩል ሲታይ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ነው፤ አኹን በእርሱ በኩል እየመጣ ነው፤ እኛም ወደዚያው እየሔድን ነው፤” በማለት በተለይ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስጊ እንደኾነ ገልጸዋል፡
አደጋው እንደተሰማ፣ የአዱላላ ከተማ አስተዳደር፣ ሕዝቡ ወደ እሳቱን ወደማጥፋት እንዲሔድ መቀስቀሱ የተሰማ ሲኾን፣ ነዋሪውም ወደ ስፍራው በመንቀሳቀስ የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንዳለ ታውቋል፡
የመከላከያ ኃይልን ጨምሮ ሌሎችም አካላት አፋጣኝ እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ቃጠሎውን ለመቆጣጠር በመረባረብ ላይ የሚገኙ ገዳማውያንና ምእመናን ጠይቀዋል፡፡
የቃጠሎውን መንሥኤ በተመለከተ፣ ትክክለኛው ምክንያት ለጊዜው ባይታወቅም፣ “እንደተለመደው ከሰል አክሳዮችን ነው የምንጠረጥረው፤” ብለዋል፣ ከገዳማውያኑ አንዱ አባት፡፡