spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeነፃ አስተያየትየማህበረሰብ ጠንቅነት ዝንባሌን እንዴት ማወቅና መጠንቀቅ እንችላለን? የነገሰው(ትርጉም በአማኑዔል)

የማህበረሰብ ጠንቅነት ዝንባሌን እንዴት ማወቅና መጠንቀቅ እንችላለን? የነገሰው(ትርጉም በአማኑዔል)

በየነገሰው (ትርጉም በአማኑዔል)
መጋቢት 2 2009 ዓ ም

Ethiopia-society

ላለፉት በርካታ አመታት እኛ በውጭና በሀገር ዉስጥ የምንገኝ ኢትዮጵያውያንና ትዉልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያ ዉስጥ የተሻለ መንግሥታዊ አስተዳደር እንዲመጣና ባጠቃላይ ፍትህ እንዲሰፍን ያላሰለሰ ጥረት ስናደርግ ቆይተዋል:: ይሁን አንጂ በተለያዩ ተቆጥረዉ በማያልቁ ምክንያቶች፣ አብዛኞቹ ደግሞ እራሳችን በፈጠርናቸዉ ድክመቶች እስካሁን የከፈልናቸዉ መሥዋቶች፣ ድካማችንና ልፋታችን የታለሙለትን ያህል ግብ ሊመቱና ፍሬያማ ሊሆኑ አልቻሉም:: በዚህም የተነሳ ብዙዎቻችን በመሰላቸትና በምሬት ይመስላል፣ ከዋናዉ ጠላታችን ከወያኔ ጋር ከመታገል ይልቅ ምሬትና ብስጭታችንን ስርዓቱን በሚደግፉ የዉጭ ሃያላን መንግሥታትና ባመዛኙ ደግሞ ኃይላችንን እርስ በርሳችን በመነታረክ ላይ እያባከንን እንገኛለም(ተጠምደናል):: ከዚህ በፊት ስንጓዝበት ከነበረዉ የተሳሳተ ጉዞ ሳንማር አሁንም የቀድሞ ስተታችንን በመደጋገም፣እያንዳንዳችን በግል ኃላፊነት እንደሚሰማዉ ግለሰብና ዜጋ ለህዝባችን ሰላምና ለትዉልድ የምናወርሰዉ ሀገር ለመፍጠር መፍትሄ ከመሻት ይልቅ አንዱ ልላዉ ላይ ጣት በመቀሰር፣ እርስበርስ ስም ለማጥፋት መሞከር ፣ አንዱ ብሔር ሌላዉን ለቀድሞዉና ለአሁኑ ችግሮቻቺን ተጠያቂ ለማረግ በመጣርና የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ከትግላችን ይልቅ እንደዉም የምንታገለዉን መንግሰስት በሚጠቅም መልኩ የእርስ በርስ ትርምሱ ላይ በማተኮር ህዝባችንንና ራሳችንን ከዚህ አስከፊና የታሪክ ጠባሳችን ከሆነዉ ስርዓት ለማላቀቅና ለመታደግ የምናደርገዉን ጉዞ እያወሳሰብነዉ መተናል ::

እዚህ ላይ ባንክሮ ሊሰመርበት የሚገባዉ ነገር ይህ አባባል(ከላይ የተጠቀሱት ትችቶች)ግን በአሁኑ ሰዓት በተለያየ መልኩ በተናጥልም ሆነ በጋራ እየተደረጉ ያሉትን ትግሎችና መስዋቶችን ለማኮሰስ የታለመ ሳይሆነ በአንፃሩ ግን ለትግሉ ሕይወታቸዉን አሳልፈዉ የሰጡና መስዋትነት እየከፈሉ ያሉ ወገኖቻችን ላይ ደንቃራ ወይም መሰናክል በመሆን ከላይ በተጠቀሱት ትግሉን ለማሽመድመድ አስተዋፆ እያደረጉ ባሉ ዘለፋ፣ትችትና ከጥቅማቸዉ ጉዳታቸዉ በሚያመዥን ንትርኮች ላይ አላስፈላጊ ግዜና ኃይላቸዉን እያጠፉ ያሉ የሕብረተሰባችን ክፍሎችን ለማለት ነዉ:: በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅስ ማለፍ የማልሻዉ ነገር ደግሞ አዳጋች፣ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ሁኔታዎችን በቆራጥነት በማለፍ እስከ ከፍተኛዉ የህይዎትና ሌሎች መስዋትነቶችን ለሀገራቸዉና ህዝባቸዉ ነፃነት ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ ወጎኖቻችን አድናቆትና ምስጋና ማቅረብ ብቻ ሳይሆን በምንችለዉ አቅማችን ሁሉ ላጋርነት መዘጋጀት የዜግነት፣ የትዉልድና የወገን አጋርነት ግዴታችን መሆኑን ነዉ ::

ባሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ መስዋትነት እየከፈለ መሆኑ አጠያያቂ ባይሆንም ዳሩ ግን ከዚህ ህዝባችን ከተዘፈቀበት የኑሮ እሽክርክሪት፣ ሽኩቻና የማህበረሰብ ሽባነት በተፈለገዉ ፍጥነት ፈልቅቆ ለማዉጣትና ባንድነት ወደተሻለ የጋር እቅድ፣ የትግል ስልትና ለድል ለማብቃት ከፊታችን የተጋረጡብን መሰናክሎች ምንድናቸዉ? እስካሁን የተጓዝንባቸዉን የትግል ስተት መስመሮች ወደኋላ ትተንና ተምረን ሁላችንንም ነፃ ሊያወጣ የሚችለዉን መንገድ እንዴት እንቀይስ? ህብረተሰባችን አቅሙን አስተባብሮ በጋር ለነፃነቱ፣ እንደ ጥንት አባቶቹ ባንድ ላይ፣ ነፃ መዉጣት እንደሚሻ ህብረተሰብ በጋራ መቆም ያልቻለዉና አቅሙን ያሽመደመዱት ሁኔታዎች ምንድናቸዉ ?

እንደኔ ግንዛቤ ከላይ ከተዘረዘሩትና እንዲሁም ተቆጥረዉ ለማያልቁ ችግሮቻችን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ካሉ መሀበራዊ ችግሮቻችን መካከል ቀላል የሚመስል ነገር ግን ማህበረሰባችንን በጋር አብሮ በሚያረጋቸዉ ጥረቶች ሁሉ ጣልቃ በመግባት እያሽመደመዱት ወይም የህብረተሰብ ሽባ እያደረጉት ካሉት መካከል እንደ ሰደድ እሳት በፍጥነት እየተስፋፋና እየተሰራጨ ያለዉ ፀረ-ኢትዮጵያዊነት፣ ፀረ-ሕዝብ፣ ፀረ-ሕብረተሰብ፣ በተለይ በወጣቱ ትውልድ መካከል ቀላል የሚመስል ነገር ግን አደገኛ የማህበረሰብ ጠንቅነት አዝማሚያ ወይም ዝንባሌ እየተበራከት መምጣቱ ነዉ:: ወደድንም ጠላንም ሕዝባችን በማህበረሰብ ጠንቆች (ፀረ-ኢትዮጵያ ግለሰቦችና ቡድኖች) እየተዋጠ ይገኛል:: ሁኔታዉን ዉስብስብ የሚያደርገዉ ደግሞ እነዚህ ማህበራዊ ጠንቆች ይህን አደገኛ ስነምግባር (dangerous role model)የወረሱት ከዋናዉ የሕብረተሰባችን ጠንቅ ከሆነዉና በመንግሥትነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከተዘፈዘፈዉ ከወያኔ የዱርዬና ተላላኪ ስርዓት መሆኑ ነዉ:: ስለሆነም ዋናዉና ትልቁን የማህበረሰባችንን ችግር ተነጋግሮና ተወያይቶ በጋራ ለመፍታት ይህን አይነቱን እንደሰደድ እሳት እየተስፋፋና በተለይ ወጣቱን የህብረተሰባችን ክፍል በፍጥነት እየበከለ ያለ የህብረተሰብ በሺታ ከምንጩ ለማድረቅና የተመረዙ የሕብረተሰባችን ክፍሎችን፣ ቤተሰባችንንና ወዳጆችችንን ከዚህ አስከፊና አደገኛ ዝንባሌ ለማዳን በግልና በጋር መዉሰድ ስላለብን እርምጃዎች መምከር አለብን:: ህዝባችን ከገባበት አጣብቂኝ ሁኔታዎች እንዲወጣና በጋራ ጠላቱ ላይ ባንድነት እንዲነሳ፣ በጋር ጥቅም ላይ የተመሰረት ተራማጅ አጀንዳና የጋራ ግብ ላይ ለማሰለፍ ከተፈለገ እነዚህ አደገኛ ተልኮና አዝማሚያ ያላቸዉ ነገር ግን ራሳቸዉን በተለያየ ጭምብል የሸፈኑ የህብረተሰብ ጠንቅ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና የትዉልድ ጠንቅ የሆነ አፍራሽ ተልኳቸዉ በማህብረሰባችን ዘንድ በግልፅና በይፋ መታወቅ አለበት :: በዋናነት አሳሳቢ እየሆነ የመጣዉ ደግሞ እነዚህ የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች ከግዜ ወደግዜ ቁጥራቸዉ እየጨመረ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን የተማሩ እያልን ከምንጠራቸዉ የሕብረተሰባችን ክፍል ዉስጥ መሆኑና ከዚህም ጋር በተዛመደ በህብረተሰቡ ዉስጥ ያላቸዉን ቦታ(their status in society) ለተለያዩ መሰሪ፣ ጎጂና ለአፍራሽ ተልኮዎች በመጠቀም አብሮ በኖረ ሕዝብ ዉስጥ፣ በተለይ ወጣቱንና ያልጠረጠሩ የዋሆችን በመደለልና በመጠምዘዝ ወደ አደገኛና አሳሳቢ ዝንባሌ ለመምራት፣ የመርዝ መልእክት በቀላሉ ማሰራጨት መቻላቸዉ ነዉ:: ከላይ እንደተጠቀሰዉ ያለጥርጥር የነዚህ የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች አመለካከት የተቀረፀዉ(role model የሆናቸዉ) በመንግስትነት ደረጃ ተቀምጠዉ ህዝባችንን ከሚያጭበረብሩና ከሚያወናብዱ ወያኔ ተላላኪዎች ቢሆንም በመሃላችን ግን እራሳቸዉን በተለያየ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት/ተከራካሪነት ስም ከናንበዉና በተለይ ወጣቱን የምያማልሉበት የዘር ፖለቲካና ጥላቻ ሌት ተቀን ሲሰብኩ ይዉላሉ::

እነዚህ ከኛዉ ሕዝብ ዉስጥ የወጡና የሕብረተሰባችን አካል ሆነዉ ሳለ በማያሻማ ሁኔት አዉቀዉም ይሆን ሳያዉቁ(ለማለት ባያስደፍርም) ለሕዝባችን የማያልቅ ስቃይና መከራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ :: ስለሆነም ከእያንዳንዳችን፣ ስለ ሀገር፣ ስለዜጎችና ወገኖቻችን የመቆርቆር ኃላፊነት ከሚሰማን ሁሉ ምን ማድረግ ይጠበቃል ወደሚለዉ አንኳር ጥያቄ ስናመራና እነዚህን በማህበረሰብ ጠንቅነት በሺታ የተመረዙ የህዝባችን ጠንቅ ከመሆን ይልቅ ጠቃሚ አባል/አካል እንዲሆኑ ምን ማድረግ እንችላለን ብለን ስንጠይቅ፤ከሁሉም በላይ ደግሞ ከንደዚህ አይነት ቡድኖችና ግለሰቦች እያሰራጩብን ካለው ማኅበራዊ በሽታ ራሳችንን፣ቤተሰባችንና ክፉ የማንመኝላቸዉን ወገኖቻችንን እንዴት እንከላከል የሚሉትና የመሳሰሉትን አንገብጋቢ ጥያቄዎች አንስተን መፍትሄ ለመሻት ትኩረት መስጠት ያለብንና ጠቃሚ ይመስሉኛል::
እንደመነሻም እዲሆነን ግን ስለ ማህበረሰብ ጠንቅነት ባህሪ(ዝንባሌ) መጀመሪያ በሚገባ መረዳት ለመፍትሄዉ ተቀዳሚ ጉዳይ ይመሥለኛልና እስቲ ስለህብረተሰብ ጠንቅነት ባህርያት ግንዛቤ ለማስጨበት የሚረዱና በዚያዉም የዚህ የማኅበረሰብ በሺታ በእኛ ኅብረተሰብ በተለይም ወጣቱን ለመጠበቅና ታማምዎቹንም ለመርዳት(ሊረዱ የሚችሉትንና ፈቃደኛ የሆኑትን ማለቴ ነዉ ) አስተዋፆ ያረግ ዘንድ ስለባህርያቸዉ ትንሽ እንበል::

የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች አዲስ የተከሰቱ አደሉም፣ በህብረተሰብ ዉስጥ ለዘመናት በመግደል፣ በማስገደል፣ በጅምላ ፍጅት ዉስጥ በመሳተፍ አልያም የሃይማኖት ወይም ሌላ የቡድን ከታዮቻቸዉን(cults)ባላቸዉ የተፅኖ የመፍጠር፣ የማታለልና የመዋሸት ከፍተኛ ችሎታ በመጠቅም ራሳቸዉን በግልና በጅምላ እንዲያጠፉ ሲያሳምኑ፣ ሲያስፈጁና ሲፈጁ፣ ሲገሉና ሲያስገድሉ ነረዋል:: ዛሬም በዚህ ባለንበት ክፍለ ዘመን(modern era) መረጃ በተፈለገዉ ፍጥነት በሚሰራጭበት፣ ዉሸትና እዉነት በቀላሉ ማመሳከር በሚቻልበት ዘመንም እንኳ ብዙ ቁጥር ያላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች በንደዚህ አይነት ግለሰቦችና ቡድኖች ሲያታልሉ፣ሲጎዱና በተለያየ አስከፊ የህይዎት ዉጣዉረድ ዉስጥ ሲማገዱ ይስተዋላል:: ስለሆነም በነዚህ የማህበረሰብ ጠንቆች ተፅኖ ስር፣ በግልም ሆነ እንደማህበረሰብ፣ ሳንወድቅና ችግር ዉስጥ ሳንዘፈቅ ልናዉቃቸዉና ለራሳችን፣ ለቤተሰባችንና አጠቃላይ ለሕብረተሰባችን ጥንቃቄ እንድናደረግ የሚያስችሉን አንዳንድ አይነተኛ የሆኑ የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች አይነተኛ ባህሪያትን በጥቂቱ እንመልከት፤

1ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች ከፍተኛ የማሰብና የማስተዋል አቅም ሲኖራቸዉ ነገር ግን ይህ ተሰጥዖቸዉን(የአዕምሮ ከፍተኛ የማሰበ ችሎታቸዎን) ሌሎችን ከማገዝና ከመርዳት ይልቅ ለማታለልና ለማጭበርበር ይጠቀማሉ:: ይህም ከፍተኛ የአዕሮ የማሰብ ችሎታቸዉና አፍራሽ ዝንባሌቸዉ በሕብረየሰብ ዉስጥ አደገኛ ያረጋቸዋል:: ለዚህም ነዉ ብዙዎቹ ብዙውን ጊዜ በህግ አስከባሪዎችና ሕዝብ ሳይጠረጠሩ ወይም ሳይያዙ በተሳካ ሁኔታ ወንጀል ሰርተዉ ለማምለጥ ወይም ለመሰወር የሚችሉት::

2ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች የጥፋተኝነት፣የኃፍረት ወይም የጸጸት ስሜት የሚባል ነገር አልፈጠረባቸዉም:: አንጎላቸዉ አነዚህን ስብዕናዎችና ስሜቶችን የሚያከናዉኑ ክፍሎች ይጎሉታል::በዚህም የተነሳ፣ የቅርብ ጓደኞቻቸዉ ላይ ሳይቀር፣ ማንኛዉም ሰዉ ላይ ያለምንም ማመንታ ማንኛዉንም አይነት ጉዳት ከማድረስ፣ ክደት ከመፈፀምና ብሎም ጥቅም ካስገኘላቸዉ ግድያን ከመፈፀም የሚከለክላቸዉ ስብዕና አልተፈጠረባቸዉም:: የፈለገዉን ያህል ሌላዉን ግለሰብ ወይም ህብረተሰብ ሊጎዳ ቢችልም ጥቅማቸዉን ልያስከብር የሚችል ማንኛዉንም ነገር ከማረግ ወደኋላ አይሉም:: ለዚህም ነዉ ብዛት ያላቸዉ ከፍተኛ በተለይ ያምባገነን መንግስት ስልጣን ላይ የደረሱ እንዲህ አይነት ግለሰቦችንና ቡድኖችን ማግኘት የተለመደ የሆነዉ ::

3ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች ብዙዎቹ ትኩረትን የሚስቡ እና የሚመስጡንግግሮችን የማረግ ችሎታም አላቸዉ:: ያድማጭን ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ ቃላት የመምረጥና ያለምንም ማቋረት ኃሳባቸዉን በትረካ አገላለፅ በማቅረብ የተጠበቡ ባለቅኔዎችም ሊሆኑ ይችላሉ::

4ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች የፈጠራ ዉሸትና ስለራሳቸዉ የሕይወት ተሞክሮ ከመጠን በላይ አጋነዉ ማዉራት ይወዳሉ፣ አዉርተዉም አይጨርሱም፣ነገር ግን ኪነጥበባዊ በተላበሰ መልኩ ሲናገሩት ላድማጭ ተዓማኒና ተቀባይነት እንዲኖረዉ የማረግ ኃይል አላቸዉ::

5ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች በሌሎች ላይ የበላይነትንና ማንኛዉንም መስዋዕትነት ከፍለዉ ክርክርን ማሸነፍ ይፈልጋሉ:: በክርክር መረታትን በጣም ከመጥላታቸዉ የተነሳ የዉሸት ናዳና ትርጉመ ቢስ ማስረጃዎችን ወይም ምክንያቶችን በመደርደር ተፎካካሪቸዉንና ባላንጣ መስሎ የምታያቸዉን ሰዉ ሁሉ ለመርታት ማለቂያ ወደሌለዉ ጭቅጭቅ ዉስጥ ይገባሉ:: እነዚህን ሰዎች በምንም ዓይነት ምክንያታዊ ጋጋታ ማሳመን ማሸነፍ/መርታት አይቻልም:: እንደዉም ከራሳቸዉ ሃሳብ በተቃራኒ ማሳመኛ ምክንያቶች ወይም አሳማኝ መረጃዎች ከቀረቡላቸዉና መረጃዎቹ በበዙባቸዉ ቁጥር ንዴትና እልህ ዉስጥ ይገባሉ::

6ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች ብዙን ግዜ ጥሩ ተክለ-ሰዉነትና የደስደስ አላቸዉ:: ሰዎችንና ተከታዮችን የመሳብ ተሰጥዖ አላቸዉ በተለይ በተለያየ ምክንያት እርዳታ ፈላጊ፣ በህይወታቸዉ ዉጣዉረድና አስቸጋሪ ሁኔታዎች የገጠማቸዉና ምክር ወይም የህይዎት አቅጣጫ(guidance) የሚፈልጉና የሚሹ ሰዎች ሲያጋጥሟቸዉ ከመርዳት ይልቅ፣ ደካማ ጎናቸዉን በመጠቀም ለራሳቸዉ ጥቅም ብቻ ኢላማቸዉ ያረጓቸዋል:: አብዛኞቹ የማህበረሰብ ጠንቆች ጠንካራ የወሲብ መስህብና አንዳንዴም ግራ የሚያጋባ የፍትወት ባህርያት(absurd sexual appetite) ያሳያሉ:: እዚህ ላይ ግን ሁሉም ጠንካራ የወሲብ መስህብና ፍላጎት ያላቸዉ ሰዎች ሁሉ የማህበረሰብ ጠንቆች ናቸዉ ብሎ ለመደምደም አደለም::

7ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች ከተራዉ ሕብረተሰብ በተለይ ሁኔታ ግብታዊና ጥልቅ (intense)ናቸዉ:: አንዳንድ ግዜም መደበኛ ሰዎች ሊሰሯቹ የማይፈልጉ ወይም የማይወዱትን ግራ የሚገባ ድርጊት ሲያረጉ
ይታያሉ :: ህገወጥ ወይም በሕግ የተደነገጉ ባይሆኑም ማህበረሰብ በጋር ባህልን፣ደንብን ወይም ሃይማኖትን መሰረት ያረጉ ከማኅበራዊ ውሎች(social contracts/norms)ና ስነምግባሮች ተፃራሪና ጥራዝ ነጠቅ የሆኑ ተግባሮች ሲያረጉ ይስተዋላሉ::

8ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች ስለፍቅር ያላቸዉ አመለካከት ሙሉ በሙሉ የራስን ጥቅም በማስጠበቅ (completely self-serving or selfishness) ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሲሆን አላማዉም እራሳቸዉ የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት እንጂ እንደ ጤነኛ ሰዉ አይነት የፍቅር ወይም ርኅራኄ ስሜት በዉስጣቸዉ አልፈጠረባቸዉም::

9ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች ራሳቸዉን ፍፁም አርገዉ ነዉ የሚቆጥሩት:: በነሱ አመለካከት ስህተት የሚባል ፈጽሞ አያቃቸዉም:: በዚህም ምክንያት ማስረጃ ቢደረደርላቸዉም እንኳ ፈፅሞ የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማቸዉም:: ለሌላ ሰዉ ስተትም ሆነ ለራሳቸዉ ስተት ይቅርታ አያውቁም::ባጠቃላይ አዕምሯቸው ጥፋተኝነትን፣ ይቅርታንና መሸነፍን የሚያከናዉን ክፍል ይጎለዋል ማለት ይቻላል::

10ኛ) የማህበረሰብ ጠንቅ ግለሰቦች የተነፈሱት ወይም የተናገሩት ሁሉ፣ በነሱ አንደበት ስለተነገረ ብቻ፣ አዉነት ነዉ ብለዉ ያምናሉ::

Sociopath
http://www.cnn.com/2013/09/30/us/manson-family-murders-fast-facts/

እናም ወደኛ ወቅታዊ ጉዳይ ስንመለስ በርግጥም በጅጉ በሚያሳስብ ደርጃ በህብረተሳባችን ዉስጥ እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ባህርያት የሚያንፀባርቁ ግለሰቦች በቁጥር ከግዜ ወደግዜ እየጨመረ መምጣቱን በግልፅ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች በተጨባጭ እየታዩ ሲሆን ለግዜዉ ከንደዚህ የማህበረሰብ ጠንቅነት ባህሪ እያንፀባረቁ ካሉት መካከል እንደ አይነተኛ ምሳሌ (typical)ሆኖ ያገኘሁት በቅርቡ በፌስቡክ ላይ በሚያደረገዉ አደገኛ፣ከፋፋይና ለሕዝባችን ጠንቅ የሆነ እንቅስቃሴዉና ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ የሚስተዋለዉ ፀጋዬ አራርሳ የተባለዉ ሲሆን ይህ ግለሰብ ከፌስቡክ ገፁ ለማወቅ እንደቻልኩት በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ(ዶ/ር)፣ የኦሮሞ ሕዝብ ሰባዊ መብት ተከራካሪ ነኝ የሚል፣ የኦሮምኛ ቋንቋ የማይናገር(የማይችል)፣ራሱ(አሁንም በማህበራዊ ድረ-ገፅ በሚያሰራጨዉ መረጃ ነዉ-እኔ በአካል ግለሰቡ መፈጠሩንም አላቅም) እንደሚለዉ ኦሮምኛ ቋንቋ ገና እየተማረ እንደሆነ ይልቁንም አማረኛ ጠንቅቆ እንደሚናገር(ለግንዛቤ እንጂ ቋንቋ የማንኛዉም ሰባዊ መብት ተከራካሪነት ቅድመ ሁኔት አይሆንም) ወዘት በማለት ይቀጥላል ::በዚሁ የፌስቡክ ገፁ እኔን ያስደመመኝ/የገረመኝ ደሞ በየቀኑ የኦሮሞን ሕዝብ በተለይ ከአማራዉ ለመለያየት ለማቃቃር በሚፈለስፋቸዉና ፖስት አድርጎ ያልጠረጠሩና የዋህ አንባቢዎቹ በሚለግሱት ላይክ፣ ኮመንትና ሼር እንደታዳጊ ወጣት ሲቦርቅና ሲፈነድቅ መታዘቤ ነዉ::

እዚህ ላይ ማሳሰብ ያለብኝ ነገር ደግሞ ብዙ ግዜ እንደዚህ አይነት ትችቶች ሲነሱ ብዙዎች ተከፋፍሎ ያለ ሕብረተሰብን ለበለጠ ክፍፍል አስተዋፅኦ ማበርከት ይሆናል የሚሉ አሉ ነገር ግን እኔ እላለሁ የችግሮችን መንስዔ በግልፅ አዉጥቶ ሳያደባብሱ መወያየት በፍፁም ችግሮችን አያባብስም እንደዉም የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ ከመርዳት በስተቀር ::እናም ይህ አስተያየቴ ተጨማሪ ልዩነት ለመፍጠርና ግለሰቦችን ለመወንጀል/ለመተቸት/ለመኮነን ሳይሆን የችግሮችን መነሻ አዉቆ መፍትሄ ለመሻት ይረዳ ይሆናል ከሚል ሃሳብ የመነጨ ነዉ::

ለመንደርደሪያ ይሆነን ዘንድ ግን ለቀባርዉ ማርዳት ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳና የኦዔምን(OMN) ባልደረቦቹ ለሰብአዊ መብቱ በብቸኝነት እንታገልለታለን ወይም ቆመንለታል (አትንኩብን ለኛ የተመደበ የግል ስራችን ነዉ የሚሉ በሚመስል መልኩ) የሚሉንን የኦሮሞን ሕዝብ ባሁኑ ሰዓት ያለበትን ሁኔታ በአጭሩ እናንሳ፤ በሽዎች የሚቆጠሩ የኦሮም ብሔር ተወላጆች በወያኔ እስርቤትና ማጎሪያ ቤቶች ዉስጥ እየማቀቁ እንደሚገኙ ያደባባይ ሚስጥር ነዉ፣ የዛኑ ያህል ደግሞ በቅርቡ ከነዚሁ እስር ቤቶችና ማጎሪያዎች ዉስጥ ሰባዊነትን በሚያኮሥስና በሚያሸማቅቅ ሁኔታ ይቅርታ ተደረገላቸዉ ተብሎ የወያኔ አራዊቶች ሲመፃደቁባቸዉ ሁላችንም ያየነዉና ከንፈር ያስመጠጠን ሃቅ ነዉ፣ በሙሉ ለማለት በሚያስችል የኦሮሞ ተቃዋሚ ሃይሎች መሪዎች ፣ እነ አቶ በቀለ ገርባና ዶ/ር መራራን ጨምሮ አሁንም በዚሁ በወያኔ ማጎሪያና ማሰቃያ እስር ቤቶች ዉስጥ አየተጉላሉ መሆናቸዉ ይታወቃል:: በዚህ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለን ሰቆቃ ዘርዝሮ መጨረስ የሚቻል አይመስለኝም፤ የኢሬቻዉ ፍጅት፣ በግብፅና በሜድትራኒያን ባህረ ዉስጥ የሚያልቁና በኬንያና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት ዉስጥ የሚደርሱባቸዉም መከራዎች መቋጫ አልተበጀላቸዉም:: እንደዉ በኦሮምያ ክልል ያለዉን ሁኔታ ለፅሁፌ ተዛማጅነት አነሳውሁት እንጂ ይህ ሁኔታ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎችና ህዝቦች ማለትም በአማራዉ ክልል በሶማልዉ እንዲሁም በደቡቡ ያለዉ ሁኔታ እንደሚታወቀዉ ተመሳሳይ ነዉ.: የኦሮምያዉን ላተኩርበት የፈለኩት የኦሮሞ ብሄረሰብ መብት ተከራካሪ ነን እያሉ ጠዋት ማታ የምያደርቁን እንደ ዶ/ር ፀጋዬ አራርሳና ኦዔምን(OMN) ያሉ ጓደኞቹ ከላይ የጠቀስኳቸዉን የኦሮሞ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት እየደረሱበት ያለዉን አበሳና ሰቆቃ ችላ በማለት ይልቁንም እስካሁን አንዲት መረጃ ባልተገኘለትና ይልቁንም ከጥላቻ፣ ከግለሰብ አጀንዳና የፖለቲካ ግብ የመነጨዉን ስለሚኒሊክ የኦሮሞ ሕዝብ ጭፍጨፋና የአማራ ህዝብ በሌላዉ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ላይ ስለነበረዉ የበላነት የወያኔ ፈጠራ ታሪክ ለኦሮሞ ወጣቶችና ላልጠረጠሩ የዋህ ተከታዮቻቸዉ ሲያስተምሩና ግራ ሲያጋቡ በመታዘቤ ነዉ::

የኦሮሞ ሕዝብ በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ እያለ፣ ከግል አጀንዳና ጥቅም በስተቅር፣ ለማንም ለምንም በማይጠቅም ጉዳይ ላይ ያለ የሌለ እዉቀት፣ ግዜና ሃይላቸዉን ተጠቅመዉ በዚህ ሕዝብ ደም ላይ በመረማመድ ዝናንና ሌላም ሌላም ግላዊና ሰዋዊ ፍላጎታቸዉን ለማሟላት ብቻ ሲራወጡ እያየን እንዳላየ ወይም ዝም ካልን ሰባዊነታችንን መካድና የእነዚህ በኦሮሞ ሕዝብ ደም ላይ አንደዋዛ የሚረማመዱትና የሚነግዱት ስተት ብቻ ሳይሆን የኛም ከዳር ቆመን ተመልካቾቹም ለዚህ ሕዝብ ስቃይ እኩል አስተዋፅኦ እያበረከትን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል:: ምክንያቱም ዛሬ ሀገርን በዉሸትና በፈጠራ ሲያፈርሱ ፣ ሕዝቦች አብሮ የመኖር ፍላጎትና መብታቸዉ በአጭበርባሪና አካበትነዉ በሚሉት እዉቀት ሽፋን በየዋሁ ህዝባችን ላይ ሲነግዱበት በግልፅ እያየን፣ የታሪክ ወይም የሕግ ዶ/ር፣ ፕሮፌሰር ወዘት ነን እያሉ በወያኔ ስር የሚማቅቀዉን የኦሮሞና ሌላዉንም ሕዝባችንን ለነፃነቱ ባንድነት እንዳይታገልና ለሕብረቱ ደንቃራ በመሆን፣ ይልቁንም የገጠመዉ ሀገር በቀል ጠላት ልጆቹን፣ እናቶችን፣ አባቶችን፣ወንድም፣ እህቶቹንና አጠቃላይ ወገኑን ፊት ለፊት እየገደለበት ያለዉን የወያኔ ቅጥረኛ ገዳይ ወደኅላ ችላ በማለት ከወቅቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለዉና ለወቅቱ ጥያቄ መልስ ሊሆን የማይችልና ማስረጃ ተፈልጎ ያልተገኘለት የነዚሁ የገዳይ ወያኔና ተመሳሳይ ድርጅቶች ፈጠራና ዉሃ የማይቋጥር ልብወለድ ታሪክ በወጣቱና ባልጠረጠሩ የዋህ የሕብረተሰባችን ክፍሎች ዉስጥ እንደመርዝ መርጨት/መስበክ ከማህበረሰብ ጠንቅነት በሺታ ሌላ ምን ብለን ልንጠራዉ እንችላለን?

ህዝቡ የጋራ ጠላቱን ተባብሮ አንዳይታገል በመሃሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ ከመሞከር ይልቅ በየቀኑ አዳዲስ ልዩነት ማጉያ ዘዴዎችን እየፈለሰፉ ህዝቡ ከዋና ጠላቱ ይልቅ በተመሳሳይ በደል ስር ካለ ዜጋዉ ጋር እንዲቃረንና በጥርጣሬ እንዲተያይ ማድረግ ምን አይነት የሰብዓዊ መብት ተከራካሪነት(human right activism) ብለን እንጥራዉ? ይህ ታዲያ ከማኅበረሰብ ጠንቅነት ባህሪ ሌላ ምን አይነት የሰዉ ባህሪ እንበለዉ? ይሄን የሰብዓዊ ፍጡር ባህሪ የህብረተሰብ በሽታ/ጠንቅ ብሎ ለመፈረጅ ደግሞ የግድ የስነልቦና ዶክተር ወይም ጠበብት መሆን ያስፈልጋል ብዬ አላምንም:: በኔ በኩል እነዚህ ግለሰቦች ታመዋል ህዝባችንንም በዚህ በሽታ አየበከሉ ነዉ ::
ሕዝባችን በወያኔ የምድር ላይ ገሃነም እስርቤቶች ታጉሮ እየተሰቃየ፣ እናትን በገደለዉ የልጇ እሬሳ ላይ ተቀመጭ የሚል አዉሬ የወያኔ ስርዓት ከፊታችን ተደቅኖ ፣ ለተራበ ሕዝብ እያለ ባለማቅፍ ደረጃ በልመና ንግድ ላይ የተሰማራ ስርዓት ህዝባችን ጫንቃ ላይ ተዘፍዝፎ ሳለ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ መብት ተከራካሪ ነን የሚሉት እነ ዶ/ር አራርሳ እና የኦኤምን(OMN) ጓደኞቹ ጠዋትና ማታ የሚኒሊክ ፍጅትና የአማራ የበላይነት የስማ በለዉ የልብወለድ ታሪክ መስበክና የወጣቱን አዕምሮ በጥላቻ መመረዝ፣ የመማሩን ነገር ችላ እንበለዉና፣ የጤነኛ ሰዉ አእምሮ አመለካከት መሆኑን የሚያስርዳኝ ሰዉ ለኔ ትልቅ ባለዉለታዬ አርጌ ነዉ የምቆጥረዉ:: ለኔ የነዚህ ሰዎች (የነ ዶ/ር አራርሳና የኦዔምን(OMN) ጋንጎች) ነገር ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲህ ነዉ የሆነብኝ:: ምክንያቱም ባሁኑ ሰዓት የኦሮሞ ህዝብና በተመሳሳይ የጭቆና ቀምበር ዉስጥ ያሉት ኢትዮጵያኖች እያሉ ያሉት እኮ “ጠላታችን፤ ልጆቻችንን፣ እናቶቻችንን፣ አባቶቻችንን፣ እህት ወንድሞቻችንንና ባጠቃላይ ወገኖቻችንን እፊት-ለፊታችን እየገደለ ያለዉ ወያኔ ነው፣ ከዚህ በሃያላን መንግሥታት እየተደገፈ እየገደለንና የልጅ ልጆቻችን መኖሪያ ሀገር ጭምር እያጠፋና እየሸጠ ያለዉ ቅጥረኛዉ ወያኔ ነዉ ::” ነዉ :: ብዙዎችን ግራ ያጋባዉና እኔንም በፍፁም ሊገባኝ ያልቻለዉ ደግሞ እነ ኦዔምን(OMN gangs) እና ዶ/ር አራርሳ በተፃራሪዉ ጠዋትና ማታ በተለይ የኦሮሞን ሕዝብ ለብቻ በመለየት የሚሉት ደግሞ “አንገብጋቢዉና አፋጣኝ መልስ የሚሻዉ ከላይ ያላችሁት ሳይሆን እኛ የተማርነዉና የተመራመርነዉ የምንለዉና ወያኔ(ያሁኑ ገዳያቹ) ለ40+ አመታት አስረግጦ የሰበከን፣ ከሺ አመታት በፊት ተከስቷል ብለን ያመንበት፣ የምኒልክ ፍጅትና ያማራ ሕዝብ የበላይነት ነዉ ::” ነዉ:: ለኔም ፐዝል የሆነብኝም ይሄዉ ነዉ፤ የኦሮሞ ሕዝብ(በመሰረቱ የሁሉም የኢትዮጵያዉያን ሕዝብ ጥያቄ ) እና የዳያስፖራ ኦሮሞ መብት ተከራካሪዎች መልስ:: እነዚህ ሁለት ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲህ ነገሮች እንዴት እንደሚጣጣሙ በቀላል ቋንቋ የሚያስረዳኝ ሰዉ ነዉ ያጣሁት:: እናም እንዚህ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲህ ፈፅሞ እርስበርሱ የማይጣጣም ፍልስፍና እንበለዉ ሃሳብ(idea)ተዋኒዎችን እንዴት እንርዳቸዉ?፣ ዋናዉ ቁም ነገር ደግሞ እራሳችነንና ዉድ ወገናችንን በተለይ ወጣቱን ከዚህ ተላላፊ በሽታ እንዴት እንጠብቅ? እንደማህበረሰብ እንደ አንድ ሀገር እንደሚጋራ ሕዝብ እነዚህ ለህዝባቸዉ ጤናማ አመለካከት የሌላቸዉ(ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ሕብረተሰብ) ከኛዉ ሕብረተሰብ ዉስጥ የወጡ ወገኖቻችን እንደመሆናቸዉ መጠን የሚረዱበትንና በዛዉም የራሳችንንም የወደፊት እጣፈንታ በተለይ ወጣቱን ከዚህ አደገኛ ዝንባሌ መከላከል የምንችልበትን መንገድ መቀየስ የግድ ይላል:: ሆኖም ብዙ ሥራ ይጠይቃል ፣ ትግስት አስጨራሽ አሰልችና አስቸጋሪም ነዉ :: በተለይ መፍትሄዉን ዉስብስብ የሚያደርገዉ፤

1ኛ) እነዚህ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ነን ባዮች በትክክል ግን የማህበረሰብ ጠንቆች ሁኔታዉን ከዘርና ከተፈለሰፈ ታሪክ ጋር ለማያያዝ መጣራቸዉ፣
2ኛ) እነዚሁ ዘርን ያተኮረ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነን ባዮች የማህበረሰብ ጠንቆች በሚያሳስብ ሁኔታ የተማሩ እያልን ሁሌ እሽሩሩ ከምንላቸዉ የሕብረተሰባችን ክፍሎች በብዛት እየተፈለፈሉ መምጣታቸዉና
3ኛ) እኛዉ እራሳችን የነዚህ የማህበረሰብ ጠንቆች አጀንዳቸዉ ፈፅሞ ለሕዝባችን ፋይዳቢስ ቅዥት እንደሆነ አለመረዳትና እዉነትና ዉሸትን ለመለየት ጥረት (fact finding effort) ባለማረግ ዝም ብለን እንደቦይ ዉሃ መነዳታችን ሲሆነ የተረዳነውም ብንሆን ይሄን አፍራሽ ጠንቅ ሃሳባቸዉን ሙሉ በሙሉ ላለመቀበል ወይም ለማስወገድ (to refuse and reject) የሚችል ኮስታራ ሃሞት አጥተን አብረን ለመልፈስፈስ በመምረጥ ቦታ፣ ግዜና ድጋፍ መቸራችን ነዉ::

ጸሃፊውን የነገሰውን በ yenegesew3@gmail.com የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል። በዚህ ጽሁፍ ላይ የቀረበው ሃሳብ የጸሃፊውን እንጂ የግድ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቅም። ጽፉፍ በዚህ ድረገጽ ላይ ለማሳተም ከፈለጉ በ editor@borkena.com ወይንም info@borkena.com መላክ ይቻላል።
__________

የዚህን ጽሁፍ የእንግሊኛ ቅጂ ለማንበብም ሆነ ለማጋራት ይሄንን ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here