spot_img
Saturday, May 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትእምባ በተቀነባበረ ህዝባዊ እምቢተኝነት መተካት አለበት (ዓለም ማሞ)

እምባ በተቀነባበረ ህዝባዊ እምቢተኝነት መተካት አለበት (ዓለም ማሞ)

“….ብቸኛ ምሬት ነው ሃይሉ ወኔ መስለቢያው ነው እምባ ……” 1
ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን “ የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” ግጥም የተወሰደ

ከዓለም ማሞ

መጋቢት 10 ፤ 2009 ዓ.ም

ከመከረኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘረፉት ሃብት ንብረት ጠግበው የሚያቀረሹት የህወሃት/ ኢሕአዴግ የጥፋት መልእክተኞች በዚህ ባለፈው ሳምንት የትውኪያቸው ጎርፍ ገደብ ጥሶ በወገኖቻቻን ላይ ያደረሰው የሞትና የመቁሰል አደጋ በአገራችን ላይ ለሃያ ስድስት አመታት ያለማቋረጥ የሚደርሰውን ብሄራዊ ውርደት እጅግ አሰቃቂ ደረጃ ላይ አድርሶታል። ህጻናት አዛውንት ወጣቶች ሴቶችና ወንዶች የቆሻሻ ክምር ተንዶባቸው ህይወታቸውን ሲያጡና ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ ማየት ዘግናኝነቱ ስብእና ለሚሰማው ልብ ሁሉ በጽኑ የሚያም ነው። አንድ በእድሜዬ ከፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ጀምሮ “ ሁሉን አይቻለሁ” የሚሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ አዛውንት እንዳሉት “ ከዚህ የከፋ ብሄራዊ ውርደት አይመጣብንም። በቆሻሻ ዙርያ መኖሪያቸውን ያደረጉ ወገኖቻችን መኖር ከተከለከሉ ከእንግዲህ በዚህች ምድር መኖር ምን ትርጉም አለው?” ሲሉ በምሬትና እንባ በሚተናነቀው ድምጽ ተናግረዋል።

አዎ ንዋያዊ ድህነትና ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የነበሩ ያሉና ወደፊትም የሚኖሩ ናቸው። እኛ ኢትዮጵያዊያን በሃብትና በቴክኖሎጂ ከዳበሩ ሃገሮች ጋር ስንወዳደር ብዙም ሚዛን የሚደፋ ደረጃ ላይ አይደለንም። እንደ አገርና እንደ ህዝብም በውጫዊና በውስጣዊ ምክንያቶች በርካታ ፈተናዎችና መሰናክሎች ተቋቁመን አልፈናል።አንድም ጊዜ ግን በዚህ ደረጃ ብሄራዊ ውርደት ደርሶብን አያውቅም። የህወሃት/ኢህአዴግ ግፈኛ አስተዳደር በውጭ ወራሪ ከሚደርስ ግፍ በመረረና በከፋ ሁኔታ አገራችንን ህዝቡንም እያዋረደና እያሰቃየ መግዛቱን ቀጥሎበታል። ይህ በተለምዶ ቆሼ እየተባለ በሚጠራው አካባቢም የደረሰው ሰቆቃም የዚህ ስርአት አመታት ያስቆጠረ ጭቆናና ምዝበራ ውጤት ነው።

አንድ ህዝብን አገለግላለሁ የሚል መንግስት ሃላፊነትም የህዝብን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብት አስከብሮና አረጋግጦ ህዝቡ አንገቱን ቀና አድርጎ በብሄራዊ ማንነቱ እንዲኮራ ማድረግ ነው። በአገራችን ለሃያ ስድስት አመታት የዘለቀው ግፈኛና ዘረኛ ስርአት ግን ከክብር ይልቅ ውርደትን በልቶ በማደር ቦታ መታረዝና መተማትን ተክቶ እያዋረደን ይገኛል። እለት ተለት ያለማስለስ መንግስት ተብዬው “ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግቤአለሁ” እያለ በሚደሰኩርበት አገር ከቆሻሻ ውስጥ ተበጥሮ በሚገኝ ልቅምቃሚ ራሳቸውንንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳደሩ ወገኖቻቸን በየቀኑ የሚገፉት የመከራ ኑሮ ሳያንሳቸው ለሞትና ለተጨማሪ መከራ መዳረገቻው የሰው ልጅ ሊሸከመው ከሚችለውና ከሚገባው በላይ ነው። እነኝህ ግፈኞች ከቪላ ቪላ እያማረጡ ልጆቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ለትምህርትና ለህክምና ወደ ወጭ አገር እየላኩ ሲቀናጡ አገራችን እናቶች ልጆቻቸውን በክንዳቸው እንዳቀፉ ከተጫነባቸው ቆሻሻ ስር ለመጨረሻ ጊዜ የሚያሸልቡባት የመከራ ምድር ሆናለች።

የእናቶች ደረት መትቶ ለወያኔ ግፍ ሰለባ ለሆኑ ልጆቻቸው ሙሾ መደርደር የሚያበቃው እምባችንን በህዝባዊ አመጽና ህዝባዊ እምቢተኝነት ስንተካ ብቻ ነው። አባቶች ለወያኔ ሰለባ የሆኑ ልጆቻቸውን መቅበር የሚያበቃው ግፍና መከራ ትወግዶ አምባገነንነት አብቅቶ በህግ የበላይነት ላይ የቆመ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሲገነባ ነው።

ካመት አመት ደረት መትተን
ቀን ከማታ እምባ ረጭተን
ስንላቀስ ሙሾ አውጥተን
ስናነባ ግፍ በዝቶብን
ዘመን ሄዶ ዘመን መጣ
በግፍ ቀንበር ተቀፍድደን ስንቀጣ
እረ ጎበዝ በቃ እንበል
እምባችንን አበስ አርገን
ሰቃችንን በውል አስረን
ክብራችንን እናስመልስ
ለነጻነት ቃል እናድስ።

ባገራችን “ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው” የሚለው አባባል ዛሬ ክተረትነት አልፎ እውን ሆኗል። በእንግሊዝ አገር የሚታተመው ዘጋርድያን የተባለው ጋዜጣ በማርች 9 2017 እትሙ የውጭ ውሃ አሽገው የሚሸጡ ባለ ንዋዮችን በምታስተናገደው ከተማ ነዋሪዎች የሚጠጡት ውሃ የላቸውም ሲል የህወሃት/ኢህአዴግን የግፍ ስርአት አጋልጧል”2 ውሃ፡ መሬት፡ ከከረሰ ምድር በታች ያሉ ማእድኖች ሁሉ ለስርአቱ አውራዎችና ተባባሪዎቻቸው የግል ጸጋ በሆኑበት የወገኖቻችን መጠማትና መታረዝ ሊያስገርመን አይገባም። ይህ ለከት ያጣ ሙስናና በህዝብ ላይ ሰቆቃን መፈጸም ሙያው ያደረገ ስርአት ሰብእና የሌለው አረመኒያዊ ነውና መወገድ ያለበት ነጻነታችንን ለማወጅ ብቻ ሳይሆን ክብራችንንም ለማስመለስ ነው።

ይህ ሙታንን መውቀስ የማያሳፍረው የግፍ አስተዳደር በአውሮፓውያን አቆጣጠር አፕሪል 15 2015 አመተ ምህረት እራሱን ዳኢሽ ወይንም አይሰስ እያለ የሚጠራው የአሽባሪዎች ነብሰ በላ ቡድን 30 ወገኖቻችንን በግፍ ሲቀላ3 በግፍ የተገደሉት ወገኖቻቻን ወንጀለኛ አድርጎ “ከመጀመርያውኑ መሄድ አልነበረባቸውም” በማለት ሲወቅስ ተሰምቷል። ይህ የግፍ ስርአት በቁስላችን ላይ እንጨት እየሰደደ በህመማችን እየቀለደ መኖሩ ማብቃት አለበት። ከእንግዲህ ለሚቀጥለው ወሳኝ ትግል እንጂ ለሚቀጥለው ቀብር ከእንግዲህ የነጻነት ቀንን ለሚያቀርበው አመጽ እንጂ ለሌላ ሙሾ አንዘጋጅም። በዚህ ግፍን ሙያው ባደረግ ስ ር አት ለተሰው ወገኖቻቻችንም ቃል መግባት ያለብን እምባችንን ጠርገን ስናበቃ እጅ ለእጅ ተያይዘን የስ ርአቱን የመከፋፈል ሴራ አምክነን የነጻነት ትግሉን ከዳር ማድረስ ነው። የተስውት ወገኖቻችንም የምንዘክረው ይህ የበደል ስ ርአት እስካላበቃ ድረስ ትግላችንን ላፍታም ቢሆን እንደማንገታ ቃል ስንገባ ነው።

ጸሃፊውን በ alem6711@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

____________

1ጸጋዬ ገብረመድህን። እሳት ወይ አበባ።

2 https://www.theguardian.com/global-development/2017/mar/09/ethiopia-boomtown-waterfirms-locals-thirsty-sululta-oromia

3 http://www.dailymail.co.uk/news/article-3045711/Slaughter-beach-ISIS-behead-shoot-Ethiopian-
Christians-sickening-new-propaganda-video.html

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here