ቬሮኒካ መላኩ
ሚያዚያ 18 2009 ዓ ም
………………
የመጨረሻው መጀመሪያ
…
ባለፈው ወር አካባቢ የቦርከና ድረ ገፅ ባለቤት የእለት ስራውን እያከናወነ እያለ ከሌላኛው የአለም ጫፍ ከወደ አውስትራሊያ አንድ አጠር ያለች መልእክት ትደርሰዋለች ። ይች መልእክት ቦርከና የመልእክት ሳጥን ውስጥ በገባችበት ሰአት በሌላኛው የአለም ጫፍ አንድ በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሰው ዳላስ ውስጥ ምናልባት ራሱ ያፈላውን ቡና ከሲጃራው ጋር እያወራረደ ይሆናል ወይም ደሞ ብዙውን ጊዜውን የሚያዘወትርበት ቤተ መፅሃፍት ቤት ውስጥ ይሆናል ። ሁለቱንም ልማዶቹን በጣም ይወዳቸዋል ። ይህ ሰው በሙሉ ጤንነት ይገኝ የነበረው አሰፋ ጫቦ ነበር ።
መልእክቷ ምን ትላለች?
የቦርከናው ድረ ገፅ ባለቤት መልእክቷን ሲከፍታት እንደዚህ ትላለች :
…
” ሰላም ጠና ይስጥልኝ ። ስሜ ግሪጎሪ ማኬንዚ ይባላል ። አቶ አሰፋ ጫቦ ጋር እንተዋወቃለን ። ሁለታችንም በዓለም በቃኝ እስር ቤት ጓደኛ ነበርን ። እባክህ የአቶ አሰፋ ጫቦን የኢሜይል አድራሻ ላክልኝ። ከምኖርበት አውስትራሊያ ወደ አሜሪካ ስለምጓዝ አሰፋን ማግኘት እፈልጋለሁኝ ። ሁለታችንም ስላረጀን የመጨረሻ እድሌ ሊሆን ይችላል ። ” ይላል
…
ይች አጭር መልእክት የደረሰችው የቦርከናው ድሜጥሮስ ብርቁ ወድያውኑ ለአቶ አሰፋ በፌስ ቡክ ሜሴጂ በኩል የሚከተለውን መልእክት ይልካል :
” ጋሼ አሰፋ ሰላም ነዎት ወይ? አንድ ግሪጎሪ ማኬንዚ የሚባል ሰው ከወደ አውስትሪሊያ ኢሜሎትን ጠየቀኝ ። ሰውየው በአለም በቃኝ እስር ቤት አብረን አሳልፈናል እያለ ነው ። ጓደኛየ ነበሩ ብሏል ። ግለሰቡን ያውቁታል ወይ ? ” በማለት ይፅፍላቸዋል ።
አሰፋ ጫቦም ስሙን በማስታወስ ” አዎን ! በማእከላዊ እስር ቤት ካገኘኋቸው አዋቂ የምላቸው ሰዎች አንዱ ነው ፤ ኢሜይሌን ስጠው ” ብለው መለሱ።
…
የአቶ አሰፋን መልስ ያገኘው የቦርከናው ድረ ገፅ ባለቤት አቶ አሰፋ የሰጡትን የኢሜይል አድራሻ ለግሪጎሪ ማኬንዚ ይልክለታል ።
ከቀናት በኋላም አቶ አሰፋ ወደ ቦርከና በላኩት መልእክት ” ግሪጎሪ ማኬንዚ በስልክ እንዳገኛቸው እና ወደ አሜሪካ ሲመጣ ዳላስ ቴክሳስ ለመገናኘት እንደተቀጣጠሩ ይነግሩትና ። ” ምስጋና ጨምረው ይፅፉለታል ።
…
ቀድሞ በተያዘው ቀጠሮ መሰረት አቶ አሰፋ ጫቦ እና “ሊጎበኛቸው” ዳላስ ድረስ የሄደው ግሪጎር ማኬንዚ ማርች 27 ቀን ዳላስ (ዳውን ታውን) ተገናኙ።
በወቅቱ ሁለቱ ግለሰቦች ሲገናኙ አቶ አሰፋ ጫቦ ምንም አይነት የህመምም ሆነ የድካም ምልክት ያልነበራቸው እና እንዲያውም ለእድሜያቸው በጣም ጠንካራ የሚባል ሁኔታ ላይ እንደነበሩ ነበሩ ።
ይሄንም የሚያረጋግጥ ምናልባት ከራት ሰዓት በፊት በሚመስል ሁኔታ አብረው የተነሱትንም ፎቶ ግራፍ አለ።
ሶስት ሰዓት በዘለቀው ቆይታቸው ፤ በእራት ሰዓት በአንድ የጣሊያን ሬስቶራንት ራት በልተው ፤ እንደገና ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ተለያዮ።
…
በማግስቱ አቶ አሰፋ ጨቦ ታመው ሆስፒታል ሄዱ። አቶ አሰፋ ጫቦ የመጨረሻዋን ኤሜይል ለግሪጎሪ ፃፉ “በምግብ መመረዝ” ። እንደታመሙ እና ስለህመማቸው ስሜት በዝርዝር ከፃፉለት በኋላ ዳግም ሊያገኙት ያልቻሉበትን ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸው እንደሆነ ገለፁለት ። ”
…
ከአውስትሪሊያ ወደ አሜሪካ አቶ አሰፋን ጫቦን ለማግኘት ብዙ ሺህዎች ማይል አቋርጦ ዳላስ የደረሰውና አብሮአቸው ራት የበላው ግሪጎር ማኬንዚ ምንም የሆነው ነገር የለም።
ከዚያ በኋላ አቶ አሰፋ ከሆስፒታል አልተመለሱም። የግሪጎሪ ማኬንዚን እራት ተከትሎ ወደ ሆስፒታል የገቡት አቶ አሰፋ ከሆስፒታሉ ድነው ሳይሆን የወጡት ህይወታቸው አልፎ ነበር ።
እንቆቅልሹ የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው ።
…
ለአለፉት 40 አመታት አቶ አሰፋ ጫቦ ከተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ግልፅና ስውር ሽኩቻ ሲያደርግ ቆይቷል ። ዋጋም ከፍሎበታል ። ኢትዮጵያ ውስጥ እና በአካባቢው ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ወያኔ ፣ ኦነግ ፣ሸአቢያ ፣ ኢህአፓ እና መኢሶኖች አሰፋ ጫቦ ላይ ብዙ ክሶችን ፅፈውበታል ። እሱም የሚያውቀውን የድርጅቶችን ገበና ሳያቅማማ ሲፅፍ ነበር ። እነዚህ ፓርቲዎች በግለሰብ ደረጃ እንደ አሰፋ ጫቦ በእጅጉ የሚፈሩት አልነበረም፡፡ የሸአቢያን ፣ የወያኔንና የኦነግን ሴራ የሚያጋልጠው ፅሁፉ ፅፎ ካሰራጨና በመላው አለም መነጋገሪያ ከሆነ እንኳን ሁለት ወር አይሞላውም ነበር ።
አሰፋ ጫቦ በብሩህ አዕምሮውና በላቀ የእውቀት ደረጃው ብዙዎቹን ፖለቲከኞች በእጥፍ ድርቡ ያስከነዳቸው ነበር ፡፡ በዚህ የተነሳም አሰፋ ጫቦን ለአመታት ሲሰሩት የነበረውን ድብቅ ሴራ አውጥቶብናል ገና ወደፊትም ያወጣብናል እያሉ አጥብቀው ይፈሩትና አምርረው ይጠሉት ነበር ።
…
አሰፋ ጫቦ ጠንቃቃና የማስታወስ ችሎታ የነበረው አዛውንት ስለነበር በኢትዮጵያ ውስጥ እና በኢትዮጵያ ላይ የተሰሩ የድብቅ ሴራዎችን በጥንቃቄ ይዟቸው ኖሮ እያወጣ መጎልጎል ጀመረ ።
በመለስ ዜናዊ የውሸት ክስ ሀገር የተባረረው አሰፋ ጫቦ በአሜሪካ አገር በስደት መኖር ጀመረ፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ግን በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሰው ሀገር የሚኖር ቢሆንም የአሰፋ ጫቦ ነገር እንቅልፍ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ብዙ ጠቋሚ ምክንያቶች ነበሩ ።፡ አቶ አሰፋ ጫቦ በተለያዬ ጊዜ በሚፅፋቸውና በሚያጋልጣቸው ድብቅ ሴራዎች “የቀን ቅዠት ሆኖ እያባነነና እያስበረገጋቸው እንደነበር ይታወቃል። ሌሎቹንም የተደበቁ ሴራዎች እየፃፈ እንደነበር ተናግሯል ።
…
የአቶ አሰፋ ጫቦ የማስታወሻ ደብተር ብዙ ጉዳዮችን አጭቂ የያዘ እንደነበር መገመት አይከብድም ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ቆሰለ ጅብ የመበላላት አባዜ የተጠናወተው ነው ። ሸፍጡን እና ሴራውን ለመደበቅ አንዱን ገድሎ ስልጣኑን ማደላደል የተለመደ ነው ። ይሄ ለአመታት የተለመደ መርዘኛ ሂደቱን ቀጥሏል ። ከአንድ ሰሞን ከንፈር መምጠጥ ባለፈ “ ይሄ ሰው እንደት ሞተ? “ለምን ተገደለ?” በማን ተገደለ? ገዳዩ ለፍርድ ይቅረብ ወዘተ” የሚል ባህል የለንም ።
…
የአሰፋ ጫቦ ጉዳይ ገዳይ ተገዳይ ድራማ ያለበት መስሎ ይሰማኛል ፡፡ በዚህ የገዳይ ተገዳይ ድራማ ውስጥ ብዙ ተሳታፊዎችን መጥቀስ ይቻላል ። አሰፋ ጫቦ በብእሩ ጫፍ ያቆሰላቸው ብዙ ናቸው ። “የትዝታ ፈለግ ” በሚለው መፅሃፉ CIA ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሱዳን ካርቱም ላይ መሰርቶት የነበረውን ጣቢያ አጋልጧል ።
“የተሰነይ ጉባኤ ” በሚለው ፅሁፉ ወያኔ ፣ሸአቢያ እና ኦነግ በኢትዮጵያ ላይ የሰሩትን ሴራ ለህዝቡ አሳውቋል ። ለወደፊቱም የሚያጋልጣቸው ብዙ ሚስጥሮች እንዳሉት እና እያዘጋጃቸው እንደነበር ነግሮናል ።
…
ስታሊን ከአባት ሀገር ያባረረውን ሊዮን ትሮትስኪ በብዙ ሺ ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሰው ሀገር ሜክሲኮ የሚኖር ቢሆንም የሊዮን ትሮትስኪ ነገር እንቅልፍ ሊሰጠው ስላልቻለ በመጥረቢያ አስፈልጦ አስገደለው ። ወያኔ በኬኒያ እና በሱዳን የሚኖሩ ተራ ስደተኞች እረፍት ሲነሷት ወደ አገሮቹ ጎራ በማለት እንደምትገድል ይታወቃል ። CIA ም ቢሆን ጠላቴ ትንሽ ነው ብሎ አይንቅም ። ኦነግም አቶ አሰፋ ጫቦ በሚፅፋቸው መራራ ሃቆች ሲቆስል ኖሯል ። ዛሬ አሰፋ ጫቦን አጥተነዋል ነገር ግን ስለአሟሟቱ እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ብዙ ጥርጣሬዎች አሉ ። አሰፋ ጫቦ ተገደለ ወይስ ” ሞተ? ” ። ይሄ እንቆቅልሽ ይፈታ ዘንድ ሁላችንም መጠየቅ እና ትክክለኛውን መልስ ማግኘት አለብን ።