spot_img
Wednesday, May 29, 2024
Homeነፃ አስተያየትየአማራውን ማህበረሰብ የመብት ትግል የማጠልሸት ዘመቻ (ሃመልማል)

የአማራውን ማህበረሰብ የመብት ትግል የማጠልሸት ዘመቻ (ሃመልማል)

ግንቦት 16 2009 ዓ ም
(ሃመልማል)

ባለፉት 40 እና ከዛ በላይ ለሚሆኑ ዓመታት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የተነሱ የውጭም ሆነ የውስጥ ሃይላት በአማራው ማህበረሰብ ላይ ያላካሄዱት የማጠልሸት እና የማጥላላት ተግባር አልነበረም።በሲያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ ወራሪ ሃይል አማራውን ቀንደኛ ጠላት አድርጎ ቀስቅሶአል።ኤርትራን ለመገንጠል የታገሉ ምንደኞችም የነጻነት ትግላቸው አማራ ከሚባል ህዝብ ጋር የተደረገ በማስመሰል እንደነበር እናስታውሳለን።ወያኔ ገና ከመነሻው አማራውን እንደ ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳው ኢላማው እንድርጎአል።ይህ ተግባር ስልጣን ከያዘ በሁዋላም በመንግስታዊ በመናኛ ብዙሃን ሳይቀር የቀጠለ ተግባር ሆኖ እናገኘዋለን።እንደ ኦነግ እና መሰል ጽንፈኛ የጎሳ ፖለቲከኞች አማራውን ለከት በሌለው የጥላቻ እና የሃሰት ታሪክ ድሪቶ በመኮነን የፖለቲካ ንግግር ማሳመሪያ ማድረጋቸውን አሁንም የምንታዘበው ሃቅ ነው። የሚገርመው ነገር ቅጥፈት ቅጥፈትን እየወለደ ይህ የጥላቻ ፍረጃ እና አመለካከት እየጎለበተ ስጋ በመልበስ በአሁኑ ወቅት በአማርኛ ተናጋሪው ህብረተሰብ ላይ ይህ ነው የማይባል ወከባ እና ግፍ በመፈጸም ላይ ይገኛል።

ይህ ታሪክን፣ እና እውነትን ለማንሻፈፍ የሚደረግ ዘመቻ አንዳንዴ ድንበር ተሻግሮ በውጭ ሃገር ሰዎችም ሲፈጸም ይታያል።በተለይ ደካማ የስነ-ሰብ ተመራማሪዎች (Anthropologists) ፣የቅኝ አዘዛዝ ስርዓት ጉዳይ አስፈጻሚ ምሁራን እና ጋዜጠኞች፣የፋሺዝም አፈቀላጤዎች፣ እንዲሁም ሃይማኖትን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ የአካባቢው ተስፋፊ መንግስታት አጀንዳ አስፈጻሚዎች ሃገራችንን ከዓለም ካርታ ላይ ለመፋቅ ታሪክን አጣሞ ማቅረብ የድርጊታቸው ዋነኛ አካል አድርገው ተንቀሳቅሰዋል።አሳዛኙ ነገር ከላይ የተጠቀሱት ወገኖችን ደባ እንደወረደ በመቀበል የሚያስተጋቡ የሃገር ውስጥ የታሪክ እና የፖለቲካ ሰዎች መኖራቸው ነው።

በተቃራኒው ግን፣ ጉዳዮ ሊያሳስበን የሚገባ ሀገር ወዳድ ወገኖች ዝምታ እና ቸልታ በታሪካችን እና የህዝባችንን ገጽታ ለማጠልሸት እየተሰራ ያለው ሽፍትነት ለከት እያጣ በመሄድ ላይ ይገኛል።ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝም ከሰሞኑ በአንድ የመገናኛ ብዙሃን፣ የጀርመን ድምጽ እንግሊዘኛው ፕሮግራም፣ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ የመብት እንቅስቃሴ የገለጸበት መንገድ (Amhara people pine for the Ethiopia of old )አስተዛዛቢ ሆኖ ስላገኘሁት ነው። በዘገባ መሰረት በተለይ በአማራ ክልል በመካሄደ ላይ ያለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንደሌሎች የመብት ትግል ሳይሆን የቀድሞ ስርዓትን ለመመለስ የሚደረግ ተጋድሎ እንደሆነ አስመስሎ አንሻፎ አቅርቦአል።ይህ ህዝባዊ መሰረት ያለውን ተጋድሎ ባለፈው ስርዓት ናፋቂነት የመፈረጁ ድርጊት ብዙ ፖለቲካዊ እንድምናዎችን እና መዘዞችን እንደሚያስከትል መናገር ይቻላል።

በእውነት ለመናገር በጎንደርም ሆነ ሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች በተካሄዱ ትግሎች ተሳታፊ እና አመራር ሰጪ የነበሩት በአብዛኛው እድሜያቸው ከ25 እና ከዛ በታች የሆኑ ወጣቶች ናቸው። የሚገርመው ነገር እነዚህ ወጣቶች ያለፈውን ስርዓት የሚያስናፍቅ አንድም ምክንያት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ ተወልደው እስኪያድጉ ድረስ የሚያውቁት አንድ የፖለቲካ ስርዓት ቢኖር የህወሃት/ወያኔ አገዛዝን ነው።በሁሉም የአማራ አካባቢዎች በተደረጉ የተቃወሞ ሰልፎች የተሰሙ መፈክሮች ሰለመብት፣እኩልነት፣ እና ፍትሃዊ የሆነ ስርአት የመመስረት ጥያቄ ዙሪያ እንደነበረ እናስታውሳለን።የቀደሙት ስርአቶችን የሚያወድስ ሆነ፣ ናፋቂ የሚያሰኝ አንድም መፈክር ባልታየበት ሁኔታ የዚህ አይነት ዘገባ ማቅረብ የወረደ የጋዜጠኝነት ስራ ብቻ ሳይሆን እውነትን ለማጣመም ሆነ ተብሎ የተደረገ ደባ ያስመስላል።

በመጀመሪያ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሰፍነኖ በነበረው የአገዛዝ ስርዓት ተጠቃሚ ሊሆን ቀርቶ ስርዓቶቹ ባደረሱበት በደል የተጎሳቆለ እና ከማንም ህዝብ በበለጠ የሃይለስላሴንም ሆነ የደርግን አገዛዞች ለመጣል ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ ነው።በምንም መነሻ ቢሆን አንድ ህዝብ ታግሎ የጣለውን ስርዓት የሚናፍቅበት ምክንያት የለም። ባለፈው ስርዓት ናፋቂነት አማራውን መወንጀል ይህ ህዝብ የከፈለውን መራር መስዋእትነት መካድ ጭምር ነው። ሁለተኛው መነሳት ያለ ነጥብ እንዲህ አይነት አመለካከቶች ከዚህ ቀደም የነበሩ የአገዛዝ ስርዓቶች የአማራ ህዝብ ሙሉ ድጋፍ የነበራቸው በዚህም ተጠቃሚ አድርጎ የማቅረብ ችግር አለበት።ከዛም አልፎ የአገዛዝ ስርዓቶቹ አማራውን በሌሎች ኪሳራ የጠቀመ እንደሆነ በማድረግ የመወንጀል ድርጊት ነው። ሲስተኛው ነጥብ በሌሎች አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የመብት ትግል፣ ነገር ግን በአማራ ክልል የሚደረጉ ትግሎች የድሮ ስርአትን የመመለስ ይዘት ያላቸው አድርጎ በማቅረብ የማሳነስ ነው። በዚህም የተነሳ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ አማርኛ ተናጋሪው የሚያነሳው የእኩልነት፣የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄ እንዳልሆነ በማቅረብ የሞራል ተቀባይነት እንዳይኖረው የማድረግ ሴረኛ አካሂያድ ነው።በሌላ በኩልም የህዝብ ተቃወሞ ሲነሳበት ህወሃት/ወያኔ የተቃወሞውን ገጽታ ለማጠልሸት የጥቂት ከተሜዎች እና ስልጣናቸውን ያጡ አካላት ሙከራ እንደሆነ በማድረግ የሚያቀርበውን የሃሰት ቅስቀሳ ማስተጋባት ነው።

በሌሎች ክልሎች የሚደረጉ ትግሎችን እንደመብት ትግል በመቁጠር፣በአማራ ክልል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የተለየ ገጽታ ማላበስ በሰብአዊነት ላይ የሚደረግ ማላገጥ ነው።በአንድ በኩል መብት ለሁሉም ይገባል እየተባለ፣በሌላ በኩልም ሁሉንም የመብት ትግሎች በእኩል አይን ለማየት አለመቻል፣በዚህ ጽሁፍ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው አንድን ማህበረሰብ ነጥሎ በማጥላላት እና ጥላሸት በመቀባት ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ አካል ነው እንድንል ያደርናል።

የውጭ ዜና አውታሮች ፣ምሁራን እና አንዳንድ ተንታኞች ከገዢው መንግስት ወይንም የጎሳ ጽንፈኞች የሚያገኙትን የጥላቻ ፍረጃ እንደወረደ ተቀብለው በማስተጋባት ሌላው ዓለም የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው እያደረጉ ነው።የዚህ አንደኛው ምክንያት ሀገር በቀሎቹ ጽንፈኛ ጎሰኞች የሚያደርጉትን የጥላቻ ዘመቻ እግር በእግር እየተከታተከሉ የማጋለጥ ስራ አለመስራት ሲሆን፣ሁለተኛው ደግሞ በውጭ ሃገር ያሉ ጋዜጠኞችም ሆኑ ምሁራን በተሳሳተ ሁኔታ የህዝባችንን እና ሃገራችንን እውነታ ሲገልጹ እንዲታረሙ ጥረት አለማድረግ ነው።

ሌላው ይህን ጉዳይ በንቃት ተከታትሎ የአጸፋ ስራ መስራት የትግሉ አንድ አካል መሆኑን የመረዳት ችግር ነው። ጠላታችንን ማሸነፍ የምንችነው በአንድ ግንባር በሚደረግ ትግል ብቻ ሳይሆን የተነሳንለት አላማ እና ግብ ፍትሃዊ እና የመብት ትግል መሆኑን የተቀረው የአለም ማህበረሰብ ግንዛቤ በማስጨበጥ አጋር ማድረግ ስንችል ብቻ ነው።

በዚህ ወቅት በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚደረግ ትግል ሂደቱ እና ውጤቱ በአንድ አካባቢ ወይንም ሁኔታ ማይወሰንበት ደረጃ ላይ እንደመገኘታችን የአንድ አቅጣጫ ትግል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዘነ ነው፡፡የእኛን ጥፋት የሚመኙ ሃይላት እንደ ስፍር ቁጥር በበዙበት ዓለም ነገሮችን በቸልታ እና ንቆ በመተው መመልከት የሚያስከትለው ጉዳት የትእየለሌ ነው።ስለ ትግሉ አላማ እና ግብ የተቀረው ዓለም የሚይዘው አቈዋም ከወሳኝ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን በመረዳት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የውጭው ማህበረሰብ ስለ መብት ትግሉ ማስገንዘብ ሊተው የሚገባ ተግባር አይደለም፡፡ለምሳሌ አፓርታይድን ለማስወገድ በደቡብ አፍሪካ የካሄደው ትግል ስኬታማ ለመሆን የቻለው በመላው አለም የትግሉ ወዳጆች እና ደጋፊዎችን ማፍራት በመቻሉ ነው።በታላላቅ የዓለም ከተሞች ውስጥ የተካሄዱ ጸረ-አፓርታይድ ሰልፎች እና የተቃወሞ እንቅስቃሴዎች ተጽእኖ መፍጠር ችለው አብዛኞቹ የዓለም ሃገራት ከአፓርታይድ መንግስት ጋር ያላቸውን የንግድ እና ዲፕሎማሲ ግንኙነት ከማቈዋረጥ ጀምሮ የተናጥል እና የጉዞ ማእቀቦችን በማድረጋቸው ነው የአፓርታይድ መንግስት ለመንበርከክ የቻለው።

በተለይ በውጭ ሃገራት የምንገኘ ሃገር ወዳድ ዜጎች በተገኘው አጋጣሚ መታረም የሚገባቸውን የዜና ዘገባዎችም ሆነ ሪፖርቶች እንዲታረሙ በማድረግ፣ በማስተካከል፣ዓለም አቀፉ ማህበረሰቡን የትግሉ አጋር ለማድረግ መንቀሳቀስ ይኖርብናል።ይህ ብዙም ጥረት የማይጠይቅ ትግል ከምናውቃቸው ታላላቅ የውጭ ሃገራት ተጽእኖ ፈጣሪ ዜጎች ጀምሮ፣ጋዜጠኞች፣ምሁራን፣ የፖለቲካ መሪዎች እና የጥበብ ባለሙያዎችን በመቅረብ ህዝባችን የሚገኝበትን አስከፊ ሁኔታ በማስረዳት ወዳጅ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

የዶቼ ቨሌ ዘገባ
Amhara people pine for the Ethiopia of old (10.05.2017)
http://www.dw.com/en/amhara-people-pine-for-the-ethiopia-of-old/g-38771344

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here