spot_img
Friday, December 1, 2023
Homeአበይት ዜናየዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ምርጫ ሰም እና ወርቅ (በመስከረም አበራ)

የዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ምርጫ ሰም እና ወርቅ (በመስከረም አበራ)

advertisement

(በመስከረም አበራ)
ግንቦት 19 ፤ 2009 ዓ ም

Gates-World-Health-Organization-Tedros-Adhanom

አለም አቀፉ የጤና ድርጅት በእንግሊዝኛ ምህፃሩ “WHO” በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩትን ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ሊቀመንበሩ ድርጎ ሰሞኑን ሾሟል፡፡ ሰውየው የኢትዮጵያን ሁለመና እንደ እንዝርት ከሚያሾረው ህወሃት ዋና ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ይህ ከዕጩነታቸው እስከ ምረጡኝ ዘመቻቸው ሁሉን ሙሉ ሁሉን ዝግጁ ሳያደርግላቸው አልቀረም፡፡

ሰውየው ለጤናው ዘርፉ ቀጥተኛ ባለሙያ የሚያደርጋቸው የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ከጥቂት አመት በፊት ለኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትርነት በአቶ መለስ አቅራቢነት ታጭተው ለፓርላማ ሲቀርቡ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ዘንድ ለስፍራው ተገቢ የመሆናቸው ነገር ተነስቶ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ የእሳቸው መንገድ ብቻ እውነትም ህይወትም የሚመስላቸው የማይበገሩት አቶ መለስ ታዲያ ቆጣ ብለው “ቴድሮስ የተፈለገው ለጤና ሴክተሩ አስተዳደራዊ ስራ እንዲሰራ እንጅ መርፌ እንዲወጋ አይደለም” ሲሉ ወዲህ ጓዳቸውን ወዲያ የወንዛቸውን ልጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን የሃገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሆኑ አደረጉ፡፡

የተሻለ ብቃትም ሆነ ለጤናው መስክ ቀጥተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን ባሉበት ሁኔታ ዶ/ር ቴድሮስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መሆናቸው ሰውየው በወቅቱ የሃገሪቱን ፖለቲካ በመሃል እጃቸው ይዘው በነበሩት መለስ ዜናዊ ፊት ሞገስ እንዳላቸው ከማስመስከር በቀር ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ዶ/ር ቴድሮስም ከሞቱ በኋላ ሳይቀር “የምንወደው መለስ” እያሉ ሟች ሿሚ ሸላሚያቸውን በስስት ይጠራሉ፡፡ዶ/ር ቴድሮስ የሚወዷቸው መለስ አግባብነቱ እያጠያየቀም ቢሆን የወንዛቸውን ልጅ በጤና ሚኒስትርነት ሾመው ብቻ ዝም አላሉም፡፡ የሰሩ ያልሰሩት በጎ ነገር ሁሉ እየተነሳ ሲመሽ ሲነጋ እንዲወደሱ በጎ ፈቃዳቸውን ችረዋቸዋል፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩ ሰዓት የሚወደስ የሚሞገሰው የፓርቲው ሰው ሁሉ የእርሳቸውን እና የባለቤታቸውን የወ/ሮ አዜብን ይሁንታ ካላገኘ ውዳሴ ቅዳሴው ውሎ አያድርም፡፡ ለዚህ ምስክሩ ፖስተራቸው የአንድ ቀን እድሜ ሳያገኝ ከፒያሳ እንዲነሳ የተደረጉት ዶ/ር አርከበ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት ወንበር መቀመጣቸው እንኳን በዛ ተብሎ ሲያነጋግሩ የኖሩት ዶ/ር ቴድሮስ ዛሬ የዓለም ዓቀፉ የጤና ድርጅት ዋና ለመሆን ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ሁለት ተቃራኒ እይታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ‘ዶ/ር ቴድሮስ ጉድ የሆነ ብቃት ስላላቸው ብቻ ዓለም ልምድ ችሎታቸውን ክፉኛ ተመኝቶ በሰፊ ድምፅ መረጣቸው’ የሚለው የፓርቲያቸው ወዳጆች እና በአብዛኛው የወንዛቸው ልጆች እሳቤ ሲሆን ሁለተኛው ከዚህ በተቃራኒው የቆመ ነው፡፡ሁለተኛው እሳቤ ሰውየው በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃም ሆነ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ወቅት የፓርቲያቸው ጉዳይ ፈፃሚ ሆነው ብዙ ግፍ የሰሩ፣ ሲሰራ የተባበሩ ሰው ናቸው፡፡ ስለዚህ አድሎ በዞረበት የማይዞረውን የጤና ጥበቃ አገልግሎት ለዛውም በአለም አቀፍ ደረጃ ለመምራት ወንበሩ የሚሰፋቸው፤ አድሎ ያልጎበኘው ስብዕናም የሚያንሳቸው ሰው ናቸው የሚል ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ሰውየው ይሰፋቸዋል በተባለው ወንበር ላይ ለመቀመጥ እንደቋመጡ ተሳክቶላቸዋል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ የዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ የስምረቱን ዋነኛ ምዕራፍ ያለፈው የአምባገነን መንጋ በሚርመሰመስበት የአፍሪካ ህብረት እጩነታቸው ተቀባይነት ያገኘ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ስኬታማነትን እንዲቀዳጁ የወንዛቸው ልጆች የሚዘውሩት የኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ይነገራል፡፡ ከትልቁ አስተዋፅኦ ዋነኛው አፍሪካን ወክለው ሊወዳደሩ ያሰቡ ሌሎች ሶስት አፍሪካዊ እጩዎች መንገዳቸው አልጋ ባልጋ እንዳይሆን የኢትዮጵያ መንግስት ተፅዕኖ ስለፈጠረ እንደሆነ ተንታኞች ይከራከራሉ፡፡ይሄ ደረጃ ለዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ በጣም ወሳኝ የሚሆንበት ዋነኛ ምክንያት እድሉን አግኝቶ የማያውቀው የአፍሪካ አህጉር እጩ የሚያደርጋቸው በመሆኑ ብቻ አይደለም፡፡በተጨማሪ በስመ አፍሪካዊ እጩ የፓርቲያቸው ደመኛ ኤርትራ ሳትቀር የሃምሳ አራቱን የአፍሪካ ሃገራት ድምፅ አፈፍ ለማድረግ ስለሚረዳቸው ነው፡፡በዚህ ላይ ሃገራችንን የሚዘውረው ፓርቲያቸው ሳይሰስት የሚያቀርብላቸው ለምረጡኝ ቅስቀሳ የሚሆን ምቹ ሁኔታ ሲደመር የቢልጌትስ ረብጣ ዶላር ለሌሎቹ ተፎካካሪዎቻቸው እንደሰማይ የራቀ፤ ለእርሳቸው ሙዝ እንደመላጥ የቀለለ ነገር ነው፡፡

ህወሃት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ደጋፊ የፓርቲያቸው አባላት፣የወንዛቸው ልጆች የዶ/ር ቴድሮስን መመረጥ በጥፍራቸው ቆመው የሚኙት ብቻ ሳይሆን በአንድ እግራቸው ቆመው የሚፀልዩበት ጉዳይ እንደሆነ ሲናገሩ ከቃላቸው፣ ሳይናገሩ ከአአድራጎታቸው መረዳት ቀላል ነው፡፡ ለዶ/ር ቴድሮስ የምርጫ ስኬት በሃገራችን መንግስት የተደረገው ከፍተኛ የማሻሻጥ ስራ ከዚህ ቀደም ለአፍሪካ ልማት ባንክ ዳይሬክተርነት ለተወዳደሩት በችሎታቸውም እንደ አብዛኖቹ ኢህኤደግ ባለስልጣናት እንደነገሩ ላልሆኑት አቶ ሶፊያን አህመድ ሲደረግ አላየንም፡፡ ይህ ለምን ሆነ፤የቴድሮስ መመረጥ ለእናት ፓርቲያቸው ህወሃት ምኑ ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

ለጠንካራ ሰው ጠኔ ፈውስ

ዶ/ር ቴድሮስ ዋና የሆኑበት በስመ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን የሚያሾረው ህወሃት ሁሉን በትከሻቸው ጥሎባቸው የነበረው ደንዳናው አምባገነን መለስ ዜናዊ ድንገት ወደማይቀረው ከሾለኩ በኋላ ፓርቲው ውቃቢ ርቆታል፡፡ ከ1993ቱ የፓርቲው ስንጥቃት ወዲህ ለረዥም ጊዜ በአቶ መለስ ጠንካራ መዳፍ ከመጨምደዱ የተነሳ በአንድ ሰው አድራጊ ፈጣሪነት መመራትን፤ የሰውን ልጅ እንደመለኮት የማየት ነገር በህወሃትም ሆነ በኢህአዴግ ውስጥ እንደ ትክክለኛ ነገር ይወሰዳል፡፡ በመሰረቱ ለዲሞክራሲ ተራራውን ቧጠጥኩ፣ በእሾህ አሜከላ፤ በጠጠር በጭንጫ አስራ ሰባት አመት ተራመድኩ የሚል ፓርቲ የፀረ-ዲሞክራሲያዊነት ባንዲራ የሆነውን አምባገነን የማንገስ ኋላ ቀርነት እንደ ደህና ሙያ ማውራት አልነበረበትም፡፡ ያለ አምባገነን ሃገርን ጥሩ አድርጎ መምራት እንደሚቻል መረዳት ለዲሞክራሲ ሞቼ ተነስቼ ለሚል አካል ቀርቶ ለማንም ሰው ከባድ አይደለም፡፡

ወደው ይሁን ከአቶ መለስ ጋር የመጋፋቱን አቀበት አስቸጋሪነት ተረድተው የህወሃትም ሆነ የኢህአዴግ መኳንንት አቶ መለስን “እንዳልክ” ማለቱን መርጠው ኖረዋል፡፡ በዚህ መሃል ሳይታሰብ የመጣው ማንንም የማይፈራው ሞት ከአምላክ የሚያስተካክሉትን ሰው ይዞት እብስ ሲል (ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ትዝ እንዳይላቸው አድርገው ረስተዋልና) ሃሳባቸውን የሚጥሉበት፣እንደ ልዕለ-ሰብ የሚመኩበት በሟቹ እግር የሚተካ ተመላኪ ይሻሉ፡፡ ከሰው ፍጥረት የሚስተካከለው እንደሌለ ተናግረው ከማይጠግቡለት የአምባገነኑ መለስ “የአዋቂነት” ሙላት የሚተካከል መፅናኛ ከህወሃት ወገን እንዲወጣ ያማትራሉ፡፡ አምባገነንነት ከባለራዕይነት፣ እብሪት ከአዋቂነት፣ ሴረኝነት ክህደት ሳይቀር ከልቅና የተፃፈለትን መለስን ለመተካት ከህወሃት መንደር ፈልጎ ማግኘቱ ቢቸግርም የበለጠው ችግር ሌላ ነው፡፡

ዘላለም ህወሃትን በዋናው ወንበር ማስቀመጡን መታገስ እየከበደው በመጣው የኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ህወሃቱ አቶ መለስ በተነሱበት የእውነት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ላይ ሌላ የህወሃት ሰው ማስቀመጡ ነው እንደ ጉተና ከባዱ ነገር፡፡ይሄን ነገር ማድረጉ ወከልነው የሚሉት ህዝብ ዘንድ ሞገስ የሌላቸውን ብአዴን እና ኦህዴዶች ፊትም ሳያጠቁር አይቀርም፡፡ ይህን እንቅፋት ለመቀነስ ከብአዴን፣ኦህዴድ እና አጋር ተብየዎች ይልቅ የህወሃት ሰዎችን በዓለም መድረክ ሳይቀር ክፉኛ የመፈለግ ልቅና “በተግባር” ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ በእጅም በእግርም የሞት የሽረት ሩጫ አድርጎ ዶ/ር ቴድሮስን ለአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ማስመረጡ ጥቅሙ ለሰውየው ብቻ ሳይሆን ለእናት ፓርቲያቸውም የሚተቅመው ለዚህ ነው፡፡

ህወሃቶች በኢህአዴግ ከታቀፉ ፓርቲዎች ሁሉ ራሳቸውን በፖለቲካ የበሰሉ፤ ይገዙ ይነዱ ዘንድ የተገባ አድርገው እንደሚያስቡ በአቶ ገብሩ አስራት መፅሃፍ ላይ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተቀምጧል፡፡ ተዘዋዋሪው ብዙ ቢሆንም በቀጥታ የተቀመጠው ግን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ህወሃቶች እየተሰበሰቡ ስለጉዳዩ ሲፈጩ ሲሰልቁ ሌሎች የኢህአዴግ አባል/አጋር ፓርቲዎች ያልተገኙት በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ህወሃቶች ስለሆኑ በመጀመሪያ እነሱው ነገሩን እንዲያብላሉት፤በውሳኔው ላይም ከፍተኛ ሚና መጫዎት ያለባቸው እነዚህ “ምጡቅ ተገንዛቢዎች” እንዲሆኑ ታስቦ እንደነበረ በመፅሃፉ ገፅ፡206 ላይ ተገልጧል፡፡ ሌላው አጋጣሚ አቶ መለስ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ህወሃት ብቻ የናኘበትን ምክንያት ሲጠየቁ ነገሩ የችሎታ ጉዳይ እንደሆነ የገለፁበት አስገራሚ ንግግር ነው፡፡ ሶስተኛ ለመጨመር ያህል እስከ ቅርብ ጊዜ የህወሃት መኳንንት የጦር ጀነራልነቱን ቦታ የተቆጣጠሩበትን ሚስጥር ሲያስረዱ ህወሃቶች ያላቸውን “ምጡቅ የውትድርና እውቀት እና ልምድ” በመጥቀስ፤ ይህንኑ “እውቀት ጢቅነታቸውን” ለሌሎች እስኪያካፍሉ ድረስ ብቻ በጀነራልነቱ ላይ እንደበረከቱ ፈርጠም ብለው ሲያስረዱ ትናንት ስልጣኑ ላይ የወጡ እንጅ ሃያ ምናምን አመት የኖሩ አይመስሉም፡፡

እስካሁን በስልጣ ላይ ተወዝተው ለመኖራቸው፤ ወደፊትም ለሰባት ጉልበታቸው የሚመኙትን ስልጣን በእጃቸው ለማቆየት ህወሃቶች እንደ ማሳመኛ የሚያነሱት በፖለቲካ ውትድርናው “አለን” የሚሉትን ልቅናቸውን ነው፡፡ የሰሞኑ የዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ ታዲያ በመለስ እግር ይተኩት ዘንድ ሲዋትቱለት የኖሩትን የጠንካራ ሰው ሃራራቸውን ተንፈስ ለማድረግ፤ የፓርቲያቸውን አባላት ሃገር ቀርቶ ዓለምን ለመምራት የመመረጥ ምጡቅነት ለተገዳዳሪዎቻቸው ለማሳየት እንደጥሩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል፡፡በጓዶቻቸው ዘንድ ምጡቅነታቸው ብቻ እንዳስመረጣቸው ሆድ ሲየውቅ የሆነ ከበሮ የሚደለቅላቸው ዶ/ር ቴድሮስ “WHO”ን መርተው እስኪመለሱ (ህወሃት ሌላ ክፉ እጣ ካልገጠመው) በስመ ኢህአዴግ ሃገሪቱ በአቶ ኃይለማርያም እንደነገሩ እያዘገመች እንድትቆይ አድርጎ ለዶ/ር ቴድሮስ የእውነተኛ ጠቅላይነቱን ገፀ-በረከት እነሆ ለማለት የሚጠይቀው ቀላል ነገር “WHO”ን የሚያክል ታላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅትን የመሩበትን ምጥቀታቸው በኢቢሲ ሰሚን እስኪያቅረው መተረክ ብቻ ነው፡፡

ለቤት ጣጣ መላ

የዶ/ር ቴድሮስ መመረጥ ህወሃትን አገኘው ለሚባለው “ለባዕድ” ጮክ ብሎ የማይነገር ውስጠ-ፓርቲ መጎሻመጥ እንደ አንዳች ማስታገሻ እድል ተደርጎ መወሰዱም አይቀርም- በመለስ ራዕይ አስፈፃሚ ነን ባዮች፡፡ልብ ብሎ ላደመጠ በ1993ቱ ስንጥቃት ተባራሪ የህወሃት መኳንንቶች ፅሁፍ ንግግር ሳይቀር (በማወቅ ሳይሆን ባለማወቅ፣ በቀጥታ ሳይሆን በዘወርዋራ) እንደሚገለፀው የህወሃት ከኳንንት “መለስ ራዕይ አይቷል አላየም”፣ “የህዝባዊ አመፁምክንያት ውስጥ ነው ከውጭ” በሚልም ሆነ በሌላ ምክንያት ለሁለት ጎራ ተከፍለው እንደሚቆራቆሱ ማወቅ አይከብድም፡፡ “የምንወደው መለስ” ሲሉ ሟቹን አለቃቸውን የሚያሞካሹት ዶ/ር ቴድሮስ ምድባቸው ‘መለስ ራዕይ አይቷል እኛ ደግሞ እሱን ውልፊት ሳይል እናስፈፅማለን’ ከሚሉት ወገን እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ሰውየው ከሰሞኑ በለስ ቀንቷቸው ወደ አለም ዓቀፍ ተቋም ዋናነት ወንበር መውጣት በምዕራባዊያን ዘነድ የቅቡልነት ምልክት እንደሆነ ታስቦ ለተቀናቃኝ የዘመድ ፀበኞቻቸው በመጠኑም ቢሆን የመለስ ራዕይ ሰባኪዎች የበላይነታቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ አድርገው መውሰዳቸው አይቀርም፡፡

ከምዕራባዊያን ጋር ፍቅር እንደገና

በስተመጨረሻው “ጥሩ” አምባገነን የወጣቸው አቶ መለስ የዛሬ 27 አመት በተወለዱ በ33 አመታቸው ወደ ስልጣን ሲወጡ በምዕራባዊያን መሪዎች ዘንድ “ወጣት ዲሞክራት መሪ” የሚል ችኩል ሊሻን ተለጥፎላቸው ነበር፡፡ ማድበስበስ፣ ማስመሰል፣ ፍርድ መገምደል መለያቸው የሆነው ምዕራባዊያን መሪዎች እንደ ድሮው ማሞካሸታቸውን ቢቀንሱም አሁንም ኢህአዴግ የሚፈልገውን በውሸት ሳቃቸው አጅበው መናገራቸውን አልተውም፡፡ እንደ ትጥቅ ትግል የሚሞክረውን በጥይት ድምፅ የታጀበ፣በእስር ስደት ያረገን ምርጫ “ውጤቱ እንጂ ሂደቱ ደግ ነበር” ከማለት አፋቸውን ሞልተው “ዲሞክራሲያዊ ነው” እስከማለት ፍርድ ሲገመድሉ ያጋጥማል፡፡

ምዕራባዊያኑ መንግስታት እንዲህ የተውሸለሸለ አቋም ቢኖራቸውም በእነሱው የሚደጎሙ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከኢህአዴግ ጋር ቢያንስ በአመት አንዴ (አመታዊ ሪፖርታቸውን ሲያወጡ) መነታረካቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ተቋማት “እንከን አልቦ ነኝ” ለማለት የሚሞክረውን የኢህአዴግን መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዝ ኋላቀርነት አብጠርጥረው ገበያ የሚያወጡ በመሆናቸው በአለም መድረክ የነበረውን የፖለቲካ ኪሎ በትንሹም ቢሆን ሳይቀንሱበት፤ከየአቅጣጫው ማፈስ የለመደውን ዶላር ሳያመናምኑበት አልቀሩም፡፡

ሁሌ ጥግ የሚፈልገው ኢህአዴግ ታዲያ የምዕራባዊያንን እጅ ማጠር፣ውዳሴ መቀነስ ተከትሎ የተሰማውን ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ቻይናን እንደ ምትክ ካፖርት መልበሱ ብቻ ስላላስታገሰለት የአፍሪካ ሃገራትን ደርቦ “ሰው በሰው ይተካልን” ማዜም ይፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ በጣም ይመካበት የነበረው በአፍሪካ ቀንድ በተለይ በሶማሌ አለኝ የሚለው የሠላም አለቅነት ሚና ከሶማሌ አዲሱ ፕሬዚደንት ፋርማጆ መመረጥ ወዲህም ሆነ ቀድም ብሎ እያጣ እንደመጣ ነው ሁኔታዎች የሚያሳዩት፡፡የኢትዮጵያ መንግስት ከፋርማጆ መመረጥ ትቂት ቀደም ብሎ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ ጦሩን ከሱማሌ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ወደ ሳዑዲ በተጓዙ ሰዓት ፋርማጆን ሪያድ ላይ አስጠርተው እንዳናገሩ፤ፋርማጆም በአሜሪካ የሚደገፍ ሃገርኛ ጠንካራ ጦር ለሃገራቸው እንደሚሹ እንደተናገሩ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡ ነገሩ ወትሮም በሃገራቸው ፖለቲካ የኢትዮጵያን አድራጊ ፈጣሪነት የማይወዱት አዲሱ የሶማሌ ፕሬዚደንት ኢትዮጵያን ገሸሽ በማድረጉ ላይ እንዳመረሩ ያሳያል፡፡ ይሄ ደግሞ የኢህአዴግ መንግስት ከምዕራባዊያን ጋር አቆራኝቶኛል ሲል የሚመካበትን የፀረ-ሽብር ዘመቻ ፊት አውራሪነት፣ የምስራቅ አፍሪካ የሰላም አለቅነት ክር እያሰለለው መጥቷል፡፡ ነገሩ ሲብስ ኢህአዴግ መራሹ የሃገራችን መንግስት በሁለቱ ሱዳኖች ላይ እንዲኖረው የሚፈልገውን የሽምግልና ሞገስ እያጣ በምትኩ በሳልቫኬር በኩል በተለይ በጥርጣሬ እየታየ መምጣት እና ሳልቫኬር ከኢትዮጵያ ይልቅ ለጋንዳ ያላቸው እምነት እየበለጠ መምጣቱ ተደማምሮ መታየት የሚወደውን ኢህአዴግን መታያ ስፍራ አሳጥቶታል፡፡

ከዚህ ሁሉ የተነሳ በምዕራባዊያን ዘንድ ተፈላጊነቱ መቀዛቀዙ የሚገባው ህወሃት/ኢህአዴግ ዛሬ ዋና ሰው ዶ/ር ቴድሮስ በምዕራባዊያን ለሚዘወር አለማቀፍ ተቋም ዋና መሆናቸው ትልቅ ባይሆንም ትንሹን አተልቆ ማየት የሚፈልገው ኢህአዴግ እንደመፅናኛ ሊወስደው፤እየሰለለ የመጣው ከምእራባዊያን ጋር ያስተሳሰረው ገመድ ማፋፊያ አድርጎ ሊቆጥረው ይችላል፡፡

“ነብይ በሃገሩ አይከበርም” እንደማለት?

የዶ/ር ቴድሮስ ለዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መመረጥ ጉዳይ የበሰለው ሰውየው አፍሪካን ወክለው የሚወዳደሩ ብቸኛ እጩ የመሆኑናቸውን ነገር የሃገራቸው መንግስት አይገቡ ገብቶ እንዲሰምርላቸው ሲያደርግ ነው፡፡ ህወሃት መራሹ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ሲያደርግ መታየት ያለበት (ዞሮ ዞሮ ወደ ህወሃት የስነ-ልቦና ጉዳይ የሚወስደን) ነገር “ለምን ዶ/ር ቴድሮስን?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዶ/ር ቴድሮስ ለዓለም አቀፉ ተቋም መሪነት በሚወዳደሩበት ወቅት የሃገራችን የጤና ሚኒስትር አልነበሩም፡፡ ሰውየው ውድድራቸውን በሚያጧጡፉበት ወቅት የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ይመራ የነበረው በዶ/ር ከሰተብርሃን ከዛም ፕ/ሮ ይፍሩ ብርሃኑ ነው፡፡ በተለይ ፕ/ሮ ይፍሩ ከበድያለ የትምህርት ዝግጅት እና ሰፋ ያለ በጤናው ዘርፍ ምርምር የመስራት፣የጥናት ወረቀቶችን በማሳተም፣የጤና ፖሊስ አቅጣጫዎችን የማሳየቱ ጠብሰቅ ያለ ልምድ ያላቸው፣በቁጥር ትቂት የሆነውን የህክምና የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙ፣በሰው ፊት ቢቀርቡም የማያሳፍሩ ምሁር ናቸው፡፡ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ መማሪያ ሆስፒታል በሚያስተምሩበት ወቅት በብዙ ታካሚዎች ዘንድ የሚወደዱ፣ የግል የህክምና ክሊኒክ መክፈት እንኳን የማይፈልጉ በምትኩ ከማስተማር የተረፈውን ጊዜያቸውን ሁሉ በዚሁ ሆስፒታል ሆነው ደሃውን ህዝብ የማገልገልን መልካም እድል መርጠው የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ሰውየው ከህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ጋር የመስራት ፍላጎቱ ካላቸው አይቀር ቀደም ብለው ወደ ሴክተሩ መምጣት የሚገባቸው ሰው ነበሩ፡፡

ፕ/ር ይፍሩ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነቱ አስተዳደራዊ ስራ እንግዳ ስለሆኑ ለ WHO መሪነት አልታጩም ቢባል እንኳን ከእርሳቸው ቀደም ብለው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መስሪያቤቱን የመሩት ዶ/ር ከሰተብርሃን ለውድድሩ ለመታጨት ምን አነሳቸው? ዶ/ር ከሰተብርሃን ከዶ/ር ቴድሮስ በተሻለ በጤናው መስክ ቀጥተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ሰው መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ ኢትዮጵያን የመወከል ነገር ከሆነ እሳቸውም ቢያንስ በሃገር ውስጥ ከቴድሮስ ጋር መወዳደር ነበረባቸው፡፡ ዶ/ር ቴድሮስ የመጨረሻው እጩ የሆኑት በሃገር ውስጥ ባሉ ባለሙያዎች መካከል የተሻለውን ለመምረጥ ውድድር ተደርጎ መሆን ነበረበት፡፡ ሆኖም ዶ/ር ቴድሮስ ብድግ ተደርገው ኢትዮጵያን ወካይ ብቸኛ ምጡቅ ሰው የተደረጉበት ስየማ መለኪያው ምን እንደሆነ፣እነማን መራጭ ሆነው፣ በምን መለኪያ ከማን ጋር ተወዳድረው የተደረገ እንደሆነ ስለማይታወቅ ያው ህወሃትነታቸው ከብዙ እውቀት ተቆጥሮላቸው ነው ለማለት ያስገድዳል፡፡

በህወሃቶች ዘንድ ምጡቅ እንደሆኑ የእውቀት ጢቅነታቸው ነገር በሰፊው የሚነገርላቸው ዶ/ር ቴድሮስ በተግባር ሲመዘኑ እንዴት እንደሆኑ በጤና ጥበቃ ሚኒስትርነታቸው ወቅት ስላደረጉት ክፉ በጎ ስራ በጥናት ተደግፈው የወጡ መረጃዎች ስላሉ እዚህ መተረክ አስፈላጊ አይሆንም፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስርትርነታቸውም ወቅት እነ አክሊሉ ሃብተወልድን የመሰሉ ሰዎች ተቀምጠውበት የነበረው ወንበር በጣም ሰፍቷቸው እንደነበረ ማሳያው ብዙ ነው፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያ ብቅ ብለው በነበረበት ወቅት ኦባማን ፎቶ ለማንሳት ሞባይላቸውን ወድረው ከጓዶቻቸው ለመቅደም ሲሳመጡ የሚያሳየው ፎቶ ስለ ዶ/ር ቴድሮስ ብዙ ይናገራል፡፡ በአረብ ሃገር ወገኖቻችን የት ወደቃችሁ የሚላቸው ጠፍቶ በነበረበት ሰዓት አንድ የረባ የሚመዘገብ ስራ ሰርተው እንዳላሳዩ ግልፅ ነው፡፡ በግብፅ ወንድሞቻችን ቢለዋ ሲያፏጭባቸው ዶ/ር ቴድሮስ ‘ቆይ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ላጣራ’ ሲሉ እቃ ወድቆ የተሰበረባቸውም ሳይመስሉ ነበር፡፡

የውጭጉዳይ ሚኒስትርነቱ ወንበር ከብዶ እንዳንገዳገዳቸው ዶ/ር መረራ ጉዲና ላለፈው ምርጫ ክርክር ቢጤ ሊያደርጉ በተገኙበት ወቅት በደንብ ተናግረውታል፡፡ ይህ የዶ/ር መረራ ንግግር በቦታው ሊከራከሩ የተገኙትን ዶ/ር ቴድሮስን ክፉኛ አስደንግጦ በራስ መተማመናቸውን የተፈታተነ፣ የወንዛቸውን ልጆች የህወሃት አባላትንም ክፉኛ እንዳስቆጣ ያስታውቅ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ብዙ በማይጨክንባቸውን ዶ/ር መረራ ላይ ጥርሱን የነከሰውም ያኔ ይመስለኛል፡፡ ህወሃቶች የዶ/ር ቴድሮስን ለወንበር ብቁ አይደሉም መባል የሚወስዱት እንደ ህወሃትን የማዋረድ ሴራ እንጅ ያለ የነበረ የምርጫ ክርክር ወግ አይደለም፡፡ ስለሆነም ዶ/ር ቴድሮስን ለዚህ ቀርቶ ለሌላ (ለአለም አቀፍ መድረክ) መሆን እንደሚችሉ አሳይቶ ፣ የህወሃትን ስም ከፍ ከፍ ማድረግን ስለሚሹ በሃገሪቱ ሌላ ሰው የሌለ ይመስል ምንም አይነት ውድድር ሳይደረግ፣ ቴድሮስን አንጠልጥለው ለአምባገነኖች ማህበር (ለአፍሪካ ህብረት) አቅርበው በአንድ አፍ የአፍሪካ ወኪል አድርገው የፈለጉትን አገኙ፡፡ ይህ ሲሆን የዶ/ር መረራ ክርክርም ሆነ ሌሎች ስለ ዶ/ር ቴድሮስ ሳንካ መረጃን ተንተርሰው የሚናገሩ አካላት “የሃገራቸውን ነብይ እንደማያከብሩ” አላዋቂዎች፣ባንዳዎች ተደርገው እንደሚቆጠሩለት ያስባል- በደስታ ሊሞት የደረሰው ህወሃት!

መስከረም አበራን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል ፤ e-mail meskiduye99@gmail.com

____
መረጃዎችን በማህበራዊ ድረገጽም ለማግኘት ቦርከናን ፌስ ቡክ ላይ ላይክ ያድርጉ። ይሄንን ይጫኑ

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here