(በመስከረም አበራ;e-mail meskiduye99@gmail.com )
‘በደሜ በላቤ ደማቅ ታሪክ ፀፍኩ’ ባዩ ህ.ወ.ሃ.ት ለመንገዴ መቅናት ምክንያቱ የትግራይ ህዝብ አጋርነት ነው ይላል፡፡ ይህ ግማሽ እውነት ነው፡፡በህወሃት ጥላስር ይታገሉ የነበሩት ትግሬዎች ብቻ አልነበሩም፡፡የቀድሞው የህወሃት ታጋይ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እንደሚናገሩት ስሙ አይነሳም እንጅ ከህወሃት መስራቾች አንዱ ጎንደሬ አማራ ነው፤ሰውየው በአሁኑ ወቅት በሽተኛ እና ችግረኛ ሆኖ አንዳንዴ ቤታቸው እየጠሩ እንደሚያስታምሙትና እንደሚያሳክሙት በአንድ ወቅት መስክረው ነበር፡፡በቅርቡ እንደሰማሁት ይህ ሰው በቂ ህክምና እንኳ ሳያገኝ ህይወቱ እንዳለፈ አንብቤያለሁ፡፡
ከደርግ ግፈኛነት የተነሳ ህ.ወ.ሃ.ት የሚለውን ስም እንደከልካይ ሳይቆጥር ትግሬ ያልሆነ ኢትዮጵያዊም የህወሃት አባል ሆኖ ደርግን ተፋልሞ ነበር፡፡ህ.ወ.ሃ.ቶች ግን ይህን ማንሳት አይፈልጉም፡፡ከዚህ ይልቅ መላው ኢትዮጵያዊ ከደርግ ተፋልሞ ነፃነቱን ላቀዳጀው የትግራይ ህዝብ ባለ እዳ እንደሆነ፣የትግራይን ህዝብ ቤዛነት እና ጀግንነት በአንደበታቸውም በድርጊታቸውምያስተጋባሉ፡፡ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት “ኢንዶውመንት” በሚል የዳቦስም ትግራይን የፋብሪካ መክተቻ ማድረጉን ተያያዙት፡፡ ‘ምነው ይህ በረከት ለሌላው የኢትዮጵያ ምድር ቢደርስ?’ የሚል ከተገኘ መልሱ ‘የትግራይ ህዝብ በጦርነት የተጎዳ ጀግና ህዝብ ስለሆነ ይህ አይበዛበትም፤ተራ ቅናታችሁን ትታችሁ የትግራይን ልማት ሬት ሬት እያላችሁም ትቀበሉታላችሁ’ የሚል ነበር፡፡ይህን የሚሉት ስለ “እውቀት ጢቅነታቸው” በጀሌ ካድሬዎቻቸው ማህሌት የሚቆምላቸው አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ የአቶ መለስ ጉድ የተባለ “ጥልቅ እውቀት” ጀግንነት በዘር የሚተላለፍ ቡራኬ አድርጎ ለማቅረብ የማያፍር ነው፡፡ እርሳቸው የወጡበትን ዘውግ ልዩ የሆነ የጀግንነት ቅመም እንዳለው ከአንድም ሁለት ሶስቴ በአፋቸው የተናገሩት አቶ መለስ በተግባራቸው ያደረጉት በአፋቸው ካወሩት እጅግ ዘለግ ያለ ነው፡፡
የኢፈርት እና ደጀና “ኢንዶውመንቶች” ነገር..!
አቶ መለስ የሚመሩትን መንግስት ዋና ዋና ወታደራዊ እና የሲቪል ስልጣን ለወንዛቸው ልጆች ካደሉ በኋላ ለወጡበት ዘውግ ይገባል ያሉትን ሁሉ ከማድረግ እጃቸውን አልሰበሰቡም፡፡ኢፈርት የተባለውን አደናጋሪ እና ሚስጥራዊ የንግድ ኩባንያዎች ባህር አቋቁመው ሚስታቸውን (ያለ አቅሟም ቢሆን)ይህን የፋብሪካ ባህር እንድታስተዳድር ሰየሟት፡፡ወ/ሮ አዜብ ወደ ኢፈርት ቁንጮነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት አዛውንቱ ስብሃት ነጋና ሌሎች ትግራዊያን ኢፈርትን ዘውረዋል፡፡የኢፈርት ፋብሪካዎች ወደ ሰማኒያ የሚደርሱ ሲሆኑ አንዱም “በስህተት” እንኳን ከትግራይ ውጭ አልተገነባም፤ከትግራይ ባልሆነ ኢትዮጵያዊም ተዳድሮ አያውቅም፡፡በአንፃሩ ፋብሪካዎቹ የሚያመርቱት ሸቀጥ በመላ ሃገሪቱ ይራገፋል፣ወደባህር ማዶም ይሻገራል፡፡የፋብሪካዎቹ በአንድ ቦታ መከማቸት ከትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት አንፃር ሲታይ ፋብሪካዎቹ ‘በስኩየር ኪሎሜትር ስንት?’ ተብለው ሊቆጠሩ ምንም ያልቀራቸው ያስመስላል፡፡ የኢፈርት በትግራይ ብቻ መከተም፣በትግራዊ አስተዳዳሪዎች ብቻ መተዳደር ጉዳይ በጣም እያነጋገረ ባለበት ሁኔታ ደግሞ ሌላ ወንድም “ኢንዶውመንት” በእዛው ክልል በቅርቡ ተመስርቷል፡፡የዚህ ምክንያቱ የኢፈርት ኩባንያዎች መበራከት አለቅጥ ሰፍቶ ለአስተዳደር አመች ወደ አለመሆን ግዝፈት በመድረሱ ሌላ ኢንዶውመንት እንዳስፈለገ ወ/ሮአዜብ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡የኢፈርት ግዝፈት ሊያመጣ የሚችለውን አስተዳደራዊ ውስብስቦሽ ለመታደግ “ደጀና” የተባለ ትግራይ ከታሚ ኢንዶውመንት በዚህ ከሶስት አመት አካባቢ በፊት ተቋቁሞ እነ አበርገሌን አይነት ኩባንያዎች አቅፎ ልማቱን እያሳለጠ እንደሆነ ሰርክ ይወራል፡፡ አዲሱ ደጀና ኢንዶውመንት ከአስር በላይ ኩባንያዎች በስሩ አቅፎ ታላቁን ኢፈርትን ለመፎካከር ድክ ድክ እያለ ነው፡፡
እነዚህ ኢንዶውመንቶች ከትርጉማቸው ጀምሮ ባለቤትነታቸው፣ኦዲት ያለመደረጋቸው ጉዳይ፣ በአንድ ክልል(በትግራይ) ብቻ እንዲከትሙ ያደረጋቸው ምስጢር ወዘተ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የሚያስቆጣ ጥያቄ እየሆነ ከመጣ ዋል አደር ብሏል፡፡የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት እነዚህ ፋብሪካዎች ኦዲት የማይደረጉበት፣የኦዲት ሪፖርታቸውም የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት ለሆነው ፓርላማ የማይቀርብበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ተገቢ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ለዚህ የአቶ መለስ መልስ ‘እነሱ እኮ ኢንዶውመንቶች ናቸው ግልፅ ሪፖርት ማቅረብም አይጠበቅብንም’ የሚል የተለመደ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡ አቶ ተመስንም የዋዛ አይደሉምና “ኢንዶውመንት” የሚለውን ቃል ትርጉም በአማርኛ ሆነ በኦሮምኛ በአፋርኛ ሆነ በትግርኛ በፈለጉት ቋንቋ ተርጉመው እንደዚህ አይነኬ የመሆኑን ሚስጥር ያስረዱን” ሲሉ ቢወተውቱም አቶ መለስ በማስቀየስ እንጅ መልስ በመመለስ ስማይታሙ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡የሆነው ሆኖ “ኢንዶውመንት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአብዛኛው የኮርፖሬት ፈንዶችን ለመግለፅ የሚያገለግል ፅንሰሃሳብ ነው፡፡ከሌሎች የንግድ ማህበሮች በተለየ ከኢንዶውመንት ኮርፖሬት ፈንዶች የሚገኝ ትርፍ ተመልሶ ለልማት የሚዉል እንጅ ለባለቤቶች የሚከፋፈል አይደለም፡፡ የአቶ መለስ “ኢፈርት እኮ ኢንዶውመንት ነው” የሚለው መልስም ትርፉ መልሶ ለሌላ ልማት የሚውል ነው ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህ በግልፅ ኦዲት ካለመደረግ ጋር የሚያገናኘው ነገር በበኩሌ አይገባኝም፡፡
የኢንዶውመንቶቹን ባለቤትነት በተመለከተ የኢፈርት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአንድ ወቅት ‘ኢፈርት በተዘዋዋሪ የትግራይ ህዝብ ነው’ ሲሉ ሰምቻለሁ:: ‘በቀጥታስ ባለቤቱ የማን ነው?’ የሚለው እስከዛሬ ሚስጥር እንደሆነ አለ፡፡ ለጊዜው በግልፅ ወደ ተነገረን ተዘዋዋሪው ባለቤት የትግራይ ህዝብ እና የኢፈርት መስተጋብር ስንሄድ ኢፈርትን የሚያክል የፋብሪካ ባህር በትግራይ ብቻ እንዲንጣለል ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ማለፍ አይቻልም፡፡ ህወሃት እንደሚለው ኢፈርት እና ደጀና በትግራይ የከተሙት የትግራይ ህዝብ ወኪል የሆነው ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያፈራውን ገንዘብ ለቆመለት ህዝብ ልማት ማዋል ስላለበት ነው፡፡እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ አንደኛው ለህዝብ ነፃነት የታገለው ህወሃት ምን ሰርቶ ይህን ያህል ገንዘብ አፈሰ? ጠመንጃ ተሸክሞ መባተልን የሚፈልገው የትጥቅ ትግል ሲራራ ንግድ አይደለምና ጥሪት አስቋጥሮ የኩባንያ ባህር ማቋቋም ያስቻለውስ እንዴት ነው? ገንዘቡ በትጥቅ ትግል ወቅት የተገኘነው ከተባለስ የትጥቅ ትግሉ የተካሄደው በትግራይ ብቻ አልነበረምና ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ ኢፈርት ያሉ ባለግዙፍ ኢንዶውመንቶች ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡
የትግሬነት እና ህወሃትነት ልዩነት ትርክት ሳንካዎች
በሃገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እንደ የትግራይ ህዝብ እና የህወሃት መስተጋብር ያለ ግራ አጋቢ፣ ብዙ እንደማነጋገሩ ፈር የያዘ መልስ ያልተገኘለት፣ለትንታኔ አስቸጋሪ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ህወሃት የኢህአዴግ ልብ ሆኖ ሃገሪቱን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሲዘውር ከፊት የሚያሰልፋቸው ዋና ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች ከትግራይ የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ነገር ህወሃት ለሁለት ጥቅም ያውለዋል፡፡ አንደኛው የወንዙን ልጆች በወሳኝ ቦታዎች ኮልኩሎ ከውልደቱ ጀምሮ የተጣባውን የዘረኝነት ዝንባሌ ያፀናበታል፡፡ በሁለተኛ እና በዋነኝነት የትግራይን ህዝብ ደጀን ለማድረግ ልቡን ማግኛ መንገድ አድርጎ ያየዋል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ለተመለከተ ለህወሃት ሁለቱም የተሳኩለት ይመስላል፡፡ለዚህ ማሳያው የህወሃት የሃረግ መዘዛ ፖለቲካ ከእርሱ አልፎ በመላ ሃገሪቱ ማርበቡ ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ የመተባበርም ሆነ ያለመተባበር፣ የመተማመንም ሆነ የመጠራጠር ምንጩ ሃረግ መማዘዝ ሆኗል፡፡ይህ በአንድ እናት ሃገር ልጆች መሃከል ከፍተኛ ያለመተማመን አምጥቷል፡፡ ሌላው ህዝብ እርስ በርሱ በጎሪጥ የሚተያይ ተጠራጣሪ ሲሆን የትግራይን ህዝብ ደግሞ የአፋኙ የህወሃት ጠበቃ አድርጎ የመፍራት አዝማሚያ ይታያል፡፡ይሄኔ ከላይ የተጠቀሰው የህወሃት እራሱን ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እና ያው አድሮጎ የማቅረቡ አላማ ይሰምራል፡፡ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ጋር አንድ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ምንጩ የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡በላይኛው የውትድርና ማዕረግ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከትግራይ የወጡ ሰዎች መያዙ፤ በሲቪሉ ክንፍም ቢሆን ለረዥም ጊዜ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትነት፣የሃገር ደህንነት ኤጀንሲ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣በስመ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመካሪነት የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን ማሾሩ፣ በአዲስ አበባ መስተዳድር ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የሃፊነት ቦታ የትግራይ ተወላጆች መበራከት፣ይህ ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ሲወገዝ አለመታየት ለተመልካች ትግሬን እና ህ.ወ.ሃ.ትን አንድና ያው አድርጎ ያይ ዘንድ ይገፋዋል፡፡አሁን ሃገራችን በምትመራበት የዘውግ ፌደራሊዝም ሁኔታ ህ.ወ.ሃ.ት ድርና ማግ ሆኖ መምራት የሚችለው የትግራይ ክልልን ብቻ መሆን ሲገባው የህ.ወ.ሃ.ት ሃያል ህልውና በአዲስ አበባም መስተዳድር ቢሮዎችም ሆነ አዲስ አበባ በከተመው የፌደራል መንግስትም ሚታይ የመሆኑ አደገኛ አካሄድ ለህወሃት መራሹ ኢህዴግ የታየው አይመስልም፡፡ባለሃብትነቱም ቢሆን ለሁሉም ባይሆንም ለትግራዊያኑ ብዙ ጊዜ የማይወስድ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡
ከትግራይ የሆኑ ዜጎች በስልጣን እና በሃብት ማማ ላይ በርከት ብሎ መታየት በተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚታይበትን መንገድ በሰፊው ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡መጠኑ ቢለያይም ትግሬ ሁሉ ህወሃትን ይደግፋል፤ትግሬ ሆኖ ከልቡ የህወሃትን ሁለንተናዊ የበላይነት ማብቃት የሚፈልግ ማግኘት አይቻልም የሚለው ሙግት ነው፡፡በዚህኛው ወገን ያሉ አሳቢዎች ክርክራቸውን የሚያጠናክሩት እስከዛሬ በትግራይ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቶ አለማወቁን ነው፡፡ ተከራካሪዎቹ በተጨማሪ የሚያነሱት ነጥብ ከትግራይ የሚነሱ የህወሃት ተቃዋሚዎችም ሆኑ አክቲቪስቶች እንደ ኢፈርት እና የወልቃይት ጥያቄን የተመለከተ ከህወሃት የተለያ አቋም ለማንፀባረቅ ይቸገራሉ የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል የቆሙ ተከራካሪዎች ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ ተለያይተው መታየት እንዳለባቸው አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡እነዚህኞቹ ለክርክራቸው ማጥበቂያ የሚያነሱት ሃሳብ የትግራይ ህዝብም የህወሃት ብልሹ አሰራር ሰለባ መሆን፣ሌላ አማራጭ ሃሳብ መነፈግ እና በአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ መጠለፍ፣የአብዛኛውን የትግራይ ህዝብ የድህነት ኑሮ ወዘተ ነው፡፡
የትግራይን ህዝብ እና የህወሃትን አንድነት ልዩነት በተመለከተ የሚነሱት እነዚህ ጎራዎች በየፊናቸው ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎችን አስከትለው ሲያሟግቱ የኖሩ ቢሆኑም ሁለተኛው ማለትም የትግራይን ህዝብ እና ህወሃትን ለይተን እንይ የሚለው ክርክር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡በበኩሌ የዚህ ክርክር ደጋፊዎች መመናመን አብሮነታችንን የሚፈትን፣ የትግራይን ህዝብ ስጋት ላይ የሚጥል አሳሳቢ ነገር ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የህወሃትን ጥፋት የትግራይ ህዝብም አድርጎ የማየቱ ነገር በተቻለ ፍጥነት መቀየር ያለበት ነገር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ዋነኛውን ድርሻ መውሰድ ያለበት ደግሞ ራሱ የትግራይ ህዝብ ይመስለኛል፡፡
ከትግራይ ህዝብ ምን ይጠበቃል?
ህወሃት እርሱ በስልጣን ሰገነት ላይ ከታጣ ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ እሳት ሆኖ እንደሚበላው ያስፈራራል፡፡ ቀላል የማይባለው ትግራዊም ይህን ተቀብሎ የህወሃት ወንበር የተነቃነቀ በመሰለ ቁጥር ስጋት ይወርሰዋል፡፡ይህን የአብዛኛው ትግራዊ ስጋት የሚረዳው ሌላው የሃገራችን ህዝብ ትግራዊያንን የግፈኛው ህወሃት ወንበር ጠበቃ አድርጎ ያስብና የህወሃት የግፉ ማህበርተኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ያሳያል፡፡ ይህ ህ.ወ.ሃ.ት ታጥቆ የሰራበት እና ስኬታማ የሆነ የሚመስልበት ፈለግ ነው፡፡ ይህ ነገር ግን መቆም አለበት፡፡ ነገሩን ለመቀየር ደግሞ የትግራይ ህዝብ ማሰብ ያለበት የዚህን ሁሉ መነሻ ምክንያት ነው፡፡ መነሻው የህወሃት ‘ከሌለሁ የላችሁም’ ስብከት ነው፡፡ ይህንን መመርመሩም ደግ ነው፡፡ የምርምሩ መነሻ ‘ህወሃት ሳይኖር ትግሬ አልነበረም ወይ?’ ብሎ ቀላል ጥያቄ መጠየቅ ሲሆን መልሱ ትግሬ ከህወሃት በፊት ነበረ ነው፡፡ ትግሬ ከህወሃት በፊት ከነበረ ዛሬ እኔ ከሌለሁ የላችሁም የሚለው የህወሃት ዜማ እንዴት መጣ የሚለውን ማስከተልም ተገቢ ነው፡፡የዚህ ዜማ መነሻው ብልጣብልጡ ህወሃት በመላው የትግራይ ህዝብ ስም ግን ለጥቂት ትግሬዎች የሰራው/የሚሰራው አድሎ እና ዘረኝነት ነው፡፡እንደ አሸን ፈልተው ትግራይ የከተሙ የኢፈርት እና ደጀና ኢንዲውመንት ፋብሪካዎች፣በሁሉ ቦታ ብቅ የሚሉ የትግሬ ሹማምንት፣የትግሬ ብቻ የጦር ጀኔራሎች፣ቱጃር ለመሆን የሳምንት እድሜ የሚበዛባቸው ትግራዊ ባለሃብቶች መበራከት ወደ ትግራዊያን ያጋደለው የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል ማሳያዎች ናቸው፡፡ባልበላው እዳ ላለመጠየቅ የሚወድ ትግሬ ሁሉ ይህን አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን ማውገዝም አለበት፡፡
ወደዚህ ልቦና ለመምጣት ሰፊው የትግራይ ህዝብ ራሱን በሌላው ኢትዮጵያዊ ጫማ ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ ‘እኔ ትግሬ ባልሆን ኖሮ ይህን ጉዳይ እንዴት አየው ነበር’ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር መለስ እና ደቀመዛሙርቶቻቸው ትግሬነታቸው ቀርቶ አፋር ቢሆኑና ኢፈርትን እና ደጀናን የመሰሉ የልማት ተቋማት አፋር ብቻ እንዲከቱ አድርገው፤ በአፋር አለቆች እንዲዘወሩ ቢያደርጉ፤ ይህ ሳያንስ ደግሞ የአፋር ህዝብ ለእንዲህ ያለው አስተዳደር እድሜ ሲለምን ባየው የሚሰማኝ ምንድን ነው ማለት ያስፈልጋል፡፡ከስልጣን የማይወርዱ የአፋር የመንደር ልጆች የራሳቸው ስልጣን ላይ ሙጥኝ ማለት ሳያንስ የአፋር ባለሃብቶችን የመፍጠር ፕሮጀክት ቀርፀው ሌላውን ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ ባይትዋር ቢያደርጉ ምን ይሰማኝ ነበር? የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ተብለው በፌደራል ወንበር የተቀመጡት ሰውየ የትግራይን ክልል የኢንዱስትሪ ዞን ለማድረግ እቅድ አውጥተው ነበር ተብሎ ከገዛ ባለቤታቸው ሲነገር መስማት ትግራዊ ላልሆነው ሰፊ ህዝብ ደስ የሚያሰኝ ትርጉም አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ አሁን ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚሰማውን ስሜት ለመረዳት ይበጃል፡፡
በግሌ ከትግራዊ ወዳጆቼ እና ጓደኞቼ ጋር ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስንወያይ በአብዛኛው የሚገጥመኝ ክርክር ‘ኢፈርት ትግራይ መከተሙ ለሰፊው ህዝብ ምንም የፈጠረው ነገር የለም፡፡ የፋብሪካዎቹ ባለቤት የህወሃት ባለስልጣኖች እና ዘመድ አዝማዶች ናቸው’ የሚል ነው፡፡ ይህም ግማሽ እውነት ነው፡፡ የእነዚህ ኢንዶውመንቶች ተጠራርቶ ትግራይ ላይ መከተም ለአካባቢው ሰዎች ቢያንስ የስራ እድል መፍጠሩ በሰፊው ትግራዊ መካድ የለበትም፡፡በቀጥታ የስራዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ ለከተሞች ማደግ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የፋብሪካዎቹ መኖር የመግዛት ሃይል ያለው ተከፋይ ሰራተኛ በከተሞቹ እንዲኖር በማድረግ በቀጥታ በፋብሪካዎቹ ለመቀጠር ላልቻለው ህዝብ የንግድ እድል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ይህ ሁሉ እድል ፋብሪካ በገፍ ላልተተከለለት ሌላው ኢትዮጵያዊ ያልተገኘ ነውና የእድገት ሁኔታ መዛባት ማምጣቱ ሃቅ ነው፡፡ ይህን ክዶ መነሳት የመግባቢያን ሰዓት ከማራቅ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡
ሌላው ከትግራይ ወገኖቻችን የሚገጥመኝ ክርክር ‘የህወሃት ብልሹ አሰራር የትግራይን ህዝብም መድረሻ ያሳጣ ነገር ነው’ የሚል ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡የትግራይ ለፍቶ አዳሪ ድሃ ህዝብ በመዋጮ ብዛት ፍዳውን እንደሚያይ ከቦታው ከመጡ ሁሉ የሚነገር ነው፡፡ የሙስናው ነገር፣ሌላ ድምፅ እንዳይሰማ የማድረጉ አፈና ሁሉ በትግራይም ያለ ነው፡፡ ግር የሚያሰኘው ነገር ግን የትግራይ ህዝብ አለበት የሚባለውን ግፍ በግልፅ ሲቃወም አይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ለዚህ አፈናው አያሰናዝርም የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ በበኩሌ ይህ አያሳምነኝም:: ምክንያቱም ሌላው ኢትዮጵያዊም የደረሰበትን ብልሹ አሰራር የሚያወግዘው መንግስት ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረለት ሳይሆን የደረሰበት ግፍ ብዛት አፈናውን ችላ ብሎ ድምፁን እንዲያሰማ ስለገፋው ነው፡፡ ስለዚህ የተበደለ ሁሉ በዳዮች ቀንበራቸውን እንዲያለዝቡ መጠየቁ ተፈፅሯዊ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ድምፁን አጥፍቶ አስተዳደራዊ በደሉን እንዲጋት ያደረገው ምን እንደሆነ ትክክለኛውን መረጃ ከውስጥ አወቆች ለመስማት ጉጉት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ከትግራይ የሆኑ ወይም ጉዳዩን የሚያውቁ በደንብ ቢያስረዱን የትግራይ ህዝብ ያለበትን ችግር ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡
እንደ ህወሃት አገላለፅ በትግራይ የከተሙት ኢንዶውመንት ተብየዎቹ አላማ ባመጡት ትርፍ ሌላ የልማት ተቋም በትግራይ መመስረት ነው፡፡ ስለዚህ በትግራይ ልማት ልማትን እየወለደ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ለዚህ ምስክሩ በትግራይ የሚዋለዱት የፋብሪካዎች ብዛት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ፅሁፍ ስፅፍ እንኳን በ850 ሚሊዮን ብር ግዙፍ የጠርሙስ እና የብርጭቆ ፋብሪካ በእዛው ትግራይ ሊከትም እንደሆነ ትግራዊያን መኳንንት በቴሌቭዥን መስኮት እያወሩ ነበር፡፡ ከሳምት በፊት ደግሞ የመስፍን ኢንጅነሪንግ አልበቃ ብሎ የምስራቅ አፍሪካን ገበያ ታሳቢ ያደረገ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በዛው በትግራይ ስራ ሊጀምር እንደሆን ሰማን፡፡ይህን እያየን “ላለው ይጨመርለታል” ብለን እንድናልፍ ከታሰበ የማይሆን ነው፡፡
በአንፃሩ በሌላው የሃገራችን ክልል የከባድ ፋብሪካዎች ተከላ ወሬ እንደ ሃምሌ ፀሃይ ተናፍቆም አይገኝ፡፡ ይህን እኔ ትግራዊ ሳልሆን ብሰማው ኖሮ ስሜቴ ዛሬ ትግሬ ሆኘ እንደሚሰማኝ ይሆን ነበር ወይ? ይህን የሚሰራው ህወሃት እድሜ ማጠርስ ያሳስበኝ ነበር ወይ?ይህን ጉልህ የተዛባ አሰራር እያዩ ዝም ማለትስ ይቻላል ወይ? የአንድ ሃገር ሰዎች ሆነን ሳለ ይህ ሲሳይ እኛጋ ያልደረሰው ለምንድን ነው ብሎ መሞገት ወንድም የሆነውን የትግራይ ህዝብ መጥላት ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ ደግ ነው፡፡ ህወሃቶችስ ይህን የፋብሪካ መንደር በትግራይ ብቻ እንዲከትም ያደረጉት ሊጠቅሙን ነው ሊጠቀሙብን? በዚህ ሁኔታ የምናገኘው ጥቅም ምን ያህል ቀጣይነት እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል፤ ብሎ መመርመር ከሃዲነት ሳይሆን ብልህነት ነው፡፡
የህወሃት ወንበር ሲነቀነቅ የትግራይን ህዝብ የሚያሳስበውን ያህል የብ.አ.ዴ.ን ህልውና የአማራን ህዝብ፣የኦ.ህ.ዴ.ድ በስልጣን ላይ መሰንበት የኦሮሞን ህዝብ፣የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በስልጣን ላይ መታየት የደቡብ ህዝብን፣የሶ.ህ.ዴ.ፓ እድሜ የሶማሌን ህዝብ ወዘተ ያሳስባል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡መልሱ ተቃራኒ ነው፡፡አብዛኛውን ትግራዊ የህወሃት ህልውና ክፉኛ ሲያሳስበው ሌላው ኢትዮጵያዊ እነዚህን ቆምንልህ የሚሉትን የገዥው ፓርቲ አባል/አጋር ፓርቲዎች እንደ የባርነት ወኪል አድርጎ ያያል፡፡ የእድሜያቸው ማጠር ከሚያስከፋው የሚያስደስተው በብዙ እጥፍ ይበዛል፡፡ለዚህ ከሰሞኑ በሃገራች ከተሞች ወከለናችኋል የሚሉዋቸውን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አባል ፓርቲዎች ለማውገዝ ጎዳና የወጣው ህዝብ ብዛት ማሳያ ነው፡፡የትግራይ ህዝብም እንደሌሎች ወንድሞቹ ቆምኩልህ እያለ ሌት ተቀን የሚሰብክ የሚያስፈራራውን ህወሃት ህፀፆች ለማውገዝ ማመንታት የለበትም፡፡ ‘ከሌሉ የለሁም’ የሚለውን አጓጉል አስተሳሰብ ትቶ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኖ ህወሃትን ታገስ ተመለስ ፣ካልሆነ ለሚችል ልቀቅ መለት አለበት፡፡ ይህንንም በአደባባይ ማሳየት አለበት፡፡ በተጨባጭ የሚታየውግን ሌላ ነው፡፡
ከላይ በትቂቱ ለማሳየት የተሞከረውን ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል አንስቶ በምክንያት የሚሞግት ሰው ከአብዛኛው ትግራዊያን ዘንድ የሚሰጠው ትርጓሜ ‘እንዲህ የሚያስበው ትግሬን ስሚጠላ ነው’ የሚል ሲሆን ያጋጥማል፡፡ ይሄ ደመነፍሳዊነቱ የበዛ፣ ለመሞገት የሚያስችል የእውነት ስንቅ የማጣት የሚያመጣው የሽሽት መልስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሬ ወገኖቹን ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ጀማሪ፣እጅግ ሰው አክባሪ፣እንግዳ ተቀባይ ነውና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ህዝብ የሚወድበት እንጅ ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምክንያት የለውም፡፡ልክ ያልመሰለውን ነገር ሲጠይቅ ደግሞ ‘ይህን ያልከው እኛ ትግሬ ስለሆን’ ነው ማለት የጥላቻን መንገድ መጥረግ እንጅ ሌላ ጥቅም የለውም፡፡አሳማኝ ምክንያት ሳያቀርቡ ‘የምታዩትን አድሎ እንዳላያችሁ እለፉ፤ያኔ እንደምትወዱን እናውቃለን’ ማለት አብሮነትን የሚፈትን አስቸጋሪ አቋም ይመስለኛል፡፡
ከትግራይ ህዝብ አንፃር ይህ ሁሉ ሲጠበቅ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለትግራዊ ወንድሞቹ የሚያቀርበውን ጥያቄ የሚሰነዝረው ረጋ ብሎ፣ ጥላቻን አርቆ መሆን አለበት፡፡እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት የሆነውን መዛባት ሁሉ ያመጣው ህወሃት ከትግራይ ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ ተመካክሮ አይደለም፡፡ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ወደትግራይ የሚተመው ፋብሪካ ሁሉ ሲተከል ሰፊው የትግራይ ህዝብም እንደ እኛው በቴሌቭዥን ይሰማል እንጅ የሚያውቀው የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ ‘ሌላውን ረስታችሁ ለእኔ ይህን አድርጉልኝ’ ብሎ አዞ ያስደረገው ነገርም አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከትግራዊ ወንድሞቻችን ጋር ስንነጋገር ይህን ሁሉ አስበን መሆን አለበት፡፡ ‘ህወሃት የትግራይን ህዝብ አይወክልም’ ከሚለው ሾላ በድፍን የሆነ ዘይቤ ወጥተን ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ነባራዊ ሃቆች ላይ ተመስርተን አፍረጥርጠን መነጋገር ያለብን ቢሆንም ንግግራችን ‘እኛ እና እነሱ’ የሚል ግድግዳ የተገነባበት መሆን የለበትም፡፡ ከዛ ይልቅ የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን እያሰብን፤ እንደቤተሰብ ውይይት ፍቅር እና መተሳሰብ ባልተለየው መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አሁን እያነጋገረን ያለው ጉዳይ ረዥም ዘመን ከተጋራነው ወንድማማችነት የሚገዝፍ አይደለም፡፡ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር ከስሜታዊነት የራቀ መሆን አለበት፡፡ ከስሜታችን ምክንያታችን መብለጥ አለበት፡፡ ይህ ካሆነ ዛሬ እንደቀልድ ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር ነገ የምንፀፀትመበትን ጥፋት ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ስለዚህ ጉዟችን ሁሉ ማስተዋል የተሞላበት መሆን አለበት፡፡ በፍቅር ከመነጋገር እንጅ ከጥላቻ እና ከመጠፋፋት ትርፍ ያገኘ ህዝብ የለምና ንግግራችን ሁሉ ፍቅርን፣እርጋታን እና ምክንያታዊነትን የተሞላ መሆን አለበት፡፡ይህ ካልሆነ ህወሃትን እያገዝነው እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡