spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeነፃ አስተያየትየጄነራል ፃድቃን መልሶ ልብ ማውለቅ....

የጄነራል ፃድቃን መልሶ ልብ ማውለቅ….

በመስከረም አበራ
ሰኔ 19:2009 ዓ ም

Meskerem Abera - article
Meskerem Abera
ከዕለት ተዕለት ግላዊ የኑሮ ግብ ግብ አለፍ ብሎ ለህዝብ ነፃነት፣የህይወት ለውጥ፣ መከራ ቅለት ሊታገሉ መነሳት ራመድ ያለ ማንነትን ይጠይቃል፡፡ ታግሎ ማሸነፍ ደግሞ የበለጠ ብርታት ይጠይቃል፡፡ ጀነራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ የልጅነት ዘመናቸውን በጫካ የገፉ በመሆናቸው እንዲህ ካሉት ወገን ለመመደብ የሚችሉ ናቸው፡፡ ለህዝብ ነፃነት የልጅነት ጊዜን ሰውቶ በረሃ መገኘት ከበድ ያለ ስብዕና አካል ቢሆንም በረሃ መውረዱ፣ጠመንጃ ዘቅዝቆ አቀበት ቁልቁለቱን መሮጡ በራሱ ውጤት ስላልሆነ በቂ ነገር አይደለምና ውጤቱ በምክንያት መመርመር አለበት፡፡ በረሃ የወረደ ሁሉ፤ነፍጥ አንስቶ ባሩድ ያቦነነ ባጠቃላይ፤ “ታግየ ነፃ አወጣኋችሁ” ባይ ውለታ አስቆጣሪ በነሲብ ፤ “ዘር አዝርቴ ሞቶ አቆማችሁ” ባይ ሃረግ መዛዥ በሞላ “ከተዋጋ ዘንዳ እንደፈለገ ይሁን፣ያሻውን ያጥፋ፤ ጥፋትም በጥፋት ላይ ይደራርብ” የሚባልበት ዘመን ከነበረም አልፏል፡፡ ያለንበት ጊዜ የምክንያት እንጅ የግዝት ዘመን አይደለምና ድርጊቱ ተመርምሮ መጠየቅ ያለበት ሁሉ በህግም፣በህሊናም ይጠየቃል፡፡ በአንድ ወቅት ደደቢት በረሃ ወይ ደንቆሮ ዋሻ መገኘት የተጠያቂነት ድነሽነት(Immunity) አይደለምና ጀነራል ፃድቃን እና ጓዶቻቸው ላጠፉትም ሆነ በጥፋታቸው ላይ እየደራረቡት ላለው ከቀደመው የባሰ ጥፋታቸው መጠየቅ አለባቸው፡፡

ደርግን መጣል የህግ ሁሉ ፍፃሜ፣የትክክለኝነት ሁሉ ዳርቻ የሚመስላቸው ህወሃቶች በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ያላቸው ግምት ራሳቸው ለራሳቸው ካላቸው ሚዛን ጋር በእጅጉ ይራራቃል፡፡እነሱ ራሳቸውን የኢትዮጵያ መድህን፣ምትክ አልቦ ክስተት፣መታደስ እንጅ መቀየር የሌለባቸው ምጡቃን አድርገው ሲያስቡ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ለነሱ ብቻ የሚታያቸውን ፍፅምናቸውን መሬት ላይ ፈልጎ ከማጣቱ የተነሳ ነገራቸው ሁሉ ታክቶታል፡፡ እነሱ የትም እንደ ማይሄዱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተናግረዋል፤አለፍ ሲልም ጠመንጃቸው በትከሻቸው ነው፡፡ ህዝቡም መሄጃ ስለሌለው እንዳለአለ፡፡ ህዝቡ በህወሃት/ኢህአዴግ ለሃገር የመቆም ልዕልና ላይ ተስፋ ከቆረጠባቸው ምክንያቶች አንዱ ትልቋን ሃገር ወደብ አልቦ ለማድረግ የሮጠበት የእብድ እሩጫ ነው፡፡ ወደብን ያክል ወሳኝ ነገር እንደ መርገም ‘ነገ ዛሬ ሳትሉ ከእጄ ላይ ውሰዱልኝ’ የሚል “አዋቂ” ከህወሃት ውጭ፣ከአቶ መለስ ሌላ ከየት ምድር ተፈልጎ ይገኛል? ጄሌ ካድሬዎቹ ተናግረው የማይጠግቡለት የአቶ መለስ “እውቀት ጢቅነት” ኢትዮጵያን ለባህር እጅግ ቀርባ ወደብ አልቦ የሆነች የመጀመሪያዋ የጉድ ሃገር አድርጓታል፡፡

የዓለማችን ወደብ አልባ ሃገራት(ለምሳሌ ቻድ፣ዩጋንዳ፣ፓራጓይ፣ሞንጎሊያ) ወደብ ወደማጣቱ ችግር የከተታቸው የሃገራቸው ጅኦ-ግራፊያዊ አቀማመጥ ከባህር እጅግ ርቀው ከመገኘታቸው የተነሳ ይህን እድል የሚነፍጋቸው በመሆኑ እንጅ “ነፃ አውጭዎቻቸው” ከወደዱት ጋር ፍቅር ለማፅናት በገፀ-በረከትነት ስላስረከቡባቸው አይደለም፡፡ እንደውም የእውነት የህዝብ መንግስት ያላቸው ሃገራት ድንበራቸው ለባህር ቅርብ ሳይሆን እንኳን እንደምንም ብለው ለባህር በር ባለቤትነት የሚያበቃ ኮሪደር ባለቤቶች ይሆናሉ(ለምሳሌ ኮንጎ)፡፡ የጉድ ሃገራችንን ብናይ ግን ለግመል ውሃ መጎንጫነት በታጨው አሰብ ወደብ በኩል ከባህር ያላት ርቀት አዲስ አበባ ከቢሾፍቱ(ደብረ ዘይት) የሚርቀውን ያህል ነው፡፡ስለ ወደብ ጉዳይ ጮኽው የማይደክማቸው ዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያም እንደውም ርቀቱን ‘የእግር መንገድ ያህል የቀረበ’ ይሉታል፡፡

የአሰብን ወደብ ለሃገራችን አስቀርቶም የጠናባቸውን የኤርትራ ፍቅርም አለማጣት ይቻል እንደነበር ለማሰብ ፅኑ ፍቅሩ የፈቀደላቸው ያልመሰለኝ አቶ መለስ እና ጓዶቻቸው ወደብ አስረክበው ያመጡብን ፈተና ከዚህ በመለስ የሚሉት እንዳልሆነ ከነባራዊው ህይወታችን በተጨማሪ የዶ/ር ያቆብ ኃ/ማርያምን “አሰብ የማናት?” የሚል መፅሃፍ ማንበብ ነው፡፡ የትልቁን ጉዳት ትቂት ገፅታ ለማንሳት ያህል ወደብ የሌለው ሃገር ለዓለም አቀፉ ንግድ ያለው ቅርበት በሰው እጅ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ መርፌ ምላጭ ሳይቀር ከውጭ ለሚያስመጣ ድሃ ሃገር ሁለመናውን የሚያስገባው የሚያስወጣው በሰው ደጅ ነውና ጥብቅ ሚስጥራዊነት የሚሻው የፀጥታም እና የደህንነት ጉዳዮቹ ሁሉ አደባባይ የተሰጡ ናቸው፡፡ ልመና አኮፋዳ ይዘን፣ የሰው ደጅ ላይ ቆመን የምናገኘው የእርዳታ እህል ርሃብ ለሚቆላቸው ወገኖቻችን በጊዜ እንዲደርስ የራስ የሆነ ወደብ ይመረጣል፡፡ እንደ መድኃኒት ነፍስ አድን፣ እንደ ነዳጅ አጣዳፊ የሆኑ ፍጆታዎች እንደልብ ይመላለሱ ዘንድ ማን እንደራስ ወደብ! መንግስት ባለወደቡን ሃገር ካስቀየመ የአስመጭ ነጋዴዎች ንብረት ወደብ ላይ ቀልጦ ሊቀር የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል(በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የብዙ ነጋዴ ወገኖቻችን ንብረት ቀልጦ እንደቀረ ይነገራል)፡፡

ከሁሉ በላይ ለወደብ ኪራይ የሚወጣ ገንዘብ እኛን ጎስቋሎችን ቀርቶ የባለፀጋ ሃገሮችን ወገብም የሚቆርጥ ነው፡፡አወቅኩ ባዮቹ መለስ ዜናዊ እና ጓደኞቹ እንደሚያስቡት ወደብ ገንዘብ ስላለ ብቻ እንደ በቆሎ እና ገብስ በደረሱበት የሚያፍሱት ወይ ደግሞ ከሆነ ዘመን በኋላ ትዝ ሲል ሄደው ‘አሁን የወደብ ባለቤት መሆን አለብኝ’ ብለው አፈፍ የሚያደርጉት ጥይት እንደመግዛት ያለ ርካሽ ነገር አይደለም፡፡ ረብጣ ገንዘብ ተከፍሎም እንኳን በዲፕሎማሲው መስክ ባለወደብ ሃገራትን ማባበልን፣መለማመጥን ይጠይቃል፡፡ያለአባት በሆነ ሁኔታ ደረጃችንን አውርዶ ጅቡቲን የሚያለማምጠን ይሄው ነው፡፡ ወደብ ማግኘት ቀላል እንደሆነ ሲናገር የነበረውን መለስ ዜናዊን ላሙ ኮሪደርን ለመገንባት ዙሪያ ጥምጥም ያባዝነው የነበረው ወደብ እሱ ከጫካ እንደመጣ እንዳሰበው በዋዛ የሚገኝ ነገር ባለመሆኑ ነው፡፡የሰራውን የሚያውቀው ህወሃት/ኢህአዴግ ለወደብ ኪራይ ስንት እንደሚከፍል በግልፅ ተናግሮ ባያውቅም አመታዊ ወጭው እጅን በአፍ የሚያስጭን እንደሆነ (ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል) ማንም አይጠፋውም፡፡ ይህን ለወደብ የምናወጣውን ወጭ በየትኛው የወጭ ንግድ ምርታችን በምናገኘው ዶላር እንደምናካክሰው ወደባችንን መርቆ ያስረከበውን አካል የሚያስጨንቅም አይመስለኝ፡፡

ህወሃት ከጫካው ድል መልስ ኤርትራን ካላስገነጠለ እንቅልፍ በአይኑ እንደማይዞር ‘ኤርትራን እንደመንግስት እወቁልኝ’ ከሚለው ጭቅጨቃው የተረዱት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጂሚ ካርተርም ሆኑ የአፍሪካ ጉዳይ አማካሪያቸው ኽርማን ኮህን ‘እባካችሁ ሃገሪቱን ወደብ አልባ የማድረጉን ነገር ደጋግማችሁ አስቡት’ ብለዋቸው እንደ ነበር ወቅቱን አስመልክቶ የተፃፉ መዛግብትም ያልሞቱት ኽርማን ኮህንም ምስክር ናቸው፡፡ የራሳቸው የኢኮኖሚክስ ህግ ያላቸው አቶ መለስ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበራቸው መልስ ‘ወደብ ያለመኖር በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ የለውም’ የሚል እብሪት አይኑን የጨፈነው ነበር፡፡ እሽ የኢኮኖሚው ይቅርና በሃገር ደህንነት ላይ ያለው ተፅዕኖስ ምንድን ነው ተብሎ ታስቦ ይሆን?

በወቅቱ ይህን ጥያቄ ለመጠየቅ ዛሬ መልሰው ልብ የሚያደርቅ ክርክር እያመጡ ካሉት ከጄነራል ፃድቃን እና ከሜ/ጄነራል አበበ ተ/ኃይማኖት(ጆቤ) የሚቀድም ሰው መኖር አልነበረበትም፡፡ እውነታው ግን እነዚህ ዛሬ ሆድ ሲያውቅ በሆነ ሁኔታ ደርሰው ለወደብ ደረት ደቂ የሆኑ ሰዎችም ከአቶ መለስ የተለየ ነገር እንደሌላቸው ነው፡፡ነበረን ቢሉ እንኳን ዛሬ ላይ ይሄን ቢያወሩ ማሞ ቂሎን ካልሆነ ማንንም ሊያሳምኑ አይችሉም፡፡ አቶ መለስ በዚህም አያበቁም የአሰብን ጉዳይ የሚያነሳ ሰው ‘የሃገር ሉአላዊነት የማይገባው ተስፋፊ ነውና ብቻውን እንደሚያወራ ይቆጠራል’ ይሉ ነበር፡፡

እውነት ለመናገር አቶ መለስም ሆኑ ጓዶቻቸው ወደቡን መርቀው ያስረከቡት ጆቤ በቅርቡ (ለእኔ ቀልድ በመሰለኝ ሁኔታ) እንዳሉት የወደብ ጥቅም እጅግም ስለማይገባቸው ሳይሆን እንዲገባቸው ስላልፈለጉ ነው፡፡ ከህዎሃቶች ብዙ አደናጋሪ ባህሪያት በጣም የሚገርመኝ መልሰው መላልሰው ራሳቸውን ብቻ ማዳመጥ የሚወዱበት ይሉኝታ የራቀው ልማድ ነው፡፡ እነሱ የፈለጉት፣ እንዲሆን የወደዱት ነገር ሁሉ ለሌላው ሰውም ትርጉም የሚሰጥ/መስጠት የሚገባው እውነት እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ያሰቡትን አስተሳሰብ ስሁትት እየተነገራቸውም ጆሮው ላይ ሄድ ፎን ሰክቶ እንደሚዘል ዲጄ በዛው ሙዚቃ ይደንሳሉ እንጂ የሰውም ሃሳብ ለመስማት ጆሯቸውን ሳያዘነብሉ ጎልማሶቹ አረጁ፤ያረጁት ባሰባቸው፡፡ይሄ አንድም ለእውቀት ርቆ መቆም ሁለትም ሰው ንቀት ሶስትም “መተኮስ ደጉ” ያመጣው ማናለብኝነት ነው፡፡

ሰሞኑን ጄ/ፃድቃን ፍፁም ብርሃነ ከተባለ ጋዜጠኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ሃገራችን በቀይ ባህር አካባቢ የነበራትን ህልውና መልሳ ማምጣት አለባት ብለዋል፡፡ ቀጥተኛ፣ቅን እና የሰውን ግንዛቤ ዝቅ ባላደረገ መንገድ መልስ እንደሚሰጡኝ ተስፋ በማድረግ በዚህ ንግግራቸው ዙሪያ እና አጋጣሚውን በመጠቀም ስለ በእርሳቸው እና የ1993 ስንጥቃት ጓዶቻቸው ዙሪያ ያሉኝን አንዳንድ ጥያቄዎች ላንሳ፡፡

የመጀመሪያው ጥያቄየ እናት ድርጅትዎ ህወሃት ኤርትራን ነፃ ማውጣትን ከትግል ግቦቹ እንደ አንዱ አድርጎ አንግቦ አስራ ሰባት አመት ተዋግቶ፣ ኤርትራ ቀይ ባህርንም ጠቅልላ ነፃ ሃገር ከሆነች ሃያ ስድስት ክረምት እና በጋ ካለፈ በኋላ ዛሬ ብድግ አድርጎ በቀይባህር ላይ የኢትዮጵያን ጠንካራ ህልውና ያስመኘዎት ምን ጥብቅ ጉዳይ ቢገጥምዎ ነው?

ሁለተኛ ቀይባህር የሚገኘው ኤርትራን አልፎ እንደሆነ መቼም አያጡትም፡፡እናት ፓርቲዎ ህወሃት የኤርትራን ሉዓላዊነት መንካት ቀድሞ የሚያጣላው ከእኔው ጋር ነው እያለ ሲያስፈራራ እንደኖረም ለእርስዎ አይነገርም፡፡ ከሌላ ጥቃት የሚጠብቀውን የኤርትራን ሉአላዊነት ራሱ አይነካውምና ኤርትራን ሳይነኩ በቀይባህርን ዙሪያ የኢትዮያን ጠንካራ ህልውና መመስረቱ እንዴት ይሆናል ብለው አሰቡ?

ሶስተኛ የኤርትራ ግዛት እንዳልሆነ በደንብ የሚታወቀውን፣ በደርግ ዘመንም በኤርትራ ውስጥ ሳይሆን በራሱ ራስ ገዝ በሆነ አስተዳደር ሲተዳደር የነበረውን አሰብ ወደብ ያለበትን ክልል የኤርትራ ነው ብሎ የመስጠቱ፣ቀይ ባህርም ሆነ ኤርትራ የኢትዮጵያ ግዛት ሆነው አይውቁም የሚለው ህወሃት አካል የነበሩ እንደመሆንዎ መጠን ዛሬ በጣም ከረፈደ በኋላ ቀይ ባህርን ለኢትዮጵያ ለመመኘት ሌላው ቢቀር ከሞራል አንፃር ተገቢው ሰው ነኝ፤የኢትዮጵያ ህዝብም ንግግሬን ይቀበልና ያምነኛ ከዚህ ሃሳብ ጎን ቆሞም ለስምረቱ ይሰራል ብለው ያስባሉ?

ኤርትራ ከተገነጠለች ብዙ አመታትን ማስቆጠሯ ከፊትዎ የተሰዎረ ነገር አይደለም፡፡ ሃገሪቱ የምትገኝበት ጅኦፖለቲካዊ አቀማመጥ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የአረብ ሃገራትተን ቀልብ የሚስብ ከመሆኑም በላይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ኢራን፣ሳውዲ፣የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ እና ኳታር የበላይ ተቆጣጣሪነታቸውን ለማስረገጥ የሚሻኮቱበት ቀጠና እንደሆነም አይጠፋዎትም፡፡ኤርትራ ከአመት በፊት አሰብን ለተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ እና ለሳኡዲ በኪራይ እንደሰጠች ባለማወቅም አልጠረጥርዎትም፡፡ከነዚህ ሃገራት አንፃራዊ ባለጠግነት፣ሃያልነት እና የረዥም ዘመን ቀይ ባህርን ከኢትዮጵያ ነጥቆ የአረብ ሃይቅ የማድረግ ምኞት አኳያ እርስዎ የሚናገሩለት የኢትዮጵያ በቀይ ባህር አካባቢ ተመልሶ የመጠናከር ህልም እንዴት ስኬታማ ይሆናል ብለው ነው ይህን ሃሳብ ያመጡት?

አራተኛ የሚያወሩለት የሃገራችን ተመልሶ በቀይባህር አካባቢ የመጠናከር ጉዳይ የሚከናወነው ለኤርትራ ጥብቅና በመቆም ይታወቅ በነበረው፣ከሻዕብያ ጋር ለነፍስ እየተፈላለግኩ ነው እያለ ሳይቀር የኤርትራን የነፃነት ቀን ደግሶ በሚያከብረው፣የወደብ አልቦነት ችግሩን ሁሉ በፈጠረው፣በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር ዳርቻ እንድታፈገፍግና የአለም አቀፍ ፖለቲካዊ ተፈላጊነቷ እንዲሞት ያደረገው የእርስዎ ፓርቲ ህወሃት/ኢህአዴግ መሪነት ነው ወይስ በሌላ መንገድ? በህወሃት አጋፋሪነት ከሆነ የባድመውን መጨረሻ ያየው የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም ተመልሶ እንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ የሚማገድ ነው ብለው ያስባሉ?

በመጨረሻም ከላይ ካሉት ጥያቄዎቼ ለየት ያለ ነገር ላንሳ፡፡ እንደሚታወቀው ህወሃት/ ኢህአዴግ የምር የተጣላቸውን የቀድሞ ጓዶቹን ምን እንደሚያደርግ ከታምራት ላይኔ እስከ መላኩ ፋንታ፤ ከአቶ አንዳርጋቼው ፅጌ እስከ አቶ ኦኬሎ አኳይ ድረስ የደረሰባቸውን የምናውቀው ነው፡፡ እርስዎ እና የህወሃት ስንጥቃት ጓዶችዎ ግን ከህወሃትጋር ከፉ የሚመስል ጠብ ተጣልታችሁም በሃገራችሁ እንደፈለጋችሁ እንድትወጡ እንድትገቡ እርስዎማ ጭራሽ ነግደው እንዲያተርፉ ሆነዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ለምን ይመስልዎታል? ለእርስዎ እና ለሜ/ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት በተለይ የተደረገው የህወሃት ተፃራሪን የመታገስ ያልተለመደ ባህሪ ለአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ(ያለበት እንኳን በውል ለማይታወቀው) እና ሌሎች የኢህአዴግ የቀድሞ ጓዶች የአሁን ፀበኞች ሲደገም ያልታየው እንዴት ነው? ይህን የምጠይቀው ለናንተ የዘነበው የህወሃት/ኢህአዴግ የምህረት ዝናብ ለሌሎች ወገኖችም እንዲያካፋ ከመመኘት በተነሳ ነው፡፡

በመጨረሻም በሰሞኑ ንግግርዎትን በተመለከተ በእርስዎ በኩል ያትን ነገሮች ጥያቄዎቼን ተንተርሰው ያስነብቡናል ብየ ተስፋ በማድረግ በራሴ በኩል የሚታዩኝን ነገሮች አንስቼ ላብቃ፡፡ እርስዎና ጓዶችዎ ሌላውን ለጊዜው እንተወውና ቢያንስ ኢትዮጵያን በታሪኳ አይታው በማታውቀው መንገድ የባህር በር አልባ ሃገር በማድረጉ ጉልህ ስህተት የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ስራ መስራታችሁ ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ ስህተት ማንም ይሳሳታል፡፡ እንዲህ እንደ ነጭ ፈረስ የጎላ ስህተት ግን እንደ እናንተ ፓርቲ በብልህነቱ ብዛት ደርግን መጣሉን መሽቶ እስኪነጋ ከሚተርክ፣ሁሉን አወቅ ነኝ ከሚል አካል የሚጠበቅ አይደለምና ለይቅርታ ይቸግራል፡፡ ይቅርታ መጣም አልመጣ ስህተትን ማመንም አንድ ነገር ቢሆንም ስህተትን ለማመን እና ለማረም እሩብ ምዕተ አመት መጠበቅም እንዲሁ የቅንነት አይደለምና ተቀባይነቱ የማይታሰብ ነው፡፡ በተለይ አሁን በሚያነሱት ጉዳይና ባነሱበት የጊዜ ሁኔታ የሃሳቡን ቅንነት ለመቀበል ይቸግራል፡፡ ያጠፋሰው (ያውም እንዲህ ከይቅርታ በላይ የሆነ ጥፋት) ያጠፋው ጥፋት ከይቅርታም፣ ከእርምትም ድንበር አልፎ እንደማይሆን ከሆነ በኋላ እንዲህ እንደ እርስዎ ተዝናንቶ መናገር ሰው ንቀት ይመስላል፤ ለሽንገላ እና ለበጣም ይቀርባል እንጅ ምንም ትርፍ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የወደቡ ነገር ከሆዱ ያልወጣ፣ መቼም ቀብሮት የማይገባው ጉዳይ ቢሆንም በእርስዎ እና በጓዶችዎ አንደበት እና አሳሳቢነት ያውም ከዚህ ረዥም ዘመን በኋላ ስለወደብ መስማት ግን ጅል ተደርጎ እንደተቆጠረ ከማሰብ የዘለለ ስሜት አይሰጠውም፡፡ ለእርምትም ፣ለይቅርታም፣ለመደመጥም ፣ ለመታመንም እንደ እርስዎ ፓርቲና ጓዶች ረዥም ዘመን እና ሰፊ እድል የተሰጠው የለም፡፡ ግን ያንን አልተጠቀማችሁበትም፡፡ አሁን በተለይ ይሄን ጉዳይ በተመለከተ የሚያምርባችሁ ዝምታ ነው!

***

ጸሀፊዋን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል:: email- meskiduye99@gmail.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here