ከብሩክ አበጋዝ (ብሩክ ሲሣይ)
ነሃሴ 11 ፤ 2009 ዓ ም
አንድ ወዳጄ ከሳምንት በፊት ከዚህ ቀደም ዓፄ ቴዎድሮስን እና ዓፄ ኃይለሥላሴን ተችተህ ጽፈህ ነበር ስለ ዓፄ ምኒልክ ግን ምንም ስታወራ አይቼህ አላውቅም እሳቸውንም የማትወዳቸው ይመስለኛል አለኝ። እኔም ተሳስተሃል ማንም ሰው የሚነቀፍበት እንከን ይኖረዋል ነገር ግን ስለ እምዬ ምኒልክ የማላወራው ስለምወዳቸው ነው። እሳቸውን በተመለከተ የሆነ ነገር ጽፌ ከታች የሚሰጠውን ምክንያት አልባ ፀረ ምኒልክ አስተያየት እና ስድብ ማየት አልፈልግም ብዬው ነበር። ነገር ግን ራያን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የወሎ አካባቢዎች እና ደብረታቦር ድረስ በመሄድ በርካታ ቀናት የሚወስድ ጉብኝት እና ዳሰሳ እየተዘጋጀሁ ባለሁበት ሠዓት አርዕያችን ወዳጃችን የቀድሞው የፓርላማ አባል መሃመድ አሊ ሥለ ምኒልክ ሀሳብ እሰጥ ዘንድ ቀሰቀሰኝ እና እንደሚከተለው ሀሳቤን ሰጠሁኝ።
ብልሀተኛው ንጉሠ ነገሥት እምዬ ምኒልክ ዛሬ በሕይወት በሌሉበት ዘመን እንኳን ጠላታቸው ብዙ ነው፤ እንዲያውም በሕይወት እያሉ የዛሬውን ያክል የሚጠላቸው ሰው አልነበረም። ባለፉት 40 ዓመታት በተፈጠሩ በፖለቲካ ቅኝት በተቃኙ ታሪኮች እና ትርክቶች ስማቸው ያለ ግብራቸው ይወሳል። እውነቱን ካስተዋልነው የብዙ የዘመናችን የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች የፖለቲካ እሳቤና እና ፍልስፍና የተመሰረተው በምኒልክ እና “ነፍጠኛ” በማለት በሚጠሩት የአማራ ማህበረሰብ ላይ ባነጣጠረ ጥላቻ ነው። ባለፉት 40 እና ከዚያ በላይ ዓመታት በተደረጉ የፀረ ምኒልክ እና የፀረ አማራ ፕሮፖጋንዳ የሚታለሉ የማህበረሰባችን ክፍሎች የዛሬው ዘመን ፖለቲከኞችን የሚመዝኑበት አሁን ካለው ዘመን የፖለቲካ ጠቀሜታነታቸው እና ሕዝባዊ የሆነ ጠቃሚ ሀሳባቸው ሳይሆን ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክን በተመለከተ በሚናገሩት የጥላቻ ንግግር እና አማራ እንዲህ አደረገን እያሉ በማላዘን እና በማልቀስ የላቁ ሆነው የሚታወቁትን ነው። ታዋቂ እና ተወዳጅ ፖለቲከኛም ሆነ አክቲቭስት ወይም ታጋይ ለመሆን ምኒልክን ያለ ግብራቸው መሳደብ፣ ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ አማራ አስተሳሰብ ማራመድ እንደ መስፈርት የሚወስዱ በርክተዋል።
ይህን ስነልቦና የተረዱትም እነ ተስፋየ ገብረአብ ኃብተጽዮን ለአለፉት በርካታ ዓመታት የዚህን የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉ ፀረ ምኒልክ እና ፀረ አማራ ታሪክ ቀመስ ምናባዊ ልብወለዶችን በመፍጠር ግን እውነት እንደሆነ አድርገው በመጻፍ እና በማሳተም ኪሳቸውን እያደለቡ ነው፤ ውዳሴውም በዚያው ልክ ደርቶላቸዋል። በዚህ ውዳሴ የተሞኙት እና ልባቸው ያበጠው ገዳ ገብረአብም ለእነዚህ ወገኖች ያለውን ንቀት ለማሳየት ለሚቀጥለው ዓመት በ50ኛ ዓመቴ “የከረዩ እና የጨርጨር አውራጃዎች አስተዳዳሪ እሆናለሁ” በማለት ከልብወለድ ጸሀፊነት አልፎ ነቢይነቱንም እየነገረን ነው። ሰውን ካልናቁ በቀር እንዲህ ዓይነት መጨማለቅ እስከማውራት ድረስ አይደረስም ነበር።
ወንድሜ መሃመድ የምኒልክን የትውልድ አካባቢ የሆነችውን ደብረ ብርሃንን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ምኒልክ ላይ የሚዘንበውን የጥላቻ ስብከት ለመሞገት እና በምኒልክ ተጠቃሚ ነው እየተባለ የሚሰበክለትን የሸዋ አማራ ከሌላው በተለዬ ምንም ዓይነት ነገር እንዳልተደረገለት እንዲያውም ከሌላው አንጻር የልማት ተሳታፊ ያልነበረ ማህበረሰብ እንደነበረ ያስረዳናል። አያይዞም ሸዋ ብቻ ሳይሆን ከዚያም አልፎ እስከ ትግራይ ድረስ ያለው ማህበረሰብ ከዚህ ያልተለየ እንደነበር ገልጾልናል። ወንድሜ Agezew Hidaruም የእሱን ሀሳብ በመደገፍ ሌላው ሳይቀር በዘመነ ኢህአዴግ እንኳን ጨቋኝ እየተባለ የሚሰበክለት የምኒልክ የትውልድ አካባቢ መሰረተ ልማት ያልደረሰበት መንገድ ያልነበረው ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ኋላ ቀር የሆነ እና በዚህም ምክንያት የብዐዴን ሰዎች እንኳን አካባቢውን የሚቃኙት በሄሊኮፕተር እንደነበር እውነታውን ገልጾታል። እዚህ ላይ የፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ሀሳብ እጋራለሁ፤ እሳቸው እንደሚሉት አብዛኞቹ የአማራ ክፍለ ሀገሮች በሸዌው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ሆነ ከዚያ በፊት በነበረው በዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጊዜ እምብዛም እንዳልታሠበላቸው እና አብዛኛው የነገሥታቱ ልማት ያተኮረው በከተማወች ላይ ሲሆን ተጠቃሚወቹም አዲሥ አበባ፣ አሥመራ፣ ሐረርና ድሬደዋ እንደነበሩ እንደ ጎጃም፣ ጎንደር እና መንዝ ያሉ የአማራ ክፍለሀገሮች ግን በፍፁም ተረሥተው እንደነበር ነው።
በእርግጥ እውነታው ሁለቱ ወንድሞቼ ከላይ እንዳስቀመጡት ቢሆንም፤ የፀረ ምኒልክ ሀሳብ አቀንቃኞች ይኼ ሀቅ አይጠፋቸውም ብዬ ሰለምገምት “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም” የሚባለውን አባባል ሁልጊዜም እናገረዋለሁ። እነዚህ አውቀው የተኙ ወገኖቻችን የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው እና አጀንዳቸው በእውነተኛ የሕዝብ መብቶች እና ጭቆና ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በፀረ ምኒልክ፣ ፀረ አማራ እንዲሁም ፀረ የኢትዮጵያ አንድነት ላይ የቆመ በመሆኑ ነው። ስለሆነም ከእያንዳንዱ የፖለቲካ ንግግሮቻቸው እና ትርክቶቻቸው የምኒልክ ነገር እና ስለ ምኒልክ አገር የማቅናት ዘመቻ ሊጠፋ አይችልም። ትግሬ ፀረ ምኒልካውያን በዓድዋ ዘመቻ ጊዜ በምኒልክ የተመራው የመላው ኢትዮጵያ ጦር በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ከመረብ ወንዝ ስለተመለሰ እና ኤርትራ ነጻ ስላልወጣች በምኒልክ ምክንያት ሁለት ትግርኛ ተነጋሪ ሕዝቦች እስካሁን ድረስ እንዲለያዩ ሆነ በማለት የፀረ ምኒልክ ሙሾቸውን ሲያወርዱ። ኦሮሞ ፀረ ምኒልካውያን ደግሞ በተቃራኒው ምኒልክ አንድ ከሚያደርገን ይልቅ ኦሮሚያን ጣልያን በቅኝ ግዛት ቢገዛት ይሻል ነበር ይላሉ።
.
እንግዲህ ትግሬዎቹ ኤርትራና ኢትዮጵያ ከምኒልክ በኋላ በኃይለሥላሴ እና በደርግ ዘመን አንድ ላይ መኖራቸውን እና በህወሓት እና በመለስ ዜናዊ ጽኑ ፍላጎት መለያየታቸውን የዘነጉት ሲሆን ፀረ ምኒልክ ኦሮሞዎች ደግሞ እርስ በእርሳቸው የማይተዋወቁ በዛሬው ጊዜ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል ሥር ያሉ ኦሮምኛ የሚናገሩ የተለያዩ ማህበረሶቦችን እና ግዛቶችን እምዬ ምኒልክ አንድ ማድረጋቸውን ይዘነጉታል። ዛሬ ኦሮሙማ፣ ኦሮሚያ ወዘተ ለሚባሉት ነገሮች እርሾው የምኒልክ የግዛት አንድነት ፖሊሲ መሆኑን ለማስታወስ አይፈልግም። እድሜ ለምኒልክ ፈጽሞ ሊተዋወቁ የማይችሉትን የሀረር ኦሮሞዎች ከሆሮ ጉድሩ ኦሮሞዎች አገናኝቷል፣ የቦረና ኦሮሞዎች ከሰላሌ፣ ከያያ ጉለሌ ኦሮሞዎች አገናኝቷል። በአፄ ምኒልክ አመራር በተደረገው አገር የማቅናት ዘመቻ አብዛኛው ዘማች የሚናገረው እና የሚግባባው በአማርኛ ቋንቋ ቢሆንም በዘር ግን ሁሉም አማራ አልነበረም፤ ትግራውያን፣ ኦሮሞዎችና ሌሎችም ተካፍለዋል። ይህን ያልኩት አገር የማቅናት ዘመቻውን እንደ ስህተት ቆጥሬ ወንጀሉን ነፍጠኛ ተብሎ ከአማራ ጋር የሚያያዘውን ድርጊት ለሌሎችም ለማካፈል እና ትክክል እንዳልሆነ ለመግለጽ ሳይሆን እውነታውን ለመግለጽ ነው። ማንም ይካፈል ማን በአገር ማቅናት ዘመቻው የተገኘው ድል የኢትዮጵያን የአንድነት ጎዳና ያመቻቸ ድል ነበር። አገሩ በመቅናቱ በምኒልክ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላ ለነበሩት ገዥዎችም ሆነ ማህበረሰብ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ለውጥ አስከተሏል። መንገድና መገናኛ ተዘረጋ፤ ትምህርት ቤቶች ተከፈቱ፣ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ታተመ፣ የመድሐኒት ማዕከሎች ተቋቋሙ፣ የእርሥ በርሥ ጦርነት ዘወትር በነበረበት አገር ሰላም ሰፈነ፣ በመላው አገር ለጉዞ አደገኛ የነበረውን የወንበዴወች ዘረፋ ቀጥ አደረጎታል።
ምኒልክ ከእሳቸው በፊት ከነበሩት ነገሥታት ይልቅ ህልማቸውን ያሳኩ እና ለኢትዮጵያ ይጠቅማሉ ብለው አቅደው የጀመሯቸውን ውጥኖቻቸውን ፍሬያቸውን ለማየት የበቁ እና የተሳካላቸው ናቸው። ለዚህ ስኬታቸውም ሰላም ወዳድ ባህሪያቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸው፣ ደግነታቸው፣ ሩህሩህነታቸው፣ ብልጠታቸው፣ በአጉል ጀብደኝነት ያልተሞሉ አገራቸውን ለማዘመን እና የሕዝባቸውን ኑሮ ለማሻሻል የሚተጉ ስለነበሩ ነው። ከንጉሠ ነገሥታቶቻችን የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክን ያክል ሩህሩህ፣ ደግ እና ብልሃተኛ የለም፤ ኃይለሥላሴም ቢሆን እንደዚያ ዓይነት ባህሪ አልነበራቸውም፤ ቀኃሥ የብልህነታቸውን እና የብልጥነታቸውን ያክል ክፋት እና ተንኮላቸውም በዚያው ልክ ነው። ይህን የምንሊክን መልካምነት ደግሞ የአገራችን ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በተለያየ ጊዜ እሳቸውን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ሰዎች የሰጡት ምስክርነት ነው።
.
ዓፄ ምኒልክ በብልሃታቸው የሰሜንን፣ የበጌምድርን እና የየጁን ሕዝብ ይሁንታ እና መልካምነት ለማግኘት ቀደም ባሉት ጊዚያት በእነዚህ አካባቢዎች ተሰሚነት እና ተጽዕኖ ከነበራቸው የወረሴህ ተወላጆች አንዷ የሆኑትን እቴጌ ጣይቱን በማግባት ከፖለቲካ መረጋጋት በላይ መካሪ እና አማካሪ ትጉህ ሚስትም አግኝተዋል። ከዋግሹም ጎበዜ ገ/መድህን ወይም ዓፄ ተክለጊዮርጊስ ተወላጆች እና የዋግ እና ከፊል የላስታ ሰዎች ጋርም መልካም ግንኙነት ለመፍጠር የአጎታቸውን የራስ ዳርጌን ሴት ልጅ ወይዘሮ ትሰሜ ዳርጌን ለዓፄ ተክለጊዮርጊስ በእናት በኩል ወንድም ለነበሩት ለዋግሹም ወልደ ኪሮስ ልጅ ለላስቴው ደጅ አዝማች ኃይሉ ወ/ኪሮስ አጋብተው በብልሀት የአካባቢውን ይሁንታ አግኝተዋል። ከዚህ ጋብቻም ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ተወልደዋል እሳቸውም በኋለኛው ዘመን ተዋናይ ነበሩ። ልጃቸውን ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክን ለንጉሥ ሚካዔል ዓሊ በማጋባት ቀደም ሲል ከወሎ ግዛት ጋር የነበራቸውን መልካም ግንኙነት አጠናክረዋል። ከዚህ ጋብቻም መጨረሻው የሚያሳዝነው አልጋ ወራሻቸው አቤቶ ኢያሱ ተገኝቷል። የዛሬዋ ወረዒሉ ከተማ በምኒልክ የተቆረቆረች መሆኑም ሊታወስ የሚገባው ነው።
.
ምኒልክ ሩህርህ እና አዛኝ ነበሩ፤ ገና በ11 ዓመታቸው በዓፄ ቴዎድሮስ በግዞት ተወስደው መቅደላ ቢኖርም እና ከዚያ ቢያመልጡም፤ የቴዎድሮስን መሞት ከወይዘሮ ወርቂት በደብዳቤ ሲደርሳቸው እጅግ አዝነው፣ ሕዝቡም እንዲያዝን በአዋጅ አስነግረው እንደነበር በወቅቱ እዚያው የነበሩት ጣልያናዊዩ አባ ማስያስ ጽፈዋል። በጦር ሜዳ ያሸነፏቸውን ባላባቶችን ከማረኩ በኋላ እንደገና ግዛታቸውን ሾመው ሸልመዋቸዋል፤ ይህ ነገር በቴዎድሮስም ሆነ በዮሐንስ ዘመን ያልተለመደ ነበር። ዓፄ ዮሐንስ በእንግሊዞች መሳሪያ የበላይ ሆነው አማቻቸውን ዓፄ ተክለ ጊዮርጊስን ገጥመው ሲያሸንፉ የዓፄ ተክለ ጊዮርጊስን ዓይኖች ተመንቅረው እንዲወጡ አድርገው፣ እጅና እግራቸውን ቆርጠው በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው እንዲያልፍ አድርገዋል። ዓፄ ዮሐንስ የቴዎድሮስን ሴት ልጅ የምኒልክ እጮኛ የነበረችውን ወይዘሮ አልጣሽን ፈልገው አስፈልገው በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል፤ ይህን ያደረጉት ገና ለገና ስልጣኔን የሚቀማ ወንድ ልጅ ትወልዳለች ብለው ነው። ከዚህ አንጻር ቴዎድሮስም ተመሳሳይ ነው፤ ወዳጁን ዋግ ሹም ገብረመድህንን ደብረዘቢጥ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ነበር የገደለው። ቴዎድሮስ በአመጽ ምክንያት ዮሐንስ ደግሞ ባልተለመደ መለኩ እምነት ለውጡ ወይም አገር ልቀቁ በማለት በወሎ ሙስሊም ወገኖቻችን ላይ ያደረሱት ጭፍጨፋ አስከፊ መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ዓፄ ምኒልክ ሆሮ ጉድሩ እና እምባቦ ላይ ከጎጃሜው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር ተጋጥመው ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ቢማረኩ በእንክብካቤ ይዘው ግዛታቸውን እና ማዕረጋቸውን ሳይቀንሱ መልሰው ሰጥተዋቸዋል። ምኒልክ አንተ ብትማርከኝ ምን ታደርገኝ ነበር ብለው ተክለሃይማኖትን ሲጠይቁት፤ እንዲያው ጃንሆይ አልዋሽወትም እገድለዎት ነበር ብሏቸዋል።
ተስፋዬ ገብረአብ የኑረቢን ማህደር በሚለው በአዲሱ ምናባዊ ልብወለዱ እሱ ግን እውነተኛ ታሪክ በሚለው ማጃጃያው ምኒልክን እና ጣይቱን 17,000 ባርያዎች ነበሯቸው ሲል የተለመደውን ቀደዳውን ጽፏል፤ ለነገሩ ተስፋዬ ቁጥሩን ፈርቶ ነው እንጂ 5 ሚሊዮን ባሪያዎች ነበሯቸው ቢል እውነት ነው ብለው የሚያጨበጨቡ እና የሚከራከሩለት እሱን ያመኑ እንዳሻቸው የሚነዳቸው የሀሰት እሰረኞች አሉለት። ይህን ያክል ቁጥር ያለው አይደለም ባሪያ ወታደር በራሱ በአዲስ አበባ ከተማ ይኖራል ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው። ይችን የባርነት ጉዳይ በፍቃዱ ዘኃይሉ አንድ ወቅት ጽፎ አይቻለሁ፤ በፍቃዱ በምኒልክ ዘመን የተሸጠች ከኦሮሞ ወገን የሆነች ባሪያን ምኒልክ እንደሸጧት አድርጎ እሳቸውን ለመንቀፍ ነበር ያወራው፤ ነገር ግን በፍቄ በምስራቅ አፍሪካ ወደር ስላልተገኘለት ባርያ ፈንጋይ እና ነጋዴ ንጉሥ አባ ጂፋር ያለው ነገር አልነበረም፤ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም በፍቄ ያስታወሳት ባሪያ ከአባ ጅፋር አገር የተወሰደች ለመሆኑ መገመት ይቻላል። እውነቱን ካወራን Slave የሚባለው የእንግሊዘኛ ቃል ትርጉሙ እኛ “ባሪያ” ከምንለው የአማርኛ ቃል የሚስተካከል አይደለም እንዲያውም ሌላ አማርኛ ፍቺ ያስፈልገዋል ብዬ አምናለሁ። ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ በእውነተኛ ስሙ Slave ብሎ ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ማለትም የጎረቤት አገር ድንበር ጥሰው እየገቡ በግድ አስገድደው እየወሰዱ ከሚሸጧቸው ባሮች በስተቀር ማለቴ ነው።
የኢትዮጵያ ባርያ ሁሌም በድሎትና ያለምንም ሀሳብና ጭንቀት ይኖራል። ጌታው ሃብታም እስከሆነ ድረስ ከአንድ ተራ ገበሬ ድንጋይ የበዛበት መሬቱን እንደ ዝንጀሮ እየቆፈረ፣ በአምባው እየኖረ፣ በመከራ ቤተሰቡን ከሚያስተዳድረው በላይ አንድ ባርያ ያለ ሃሳብ እና ጭንቀት ሁሌም ሆዱን ሞልቶ በድሎት ይኖራል። ጭሰኛው ወይም ገበሬው ዘመን በከፋ እና ምርቱ እዚህ ግባ በማይባልበት ወቅት ቤተሰቡን ለማስተዳደርና ከረሃብ ለመትረፍ ብድር በብድር ሆኖ ሲንገላታ ባሪያው ጌታው ምርት ካለበት ቦታ ገዝቶ በሚያስመጣው እህል ሆዱ እስኪቆዘር ይበላል። የኢትዮጵያ ባርያ ምንጊዜም ምንም አይነት ሃሳብ እና ጭንቀት አልነበረበትም። ሁሌም እስኪጠግብ ይበላል፣ ስራ ከሌለው ቀኑን ሙሉ ሲዞር እና ሲተኛ ይውላል። አልፎ አልፎ ሥራ ቢጤ ቢሰራም ቀስ እና ጠንቀቅ ብሎ ሰውነቱ ሳይጎዳ ወገቡን ሳይቆርጥ ነው የሚሰራው። እነዚህ ባሮች ንጉሠ ነገስቱ ዓፄ ምኒልክ በአዋጅ ባርነትን መሰረዙና ነፃ መሆናቸውን ከሁሉም በላይ ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንደሚኖርባቸው ሲሰሙ አብዮት ቀረሽ ግርግር ፈጠረዋል። አብዛኛዎቹ ጌታቸውን ጥለው ነፃነታቸውን ተቀብለው መሄዱን አሻፈረኝ ብለው ከጌታቸው ጋር በገዛ ፈቃዳቸው በባርነት ስር ወድቀው በዚያው ያለ ሃሳብ እና ጭንቀት ህይወታቸውን ገፍተውበታል።
ከዓድዋ ድል በኋላ ዌልያም ኤሊስ የተባለ ሀብታም ጥቁር አሜሪካዊ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዞ ከዳግማዊ ዓፄ ምንሊክ ጋር ተገናኝቶ ነበር፤ ከዚያም ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ ስለ ኢትዮጵያ ጉዞው ለተለያዩ ጋዜጣወች መግለጫ እና ቃለ ምልልስ ሰጥቶ ነበር። ከእነዚህ መካከል ፒተርስበርግ ፖስት የሚባለው ጋዜጣ በታኅሣሥ 17 ቀን 1904 ህትመቱ “ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ የአብረሃም ሊንከንን ታሪክ ሲሰሙ አለቀሱ” በሚል ርዕስ ከኤሊስ ያገኘውን ታሪክ በሰፊው አወጣ። ጋዜጣው “ . . . ፕሬዝዳንት አብረሃም ሊንከን ባሪያዎችን ነጻ ያወጣበትን ታሪክ ሲሰሙ ምኒልክ አለቀሱ። ይህንንም የአብርሃም ሊንከንን ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ መስማታቸውን ነገሩኝ። ምኒልክ እንባቸውን እየጠረጉ አብረሃም ሊንከንን ምን ዓይነት ትልቅ ሰው ኖረዋል በማለት አድናቆታቸውን ገለፁ ። ወዲያውም አየህ እንደ አብረሃም ሊንከን ማድረግ አልችልም፤ እሱ ብዙ ሥራ የሠራ ነው። እኔ ያደረግሁት ነገር እስከዛሬ በባርነት የነበሩ ሰዎች እንዲያው እንዲቆዩ ሆነው ከእንግዲህ ወዲያ እነኚያ ባሪያዎች የሚወልዷቸው ልጆች ግን ነጻ እንዲወጡ አውጃለሁ። ከዚህ ሌላ ምን ላድርግ? ቀስ በቀስ ሁሉንም ነጻ አወጣለሁ አሉኝ።” በማለት ከኤሊስ የተገኘውን ትረካ ጋዜጣው በስፋት አውጥቶታል።
እንግዲህ ይህ የምኒልክ ቃል እውን ሆኖ እና ፍሬ አፍርቶ የእነዚህ ባሪያ ልጆች ነጻ መውጣታቸውን እና የምኒልክ ተማሪ ቤት ተማሪዎችም እነሱ እንደነበሩ በሁለተኛው የጣልያን እና የኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ አማካሪ የነበረው አዶልፍ ፓርላሳክ ከጦርነቱ በፊት አዲስ አበባ እያለ የምኒልክን ትምህርት ቤት መምህርን አግኝቶ ትምህርት ቤቱን ካስጎበኘው በኋላ የሰማውን እና ያየውን የሀበሻ ጀብዱ በሚለው መጽሀፉ እንደሚከተለው አስፍሮታል። “የምኒልክ ትምህርት ቤት በእውነት ዘመናዊ ትምህርት ቤት ነው። ይኼ መምህር በፍፁም ልብ ንጽህና እና ደግነት ወደብዙ ቦታወች ወሰደኝ። በወቅቱ ስላለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታዎችና እውነታዎችም ብዙ ብዙ አጫወተኝ። አንድ ቀን ይኼው መምህር ከባርነት ነፃ የወጡ የጥንት ባሮች ልጆች ወደሚማሩበት የፍል ውሀ ት/ቤት ወሰደኝ። በት/ቤቱ ወደ 200 የሚሆኑ የተለያየ ቀለምና እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ተማሪዎች ይማራሉ። ት/ቤቱን በምንጎበኝበት ወቅት እነዚህ ተማሪዎች ተሰልፈው የኢትዮጵያን ሕዝብ መዝሙር ዘመሩልኝ።. . . ከዚህ በጣም አስደሳች ጉብኝት ስንመለስ በመንገዳችን ላይ ይኼው መምህር በኢትዮጵያ ስላለው የባርነት ችግር ያስረዳኝ ጀመር። ምንም እንኳን ንጉሰ ነገስቱ በልዩ አዋጅ ባርነትንና የባርያ ንግድን ቢያግዱም እስከዛሬ ድረስ ችግሩ አለ። ቀጥሎም “አየህ ጌታው የመጀመሪያው የዚህ ህግ ተቃዋሚዎች ማንም ሳይሆን ራሳቸው ባሮቹ ነበሩ።” እንዳለው ጽፏል።
በታላቅ ብርታት፣ ጽናት እና አመራር ከተጎናፀፉት ከዓድዋ ድል በኋላ በመላው ዓለም የምኒልክ አድናቂዎች በርክተው ነበር። እምዬ ምኒልክ በዓድዋ ድል አድርገው ከተመለሱ በኋላ በኢትዮጵያ ሄድ መለስ እያለ የቆየውን ፈረንሳዊ ወዳጃቸውን ሞንዶን ቪዳልሄይትን በአዲስ አበባ አገኙት እና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተላኩላቸውን የእነዚህን ከተለያየ የዓለም ክፍል የመጡትን የአድናቂዎቻቸውን የደስታ መግለጫ መልዕክቶችን የያዙ ደብዳቤዎችን አሳይተውት ነበር። ታዲያ ሞንዶን ቪዳልሄይትም ስለ ደብዳቤዎቹ ሲጽፍ የሚከተለውን ብሏል “ደብዳቤዎቹ ከዓለም ዙሪያ የተላኩና እንኳን ደስ አለዎት የሚል የደስታ መግለጫ የሠፈረባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ መልስ እንዲጻፍላቸውና ደብዳቤው ላይም የኢትዮጵያ ቴምብር ተለጥፎ በፖስታ እንዲላክላቸው ይጠይቁ ነበር። የዚህ ፍላጎታቸው ምክንያት ደግሞ ቴምብሩ ላይ የንጉሡን ፎቶ ግራፍ ለማየት ካላቸው ጉጉት የተነሳ ነበር። ከተላኩት ደብዳቤዎች አንዳንዶቹ ከአውስትራሊያ ፓስተሮች/ቀሳውስት/ የተላኩ ነበሩ። እነሱም ለምኒልክ ያላቸውን አድናቆት በክብር እንደሚገባቸው ገልጸዋል። ከቬንዙዌላ የተላኩት ደግሞ የእርስዎ ወታደሮች ለመሆን እንፈልጋለን የሚሉ ነበሩበት።”
ሞንዶን ቪዳልሄይት የጣልያን እስረኞች እና ምርኮኞች በእቴጌ ጣይቱ ይደረግላቸው ስለነበረው እንክብካቤ ሲገልጽ “እቴጌ ጣይቱ በግቢያቸው ውስጥ ባለው ሜዳ ላይ ምርኮኞቹን ይመግቡ ነበር። ጀኔራል አልቤርቶኒ ጨምሮ ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው እንደ አውሮፓውያኑ የአመጋገብ ባህል ምግቡ ጠረጴዛ ላይ ሆኖ በሰሀን አስቀርበውላቸው ይመግቧቸው ነበር። ለመመገቢያም ሹካ፣ ማንኪያ፣ የአፍ መጥረጊያ ፎጣ እንኳን ሳይቀር ከጠረጴዛው ላይ ይቀርብላቸዋል። ከዚህም ሌላ የሚጠጡት ወይን[ጠጅ] እና ከጠረጴዛው ላይ አበቦች እንዲቀመጥላቸው ተደርጓል። አንዳንዶቹ ምርኮኞች እንዲያውም እንኳን በእንዲህ ዓይነት የሚያስጎመጅ የምግብ ሥነ ሥርዓት ለመጋበዝ ይቅር እና ከመኮነኖቻቸው ጋር እንኳን ማዕድ ቀርበው አያውቁም በማለት ጽፏል።
ስለ እምዬ ምኒልክ ከዚህም በላይ ማለት በቻልን ነበር፣ ስለ እሳቸው ቢጻፍም የሚያበቃ ነገር አይደለም። እኔ እዚሁ ይብቃኝ እጅግ በጣም ስለማደንቃቸው እቴጌ ጣይቱ ግን ያልጻፍኩት እና ያላወሳሁት ሆን ብዬ ነው፤ ምክንያት አለኝ። ስለ እሳቸው የተዘጋጀ ነገር ቢኖረኝም ቅሉ ለዛሬው በዚሁ ልሰናበት።