spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትወይ አዲስ አበባ...! - ክፍል ፪ (በመስከረም አበራ)

ወይ አዲስ አበባ…! – ክፍል ፪ (በመስከረም አበራ)

በመስከረም አበራ
ጥቅምት 7 ፤ 2010 ዓ ም

Meskerem Abera - article -Addis Ababa
Meskerem Abera
የሃገራችን ፓርላማ የ2009 ሥራ ዘመኑን ሊያጠናቅቅ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት ስለሚገባው ህገ-መንግስታዊ የልዩ ጥቅም ድንጋጌ ማስፈፀሚያ የሚሆን ዝርዝር አዋጅ እንዲያፀድቅ ቀርቦለት ነበር፡፡ ፓርላማውም አዋጁን ተመልክቶ ለከተማና ቤቶች እና የህግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴዎች መርቶ እረፍቱን አድርጓል፡፡ የአዋጁ ሁለመና ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ይዞ ብቅ ያለ ነው፡፡ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክርቤት ብቻ የመከረበት፣በፓርላማ ያልፀደቀ ረቂቅ አዋጅ በሃገሪቱ ቴሌቪዥን እንዲነበብ መደረጉ አንዱ አደናጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ፓርላማው ሊያርፍ እየተንደረደረ ባለባቸው የመጨረሻ ቀናት አዋጁን እንዲያይ ማድረጉም ሌላው ግርታ ነው፡፡ የልዩ ጥቅም ድንጋጌው በህገመንግስት ከተቀመጠ ሩብ ምዕተ-አመት ያለፈው ሲሆን ዛሬ ብድግ ብሎ ዝርዝር የአፈፃፀም ህግ ለማውጣት እንዲህ ባለቀ ጊዜ የሚያባክነው ጉዳይም የማያነጋግር አይደለም፡፡

በፓርላማ ያልፀደቀን ዝርዝር ረቂቅ ህግ በቴሌቭዥን ማስነበቡ በተለይ መንግስት በጉዳዩ ላይ በሚያገኘው የፖለቲካ ትርፍ/ኪሳራ ላይ ምን ያህል ትኩረት እንዳረገ ያሳብቃል፡፡ከዕሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ ‘ልተገብረው ስለሆነ ዝርዝር የአሰራር ህግ ይውጣለት’ ሲል ለዕረፍት ሊወጣ ጥቂት ቀናት ብቻ ለቀሩት ፓርላማ አቤት ያለው ኢህአዴግ ጊዜ የማይሰጥ አጣዳፊ የትግበራ ፍላጎት አድሮበት አይደለም፡፡ ይልቅስ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ንትርክ ተደርጎ ሁልጊዜ ወጥመዱ የማይስታቸውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞችን የጎሰኝነት አክራሪ ማንነት አደባባይ አውጥቶ እሱ(ህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት) እንዴት “የተሻለ” አብሮ የመኖር መንገድ እንዳለው ለማሳየት ነው፡፡ ይህ በደንብ ተሳክቶለታል፡፡

በህገ-መንግስቱ ኦሮሚያ የተሰጣት አስዳደራዊ ጉዳዮችን ያማከለ የልዩ ጥቅም መብት ሆኖ ሳለ ‘ኦሮሚያ የሚገባት የአዲስ አበባ ባለቤትነት ነው፤ ከኦሮሞ በቀር ሁሉም እንግዳ ነውና ለባለቤቱ የኦሮሚያ ክልል የመሬት ግብር እየከፈለ፣ፀባዩን አሳምሮ፣የከተማው አስተዳደርም እንደ ማንኛውም የኦሮሚያ ከተማ ተጠሪነቱን ለኦሮሚያ ክልል አድርጎ መኖር አለበት፤አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሞያሌም፣ድሬዳዋም፣ ሐረርም የኦሮሚያ ንብረት መሆን አለባቸው’ ወዘተ የሚል ሃሳብ ይዘው እየተሽቀዳደሙ የሚያውጁ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞችን ያገኘው ኢህአዴግ ‘እሰይ ስለቴ ሰመረ!’ ማለቱ ይቀራል? ፖለቲካዊ ትርፉን በሆዱ የያዘው ኢህአዴግ ህገ-መንግስታዊ ዝርዝር ህጎቹን እንዲያወጣ ያስፈለገው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ እንዲኖራት የተቀመጠው ህገመንግስታዊው የልዩጥቅም ድንጋጌን ለማስፈፀም ያለው አምሮት እንደሆነ ነው በአደባባይ የሚያወራው፡፡ ሆኖም ህገመንግስቱ ራሱ ይህን የልዩ ጥቅም ድንጋጌ እንዲያስቀምጥ የሚያደርግ ከፕሮፖጋንዳ እና ከወቅቱ የተበድየ ሙሾ ባለፈ በቂ እና ተጨባጭ ነባራዊ ሃቅ ነበረው ወይ የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

የልዩ ጥቅሙ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ መሰረቱ ምንድን ነው?

በህወሃት/ኢህአዴግ የጠመንጃ ድል ተጠልሎ የአድራጊ ፈጣሪነቱን ቦታ የያዘው የተበድየ ፖለቲካ ታሪክ ያልፃፈውን እያነበበ የሰራው ስህተት የእርምቱን መንገድ ሩቅ አድርጎታል፡፡ የአፄ ዮሃንስ ዘውድ “ተነጥቆ” ሸዋ መግባቱ ሆድ ሆዱን የበላው የትግራይ የተወልጄ ፋኖዎች ቡድን ደደቢት ሲገባ የአባት አያት ዘውድ የመነጠቁን ዘውጋዊ ቅንዓት ሃሰት በሆነው የትግራይ ተበዳይነት የአማራ በዳይነት ሙዚቃ ቀየረው፡፡ የሚያብሰለሰወለውን ዘውድ የመነጠቅ እና የመበለጥ ቁጭት በፈረደበት የአማራ ብሄር ጨቋኝነት እና በዳይነት ልቦለድ አዳፍኖ አዲስ አበባ ሲደርስ በለስ ያልቀናውን የሁልዜ የበደል ፖለቲካ አላዛኝ ቢጤውን (ኦነግን) ጠርቶ፣ የበረሃ ጓዱን/አለቃውን (ሻዕብያን) አክሎ እንደምርኮ ምድር ተንበርክካ ያገኛትን ሃገር በጎሰኝት ቢለዋ ዘነጣጥሎ፣ የብሄረሰቦች የስጋ መደብ አስመሰላት፡፡

በ“ባልንጀራው” ህወሃት ድል አጥብቆ የተማመነው ኦነግ የኢትዮጵያን የብሄር ብልት በማውጣቱ ቀዳሚው ተሰላፊ ነበር፡፡የኦነግን እድሜ አጭርነት ቀድሞ የሚያውቀው፣ ያሰበውን ለማሳካት ደግሞ ማጎንበስን በደንብ የተካነው ህወሃትም የኦነግን ያለቅጥ ፈንጠዝያ ባላወቀ ማለፍን መረጠ፡፡ ህወሃት ስምንቱን አኑሮ አንዱን እንደሚያጫውተው የማያውቀው ኦነግ ያልተፃፈ እያነበበ የማይዘለቅ ማህበሩን በጠጅ ጀመረ፡፡ በውል የተመዘገበ ታሪክ ከሚያስረዳው በተቃራኒ “በሸዋ ነገስታት መስፋፋት የእኛ ህዝብ መብት ተገፏል፣ስለዚህ መብታችን ይመለስ ቢያንስ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ረገድ ኦሮሞ በፊንፊኔ ላይ መብቱ ይጠበቅ እንዲሁም ሃረርም በኦሮሚያ መካከል ስለሆነች በተመሳሳይ የኦሮሞ መብት ይጠበቅ” የሚል ጥያቄ ኦነግ አንስቶ እንደ ነበር የወቅቱ ዝብርቅርቆሽ ፊታውራሪ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሐምሌ 8/2009 ዓ.ም ለወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡

ይህን ሲደጋገም እውነት የመሰለ፣ የታሪክን ጉማጅ ይዞ የሚያላዝነውን፣ የኦነግ የተበድየ ተረክ መናነት ባለፈው ዕትም ላይ ለማሳየት ስለሞከርኩ አሁን ወደዛ ጥልቅ ታሪካዊ ጉዳይ መግባት አልፈልግ፡፡ ሆኖም በኋላ የመጣውን እና ከፊተኞቹ የኦሮሞ ተስፋፊዎች አንፃር እዚህ ግባ የማይባለውን የሸዋ ነገስታት ተስፋፊነት በዓለም ላይ ተደርጎ እንደማያውቅ ትልቅ በደል ጠቅሶ፣በማይሆን ሁኔታ አዲስ አበባን በካሳነት ለመቀበል የመከጄሉ ሙከራ የስህተቱ ሁሉ መሰረት ስለሆነ ሳያነሱ ማለፍ አይቻልም፡፡ሲጠቃለል አሁን በስራ ላይ ባለው የሃገራችን ህገመንግስት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖረው ስለሚገባው ልዩ ጥቅም የተደነገገው አንቀፅ መሰረት ያደረገው የኦነግን የተበድ ፖለቲካዊ ስነልቦና ሲሆን ይህ እንዲሆን የፈቀደው ደግሞ ህወሃት ከኦነግ በፖለቲካው ሰፌድ መቆየት ማትረፍ የፈለገውን ትርፍ ይሰበስብ ዘንድ ነው፤ እንጅ ነገሩ እንደሚባለው ታሪካዊ መሰረት ኖሮት አይደለም፡፡

በሽግግሩ ወቅት አዲስ አበባ በልዩ ሁኔታ የኦሮሞዎች ልዩ ጥቅም የሚጠበቅባት ምድር እንድትሆን የሚያደርግ በህገ-መንግስታዊ አንቀፅ ይካተትልኝ ሲል የነበረው ኦነግ ታሪካዊ ልቦለድ ለመሆን እንኳን አቅም የሌለው የበደል ድርሰት ጠቅሶነው፡፡ የደገሰውን በደንብ የሚያውቀው ህወሃት ኦነግ የተፈለገበትን የቤት ስራ እስኪከውንለት ድረስ የልደቱን ቀን እንደሚያከብር ህፃን የፈለገውን እንዲሆን የፈቀደለት ወቅት ነበረ፡፡ በመሆኑም ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ የሚያደርገው የኦነግ ተረክ የመጨረሻ እውነት ተደርጎ ተወሰደ፡፡ በወቅቱ ኦነግ ሰፋ አድርጎ ሃረርንም ቢጠይቅም ያልፈለገውን የማያየው ህወሃት የሃረሯን ጥያቄ ችላ ብሎ ኦነግ ከተባረረ በኋላም የአዲስ አበባውን የልዩ ጥቅም ጉዳይ ብቻ በህገመንግስት አፀና፡፡ የሃረሩ ጉዳይ ተድበስብሶ የቀረበትን ምክንያት “አላውቅም” ይላሉ ‘ህገመንግስቱን ለማርቀቅ ከሄዱት ሁለት የኢህአዴግ ሰዎች አንዱ ነበርኩ፣ ህወሃትም ማንንም ሳይወክል እኔን እና ዳዊት ዮሐንስን የኢህአዴግ ወኪል ሆንን’ የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ ቃለምልልሳቸው፡፡

በጋዜጣው ላይ ከዶ/ር ነጋሶ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው ጋዜጠኛ “በአዲስ አበባ ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ላይ የተለየ አቋም አልነበረም?” ሲል ጥሩ ጥያቄ አስከተለ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በወቅቱ “ንጉስ የወደደው” ኦነግ የፈለገውን መቃወም አዳጋች እንደ ነበረ በገደምዳሜ በሚያስረዳ መልኩ ይህን ይላሉ “በአርቃቂ ኮሚሽኑ በኩልችግር አልነበረም፤ሁሉም የተቀበለው ጉዳይ ነበር፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ በወጣው አዋጅ ላይ ስለነበረና የኦሮሞ ድርጅቶች ዋነኛ ጥያቄም ስለነበረ መከራከሪያ አልቀረበም ነበር”፡፡ የኦሮሞ ድርጅቶች የተባሉት ከአንጋፋው ኦነግ በተጨማሪ የእስላማዊ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር እና በአርሲ፣ ባሌ እና ሐረር አካባቢ ይንቀሳቀስ የነበረ “ቶክቹማ” የሚባል ድርጅት እንደሆነ ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ ቃለምልልስ ያብራራሉ፡፡

ከዚህ መልስ የምንረዳው ትልቅ ነገር እንደ ፍፁም ህግ ተደርጎ አስር ጊዜ የሚጠቀሰው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖራት የሚደነግገው ህገመንግስታዊ አንፅ (አንቀፅ 49 ንኡስ አንቀፅ 5) በዋናነት መሰረት ያደረገው የኦነግን ደመነፍሳዊ ፍላጎት እንደሆነ ነው፡፡የኦነግ ደመናፍሳዊ ፍላጎት የሚመነጨው ደግሞ ድርጅቱ ደቁኖ ከቀሰሰበት የተበድየ ፖለቲካዊ ስነልቦናው ነው፡፡ የተበድየ ፖለቲካዊ ስነልቦናው ተረክ ዘፍጥረት ደግሞ አስራስድስተኛውን ክፍለዘመን የአለም መፈጠሪያ የታሪክ መቆጠሪያ ጅማሬ አድርጎ ከሚወስደው እንዳይሆን የሆነ ፣ሸምበቆ የተመረኮዘ ክርክር ነው፡፡

ይህ አይነቱ ኦነግ ወለድ አካሄድ እንደማያዛልቅ የተረዳው ብልጣብልጡ ህወሃት ታዲያ ኦነግ ከሸዋ መኳንንት መስፋፋት ጋር አጣቅሶ ያመጣውን የልዩ ጥቅም ህገመንግስታዊ ድንጋጌ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር ካላት ጉርብትና ጋር ተያይዞ ከሚመጣ መስተጋብር ጋር ብቻ የሚያያዝ አድርጎ በህገመንግስቱ እንዲህ አሰፈረው “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፤እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይከበርለታል፡፡ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል”(አንቀፅ 49 ንኡስ አንቀፅ 5)፡፡ የሽግግር ዘመኑ ኦነግ እና የአሁኑ ዘመን የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች በአዲስ አበባ ባለቤትነት/ባለ ልዩ መብትነትን ለማፅናት በሚያነሱት ታሪክ ጠቀስ ክርክር እና በህገመንግስቱ ድንጋጌዎች(ህወሃት በጉዳዩላይ ያለው ፍላጎት ግልባጭ የሆነ) መሃል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡

በስህተት የአሸናፊነት ታሪክ የማይወጣቸው የኦነግ አመራሮች አያት ቅድማያቶቻቸው በመካከለኛው ዘመን ሸዋን ሲገዛ ነበረውን ንጉስ አንበርክከው፣ሸዋን እና ጎጃምን የራሳው አድርገው ሽቅብ ወደትግራይ መገስገሳቸውን እያወቁ አይወሩም፡፡በምትኩ እንዴት ሸዋ ላይ እንደተገኙ ሊናገሩ የማይፈልጓቸው ቀደምቶቻቸው በሸዋ መኳንንት ቁምስቅል ማየታቸውን እያለቃቀሱ አውርተው ካሳውም አዲስ አበባ ለኦሮሞ ሁሉ ልዩ ጥቅም መስጠት ያለባት ምድር ማድረግ እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡ የነዚሁ የኦነግ ፖለቲከኞች ተከታይ ትውልድ የሆኑት የዘመናችን አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ደግሞ የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች ኦሮሞዎች እንደሆኑ ከምድር ተነስተው እርግጠኛ ሆነው ‘አዲስ አበባ ራሷ በኦሮሚያ ክልል ሥር ሆና በኦሮሞ የጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያቤት ካልተቀረጠች ምኑን በደል ተካካሰ’ አይነት ነገር ይሰነዝራሉ፡፡

አዲስ አበባ ላይ ክፉኛ ስር የሰደደው ህወሃት/ኢህአዴግ ደግሞ ማሳረጊያው ከእርሱ ፍላጎት እንደማይወጣ ቢያውቅም አጨራረሱ ባላጋራውን እንዳይነሳ አድርጎ ድባቅ መትቶ እንዲሆን ስለሚፈልግ ለመገመት/ለመጠላት/ለመፈራት የቀረበን ሁሉ እስከጥግ እንዲገመት/እንዲጠላ/እንዲፈራ በቂ ጊዜ ሰጥቶ በዛውም የራሱን የአሸናፊነት መንገድ መጥረጊያ ጊዜም ይገዛል፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ህገመንግስቱ ራሱ ስለዚህ ጉዳይ ያሰፈረው ድንጋጌ በተጨባጭ ታሪካዊ/ፖለቲካዊ ሃቅ ላይ የቆ አይደለም፡፡ ይልቅስ ህወሃት ኦነግን በኦህዴድ እስኪተካ እሹሩሩ ለማለት ሲል ከአንገቱ በላይ የተቀበለው ነገር ነው፡፡ የድሮው ኦነግ እና የዛሬው ኦነግ ደግሞ ለህወሃት እኩል አስፈላጊነትም/ትርጉምም ያላቸውም አይደሉም፡፡ ለህወሃት የዛሬው ኦነነግ ትናንት እንዳይበረግግ ቀስ ብሎ የሚያስተኛው ‘የስለት ልጅ’ ሳይሆን ባጠፋውም ባላጠፋውም የሚረግመው ባላጋራው ነው፡፡ ስለዚህ ብልጣብልጡ ህወሃት በድሮ በሬ ከልቡ ሲያርስ አይገኝምና ዛሬም በኦነግ አንጎበር ውስጥ ያሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደሚመኙት ‘አዲስ አበባን እንካችሁ ብቻ አትቆጡብኝ’ የሚልበት ምክንያት የለውም፡፡

የአስራሰባት አመት የጫካ ትግሉ ሁሉን በአሸናፊነት የሚወጣበት ሁነኛ ቦታ ላይ ያስቀመጠው ህወሃት/ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ላይ ያለው ፍላጎት ግልፅ ነው፡፡ዋነኛው ግልፅ ነገር የዘመናችን የኦሮሞ አክቲቪስቶች እንደሚፈልጉት አዲስ አበባን በኦሮሚያ ስር አድርጎ ሰዶ ማሳደድ ውስጥ እንደማይገባ ነው፡፡ይህን ለማረጋገጥ ኤርሚያስ ለገሰ “የመለስ ቱርፋቶች፤ባለቤት አልባ ከተማ” በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሃፍ ገፅ 240 ላይ እንዳስቀመው ከ1997 አስደንጋጭ የምርጫ ሽንፈቱ በፊት ኢህአዴግ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን ፍላጎት ባሳዩ ኦሮሞዎች ላይ የነበረውን የመረረ አቋም ማስተዋል በቂ ነው፡፡ የሽንፈቱ ድንጋጤ መለስ ሲልለት በተጫጫነው ንዴት ሳቢያ ሃሳቡን በተቃራኒው ቀይሮ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን ቢፈቅድም በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ መስተጋብር ያለውን እውነተኛ ፍላጎት የሚያሳየው ግን ከንዴቱ በፊት(ከ1997) ያራምድ የነበረው አቋም ነው፡፡

ሁለተኛው ነገር የአዲስ አበባን ወሰን ከዚህ መልስ ብሎ ልማታዊ ባለሃብቶቹ አጥብቀው የሚሹትን የአዲስ አበባ እና የአካባቢውን የመሬት አቅርቦት የማድረቅ ገራገር ውሳኔ እንደማይሞክራት ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ማስረገጫ ባለፈው አመት መገባደጃ ለፓርላማ ባቀረበው እና በኢቢሲ ባስነበበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የአዲስ አበባ ከተማን ወሰንን በመከለል ላይ አንዳችም ነገር አለማንሳቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ማሳያ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ኦሮሚያ ዞኖች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መሬቶች ለልማት ከተፈለጉ ለአርሶ አደሮቹ በቂ ካሳ ይከፈላል እንጅ ከቦታቸው መነሳታቸው “የማይቀር የልማት ጥያቄ” እንደሆነ አስረግጦ ማስቀመጡ ነው፡፡

አዲስ አበቤ- የጎጥ ፖለቲካ “የእንጀራ ልጅ”?

በዚህ መሃል ፍላጎቱን እና ጥቅሙን ይተነፍስ ዘንድ መድረክ ያላገኘው የአዲስ አበባ ህዝብ አለ፡፡ ራሱን በጎሳ ማንነት የማይገልፀው የአዲስ አበባ ህዝብ ሁለቱ የጎሳ ፖለቲካ ቄሰ-ገበዞች(ኦነግ እና ህወሃት/ኢህአዴግ) በከተማዋ ላይ የሚያነሱት ክርክር ከፍላጎቱ ጋር እንደማይገጥም እርግጥ ነው፡፡ ብሄር አልቦው አዲስ አበቤ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስላለው ጉዳይ ለመምከር የሚያስችል የፌደሬሽን ምክርቤት ውክልና የለውም፡፡ በክልሎች መሃከል የሚነሳ ክርክር የሚሄደው ወደዚሁ የፌደሬሽን ምክርቤት እንደሆነ የሃራችን ህገመንግስት አንቀፅ 62 ንዑስ አንቀፅ 6 ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ደግሞ በፌደሬሽን ምክርቤት የሚወከሉት የሃገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችን የያዙ ክልሎች እንደሆኑ ያትታል፡፡ ሸገር በፌደሬሽን ምክርቤት ለመወከል ያልበቃችው በብሄር ብሄረሰቦች የማትገለፅ ባለዥጉርጉ ሆድ በመሆኗ ነው፡፡

ስለ ሃገራችን ርዕሰ ከተማ በሚያወራው የህገመንግስቱ ክፍልም አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 4 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ብቻ እንደሚወከሉ ያወሳል እንጅ በፌደሬሽን ምክርቤት ውክልናቸው ጉዳይ አንዳች ነገር አያነሳም፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር እንዲህ እንደ አሁኑ ያለ ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት የሚወስድ ጉዳይ ሲገጥመው ምን ማድረግ እንዳለበት ያስቀመጠው ነገርም የለም፡፡ የህግ የበላይነት እንደሰማይ በራቀው የሃገራችን ፖለቲካ በየትኛውም ምክርቤት መወከል ንጉስ የወደደውን ከማድረግ እንደማያስቀር የታወቀ ቢሆንም ከነጭርሱ የፌደሬሽን ምክርቤት ውክልና ማጣቱ ደግሞ የነገስታትን እንደልቡነት ይብስ ያጎላዋል፡፡

ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር ጆሮ የተጣገበው የአዲስ አበባ ህዝብ ከወደ መንግስት የሚመጣውን አብዛኛ ህግጋት አማራጭ ስለሌለው ብቻ የባሰ አታምጣ በሚል ዘየ ተቀብሎ ይኖራል፡፡ ወልዶ ከብዶ የኖረባት አዲስ አበባ ቤቱ ስላልሆነች ግብር እየከፈለ መኖር እንዳለበት ህገመንግስታዊ አንቀፅን ጠቅሶ የሚያውጅ ባለቤት ነኝ ባይ ሲመጣበት ደግሞ የባሰ እንደመጣና የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የተሻለ አድርጎ ለመቁጠር መገደዱ አይቀርም፡፡የሆነ ሆኖ የተገመተው ተገምቶ፣የተጠላው አይንህ ላፈር ተብሎ፣ማስፈራሪያ ሊሆን የተፈለገው በገዛ ምላሱ ገላጭነት አስፈሪ ምስሉ ጎልቶ ከወጣ በኋላ የሚፀናው ህወሃት/ኢህአዴግ ይሆን ዘንድ የወደደው እንደሆነ እሙን ነው፡፡

የሚሰራውን በደንብ የሚያውቀው ህወሃት/ኢህአዴግ የፈለገውን ለማፅናት የህጋዊነትን ካባ ደርቦ ከች እንደሚል የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ላለው ፍላጎቱ ህጋዊ ከለላ ለመስጠት ደግሞ ገና ድሮ የልቡን እንዲናገር አድርጎ ያበጃጀውን ህገመንግስት ከመጥቀስ የበለጠ አዋጭ መንገድ የለም፡፡ሆኖም ህገመንግስቱን አስር ጊዜ የሚያነሳሳው መንግስት ሚኒስትሮች ምክርቤት መከረበት የተባለው ረቂቅ አዋጅ ራሱ ከህገ-መንግስቱ አንቀፆች ጋር የሚተላለፍበት አካሄድ ቢኖርም የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ከሚያነሱት አስገራሚ ጥያቄ አንፃር የመንግስት ረቂቅ አዋጅ በተሻለ ለህገመንግስቱ አንቀፆች ሊቀራረብ ይሞክራል፡፡ እዚህ ላይ የባሰ አለ ለማለት እንጅ ህገመንግስታዊ አንቀፅን መሸራረፍ ለማንም የተቻለ እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡

አልተገናኝቶ…!

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት ይገባል ስለተባለው የባለቤትነት/የልዩ ጥቅም ባለመብትነት ጉዳይ ከኦሮሞ የብሄርተኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞች/ፖለቲከኞች የሚነሳው ጥያቄም ሆነ ረቂቅ አዋጅ ተብሎ በፓርላማ ሊፀድቅ በር ላይ ያለው (የመንግስትን ፍላጎት የሚያሳየው) ረቂቅ መሰረቱን የሚያደርገው ህገ-መንግስቱን ነው ይባል እንጅ ህገመንግስቱን አለመምሰሉ ይበዛል፡፡አዲስ አበባን አስመልክቶ በህገ-መንግስቱ በተቀመጠው አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በተቀመጠው ቢጀመር አዲስ አበባ የሃገሪቱ ርዕሰ ከተማ እንደሆነች ያስረዳል፡፡አስፈፃሚው የመንግስት ክንፍ ለህግ አውጭው አቀረብኩ ባለው ረቂቅ አዋጅ ላይ ደግሞ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እንደሆነችም ያትታል፡፡ ይህ መሰረት ያደረገው የህወሃት/ኢህአዴግን እና የኦህዴድ/ኢህአዴግን ወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎት ይሆን ይሆናል እንጅ በፍፁም ህገመንግስታዊ መሰረት ያለው ነገር አይደለም፡፡ የሃገሪቱ ህገመንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ህገመንግስት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እንደሆነች አይደነግግም፡፡ በ1994 በተሻሻለው የኦሮሚያ ክልላዊ ህገ-መንግስት ላይ “የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ አዳማ ነው” የሚል ድንጋጌ እንደተደነገገ ኤርሚያስ ለገሰ ከላይ በተጠቀሰው መፅሃፉ ገፅ 240 አሰቀምጧል፡፡ በክልላዊም ሆነ በፌደራሉ ህገ-መንግስት ላይ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን የሚያዝ ረቂቅ አዋጅ ማውጣት ህገመንግስታዊ ድንጋጌን ስለማስፈፀም እያወሩ ህገ-መንግስታዊ ባልሆነ አካሄድ መንጎድ ከመሆን አያልፍም፡፡ በዚህ ውስጥ ማየት የሚቻለው ነገር የሃገራችን ገዥዎች ፖለቲካዊ ጥቅማቸው በምሉዕ ሁኔታ ለማጣጣም ሲሉ ህጋዊ አካሄዶችን ለመደፍጠጥ እንደማያመነቱ ነው፡፡ ይብስ የሚገርመው ደግሞ ህገ-መንግስት ሊተረጉም የተቀመጠው የፌደሬሽን ምክርቤት ተብየው የዘወትር ዝምታ ነው፡፡

የባሰ ሲመጣ ደግሞ ለህግ መከበር ጥብቅና ሊቆሙ የሚገባቸው የህግ ምሁሩ ፀጋየ አራርሳ በ“OMN” ቴሌቭዥን ቀርበው ህገ-መንግስቱ ካለው በተቃራኒ “እንደውም አዲስ አበባን ለኦሮሚያ ትቶ ሌላ ረባዳ መሬት ተፈልጎ አዲስ ዋናከተማ መመስረት ይቻላል’ የሚል አማራጭን ያስቀምጣሉ፡፡ አማራጭ ቦታ ሲጠቁሙ ደግሞ ‘አዲሱን ዋና ከተማ ሌላ የኦሮሚያ ክልል ቦታ ላይም ሊደረግ ይችላል’ ይላሉ፡፡ ነገሩ እንዳይሆን መሆኑ ካልቀረ፣ ‘ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ዋና ከተማ በኦሮሚያ ማየት ስለማንፈልግ ሌላ ክልል ላይ ዋና ከተማችሁን መስርቱ’ ማለት አንድ የለየለት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ሌላ ዋናከተማ መመስረቱ እንደ አማራጭ ሆኖ ከቀረበ ዘንዳ አሁንም በኦሮሚያ ክልል ያለችውን አዲስ አበባን ጥሎ ሌላ ሜዳማ መሬት በዛው በኦሮሚያ ክልል ፈልጎ ሌላ ዋና ከተማ ለመመስረት መባዘኑ ለምን እንዳስፈለገ የሚያውቁት ፀጋየ ብቻ ናቸው፡፡

ሌላው ከህገመንግስታዊ ድንጋጌው ጋር አልተገናኝቶ የሆነው ጉዳይ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ስር መተዳደር አለባት የሚለው የኦሮሞ ፖለቲከኞች/አክቲቪስቶች ክርክር ነው፡፡የህገመንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 2 “የአዲስ አበባ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል፡፡ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፡፡” ሲል ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪ በህገመንግስቱ ተመሳሳይ አንቀፅ ስር ንዑስ አንቀፅ 3 “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት ይሆናል” ይላል:: ይህ በግልፅ በተደነገገበት ሁኔታ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ስር ሆና ትተዳደር ማለት ስሜታዊ እንጅ ህገመንግስታዊ መሰረት የሌለው ጥያቄ እንደሆነ የሚያነጋግር ነገር አይደለም፡፡

ይልቅስ የሚያነጋግረው ሌላው ጉዳይ የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያን መስተጋብር አስመልክቶ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም ረቂቅ አዋጅ አወጣሁ የሚለው የሃገሪቱ መንግስት ዝርዝር አዋጁን ለማውጣት በህገመንግስቱ በአንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ብቻ ብቻ መዟዟርን የመረጠበት ሚስጥር ነው፡፡ ነገሩ እውነት ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም ዝርዝር ህግ የማውጣት ጉዳይ ከሆነ በዚሁ አንቀፅ ስር በንዑስ አንቀፅ 2፣ የአዲስ አበባ ክልል መስተዳድር ራሱን በራሱ ስለማስተዳደሩ በተቀመጠው ድንጋጌ ላይ ዝርዝር ህግ እንደሚወጣ ህገመንግስቱ ያዛልና ዝርዝር ህጉ አብሮ መውጣት ነበረበት፡፡ መንግስት ግን ይህን ማድረግ አልፈለገም፡፡

የዚህ ህግ ዝርዝር አለመውጣት የአዲስ አበባን ህዝብ የራሱ ባለቤት እንዳይሆን የሚያግድ፣የመጣው ሁሉ እንደፈለገ እንዲያደርገው የሚያመቻች ትልቅ መሰናክል ነው፡፡መንግስት ይህን ያደረገው የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያን መስተጋብር በተመለከ የሚያነሳቸውን ካርታዎች ጥሎ ላለመጨረስ እንደሆነ ኤርሚያስ ለገሰ “የመለስ ቱርፋቶች” ባለው መፅሃፉ ከገፅ 240- 254 ከትንታኔ ዘለል ብሎ ትንቢት በሚመስል መልኩ በትክክል አስቀምጦታል፤ አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ የገዥውን ፓርቲ ፖለቲካዊ ማንነት አበጥሮ የሚያውቀው ኤርሚያስ እንዳስቀመጠው ነው፡፡

የመልከዓምድራዊ አቀማመጥ ወግ

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ነች የሚለው ክርክር ታሪካዊ ቀደምት ነዋሪነትን፣ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን ከማጣቀሱ ጎንለጎን የሚያነሳው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የመገኘቷን ነገር ነው፡፡ ይህ ክርክር የሚስተው አንድ ወሳኝ ነጥብ የሃገራችን ክልሎች አከላለል በዋናነት ታሳቢ የሚያደርገው መልከዓምድራዊ አቀማመጥን ሳይሆን በአንድ ስፍራ ላይ የሰፈሩ ህዝቦች የሚናገሩትን ቋንቋ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በተለያዩ ክልሎች ልዩ ዞኖች እና ወረዳዎች እንዲኖሩ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል መሃል ላይ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚገኙበት ከሚሴ የተባለው ቦታ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ዞን እንዲሆን ተደርጓል፡፡የኦሮሚያ ልዩ ዞን በአማራ ክልል መሃል ላይ በመገኘቱ ብቻ የአማራ ህዝብን ታሪክ እና ማንነት የሚያጎሉ መታሰቢያዎች፣አሻራዎች እንዲቆሙ ላይ ታች ሲባል ግን አልታየም፡፡ በዚህ እሳቤ ወደ አዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ጉዳይ ሲመጣ በከተማዋ ከሚኖረው ህዝብ የሚበዛው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይህም ስለሆነ ነው ከተማዋ ራሱን በቻለ መስተዳድር እንድትተዳደር በህገመንግስት ሳይቀር የተደነገገው፡፡

አሁን ወጣ በተባለው ረቂቅ አዋጅም ከተማዋ ሃገር አቀፋዊ ቀርቶ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላት፣ከኒውዮርክ እና ከጄኔቫ ቀጥላ የአለማቀፉ ማህበር ማዕከል እንደሆነች ተወርቷል፡፡ በዚሁ አፍ ደግሞ የከተማዋ አደባባዮች፣ጎዳናዎች፣ሰፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች የኦሮሞ ብሄርን መንፈስ እንዲያሳዩ እንዲረዳ በቀድሞው የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል፡፡ የሰፈሮቹ የቀድሞ የኦሮሞ ስም እንዴት እንደሚታወቅ ነገሩን ያመጣው አካል የሚያውቅ ቢሆንም ከተማዋ ሃገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ አላት ማለት እና የከተማዋ ሰፈሮች ስም ተቀይሮ በኦሮምኛ ስሞች እንድትጠራ ማድረግ እንዴት እንደሚገናኝ ብቻ ሳይሆን ለምን እንዳስፈለገ፣ነገሩ ራሱን ከማንኛውም ብሄር ጋር ለማያጋምደው አዲስ አበቤ ምን ትርጉም እንዳለው ግራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳድር አብዛኛ ነዋሪ ኦሮምኛ ተናጋሪ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ከተማዋ ራሱን በቻለ መስተዳድር ትተዳደራለች ተብሎ በህገመንግስት በግልፅ በተቀመጠበት ሁኔታ በዙሪያዋ የኦሮሞ ብሄር ስላለ መሃሏ የራሷን ሳይሆን የጎረቤቷን ኦሮሚያ ክልልን ታሪካዊ፣ስነልቦናዊ እና ባህላዊ ማንነት ይስበክ ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው? ይህን ካደረጉ በኋላ አዲስ አበባ ራሱን በቻለ መስተዳድር ትተዳደራለች የሚለው ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ወረቀት ላይ መቼክቼክ ምን ይፈይዳል? አራቱ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እንደሚያስተዳድሯት የሚወራው አዲስ አበባ የኦህዴድን ገፅታ ብቻ እንድታሳይ ሲደረግ ሌሎቹ ፓርቲዎች ጥቅማቸው ምንድን ነው?

‘አዲስ አበባን የሚመግባት በዙሪያዋ ያለ የኦሮሞ አርሶ አደር ስለሆነ ደላላ እንዳያታልለው አዲስ አበባ ገብቶ ምርቱን የሚሸጥ የሚለውጥበት የገበያ ሰንሰለት ያጥርለት ዘንድ ኮሚቴ አቋቁማለሁ’ ይላል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አወጣው የተባለው ህግ፡፡ አዋጁን እየተንተገተገ ያነበበው ጋዜጠኛም ንባቡን ሲያጠቃልል ‘ረቂቅ ህጉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንዲጠቅም ታሳቢ የተደረገ እንደሆነ’ አንገቱን ከፍ ዝቅ እያደረገ ተናግሯል፡፡ ሁላችንም ያጎረሱንን ሁሉ የምንውጥ ካድሬዎች አይደለንምና እዚህ ላይ ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም፡፡ ባለ ብዙ ፍጆታዋ አዲስ አበባ ከአጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች የምታገኘው የምርት አቅርቦት ብዙ እንደሆነ አሌ ባይባልም ይህ ቦታ የማይመግባት ብዙ ፍጆታ እንዳለም የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙዝ አናናስ፣ማንጎ፣አቩካዶው፣በርበሬ፣ዝንጅብሉ፣ኮረሪማው፣ቆጮው የሚጫነው ከደቡብ ኢትዮጵያ እንጅ ከአጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች አይደለም፡፡ ማሩ፣ቂቤው ጤፍ ጥራጥሬውም ከጎጃም ሌላ ሌላውም ከተለያየው የሃገራችን ክፍል ወደሸገር ይጎርፋል፡፡ታዲያ አርሶና አፈር አፍሶ ይህን ሁሉ ምርት ለሸገር የሚያጎርሰውን ከኦሮሚያ ውጭ ያለው ገበሬ በደላላ እንዳይበላ “ለሁሉም ያሰበ ነው” በተባለለት ረቂቅ ህግ ያልተወራው ለምንድን ነው? ዘመኑ የዘመናዊ ፈጣን ትራንስፖርት እንጅ በእግር የሚገሰገስበት የሲራራ ንግድ አለመሆኑ እየታወቀ በመልከዓምድር አቀማመጥ የቀረበ አርሶ አደር የበለጠ ምርት ለሸገር እንደሚያስገባ ማሰብ ሌላ አላማ ከሌለለው የለየለት የእውቀት ድርቅ ነው፡፡

እውን ይህን ረቂቅ ህግ ያወጣው ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ፓርትዎች የተውጣጣው የኢህአዴግ ስራአስፈፃሚ ከሆነ ፍራፍሬውን ወደ አዲስ አበባ ጉሮሮ በየቀኑ የሚያስገበውን ህዝብ ወከልኩ ያለው ደኢህዴን ነፍስ እና ስጋ ካለው ‘እኔ የወከልኩት አርሶ አደርስ የደላላ ጥሩር አለው ወይ?’ ማለት ነበረበት፡፡ ብአዴንስ ቢሆን ተመሳሳይ ጥያቄ ለማንሳት የማያበቃ ምርት አልቦ አርሶ አደር ወክሏል? ይህ ረቂቅ ህግ ሌሎቹን የሃገራችን አርሶ አደሮች የግብይት ነገር ችላ ብሎ ለአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሞ አርሶ አደሮች የሚያሳየው “እንስፍሳፌ”እውነት ከልብ እና የጤና ነው? ወይስ እንደ ጅብ እስኪነክሱ ማነከስ? ብሎ መጠየቁ እንጅ ብልህነት ‘ሌላው ተረስቶ እኛ የታሰብነው ለማ መገርሳ ጎበዝ ስለሆነ ነው’ ብሎ መደሳሰት ለዶሮ ውሃ የሚሞቀው ለገላዋ መታጠቢያ ነው ብሎ እንደማሰብ ያለ ተላላነት ነው፡፡

ጸሀፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል:: meskiduye99@gmail.com

___
በዚህ ድረ ገጽ መጣጥፍ ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ኢሜይል ያድርጉልን። editor@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here