spot_img
Wednesday, May 29, 2024
Homeነፃ አስተያየትኦሮሞና አማራ - ከትግል አጋርነት ባሻገር ( በመሃመድ አሊ -የቀድሞ የፓርላማ አባልና...

ኦሮሞና አማራ – ከትግል አጋርነት ባሻገር ( በመሃመድ አሊ -የቀድሞ የፓርላማ አባልና የህግ ባለሙያ/ጠበቃ)

ጥቅምት 8 :2008 ዓ ም

ውድ ጓደኞቼ/ወገኖቼ:- ጽሁፌን በትዕግስትና በጥሞና አንብባችሁ ሀሳቤን እንድትረዱልኝ በትህትና እጠይቃለሁ።
=======+========+==========

መሃመድ አሊ  (የቀድሞ የፓርላማ አባልና የህግ ባለሙያ/ጠበቃ)
መሃመድ አሊ
(የቀድሞ የፓርላማ አባልና የህግ ባለሙያ/ጠበቃ)
ማን ነበር እነዚህን ትላልቅ/ግዙፍ ማህበረሰቦች “እሳትና ጭድ” ሲል ያሟረተባቸው? የሆነስ ሆነና እነዚህ ሰፋፊ ማህበረሰቦች እንደተባለው “አጥፊና ጠፊ” ቢሆኑ ከራሳቸው አልፎ ጦሳቸው ለሌላውስ አይተርፍም ወይ? ምናልባት ሁለቱን እርስ በርስ አባልቶ በቀላሉ ገሸሽ ማለት ይቻል ይሆን?
=======+=======+=======
የተፈራው ሳይሆን ተስፋ የተጣለበት እየሆነ ይመስላል:: ባለፈው ዓመት ጎንደር ላይ ሰልፍ ሲጠራ አንዳንድ አክቲቪስቶች አጀንዳው የወልቃይት ጉዳይ ብቻ እንዲያተኩር ወትውተው ነበር። ህዝቡ ግን “የፈሰሰው የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የኛም ነው” – “በቀለ ገርባ ይፈታ” እና የመሳሰሉ የትግል አጋርነትና ወገናዊነትን የሚያሳዩ መፈክሮችን ይዞ ወጣ። እነዚያ መፈክሮች ያስተላለፉት መልዕክትና ህዝቡን ከማስተሳሰር አንፃር የነበራቸው ፋይዳ የትየለሌ ነበር።
ዘንድሮም በተመሳሳይ ሁኔታ የታላቁና ሥመ-ገናናው የናይል ወንዝ ማህፀንና የማንነታችን ማህተም የሆነው ጣና ሐይቅ “እንቦጭ” በተባለ አረም ሲወረር የኦሮሞ ወጣቶች አረሙን ከመንቀል ባለፈ አጋርነታቸውን ሊያሳዩ ፍቅር ሰንቀው ወደ ጎጃም – ባህር ዳር አቀኑ:: የአማራ ወጣቶች በበኩላቸው በተለይም የደብረማርቆስ ህዝብ ኦሮሞ ወንድሞቹን የተቀበለበት ሁኔታ እጅግ አስደማሚ ነው። በግሌ ህዝቡ በደስታ ገንፍሎና በፍቅር ደምቆ እስክስታ አወራረዱን አይቼ የደስታ ሲቃ እየናጠኝ እንባየን መቆጣጠር አልቻልኩም። ትዕይንተ ህዝቡ በወቅቱ ከፈጠረው ስሜት ባለፈ ባለፉት 27 ዓመታት ያለማሰለስ ሲነዛ የነበረውን ከፋፋይና የጥፋት ፕሮፓጋንዳ ፉርሽ በማደረግና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር ረገድ ሰፊና ጥልቅ ትርጉም አለው።
=======+=======+=======
እርግጥ ነው የኦሮሞና የአማራ ግንኙነት ወደ አደገኛ ጠርዝ ሲገፋ ቆይቷል። ኃላፊነት የጎደላቸው ኃይሎች በተሳሳተ ስሌት ሲገፉት/ሲያራግቡት የነበረው ይህ የጥፋት የኢትዮጵያን አንድነት ህልውና የሚገዳደር; የሁለቱን ማህበረሰቦች ደህንነት ጥያቄ ላይ የሚጥልና በአጠቃላይም የቀንዱን አካባቢያዊ ሰላምና መረጋጋት በዘላቂነት የሚያውክ እንደሆነ ለሁሉም ወገን ግልፅ ነው:: ይሁን እንጅ ከተራ የመንደርተኝነት አስተሳሰብና የእልኸኝነት ስሜት በቀላሉ መውጣት የተሳናቸው ኃይሎች ዐይኖቻቸውን ጨፍነውና ሌሎችንም በጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ሸብበው ወደ ጥፋት አፋፍ ሲያመሩ ታይተዋል::

ሆኖም ግን የአስተዋዩና ታጋሹ ህዝብ ሰረጋላዊ ጉዞ እየቀደመ ይመስላል። የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ምስጋና ይገባውና ዛሬ አንዳንድ ጽንፈኛ ልሂቃን ሳይቀሩ ስለኦሮሞና አማራ የትግል አጋርነት እያቀነቀኑና ለብዙዎች ተስፋን እየፈነጠቁ ነው:: ከዚህም ባለፈ ኦሮሞና አማራ የኢትዮጵያ አንድነት ሥርና ግንድ ከሚል ትንተና የሚነሱ ወገኖች የኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና ከቶም ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደማይችል ፍንጭ እየሰጡ ነው:: በተለይ ከኦሮሞ ልሂቃን ሰፈር የሚሰማው ይህ የፖለቲካ ትርክት አንዳች የመነቃቃት ስሜት መፍጠሩ አልቀረም።
=======+=======+=======
በልማዳዊ አነጋገር ቤት ሊቆም የሚችለው ምሰሶና ዋልታን አማክሎ ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ኦሮሞና አማራ የአንድነታችን ምሰሶና ዋልታ ናቸው ቢባል ስህተት አይሆንም። ይሁንና ምሰሶና ዋልታ ብቻቸውን ቤት ሊሆኑ እንደማይችሉ ሊሰመርበት ይገባል። አንድን ቤት ህልው የሚያደርጉት ምሰሶና ዋልታን አማክለው የሚቆሙት ባላና ወጋግራ ጭምር ናቸው። ቤቱ እንደቤት ሊቆም የሚችለው በአግባቡ ሲማገርና ሲከደን መሆኑን በተለይ አስተዋዩ ህዝባችን ጠንቅቆ ያውቀዋል።

ይህ ምሳሌያዊ አገላለፅ ከሀገራችን የብሔሮች/ብሔረሰቦች ጥንቅር አንፃር ሲታይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልትቆም የምትችለው ከኦሮሞና አማራ በቀር ያሉ ብሔሮች ባላና ወጋግራ ሆነው ሲቆሙ ብቻ ነው። የአንድ ቤት ህልውና የሚረጋገጠው ከላይ የገለፅናቸውን የቤት ቋሚዎች የሚያስተሳስሩ ማገሮችና አስተማማኝ ክዳን ሲኖረው ነው:: በተመሳሳይ አነጋገር; በአለማቀፍ ህግ ብያኔ መሠረት አንድ አገር አገር ለመሆን/ለመባል በተወሰነ/በታወቀ የግዛት ክልል የሚኖር ህዝብና በህዝቡ የተቋቋመ መንግሥት ሲኖረው ነው። ህዝቡን የሚያስተሳስሩትና በአንድነት የሚያቆሙት መርሆችና ህጎች (ስምምነቶች) እንደማገር ብንወስዳቸው መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንደጣሪያና ክዳን ሊያገለግለን ይችላል::

የመንግሥት ህልውና የሚረጋገጠው በህዝብ ይሁንታ ሲሆን ሥልጣኑን የሚያገኘውም ማህበረሰቡ ከመብቶቹ መካከል የተወሰኑትን ወድዶና ፈቅዶ ሲያስረክበው (surrender of rights) መሆኑን የማህበራዊ ውል ህልዮት (social contract theory) ቀማሪዎች ያስረዳሉ። የግልና የቡድን መብቶች ሥርና ሐረግም ከዚሁ ማህበራዊ ቀመር ይመዘዛል። እነዚህን እሴቶች የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ አድርገን ልንወስዳቸው እንችላለን።
=======+=======+=======
በኦሮሞና አማራ መካከል የተፈጠረው የትግል አጋርነትና የአንድነት ስሜት አበረታችና ተስፋ ሰጭ ሆኖ ሳለ፣ አንዳንድ የኦሮሞና አማራ ልሂቃን “የብዙሃን አገዛዝና የአናሳዎች መብት” የሚለውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርህ ከኦሮሞና አማራ ህዝብ ቁጥር/ብዛት ጋር አያይዘው ይተረጉሙታል:: በእነሱ እይታ ኦሮሞና አማራ በአንድነት ከቆሙ ዴሞክራሲያዊ መርህን መሠረት አድርገው የብዙሃነ አገዛዝን ማስፈን ይችላሉ።

ምናልባትም ከቡድን መብት አንፃር ይህ እይታ የሚያስኬድ ሊመስል ይችላል። ከሰብኣዊ መብት አስተምህሮት አንፃር ካየነው ግን የግለሰብ ዜጎችን መብት የሚጨፈልቅ ሊሆን ይችላል። እንደቡድን መብት እንውሰደው ቢባል እንኳ እይታው ከጠቅላይነት/አግላይነት የአስተሳሰብ ተፅዕኖ ነፃ አይደለም። ከቡድን መብት አንፃር አግላይ/ጠቅላይ የሆነና የግለሰብ መብትን ሊጨፈልቅ የሚችል አደረጃጀት ለሌሎች የሥጋት ምንጭ ከመሆኑም በላይ ዘላቂ ሰላም; የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓትና አገር ለመገንባት እንቅፋት መሆኑ አይቀርም::
=======+=======+=======
በብሔር ላይ የተመሠረተ አደረጃጀት አንዱ ሌላውን ከመገዳደር ባለፈ ከዘላቂ ሰላምና ከሀገር/ህዝብ አንድነት አንፃር የረባ ፋይዳ የለውም:: እንዳውም አጉል የፉክክርና የተቀናቃኝነት መንፈስን በማጠናከር ወዳልታሰበ ግጭትና የእርስ በርስ እልቂት ሊያመራ እንደሚችል የራሳችን ተሞክሮ ብቻውን ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና “ሥርና ግንድ” ነን የሚሉት የኦሮሞና አማራ ልሂቃን አደረጃጀታቸውን እንደገና መቃኘት እንዳለባቸው ግልፅ ነው::

ኦሮሞና አማራ እንደትላልቅ/ሰፋፊ ማህበረሰብ ለሌሎች ማዕከል ሆነው የአሰባሳቢነት ሚና ሊጫወቱ ሲገባ ከፋፋይ/በታኝ የሆነ መንገድ መከተልና ለሌሎችም ሥጋት መሆን ትልቅነታቸውን አይመጥንም። ስለሆነም ከጠባብ የብሔርተኝነት ማዕቀፍ ወጥተው ሕብረብሔራዊ በሆነ አውድ ሁሉን አቀፍ (all inclusive) በሆነ አደረጃጀት ይህን የዋህና ቅን ህዝብ; እንዲሁም ትልቅና ባለታሪክ አገር ሊታደጉትና ታሪክ ሊሰሩ ይገባል::

ከዚህ አንፃር የአደረጃጀት ጥያቄው እንደተጠበቀ ሆኖ; ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ አንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን አሰልችውን “የበዳይና ተበዳይነት” አስተሳሰብና ትርክት (victim mentality & discourse) በመቀየርና የአንድነትን ፋይዳ በማቀንቀን ረገድ ያሳዩት ዝንባሌ (paradigm shift) አበረታችና ሊደነቅ የሚገባው ነው።
ይህም ሆኖ የሀገራችን ፖለቲካ እጅግ ተለዋዋጭና የማይጨበጥ (fluid) መሆኑን አላጣሁትም። አንዱ ከመገፋት/ከመገለልና ማንነቴ ተረግጧል ከሚል ስሜት; እንዲሁም ሌላው ከመጠቃትና ራስን/ህልውናን ከመከላከል ከሚል ምክንያት በብሔር የመደራጀት አማራጭ ይዞ ሊሞግተን ይችላል:: እኛም የተሻለውን መንገድ ከማሳየት ባለፈ የማንንም መብት የማጣበብ ዓላማም ሆነ እምነት የለንም::

ይሁንና ጽሁፋችንን የምናሳርገው የሁላችንንም ቀና ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች የሚሹ ጥያቄዎች በመሰንዘር ነው።

1/ የመገፋት/የመገለልና የማንነት መረገጥ ስሜቱ; እንዲሁም የመጠቃትና የህልውና ሥጋቱ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ለዚህ ተጠያቂው ማነው? መፍትሔውስ በማን እጅ ነው? በነዚህ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ መነጋገር አይቻልም ወይ? ተቀራርቦ ለመነጋገር ተነሳሽነቱ ነው የጠፋው ወይስ ሊያቀራርቡ የሚችሉ የፍቅርና የአንድነት መልዕክተኞች?
2/ በብሔር መደራጀት መዳረሻ ግቡ ምንድነው? በብሔር መደራጀትም ሆነ በብሔር ከተደራጁ ኃይሎች ጋር የትግል አጋርነት/ጥምረት መፍጠር የት ያደርሳል? ከዚህ በፊትስ አልተሞከረም ወይ? አሁንም እንሞክረው ቢባልስ ከትግል ስልት ባለፈ ስትራቴጂያዊ ፋይዳው ምንድነው?
3/ ሕብረብሔራዊ አደረጃጀት የተሻለ አማራጭ ተደርጎ የማይወሰደው ለምንድነው? በተለይ እንደ ኦሮሞና አማራ ያሉ ሰፋፊ/ትላልቅ ማህበረሰቦች በኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና የምር የሚያምኑ ከሆነ ሕብረብሔራዊ በሆነ አደረጃጀት ውስጥ የሚያጡት/የሚያሰጋቸው ነገር ምንድነው? ከሕብረብሔራዊ አደረጃጀት ውጭ ሌሎች አናሳ ብሔሮችን/ብሔረሰቦችን እና ግለሰብ ዜጎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት ነው? ወይስ የወያኔ/ኢህአዴግን ስልትና አካሄድ እንደምርጥ ተሞክሮ ይወስዱታል?
=======+=======+=======
– በመጨረሻም ይህን ሙከራዬን ያለንበት ሁኔታ ከሚፈጥረው ጭንቀትና ፍፁም ቅንነት የመነጨ አድርጋችሁ እዩልኝ።
– ዓላማዬ ለውይይት መነሻ የሚሆን አጀንዳ ከማቅረብ ባለፈ ውስብስቡ የሀገራችን ችግርም ሆነ መፍትሔው ለእኔ እይታ ቅርብ ነው የሚል ግብዝነት የለኝም።
– በዚህ ጽሁፍ መነሻነት ገንቢ ውይይቶች ከተደረጉ እንደተሳካልኝ እቆጥረዋለሁ። ባይሳካም “ያለውን የወረወረ. ..” እንዲሉ በበኩሌ የድርሻዬን ተወጥቻለሁ።
ዘላለማዊ ህልውና እና ሁለንተናዊ ብልፅግና ለኢትዮጵያ!!!

____
መሃመድ አሊ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በፌስ ቡክ ገጹ ሃሳብ ያጋራል

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here