spot_img
Sunday, July 21, 2024
HomeመጣጥፍDV የሞላሁ ዕለት! (ሚኪያስጥ የለቲ ልጅ)

DV የሞላሁ ዕለት! (ሚኪያስጥ የለቲ ልጅ)

በሚኪያስጥ./የለቲ ልጅ)
ጥቅምት 30 ፤ 2010 ዓ ም

DV ልሞላ ሄድኩ፤ጠባቡ ቤት በሰዉ የጩኸት አረንቻታ ተሞልቷል።በኮምፒዩተርና በስካነር የተዥጎረጎረዉ የክፍሉ ድባብ፣ተረጋግቶ ለመናገርና አሰላስሎ ለማውራት ፋታ አይሰጥም።
«እህት፤የ’ኔ ተራ ወዴት ነዉ?»(ጎረምሳ ወጣት)

«ልጄ…ፎርሙን ወየት ሄጄ ልሙላዉ?»(ለመሞት አንድ ሃሙስ የቀራቸዉ ባልቴት)

«እማማ!ራበኝ!»(ችግረኛ ፍልፈላ)

በየጥጉ እንደየአፉ-ሁሉም-ያወራል።እኔም አወራለሁ፤እጠይቃለሁ፤እለፋደዳለሁ።

ከፊቴ አራት ወጣቶች የፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጠዉ፣ፎርሙ ላይ የተዘራዉን ተስፋኛ ስም፣ጾታ፣ዕድሜ…ወደኢንተርኔቱ ማህደር ይሞላሉ።

ከነ’ዛ መካከል የአንዷ ዠርባ በለበሰችዉ ስስ ልብስ በኩል በደንብ ይታያል።

ወይ ጀርባ፤ወይ ትከሻ!

ቡግርና ቢንቢ የለበለበዉ ጀርባ በቀለማት ብዛት ተቀላምቷል።

ጥቁር፣ቀይ፣ደብዛዛ ቢጫ…

ተለጣጠፉ፤ተቀጣጠሉ…እነቡግርና እነዕባጭ!

ዓይኔ ፈዘዘ።ቅላቷ ይሆናል የሳበኝ።ስረወ-ምክንያቱን አላወቅኩም እንጂ!

«አመሪካ መግባት እፈልጋለሁ።ብታዪ፣ወያኔ አስመርሮኛል!…»

ጎንደሬዉ ወጣት ከእኔ ዦሮ ራቅ ብሎ እያንባረቀ ነዉ።በባለፈው ዓመት ዓመፅ አንድ ጎድኑን በፖሊስ ቆመጥ ተወቅጦ አጥቷል።

«አመሪካ መግባት እፈልጋለሁ!…» አጠገቡ ላለች፣አንዲት ልጅ-እግር ሴት ቀደዳውን ይነፋል።

«ብታዪ(ለሁለተኛ ጊዜ)፣ታስሬ…ታስሬ!ታሽቼ፤ተወቅጬ ከብርሸለቆ ወጣሁ።ቤተሰቤ በደረሰብኝ ጉዳት በጣሙን አዘነ፤በተለይ ታላቅ እህቴ!አምርራ አለቀሰች!…»

«እምጽ!» ቅጭልጭልታ ድምጥ ከቆንዦዋ ተሰማ።

«እናልሽ፣ይህንን ግትቻ መንግስት ለማዉረድ ልቤ በጣም ተነሳሳ።ወዲያውኑ ወደበረሃ ወረድኩ።ጎቤ መልኬ ጋር ነበር-ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘሁት።ጎቤ ጥንቁቅ ሰው ነዉ።መነፅሩን አጥልቆ ክላሽ ሲያነግብ፣ውብ የሆነ ግርማ አለው።ሰለጠንኩ፤ጥሩ ተኳሽ ወጣኝ!»

አንገቱን አቀረቀረና ጭንቅላቱን ግራና ቀኝ አሾረ።

«ወይኔ!…አወየዉ፤ወይኔ!»

«ምንተዉ፣አንተዬ?» ልጅቷ አምባረቀች።

«በወያኔ ገንዘብ ተደልዬ፣ጎቤን ገደልኩት!» ጮኸ።

ዝም አለች፤ጎቤንም ሆነ ወያኔን በምንም ተዓምር አትችልም።በቤተ-መቅደስ የፀሎት ማዕጥነት ታጥና ላደገች ሴት፣ፖለቲካ ቅርቧ ቢሆን አይደንቅ።

«አማኑኤል የተባለው ጓደኛዬ የታወቀ-ዕሳት የላሰ ካድሬ ነዉ።ገንዘብን እንደማፈቅርና ሴት እንደምወድ ያውቃል።ደህንነት ውስጥ የሚሰራ ጓደኛውን ወደ’ኔ-መዠመሪያ-ላከብኝ።
ተነጋገርን፤ዓይኔ ጨፍኜ አመንኩት።
ጎቤን እንድገድለውና አምልጬ እንድሄድ ተደረገ፤ታሪኩን ላሳጥርልሽ ብዬ ነዉ እህቴ።»

ጭንቅላቷን ወዘወዘችና ማድመጡን ቀጠለች።

«አሁን ጎንደር ምን የመሰለ ቪላ ቤትና ቆንጅዬ ሴት እንዲሰጠኝና እንዳገባ ተደረገ።»
ታሪኩ ተዛዘመ፤እኔም ጆሮዬን መለስኩ።

«ቆይ…ቆይ!ቅድም-ዛዲያ-‘ወያኔ አስመረረኝ’ ስትል የነበረው ለምንድነዉ?» ገመምተኛ መሳይዋ ሴት፣አሁን አንደበቷ ሙሉ በሙሉ ተፈታ።

«ኦ…ው!እርሱ’ማ የስራዬ ጠባይ ነው!እንደአንቺ ያለውን ጠረ-ሰላም ለመመንጠር ነዉ የመጣሁት።» አለ፤በዕርካታ።
ከመቅፅበት በበስተጀርባው የሻጠውን የመገናኛ ሬዲዮ አወጣና ተነጋገረ።ከሰዓታት በኋላ፣አካባቢው በልዩ ሃይሎች ተከብቦ፣«ፀረ-ሰላም»ኡዋ ልጅ በቁጥጥር ስር ዋለች።

«ለካንስ፤ሰላይ-እንደዚህ-እንደአሸን ፈልቷል?» ለመሞት አንድ ሃሙስ የቀራቸው ባልቴት፣በምሬት ተናገሩ።

ልቦናዬ ወደዚህ ኢንተርኔት ቤት፣«DV ሙላ!» ብሎ ሲልከኝ፣ለምን እንደነበር የገባኝ ቆይቶ ነዉ።የመንግስታችንን «ፀዴ» ስራ እንድመለከት ተከሰትኩ።

ከፀሃዩ መንግስታችንና ከDV በላይ የሚያስገርሙ ነገሮች፣በዚህች ምድር ላይ ከወዴት ይገኛሉ?

ግፈኛ መንግስታችንና DV ለዘላለም ይኑሩ¡¡

__

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here