ከአኦትይፕ (ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት)
ታህሳስ 9 ፤ 2010 ዓ ም
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ኢትዮጵያ ላይ በሰፊው በመካሄድ ላይ ያለውን ተቃውሞ በትክክል መረዳት ያስፈልጋል። ምክንያቱን በትክክል ሳይረዱ መፍትሔ ማግኘት አይቻልምና። ሕዝቡ በየሰላማዊ ሰልፉ በግልፅ የሚለውንና በየግሉ የሚያንፀባርቀውን በትክክል መረዳት ያስፈልጋል። በመላው አገሪቱ በተለይም በኦሮምያና በአማራ ክልል እየተካሄዱ ያሉት የሕዝብ ተቃውሞዋች በቀጥታ የህወሃት የበላይነት የሚቃወሙ እንጂ ይህ ወይንም ያኛው ብሔረሰብ ከክልላችን ይውጣልን የሚል የሕዝብ ተቃውሞም የለም። በሰፊው የሚሰሙት መፈክሮችና አስተያየቶች የሚያንፀባርቁት ይህን እውነታ ነው። በሰፊው የሚባለውም ”ወያኔ ሌባ ነው፤ ወያኔ ይውደም፤ ወያኔ በቃን፤ አማራ ኬኛ፤ በኦሮሞ ወንድሞቻችን ለይ የሚደረገው ግድያ ይቁም ወዘተ” ናቸው። የህወሃት አገዛዝም ይህን ሀቅ በግልፅ እንዲሰማ ባለመፈለጉና ደጋፊዎቹ ምዕራባዊያን በግልፅ እንዲሰሙበት ስላልፈለግ፤ ሰላማዊ ተቃውሞዎችን በአመፅና በግድያ እያፈነና ነገር ግን ችግሩን የብሔር ግጭት ለማስመሰል በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች በህወሃት ተንኮል የተጫረው ችግር ህወሃት እየተነሳበት ያለውን ተቃውሞ ለምዕራባዊያኑ እንደማስረጃ የሚጠቀምበት አንዱ ዘዴ ነው። እኔ አገሪቶን ካልገዛው አንዱ ብሔር ተነስቶ ሌላውን ብሔር ይጨፈጭፋል የሚል የፀጥታ ስጋት መፍጠር ነው። ለምዕራባዊያን የፀጥታ ጉዳይ ከዲሞክራሲና ከሰብዓዊ መብት በላይ ነው። ህወሃት ይህን በሚገባ ጠንቅቆ ያውቃል። የሕዝቡን የተቃውሞ አጀንዳ ህወሃት ሊጠልፈውና ሊጠቀምበት አይገባም። ከጥቂት ወራቶች በፊት አባይ ፀሀዬ አገሪቷን ሊያቅጥል የሚችል እሳት ከዳር ዳር ማስነሳት እንደሚቻልና አገሪቶን ከሩዋንዳ ወደባስ እልቂት ማስገባት እንደሚቻል በግልፅ ሲደነፋበት የነበረ ጉዳይ ነው። ይህንን ኢትዮጵያ ላይ እየመጣ ያለውን ከባድ አደጋ ለመከላከል የአማራና የኦሮሞ ትብብር እጅግ መጠንከር ይኖርበታል። ኢትዮጵያንና ሕዝቡን ለማዳን ትልቁ ዕዳ በኦሮሞና በአማራ ላይ ወድቋል። ይህ ጊዜ የማይሰጠው ይደር የማይባል ከባድ ኃላፊነት ነው። ጊዜው ካለፈ በኃላ ቢፀፀቱ የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም ነው።
ህወሃት ትልቅ የተንኮል ዘዴና ልምድ ያለው ድርጅት ነው። ዋና ዋናዎቹ የህወሃት አመራሮች የኒኮላይ ማካቬሊን መፅሀፍ ተንተርሰው የሚተኙ ሰዎች ናቸው። ማካቬሊ ከአምስት መቶ ዓመት በፊት በአስራ አምስተኛው የጨለማና የድንቁርና ከፍለ ዘመን አንድ ገዢ ሕዝብን እንዴት እያሞኘ፣ እያስፈራራና እያናቆረ ሥልጣኑን ማራዘም እንደሚችል የፃፈው ለህወሃት መሪዎች ማንፌስቶ ሆኖል። በህወሃት መሪዎች ዓይን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምስት መቶ ዓመት በፊት እንደነበረው የኢጣሊያን ሕዝብ ዓይነት ነው። የህወሃቶችም ትልቁ ድንቁርናም ይሄው ነው። ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛቹህ ካልሆነ በቀር ይህ አሁን በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚሰራ አስተሳሰብ አይሆንም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልፅ እየጠየቀ ያለው የህወሃት የዘረፋ፣ የግፍና የአፈና ሥርዓት በቃን ነው። ህወሃት ደግሞ የሚፈልገው ሌብነቱንና ዘረፋው መቀጠል ግን ሌባ ብላችሁ መቃወም አትችሉም ዓይነት የልብ አድርቅ ድርቅና ነው። ሌባ ካላችሁኝ ገላለው አስራለሁ ይህም ካልበቅ አገሪቷን በእሳት አነዳለሁ ነው። ህወሃት የመግደልና የማሰር የበላይነቱን እንደ ጥንካሬ በመቁጠር አገዛዙን ማራዘም ችሎል። አሁን ግን ሕዝቡ ሞትን የማይፈራበት ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። ይህንንም የሕዝቡን ከፍተኛ ጥንካሬ ለማኮላሸት ህወሃት በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ የብሔር ግጭቶች ለመጫር ተንቀሳቅሷልም እየተንቀሳቀሰም ነው። አንዳንድ የወያኔን ተንኮል በጥልቅ ያልገባቸው ወይንም በራሳቸውን የፖለቲካ አመለካከት የታጠሩ ወይንም ህወሃትን ደፍሮ መጋፈጥ የፈሩ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ምሁራኖች አሁን በአገሪቷ ላይ ያለውን ችግር የብሔር ግጭት ነው በማለት የህወሃትን የስውርና የተንኮል አጀንዳ ሰለባዎች እየሆኑ ነው። ሕዝቡ በግልፅ የሚለው ግን ሌላ ነው። አሁን ያለው ተቃውም በሕዝብና በህወሃቶች መሀከል ነው። የሕዝቡ ድምፅ ይሰማ። ህወሃት የሕዝብ ተቃውሞውን የብሄር ግጭት እንዲሆን በግልፅና በስውር አየጣረ ይገኛል። ለዚህም ስውር ተንኮሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ምሁራኖች የህወሃትን የስውር ተንኮል በግልፅ እያስተጋቡ የሕዝቡን የተቃውሞ ጥያቄ ሊያለባብሱት ይምክራሉ። እንደውም በተቃራኒው መንገድ በአገራችን ኢትዮጵያ ከሕዝቡም፣ ከምሁራኖቹና ከፖለቲከኞቹ እየታየ ያለው የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብ መወያየትና መተባበር ነው። ይህ ክስተት እጅግ እያስደነገጠ ያለው ህወሃቶችን ነው። ለምሳሌም የህወሃት ደጋፊ ሚድያዎች ይህንን ሂደት የሚዘግቡበትን መንግድ መገምገም ይቻላል። ግጭቶችን ማባባስ ነገር ግን ትብብሮችን የማንቋሸሽና የማሳነስ ዓይነት አካሄድ ነው።
ህወሃቶች የአናሳ አገዛዝ ቀጣይነት የሌለው መሆኑን ገና ከጅምሩ ያውቁታል። ለዚህም ነው ዓይን ያወጣ የዘረፋ ድርጊቶቻቸውን ገና ከጅምሩ ያጧጧፉት። ብዙ እንደማይቆዩ በሚገባ ያውቁታል። በእውቀት፣ በቴክኖሎጂና በኃይል ግዙፍ የነበረው የደቡብ አፍሪካ የጥቂቶች አገዛዝ በደቡብ አፍሪካ ሕዝብ እልህ አስጨራሽ ትግል ሊገረሰስ ችሏል። ይህንን ህወሃቶች በሚገባ ያውቁታል። ነገር ግን እስከሚቻለው ድረስ ለመቆየት የሚቻላቸውን ተንኮል ሁሉ ለመፈፀም ዝግጁ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ህወሃቶች የበላይነታቸውን ለማቆየት አደገኛ መንገድ እየተከተሉ ነው። ይህም በአገሪቷ ውስጥ የብሔር ግጭቶችን መቀሰቀስና ማፋፋም መሁኑ በግልፅ እየታዩ ያል ክስተቶች ናቸው። የህወሃት ታክቲክ አድጓል። ብሔሮችን ከማናከስ ወደ ግልፅ ግጭት ማስገባት ተሸጋግሯል። አገሪቷ ላይ የፀጥታ ችግር በመፈጠር ህወሃቶች ልዮ ችሎታና የበላይነት አለን ብለው በሚያምኑበት የወታደራዊና የኃይል አገዛዝ በሰፊው በመጠቀም ሕዝባዊ ተቃውሞውን ለማፈን ነው። በሱማሌና በኦሮሚያ ወሰንተኞች ላይ የተሳካላቸው ቢመስልም በሌሎች አካባቢዎች በተለይም በኦሮሞና በአማራ አካባቢ የህወሃት የተንኮል ዘዴ የተነቃበት ስለሆነ የአማራና የኦሮሞ መናቆርም ሆነ መጋጨት ለኢትይጵያ ሕዝብ ትልቅ መከራ እንደሆነና እንደሚሆን ግንዛቤ ላይ እየተደረሰበት ያለ ጉዳይ በመሆኑ አሳሳቢ የሆነ የብሔር ግጭት የለም። አነስተኛ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ ልዮነቶችን በሰለጠነ መንገድ በመወያየት መፍታት እንደሚቻል በሕዝቡም፣ በምሁራኖቹም፣ በፖለቲከኞቹም ሆነ በተቃዎሚዎችም መሀከል ጥሩ አዝማሚ እየታየ ያለበት ሁኔታ ነው። ይህ በጎ አገራዊ አዝማሚያ ግን በህወሃቶች ዘንድ ትልቅ ስጋት የፈጠረ በመሆኑ የትብብር መንፈሱን ለመስበር ህወሃቶች አርፈው እንደማይቀመጡ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። በቅርቡ የኦሮማውና የአማራውን የመተባበር መነሳሳት የሚጎድ ክስተት በህወሃቶች ሊፈፀም እንድሚችል መጠበቅና በዚህም መደናበርም ሆነ መደናገጥ አይገባም። መዘናጋትም አይገባም። በአሁኑ ወቅት የአማራና የኦሮሞ የትብብር መንፈስ ለመስበር ህወሃቶች የተለያይ የፓለቲካ አጨቃጫቂ አጀንዳዎች በመቅረፅ ሕዝቡን ለመከፋፈልና ውዥንብር ለመፍጠር እየጣሩ ነው። ሰለ መንግስት፣ ስለ ፌደራሊዝም፣ ስለ ቋንቋ፤ ስለ ብሔር ግጭት፣ የከተማ ፕላን፣ ስለ ታሪክ ወዘተ በማለት የውይይት መድረኮችንን እዚም እዛም በመፍጠርና ልዩነቶችን በማናፈስ፣ በማስተጋባትና በማጋነን የሕዝብን የትብብር መንፈስ ለማዳከም እየዳከሩ ነው። በአሁኑ ወቅት የውይይት አጀንዳ መሆን የሚገባው ዋናው የአገሪቷ ችግርና ዋናው የሕዝቡ ጥያቄ የሆነው የህወሃትን የበላይነት እንዴት ይወገድ የሚል እንጂ ሌላ ጥያቄዎች አይደሉም። በሌሎች አገራዊ ጥያቄዎች ትክክለኛና ግልፅ ውይይቶች ማድረግ የሚቻለው የህወሃት የበላይነት ተወግዶ በእኩልነትና በነፃነት በሚደረጉ ውይይቶች ሲኖሩ ብቻ ነው። በከባድ አፈናና በፍርሀት ላይ ያለ ህዝብም ሆነ ምሁር ግልፅና ነፃ ውይይት ሊያደርግ አይችልም። ስለዚህ ዋናው የአገሪቷ ችግር የህወሃት የበላይነት ሲሆን፣ የሕዝቡም ዋና ጥያቄና የመታገያም ሆነ የመወያያ አጀንዳ የሆነው የህወሃት የበላይነት ይወገድ የሚለው ነው። ስለዚህ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ አንድ መሆን ይገባዋል። ይህም የህወሃት የበላይነት ይወገድ የሚል ነው።
የአማራና የኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጎጂ ንትርክ ሳይሆን ጤናማ ውይይትና ትብብር የሚጎለብትበትን መንገድ የሚያበረታቱ ሀሳቦችን በማፈላለግና በማሰራጨት፤ በአማራና በኦሮሞ ልዒቃን መሀከል የሚደረገው የታሪክ ንትርክን በተመለከት የታሪክ ባለሙያዎች በሰለጠነ መንገድ በመከባበር እንዲወያዩበት የሚገባ መሆኑን እያበረታታ። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ ግን የአማራና የኦሮም የፓለቲካ ልዒቃን የታሪክ ንትርኩን ለታሪክ ባለሙያዎች በመተው በአንገብጋቢው የወቅቱ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በማተኮር የህወሃትን አገርንና ሕዝብን የሚያጠፋ ድርጊት ለመቋቋም የሚችሉበትን የትብብር ጉዳዮች ላይ ጥረት ማድረግ ነው።
ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት
AOCPP (Amhara and Oromo Cooperation Promotion Project)
Contact: aocpp2016@gmail.com
____
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ይላኩ። editor@borkena.com