ቦርከና
ታህሳስ 10፤ 2010 ዓ ም

የኦፒዲዮ አመራሮችን(ለማ መገርሳን እና አብይ አህመድን እንደሚያካትት ተገምቷል) በህወሓት የተቀነባበረ ነው የተባለ የግድያ ሙከራ እንደከሸፈ ተሰምቷል።
እስካሁን ዜናውን ከሌሎች የዜና ተቋማት ማረጋገጥ ባይቻልም ተቀማጭነቱ በኔዘርላንድ የሆነ አክቲቪስት ገረሱ ቱፋ ተጠርጣሪ ናቸው የተባሉትን ሁለት ግለሰቦች መታወቂያ በማያያዝ በማህበራዊ ድረ ገጽ ዘግቧል። ገረሱ “በኦሮሞ የመብት ተሟጋችነት” የሚታወቅ ሲሆን በሃገር ቤት በተለይም ደሞ በኦፒዲኦ ውስጥ ምንጮች እንዳሉት ይገመታል። ከዚህ በፊትም መረጃዎችን በማካፈል ይታወቃል።
ገረሱ በመካሄድ ላይ ያለውን የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በሚመለከት ሰሞኑን ህወሓት በሃሳብ እንደተሸነፈ እና ኦፒዲዮ እና ብአዴን ተመሳሳይ አቋም ይዘው እንደተገኙ መዘገቡ ይታወሳል።
በኦፒዲዮ አመራሮች ግድያ ሊፈጽሙ ነበር የተባሉት ተጠርጣሪዎች ስም ዉብሸት ላውጋው ወልደሰማያት እና ባዮ ትህትና ዘሩ እንደሚባሉ የገረሱ ዘገባ ይጠቁማል። ነገር ግን ግድያው ለማስፈጸም ታስቦ ስለነበረበት ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮች የቀረበ ዝርዝር የለም።
በኦፒዲኦ አመራር ላይ ታስቦ የነበረውን የግድያ ሙከራ እንዲያስፈጽሙ ህወሓት ከደህንነት መዋቅር ውስጥ መልምሏቸዋል የተባሉት የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይመስላሉ። የፖለቲካ ተንታኞች ለህወሓት እጂግ አስፈሪ እየሆነ የመጣው እና እያንሰራራ ያለውን የአማራ እና ኦሮሞ አንድነት በማጨናገፍ በሁለቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የታሰበ ነው በማለት የህወሓትን ደባ ያጋልጣሉ።
ህወሓት እንደዚህ አይነት እርምጃ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል የሚገመት ቢሆንም በተንታኞች በዚህ ፍጥነት እዲህ አይነት ርምጃ በማቀናበር ቀውስ ወደሚያባባስ ሁኔታ ለመፍጠር ይፈልጋል የሚል አስተሳሰብ ያለ አይመስልም ነበር።
——
ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ማድረግ አይርሱ