spot_img
Friday, July 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትለእውነተኛው ሃገራዊ እርቅ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ወቅታዊ ኃላፊነትና ግዴታ!(በእውነቱ ሕይወት)

ለእውነተኛው ሃገራዊ እርቅ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ወቅታዊ ኃላፊነትና ግዴታ!(በእውነቱ ሕይወት)

ከበእውነቱ
ታህሳስ 12 ፤ 2010 ዓ ም

በPDF ለማንበብ ይህንን ይጫኑ

ሁላችንም ተወልደን ባደግንባት ሃገራችን ውስጥ እየሆነ ያለው የመግደልና የመገደል ትርምስ፣ እንኳን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ይቅርና ለዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ ሳይቀር አስገራሚ የመነጋገሪያ ዋና አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፤ ፖለቲከኞቻችንና ‘መንግሥትም’ ለተፈጠረው ችግር ያልሆነ ምክንያት በመስጠት የመወነጃጀሉን ሥራ ተግተው ቢቀጥሉበትም መገዳደሉ ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰጠ ልዩ ትእዛዝ መሰረት የበለጠ ተባብሷል።

የክርስቲያን ደሴት እየተባለች ለበርካታ ዘመናት የተዘመረላት ሃገራችንም፣ መገለጫ ባህሪው ፍቅር የሆነውና ሰይፍ ማንሳት የማያውቀው የመጽሐፍ ቅዱሱ እውነተኛው የክርስትና ሕይወት ምልክት እንዳልነበረን ተግባራችን እየመሰከረብን ነው፤ በሰው ልጆች የታሪክ ሂደት ውስጥ ክርስቲያን ሲገደል እንጂ ሲገድል ታይቶ ተሰምቶ አይታወቅምና፤ ይህን ስል ግን በክርስትና ስም የሚነግድ አስማሳይ የለም እያልኩ አይደለም፤ የማወራው ለሌሎች ሰዎች በረከትና ጥቅም ጭምር እንድንኖር ስለሚያደርገው ስለ እውነተኛውና ተግባራዊ ስለሆነው የክርስትና ሕይወት ነው።

ወገኖቼ እባካችሁ እናስተውልና ተደማምጠን ለገጠመን የሕይወት መጠፋፋቱ አፋጣኝ እርምጃ እንውሰድ? የውጭ ጠላት ያልደፈረን እንዴት እርስ በርሳችን በዘር በሺታ እንደፋፈር? ይህ የዘር ጉዳይ በራሱ በመንግሥት በኩል ገና ሲጀምር የሚያስከትለውን ችግር ቀድመውና አሻግረው በመመልከት ስጋታቸውን ገልጠውልን የነበሩትን የእነ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያምንና የሌሎችን መንፋሳዊ አባቶችን ምክር ባለመስማታችን ይኸው በታሪካችን ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ደረስን፤ ሲሰማና ሲታይ ለኅሊና የሚከብድና ልብን የሚሰብር የክፉ ሰዎች ሥራ! ይህ ተግባር አጥፍቶ ከመጥፋት በቀር ምን ዘለቄታዊ ጥቅም ያመጣላቸው ይሆን? አገርን/ሕዝብን ሁሉ ገሎ መሞት ፋይዳው ምን ለመሆን እንደሆነ አልገባ አለኝ!

የሆነው ሆነ! የሞቱትም ላናገኛቸው አፈር ለብሰዋል፣ አሁን ግን መጠየቅ ያለበን ጉዳይ በባሰ መልኩ እየተካሄደ ያለውን የማያባራ የእልቂት ጎርፍ እንዴት አድርገን ገደብ እናብጅለት? የሚለው ጥያቄ መሆን አለበት፤ ለዚህ ጥያቄ ታዲያ ተገቢና የማያዳግም አፋጣኝ መልስ ለመስጠት ይቻል ዘንድ በጋራና በግል ሊወሰዱ የሚገባቸውን ኃላፊነቶች ከዚህ በታች ሳቀርብ ለሁላችንም ይበጃል ብየ በማሰብ ስለሆነ የሚመለከታችሁ ሁሉ በቅንነትና በማስተዋል ተረድታችሁኝ የየራሳችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ በታላቅ ወገናዊ ፍቅር እለምናችኋለሁ፤ ከዚህ አሳዛኝና አሰቃቂ ውድቀታችን ካልተማርን መቸውንም ቢሆን አያልፍልንምና፡

1. በስልጣ ላይ ላለው መንግሥት /ኢሕአዴግ/

ለትግራይ ሕዝብ ሙሉ ውክልና አለን ለምትሉ ለሕዝባዊ የወያኔ አርነት ትግራዊ ድርጅት:-

ለ17 ዓመት በርሃ ለበርሃ የተንከራተታችሁባቸው እነዚያ የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ አመታት ትዝ እንዲላችሁ ወደ ኋላ በትዝታ ልመልሳችሁ፣ ራሃባችሁን እየተራበ፣ ሲያገኝ ደግሞ ከልጆቹ አፍ እየነጠቀ በማብላትና እየሸሸገ ከደርግ የጥይት በረዶ በማስመለጥ ለዚህ ባበቃችሁ የትግራይ ሕዝብ ላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠላትነት እንዲነሳበት የማድረግ ሥራ እየፈጸማችሁበት እንደሆነ ተገንዝባችሁ በአስቸኳይ ያበላሻችሁትን ለማረም ብትሞክሩ መልካም ይሆናል፤ በዚህ ወልዶ ባሳደጋችሁና ‘እንኳንም ካንተ አብራክ ተወለድን’ በሚል አሳፋሪ የማታለያ ንግግር ስታስጨፍሩት በነበረው ሕዝብ ስም አገር በጉልበት እየገዛችሁ፣ ኢኮኖሚውን አናስነካም በማለት በባላይነት እየተቆጣጠራችሁ፣ የሌሎችን ክልሎች የአስተዳደር ስልጣን ሳይቀር በበላይነት እየመራችሁ፣ አገሪቱ ያፈራቻቸውን እውቅ ጋዜጠኞችንና ያገር ባለራእዮችን ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እስር ቤት ማጎር ብቻ ሳይሆን ሰዎች በዘራቸው ምክንያት እንዲሰቃዩ በማድረጋችሁ ምክንያት ጥቃትና ሸፍጥ የማይወደው ተበዳይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በስሙ የወንድሞቹን ደም በማፍሰስ እየነገዳችሁበት ባለው የትግራይ ሕዝብ ላይ እንደተናካሽ አውሬ ሆ ብሎ በመውጣት የበቀል እርምጃ በወሰደ ነበር፤ ነገር ግን በደሉ እየተፈጸመበት ያለው በተወሰኑ የቤተ ሰብ ቡድን አባላትና አንዳንድ እንጀራ በበሉ ሰዎች አማካኝነት ብቻ እንደሆነ በመረዳቱ እስከ አሁን ድረስ በሳልነቱንና ከእናንተ የበለጠ አስተዋይነቱን በማረጋገጥ እራሱን ገዝቶ ቆይቷል፤ ታዲያ ለዚህ ሕዝብ የሚገባው ትልቅ ክብር እንጂ ግድያና ጭፍጨፋ አልነበረም፤ ስለዚህ እንደ ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን እኔም ዛሬ እንደ ሰው በማይዋሸው በአምላካችን በእግዚአብሔር ቃል መሰረት “ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሷት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም” (ዘኊልቍ 35፡33) በሚለው መሪ ቃል ቆምና ረጋ ብላችሁ ለማንም ሳይሆን ለራሳችሁና ለትግራይ ሕዝብ የወደፊት የሕይወት እጣ ፋንታ (ለራሳችሁ ልጆች ጭምር) ስትሉ እንደ ባለ አእምሮ ሰው አስባችሁ አፋጣኝ የመፍትሄ ውሳኔ እንድትወስዱ ወገናዊ ያገር አድን ምክሬን በአክብሮትና በምወደው የትግራይ ሕዝብ ስም እለግሳችኋለሁ! የትግራይ ሕዝብም በሌላው ሰፊ የኢትዮጵያ ወገንህ ላይ በስምህ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በደል እየሰማህና እያየህ ዝም ካልክ ከበዳይ (ከገዳይ) ጋር የመስማማት ምልክትህ ስለሚሆን አንተም የትግራዊ ወገኔ ሆይ ቆም ብለህ በማሰብ ለመፍትሔው ተነሳ! ተመካከርና ተግባራዊ አቋም እንድትወስድ አሳስብሃለሁ።

• ለኦሮሞውና ለአማራው ሕዝብ ተወካዮች ነን ብላችሁ በመንግሥትነት ያላችሁ ኦሕዴዶችና ብአዴኖች:-

በተገኛችሁበት ሕዝብ ሳይሆን ለሕወአት በሕወአት ቸርነት ለተገኛችሁበት ሕዝብ ወኪል ለመሆን ታዛዥ የሆናችሁ እናንተ ወገኖቼ ሆይ! በእነዚህ ያገሪቱ አውራ ሕዝቦች ላይ አሁን እየሆነ ያለውን ግፍና በደል እያያችሁ በእውነት እስከ አሁን ድረስ እንዴት ዝምና ቸል የማለት ጠንካራ አቋም ልትይዙ ቻላችሁ? እሺ እስቲ እንዲህ ላስብ ይፈቀድልኝ! በመጀመሪያ በሕወአት የ17 ዓመት የበርሃ ልምድ (ታግየ ያገኘሁትን ድል ስለሆነ ያካፈልኳችሁ የምለውን ብቻ ስሙ) ምክንያት አፋችሁ ሊለጎም እንደሚችል ልመን፤ ነገር ግን በ25 ዓመት ውስጥ ለተሻለ የጋራ እድገትና ቋንቋ ከማይችሉ አልሞ ተኳሾች እንድትወክሉት የተደረጋችሁትን የሕዝብ ሕይወት ለማትረፍ መንቀሳቀስ አለመቻላችሁ ባዶ እጁን በመሆን ለመብቱ እየጮኸ ከሚሞተው ጀግና የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ ውስጥ የተፈጠራችሁ አላሰመስላችሁም፤ ስለዚህ ለእናንተም ምክር አለኝና ስለሚጠቅማችሁ እባካችሁ ስሙኝ! የተፈጸመውን በደልና ግፍ በእውነተኛ ንስሃ ሸፍናችሁ አሁን ዛሬ በአለቆቻችሁ ትእዛዝ ጥይት እየወደቀ ያለውን ወገናችሁን ለማትረፍ መግደል በቃ ብላችሁ በመነሳት የተረፈውን ወገናችሁን ከሞት እንድትታደጉት እየሞተ ባለው ወገናችን ስም እጠይቃችኋለሁ???

• ለሌሎች ለተለያዩ የብሔር ብረሰብ ተወካይ ድርጅቶች እና የኢሕዴግ መንግሥት ዋና አባላት:-

ምናልባት እናንተ የወከላችሁት ሕዝብ እየተገደለ ላይሆን ይችል ይሆናል፤ ግን በጋራ አገር ውስጥ እየኖርን ጉልበተኛ ክንዱን በሌላው ወገን ላይ ሲያሳርፍ ተመልካች ብቻ መሆን ይህ የትእቢት እጅ ነገ በእናንተ ላይ ላለመዘርጋቱ በቂ ዋስትና ሊሆናችሁ ፈጽሞ አይችልምና በብሔረሰብ ተዋጽዖ ባገኛችሁት ጥርስ አልባ ስልጣን አትታለሉ! ማለት እወዳለሁ፤ ስለዚህ የተጋባሃውና ጎረቤትህ በመሆን ለበርካታ ዘመን አብሮህ የኖረው ኦሮሞው፣ጋምቤላው፣አማራው፣ ጉራጌው፣ ሃድያው፣ ትግሬው፣ አፋሩ፣ ሱማሌው፣ ከምባታው፣ ሌላው ወገን ሁሉ ወዘተ ሲገደል ዝም አትበል! ይህ የትእቢተኞችና የዘረኝነት ወረርሽኝ በሽታ ነገ ባንተ ላይ ላለመድረሱ ዋስትና የለኸምና!!!

2. በአገራችን ውስጥ እና በውጭ አገር ለምትገኙ ለኢትዮጵያውያን ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት:-

የቤተ ክርስቲያን ዋና ሥራ አመጸኛውን የሰውን ጠላት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የቃሉን ሰይፍ ታጥቃ ፊት ለፊት በመግጠም ወደሞት የሚነዱትን ሁሉ መታደግ ነው፤ ታዲያ በምድራችን ውስጥ እየሆነ ባለው የርስ በርስ መጨፋጨፍ ሒደት ላይ ቤተ ክርስቲያን ልታደርገው የሚገባትን ተግባራዊ የማስታረቅ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ተመልካች ብቻ የሆነችው ለምንድነው? በጎውን ማን ያሳየናል በሚል የህይወት ምጥ ለተያዙ ሰዎች ሁሉ በተግባር ጨውና ብርሃን ልትሆን የተሾመች ባላደራ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ታዲያ ሰው እየሞተ እያየች በጸሎት በታገዘ ተግባራዊ ሥራ መገለጥ ሲኖርባት ዝምታን መምረጧ ከሰማይ ከተሰጣት ሃላፊት አንጻር ባህሪዋ አይደለምና ዝምታዋን ሰብራ የማስታረቁን ሥራ ቀን ሳይመሽና በር ላይከፈት ሳይዘጋ ውክልናን ከድፍረት ጋር በሰጣት ጌታ ስም መጀመር ይኖርባታል።

አፈጻጸሙን በተመለከተ በአገር ቤትና በውጭ አገር ያሉ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት ተመልክተውና በከፍተኛ የስልጣን ሃላፊነት ላይ ከሚገኙ ክርስቲያን ባለስልጣናት ጋር በግልጽ ተነጋግረው በመወሰንና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የተሳተፉበት የጸጥታ ጎዞ ወደ አገሪቱ ቤተ መንግሥትና ፓርላማ በመሄድ መንግሥት ሊያደርገው የሚገባውን ሃላፊነት በእውነትና በፍቅር በመንገር መሪዎች ድርሻችውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብየ አምናለሁ፤ በውጭ አገር ያላችሁ ደግሞ በአካባቢያችሁ የሚኖረውን ወገን በሙሉ አስተባብራችሁና ወደ ኢምባሲያችሁ በመሄድ መናገር የሚገባችሁን በፍቅር ከጸሎት ጋር ብትናገሩ ቢያንስ ከህሊና ወቀሳ መዳን ይቻላል።

3. ለአማራውና ለኦሮሞው ሕዝብ በሙሉ፡

ሁላችሁም እየሞታችሁለት ያለውን የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ እውን ለማድረግ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ላይ የአገር ቀሪ ሃብት በሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ የምትወስዱትን የማፈራረስ ድርጊት በማስተዋል ብታዩት መልካም ነው፤ ነገ ተመልሰው ከመላው ወገናችሁ ጋር የናንተው ሃብት ናቸውና፤ ሌላው አንድ ነን በምትሉት መፈክር ላይ በአገር ቤትም በውጭም የሚታየው ሰፊ ክፍተት አንዳችሁ ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያዊነት ምልክት ከሆነው ባንዲራ ጋር የሙጥኝ ስትሉ ሌላው ወገን ደግሞ ሰልፍ በወጣ ቁጥር መለያ ምልክቱ ከዛሬ 25 ዓመት በፊት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለተጋዳላይ ኩማ ደመቅሳ ሰሜን ሸዋ በርሃ ላይ ባደራ ያስረከቡትን ባለዛፍ ባንዲራ ለብሶ ሲወጣ መታየቱ አንድነቱን ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፤ ለምድን ነው እነ ዶ/ር ቶሎሳ በኩራት የሚዘምሩለትን ኢትዮጵያዊነትን አብዛኛው የኦሮሞ ምሁራን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሳይቀር ላለማንበብ የሚዘሉት? ከወዲሁ ያልተሠራ የቤት ሥራ ፈተና ሲደርስ የማይወለድ የወንድ ልጅ ምጥ ነው የሚሆነውና ሳይቃጠል በቅጠል ማለት እወዳለሁ፤ ይህን ስል ለመንቀፍ እንዳልሆነ በአጎቴ የወለጋ ደም በቅድመ አያቴ ደግሞ የወዳጆ ዘር ስለሆንኩ እራሴን ለመንቀፍ የሚያስችል ኢትዮጵያዊ አቅምና ወኔ የለኝምና አባባሌን በጥሬው ወስዳችሁ ለመቆርጠም እንዳትሞክሩ አደራ!

4. በምድራችን ውስጥ እየሆነ ባለው የእርስ በርስ መዋደቅ ምክንያት በሃዘን፣ በለቅሶ፣ በጭንቅና በምጥ ላይ ላላችሁ ወገኖቼ በሙሉ/በያላችሁበት/፡

ወልዶ ባሳደገን ወገናችን መካከል እየተፈጸመ ያለው ትርምስና የሕይወት መጠፋፋት በእርግጥ ተሰምቶና ታይቶ የማይታወቅ የታሪክ ውድቀት ነው፤ ይህም ድርጊት የሰው ልብ ክፉ ነው የሚለው የእግዚአብሔር አምላክ ቃል በራሳችን መካከል ተወልደው ባደጉ ወገኖቻችን ጨካኝነት ተግባራዊ ሲሆን እያየን ነው፤ በዚህ እጅግ አሳዛኝ በሆነ ወቅትም እያንዳንዳችን ከስሜታዊነት በጸዳ መንፈስ ከዚህ ከገጠመን ክፉ ነገር መገላገል የምንችልበትን
ሥራ በጋራ መሥራት ይኖርብናል ብየ አምናለሁ።

ክፉዎችን በክፋት ሳይሆን ግብዝነት በሌለው ፍቅር ማሸነፍ ይቻላል፤ አዎ! ይህን ዋና የሆነ የሕይወት መመሪያ ብዙ ሰዎች እንደሞኝነት ሊቆጥሩት እንደሚችሉ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሁላችንም በህይወት ትምህርት ቤት ገብተን እንደተማርነው ክፉዎች ቢዘገይም ያንኑ የዘሩትን ክፋት እንደሚያጭዱ፣ ቅን ሰዎች ደግሞ በኖሩበት ቅንነት ምክንያት ከራበውና ሥጋ ከሚወድ በላተኛ አንበሳ መትረፍ ብቻ ሳይሆን የሞቀና ጣፋጭ የእረፍት ጊዜ እምነት በሚባል ሰማያዊ
ስጦታ ማሳለፍ እንደሚችሉ ከእምነት አባቶቻችን እንማራለን/ዳን 6፡22/

ስለዚህ ይህን በፊታችን የተጋረጠብንን የእርስ በርስ መተላለቅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማቆም የምንችለው በግልና በጋራ በምናደርገው የሰከነና ከቂም በቀል ነጻ በሆነ የባለቤትነት ተሳትፎ ብቻ ነው፤ በመሆኑም መንደድ መቃጠሉን፣ መስደብ መራገሙን፣ መማል መገዘቱን፣ መፎከርና ቆሞ መተኮሱን ቆም በማድረግ መልካምና ለሁላችንም የሚጠቅመን ሰማያዊ ሰላም በምድራችን እንዲመጣ ሃላፊነታችንን በግልና በጋራ ለመወጣት አሁንኑ እንነሳ፤ ይህን የዜግነት ግዴታችንንና ሃላፊነት ለመወጣት ጨክነን ብንነሳ የሚመጣውን የባሰ ጥቁር የመጠፋፋት ደመናን ገፈን መቅደድ ብቻ ሳይሆን በጋራ የጋራ አዲስ ታሪክ በምድራችን ላይ
መጻፍ እንችላለንና በዚህ ጉዳይ ላይ እንጨክን፤

ይህን በማድረግና በመጨረሻም መልካም በሆነ ውጤት ለመገለጥ እንድንችል ሁላችንም ብንሆን በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ተገቢ ትኩረት ብናደረግ ጠቅመን እንጠቅማለን ብየ አምናለሁ፤

• እውነተኛ በሆነው ነገር ላይ እንጂ አሉ በሚባል መረጃና ባልተረጋገጠ ጉዳይ ላይ ጊዜ ባናጠፋ
• ረጋ ብለን ሁሉን ነገር ጭምትነት በተላበሰ መልኩ በጥሞናና በማስተዋል ብናደርገው
• የምናስበውና የምንሠራው ተግባር ሁሉ ሰዎች በመሆናችንና ለሁላችንም የሚጠቅም በመሆኑ እንጂ ከምንም ጋር ባልተዛመደ መልኩ መሆን ይኖርበታል/ምሳሌ ከዘር፣ከቋንቋና ከሃይማኖት/
• ሁላችንም የፋኖ ክራር ምት ስንሰማ ወይም የቢራ ጠርሙስ ስንጨብጥ ከሚነቃቃ የስሜት ፈረስ ግልቢያ መጠንቀቅ ብንችል መልካም ይሆናል፤
• ትናንት የሥጋ አባቶቻችን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የሠሩትን ሥራ መቃብር ቆፍረን በማውጣት ከማሽተትና የሕዝባችንን የአብሮነት ታሪኩን ከማጠልሸት ይልቅ በፊልጵስዩስ 3፡13 ላይ እንደተባልነው በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ በሚለው መለኮታዊ ቃል እንመራ፤ የሕይወት ጉዞ ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይደለምና እንደሰው እናስብ፤
• የልባችን ሃሳብና ከዚህ ምንጭ በመፍለቅ የሚወጣው የአንደበታችን ቃል በእግዚአብሔርና በሰዎች ፊት ያማረና ሊጠቅም በሚችል መልኩ ቢሆን ተርፈን ሌላውን ወገን እናተርፋለን አንደበት የሚያቃጥል እሳት ነውና
• በአጠቃላይ በምድራችን ውስጥ ሕዝባችንን እያተራመሰና እየገደለ ያለውን የሞት መንፈስ ድል በማድረግ ሕዝባችን በሰላም የተሞላ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ ከቂም በቀል በጸዳ የይቅርታ መንፈስ ሁላችንም የእርቅ ዘር ከቤተሰባችን ጀምረን ለሁሉም ወገናችን እንድንዘራ ሰዎችን ሁሉ ከሞት ለማትረፍ ሲል እራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ በመስጠት ባዳነን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በተሰበረ ልብ ዝቅ በማለት እለምናችኋለሁ።

5. በውጭና በአገር ቤት ለምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊም ወገኖቻችን በሙሉ፡

• በታሪክ ጠንቅቃችሁ እንደምታውቁት የጋራ አገራችን የዘመናት መጠሪያዋ የክርስትና ደሴት የሚለው/እንደሚጋባ በቃሉ ባትኖርበትም/ ስም በመሆኑ አብዛኛው ትኩረቴ በዚሁ የጋራ ታሪካችን ላይ እንዲሆን ግድ ብሎኛልና በቅንነት ውሰዱልኝ፣
• እንደማንኛውም ዜጋ ሕገመንግሥቱ ለሁሉም የሚፈቅደውን የሰባዊና የሃይማኖት መብታችሁን ለማስጠበቅ የምታደርጉትን ሰላማዊ እንቅስቃሴ በበኩሌ የምደግፈው ጉዳይ ነው፤ ነገር ግን በስልምና ስም ሰይፍ አንስቶ እንደግራኝ ሙሐመድ አንገት በመቅላት ዓለምን ሁሉ በጉልበት ሙሰሊም ለማድረግ የሚደረገውን የእብዶችን ድርጊት በሊቢያ በርሃ እንደታረዱት ወንድሞቻችን
ነፍሴን ከማሳለፍ በቀር ኅሊናዬ ጨርሶ አይቀበለውም፤
• አቶ አሊ አብዶ የአዲስ አበባ ከተማን ሲያስተዳድሩ በነበረበት ወቅት የተፈጸመውን ኢፍትሃዊ የመስጊዶችና የቤተ ክርስቲያን ህንጻ ሥራ ፈቃድ አወሳሰንና በየሰፈሩ የተሠሩትን መስጊዶች ማየቱ ዓላማውን በእውነት ለእውነት በትክክል ለማየት ያስችለናል ብየ አምናለሁ
• አይደለም ኢትዮጵያውን ሙስሊም ወገኖቻችን ይቅርና የውጭ አገር ሙስሊሞች ሳይቀሩ ወደ ምድራችን ሕጋዊ በሆነ መንገድ በመግባት በድህነት ምክንያት ኑሮ የከበዳቸውን የደረሱ ቆነጃጅቶች በመወሸም ወይም በማግባት ካንዷ ስልጤ 3 ከሌላዋ 4 ልጆች የወለደ ናጀሪያዊ ገጥሞኝ በመረጃ ይዤዋለሁ፤ ታዲያ ይህን የመሰለውን ተግባር እኔ በቆምኩበት ላይ ሆናችሁ እንድታዩት እንጂ ሌላ ትርጉም እንደማትሰጡት አምናለሁ፤
• በአጠቃላይ የግልም ሆነ የጋራ መብት የሚከበረው የሌላውን መብት በማክበርና የዜግነት ግዴታን በጋራ በመወጣት ነውና በጋራ አገር በተረጋጋ ሰላምና ፍቅር አብረን ለመኖር ቅን እንሁን? ሁላችሁም ባትሆኑም የጥቂቶቻችሁ ሃሳብና ዓላማ አብሮ የሚያኖር ሳይሆን በሁላችንም ላይ አሁን እየደረሰብን ካለው መከራ የባሰ እንደሚሆን ለመገመት የግድ ነቢይ መሆን አያስፈልግምና።

ማጠቃለያ፡

አሁን ለገጠመን ችግር መፍትሄ ማምጣት የምንችለው ሁላችንም በጋራ ተነስተን በይቅርታ ልብ ለእውነተኛ እርቅ መሥራት ስንችል ብቻ ስለሆነ የሚጠቅመንን ይህን ሁሉን አቀፍ የሆነ ሃገራዊ እርቅ ለማምጣት ሁላችንም ተግተን መሥራት ይኖርብናል። እርቅ! እርቅ!! እርቅ!!! የሚሞተውን ወገን ለማትረፍ!!!!!!!
በቸሩ ቸር ይግጠመን

እውነቱ ነኝ ካለሁበት

ጸሃፊውን/ዋን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል ፤ eunethiwot@gmail.com
——
ማስታወሻ ፤ በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁት ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረ ገጹን አቋም አያንጸባርቅም። ነጻ አስተያየት ካለዎት በሚከተለው አድራሻ ይላኩ፤ editor@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here