ታህሳስ 13 ፤ 2010 ዓ ም
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ፍትህ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ አለው ስለሚባለው “ልዮ ጥቅም” ለመወሰን ዛሬ በፓርላማ በጠራው ስብሰባ ከተጀመረ በኋላ በኦህዴድ ተወካዮች ተቃውሞ እንደተሰረዘ ተሰማ።
የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ኦሮሞዎች ከሱማሌ ክልል በተፈናቀሉበት ፤ ዜጎች በግጭት ምክንያት ህይወታቸው እያለፈ ባለበት እና የክልሉ ሰላም ባልተረጋጋበት ሁኔታ “በልዩ ጥቅም” ጉዳይ ላይ ሕዝብ ሳናወያይ ተረጋግተን መወያየት አንችልም የሚል ሃሳብ ካቀረቡ በኋላ በርካታ ኦፒዲዎን ወክለው ፓርላማ ያሉ ተመራጮች ለሃሳቡ ያላቸውን ድጋፋ በጭብጨባ ካገለጹ በኋላ ነው ስብሰባው የተበተነው።
አቶ አባዱላ ገመዳ አስተያየት ሰጭዎች ያልተለመደ ባሉት ሁኔታ “በጉዳዮ መወያይበት ችግር የለውም” የሚል አቋም ይዘው እንደነበረም ተሰምቷል።
ኦሮሚኛ ተናጋሪ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተንታኞች እና ልሂቃን እንደሚሉት ህወሃት በፓርላማው በሕግ ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ በኩል ያቀረበው የውይይት ሃሳብ እየተፈጠረ ያለውን የብአዴን እና የኦህዴድ ካድሬዎች በማናቆር ህዝብ ለማጋጨት የተደረገ ሙከራ ነው ብለውታል።
በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኦሮሞዎች ቁጥር ከአጠቃላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ አምስት በመቶ ያህል ሲሆን ቀሪው አዲስ አበቤ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመምጣት አዲስ አበባ እንደከተመ እና በከተማዋ ለብዙ ትውልዶች እንደኖረባትም ይታወቃል።
———
የኢትዮጵያ ዜናዎችን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይ ማድረግ አይርሱ