ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት (አኦትይፕ)
ታህሳስ 13 ፤ 2010 ዓ ም
በአሁኑ ወቅት በመካሄድ ላይ በሚገኝው የኢህአዲግ ስብሰባ ህወሃት የኃይለማርያም ደሳለኝን የደቡብን ደኢህዲንን ሙሉ በሙሉና አንዳንድ የብአዲንና የኦህዲድን አባላትን ድጋፍ በማግኝት የሕዝቡን ጥያቄ በመርገጥ ህወሃት ስብሰባውን በድምፅ ብልጫ አሸንፎ ለመውጣት ይችላል። ይህ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብን ተቃውም አያቆምም። በኢህአዲግ ምክር ቤት አራቱም ድርጅቶች እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ዘጠኝ ተወካይ ያላቸው ሲሆን ውሳኔ የሚተላለፈው በአባላቶች የድምፅ ብልጫ እንጂ በድርጅቶች ድምፅ ስላልሆነ ሁልጊዜም የሚወሰነው በህወሃት የሚቀነቀን ሀሳብ ነው። ምክንያቱም ህወሃቶች የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ አንድ ስለሆኑና በሌሎች ድርጅቶች ደግሞ በጥቅም የተገዙ የህወሃት ታማኞች ስለሚገኙ በኢህአዲግ ስብሰባ ላይ ህወሃት በድምፅ ብልጫ ተሸንፎ አያውቅም፣ ሊሸነፍም አይችልም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢህአዲግ ስብሰባ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስ የረባ ውሳኔ መጠበቅ ሞኝነት ነው። ምክንያቱም ኢህአዲግ ማለት ፀረ ዲምክራሲያዊ የሆነ የህወሃት የበላይነት ማስጠበቂያ መሣረያ ነው። አብዛኛው የኢህአዲግ ምክር ቤት አባላት ለህወሃት ባደሩ፣ በሥልጣንና በጥቅም በተገዙ ግለሰቦች የተሞላ ነው። የህወሃት የበላይነት እንዲያከትም የሚፈልጉት የኦህዲድና የብአዲን አመራር በኢህአዲግ ምክር ቤት ውስጥ አሸንፈው ሊወጡ አይችሉም።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ኢትዮጵያ በተለይም በአማራና በኦሮሚይ ክልሎች ላይ በህወሃት ትእዛዝ እየደረሰ ያለውን የዜጎች ስቃይና እንግልት እያያቹት ነው። በሁለቱም ክልሎቹ የተነሳውን ፀረ – ህወሃት ተቃውሞ በሚገባ የተረዳችሁት መሆን አለበት። የተቃውሞዎቹ መሠረታዊ ጥያቄ የብአዲንና የኦህዲድ የአስተዳደር በደል ሳይሆን፤ የተቃውሞዎቹ መሠረታዊ ጥያቄ የህወሃት የባላይነት ይወገድና ኦህዲድና ብአዲን የህወሃት አገልጋዮች ወይም ሎሌዎች መሆናቸው ያብቃ ነው። ወገን እየሞተና እየተሰቃይ ያለው ለእናንተም ነፃነት እያለ ነው። ህወሃት እናንተን በመጠቀም ነገሩን ለማድበስበስና ለማደናገር ተቃውሞዎቹ በክልሎቹ ባልሥልጣናት የአስተዳደርና የአመራር ብቅት ማነስ የተቀሰቀሱ ናቸው በማለት የህዝቡን ተቃውሞ ወደክልሎቹ አመራሮች በመወርወር፤ የክልሎቹን አመራር በማተራምስ፤ በየክልሎቹ አመራር መሀከል ቅራኔዎችን በማባባስና በማናቆር፤ የህወሃት ታዛዥ አባላትን በየድርጅቶቹ በመጠቀም የበላይነቱን ለመቀጠል እየጣረ ይገኛል። ይህ የህወሃት መሠሪ ተግባር የነበረ ነው፤ ለወደፊቱም የሚቀጥል ነው። ለዚህ ግን በአሁኑ ወቅት መሣሪያ በመሆን ለይ ያላችሁት እናንት የህወሃት ተንበርካኪ ጥቂት የኦህዲድ እና የብአዲን አመራር ናችሁ። ድርጅታችህ ከድታችሁ ከህወሃት ጎን በመቆም፣ የአገራችሁንና የሕዝባችሁን እልውናና ዘለቄታዊ ጥቅም በጊዜያዊ በሆነ ርካሽ ጥቅም የለወጣችሁት።
የህወሃት የቅርብና የሩቅ ዓላማ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሰፊው በመቆጣጠር ለአንድ ወገን ያደላ የካፒታሊስት ቡድን ለመፍጠር ነው። ይህም ዓላማው መንግስታዊ ካፒታሊዝም በትግራይ እና ክሮኒ ካፒታሊዝም ወይም ብልሹ ካፒታሊዝም በተቀረው በኢትዮጵያ መመስረት ነው። በትግራይ ክልል ላይ እየተገበረ ያለው የመንግስታዊ ካፒታሊዝም አካሄድ የቻይናን አካሄድ የሚመስል ሲሆን፤ ዓላማው አብዛኛው የክልሉን ሕዝብ የልማቱ ተጠቃሚ በማድረግ ክልሉን የመሀከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ነው። በተቀረው ኢትዮጵያ እየተገበረ ያለው የክሮኒ ወይም ብልሹ ካፒታሊዝም አካሄድ ዓላማው ለዘረፋና ለምዝበራ አመቺ የሆነ የኢኮኖሚ ሥራዓት በተቀረው ኢትዮጵያ በመዘርጋት የወያኔ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሕገ ወጥ መንገድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በበላይነት በመቆጣጠር የትግራይ ክልልን የልማት ጉዞ የሚያግዝ ካፒታል ማግበስበስና የተቀረው ኢትዮጵያን በበላይነት መያዝ ነው። ይህ እንግዲ ወያኔዎች የሚያመልኩት የመለስ ዜናው እኩይ አእምሮ የነደፈው የዘረፋ ፕላንና ራዕይ ነው። የመለስ ዜናዊና አንዳንድ የትግራይ የፓለቲካ ልዒቃን አለመግባባት የተፈጠረው የዚህ ፕላን የአተገባበር ዘዴና ይህ ፕላን ኤርትራዊያንን ይጨምር ወይስ አይጨምር በሚለው ነው። የመለስ ዜናዊ ፍላጎትና ድሮም እንደሚያምንበት የትግራይ የረዥም ግብ ከኤርትራ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ነበር። እንደ መለስ አስተሳሰብ ትግራይ በኤርትራ ተቀባይነት ሊኖራት የሚችለው የትግራይ ኢኮኖሚ ወደ መሀከለኛ ገቢ ደረጃ ሲደርስ ብቻ ነው። ደሀ ትግራይ ኤርትራን አታጓጓም። ስለዚህ ትግራይን ከድህነት አውጥቶ ወደ መሀከለኛ ገቢ ለማድረግ ኢትዮጵያ በሰፊው መበዝበዝ አለባት። በአንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ለደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ እንዳማካረው፣ ትግራይን በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ አቅም እንደ እስራኤል ለማድረግ ምኞት እንዳለውና ለዚህም የትግራይ ምሁራኖችን ከፍተኛ ትብብር እንደሚሻ ጠቁሞ ነበር። ለዚህም ይመስላል አብዛኛው የትግራይ ምሁራኖች የህወሃት ደጋፊ የሆኑት።
ስለዚህ በአጠቃላይ የወያኔዎች ዓላማ የተቀረው ኢትዮጵያን በመጠቀም እንዴት አድርገው ትግራይን ወደ መሀከለኛ ገቢ ክልል ማሸጋገር ነው። ነገር ግን ይህ የወያኔዎች ዓላማ የተቀረው ኢትዮጵያ ላይ በጎ ልማት እየፈፀሙ ቢሆን ኖር በጄ ሊባል ይችል ነበር። ነገር ግን የአገሪቱን ድንግል መሬት ለውጭ ባለሀብት ለረዥም ዓመታት በማከራየት፤ የአገሪቱን ትልልቅና አትራፊ ኢንደስትሪዎችን ለውጭ ባለሀብቶች በመቸብቸብ፤ የአገር ውስጥ ባለሀብትን ለአገራዊ ብልፅግና ብዙም ምርታም ባልሆነው ነገር ግን ለግል ብዙ ትርፍ በሚያስገኘው የሕንፃና የቤት ግንባታ ላይ እንዲርመሰመስ በማድረግ የአገሪቱን የወደፊት ልማት እያጨነገፈ ነው። ይህ በተቀረው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ብልሹ አካሄድ በትግራይ ግን የለም። በትግራይ የተገነቡ ኢንደስትሪዎች በሙሉ የትግራይ ክልል ሀብቶች ሲሆኑ፤ በተቀረው ኢትዮጵያ ያሉ ኢንዱስቲሪዎች ግን ከትግራይ ባለሀብቶች ጋር ሽርክና ባላቸው የውጭ ባለሀብቶች እየተዋጡ ናቸው። በተቀረው ኢትዮጵያ የሚገነባው ብልሹ ካፒታሊዝም አብዛኛውን ሕዝቡ ደሀና ሎሌ የሚያደርግ ሲሆን በትግራይ የሚገነባው መንግስታው ካፒታሊዝም ግን አብዛኛውን የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ወደ መሀከላዊ ገቢ ለማድረስ የታለመ ነው። ወያኔዎች ኢትዮጵያን የመካከለኛ ገቢ አገር ደረጃ እናደርሳለን ሲሉ በራዕያቸው ያለው ትግራይን የመካከለኛ ገቢ ማድረስ ሲሆን፤ ለምን የተቀረው ኢትዮጵያም መድረስ አልቻለም ተብለው ቢጠየቁም፤ እኛም ምን እናውቃለን የክልሎቹን አስተዳዳሪዎች ጠይቁ እንደሚሉ መታወቅ ይገባውል። ለዚህም የቅርብ ማረጋገጫ የአማራ ተወካይ ነኝ የሚለው ብልጡ በረከት ስማዖን ትግራይ ላለው የትግራይ የኢኮኖሚ መነሳሳት ምክንያት የትግራይ ክልል አስተዳደር ጥንካሬ ሲሆን፤ በኦሮሚያና በአማራ ያለው ድክመት ምክንያቶችቹ ደግሞ የክልሎቹ አመራሮች ድክመት ነው በማለት ሲተች እንደነበረ ይታወቃል።
ምናልባት አንዳንድ የዋህ ሰዎች ወያኔ በተቀረው ኢትዮጵያ ትልልቅ ልማት እየሠራ ነው በማለት እንደ ዓባይ ግድብና እንድ የባቡር አግልግሎት የመሣሰሉትን በማየት ሊታለሉ ይችላሉ። የወያኔ እኩይ ዓላማም ይህው ነው። ሕዝቡን ሊያዘናጉና ሊያታልሉ የሚችሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እዚም እዚያም በማሳየት የወያኔን ዘራፊነት በሰፊው ለመቀጠል ነው። ለምሳሌ በጣም ትልቅ የሚባለው የዓባይ ግድብን ዋጋ እንመልከት። እስከ ስድስት ቢልዮን ዶላር ተገምቶል። ይህ ኤፈርት በሃያ አምስት አመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘረፈው ከሰላሳ ቢልዮን ዶላር ከሚበልጥ ሀብት ጋር ስናነፃፅረው ምን ማለት ነው? ይህ አንድ ድርጅት ብቻ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የዘረፈው ሀብት አምስት የአባይ ግድብን የሚያህል ፕሮጀክቶችን ሊገነባ ይችላል ማለት ነው። በተጨማሪም ወያኔ ለቆመለት ዓላማ ሀብት መዝረፍ የሚችለው እኮ ኢትዮጵያው ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲኖር ነው። ነገር ግን ይህ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የወያኔን ዓላማ እንዲያሳካ በብልሹ ካፒታሊዝም ዘዴ የሚተገበር ነው። የጣሊያን ኮሎኒያኒዝም በኤርትራ የገነባው ኢንደስትሪዎችና የመሠርተ ልማት በጣም ብዙ ነበረ፤ ነገር ግን ዓላማው ለኤርትራ ሕዝብ ታስቦ አልነበረም። ለኢጣሊያን ኮሎኒያሊስቶቹ ታስቦ ነበር። ከላሚቷ የሚገኘውን ወተት ለማብዛት እኮ ላሚቷ እስክታርጅና እስክትደክም ድረስ ብዙ ወተት የምትሰጥበትን ዘዴ ማድረግ ያስፈልጋል። የወያኔዎችም ዓላማ እንደዚሁ ነው የተቀረው ኢትዮጵያ እስኪደክም ድረስ በፕላንና በዘዴ መመዝመዝና መመዝበር ነው። ይህንን ነው እንግዲህ እናንተ የህወሃት ተንበርካኪ ጥቂት የብአዲንና የኦህዲድ አመራሮች ልታጤኑት የሚገባው።
የወያኔ የኢንዱስትሪ ፓሊስ ዕቅድም የሚያንፀባርቀው የተቀረውን ኢትዮጵያ የሚያራቁት ፓሊሲ ነው። የፓሊሲው ዋና ዕቅድ እንደሚያመለክተው በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሌቤት እንዲሆኑ የታለመው ከወያኔ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ጋር ሽርክና የሚገቡ ታላላቅ የውጪ ኩባንያዎች ሲሆኑ፤ እነዚህ ኩባንያዎች የሚያገኙት ትርፍ የሚከፋፈለው ለወያኔዎቹና ለውጭ ኩባንያዎች ይሆናል ማለት ነው። የተቀረው ኢትዮጵያዊ ከኢንዱስትሪ ልማቱ የሚያገኘው ጉልበቱን በመሸጥ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ መግፋት ነው። በብዙ አገሮች የኢንዱስትሪ ልማት ዋናው ተፈላጊነትና ዓላማ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ብቻ ሳይሆን እንደውም ትልቁ ዓላማው ከፍተኛ ካፒታል በማመንጨት አገሮቹ ቀጣይ የኢንዱስትሪ መስፋፋት እንዲያደርጉና የሕዝቡን ህይወት የሚለውጡ የማህበራው አግልግሎቶችን ለማስፋፋት የሚውል የካፒታል አቅም ማመንጨት ነው። ነገር ግን የወያኔዎቹ የኢንዱስትሪ ፓሊስ ዓላማ የሚያበልፅገው በአብዛኛው የወያኔዎቹ ሽርክ የሆኑትን የውጭ ኩባንያዎችና ወያኔዎች ሲሆን። ይህን በመጠቀም ወያኔዎቹ ክልላቸውን ወደ መሀከለኛ ገቢ ሊያደርስ የሚችል ካፒታል ከውጭ ኩባንያዎቹ ጋር ይከፋፈላሉ ማለት ነው። ስለዚህ በጠቅላላው በተቀረው ኢትዮጵያ ውስጥ ይተገበራል የሚባለው የኢንዱስትሪ ፓሊሲ የአንበሳ ድርሻ ተጠቃሚ የሚሆኑት ወያኔዎችና የወያኔ ሸርካ የውጭ ኩባንያዎች ይሆናሉ ማለት ነው።
ይህ ዘዴ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ይጠቀሙበት የነበረው ዓይነት ዘዴ ነው። የቅኝ ተገዢ አገሮች ለቅኝ ገዢዎቹ አገሮች ብልፅግና የሚውል ከፍተኛ ካፒታል ያመነጩ ነበረ። ይህንንም ለማድርግ ቅኝ ገዢዎቹ በቅኝ ተገዢ አግሮች ውስጥ የካፒታል ማመንጨቱን ሥራ የሚያቀላጥፉ በርካታ መሠረተ ልማቶችንና ኢንዱስትሪዎችን ገንብተው ነበር። ሩቅ ሳንሄድ በኤርትራ የጣሊያን ቅኝ ገዢዎች ያደረጉትን ማየት ይቻላል፡፡ በተለይ የእንግሊዙ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ በየኮሎኒዎቹ የእንግሊዝን የብዝበዛ መዋቅር የሚያስጠብቁና የሚያስፈፅሙ አቀባባይ ሎሌዎችን ከየአካባቢው ህዝብ ገዢዎች በመሰየምና ጥቂቶችን የአገር ተወላጆች የብዝበዛው ተጠቃሚ በማድረግ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ላይ ከፍተኛ ብዝበዛና በቀላሉ የማይሽር ከፍተኛ ጉዳት አስከትለዋል። የአውሮፓን የብዝበዛ አገዛዝ በመላው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያመቻቹና ተገባራዊ ያደረጉት “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” በሚሉ በየአካባቢው የሚገኙ የአፍሪካ ገዢ መደቦች ነበሩ። ለግል ጥቅም ብለው ህዝባቸውንና አገራቸውን በጣም ያስመዘብሩ ነበር። አንዳንድ የህወሃት ተንበርካኪ የብአዲንና ኦህዲድ አመራር የእንደዚህ ዓይነት የብዝበዛ መሣሪያ ነው መሆን የሚፈልጉት? እስከ መቼ ድረስ? ህወሃት ሃያ አምስት ዓመት አልበቃውም።
ወያኔ ዘረፋውንና ብዝበዛው ለማስቀጠል ጥልቅ የተንኮል ዘዴ ይዘይዷል። ይህ ደግሞ የወያኔ ተገዢ መሆን ይብቃን የሚሉትን የኦህዲድና የብአዲን አባላቱን በማባረር ሌሎች አዳዲስ ለመክበር የሚፈልጉትን አባላቶች መተካት ነው። በግልፅ እንደታየው ወርቅነህ ገበየው ወልደኪዳንን እነደ ወርቅነህ ገበየው ነገዎ መተካት ነው። በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተነሱት የሕዝብ ተቃውሞዎች ዋናው ቁልፍ ጥያቄ የወያኔ የበላይነት ይቁም ወያኔ ይውደም የሚል እንጂ የክልል አስተዳዳሪዎች ይቀየሩ የሚል አይደለም። ወያኔ ግን የሕዝቡን የተቃውሞ ጥያቄ በማጣመምና የራሱ መጠቀሚያ በማድረግ የሕዝቡን ጥያቄ የአስተዳደር በደል ነው በማለት የክልሎቹን አመራሮቹ በማስደንገጥና በማተራመስ የራሱን የበላይነት እንደገና በማጠናከር ላይ ይገኛል። ወያኔ ከ1997 የሚያንቀጠቅጥ የሕዝብ ተቃውሞና የምርጫ ሽንፈት በኃላ የወሰዳቸው የለየለት የአምባገነነትና የዘረፋ እርምጃዎች ስናይ፤ በአሁኑ ወቅት እየደረሰበት ላለው የሚያንቀጠቅጥ የሕዝብ ተቃውሞ የሚሰጠው ምላሽ የአምባገነንነትና የዘረፋ ተግባሩን በእጥፍ እየጨመር እንደሚሄድ ፍንጮች በመታየት ላይ ናቸው። ወያኔ አስተውሎ በፍላጎቱ የሥልጣን ክፍፍል ያደርጋል ማለት ዘበት ነው። ወያኔ በሽንገላና በማረሳሳት አድብቶ ከፍተኛ ጥቅት እንደሚፈፅም ምንም ጥርጥር የለውም። ወያኔ በሚጨንቀው ጊዜ ብዙ የማታለያና የማለሳለሻ ዘዴዎች በመጠቀም የተካነ ሲሆን። ይህን አስጨናቂ ወቅት ካለፈው ግን ወያኔ ወደ ተፈጥሮው የጨካኝ አውሬነት ባህሪ የሚመለስ አደገኛ ድርጅት ነው።
ህወሃት ኦህዲድንና ብአዲንን የሱ ተገዢ እንዲሆኑ የሚያደርግባቸው ሶስት ዋና ዘዴዎች ለመጥቀስ። አንደኛው በእያንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ የውስጥ አለመተማመን መፍጠር፤ እርስ በርስ በማናቆርና በመጠንፈግ ጥርጣሬ ማስፋፋትና አንጃ ማብዛት ነው። በኦህዲድና በብአዲን ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ከተለያዮ የህወሃት አባላቶች ጋር የግልዮሽ ግንኙነቶች ያላቸውና ለከፍተኛ ሀላፊነትም ሊበቁ የቻሉት በህወሃት አባላቶች ምልመላ ወይም አዎንታነት በመሆኑ የሚመኩትም ሆነ ሚሥጥራቸውን የሚያጋሩት ወይንም የምዝበራ መዋቅሮቻቸውን የሚዘረጉት ከህወሃት አባላቶች ጋር ነው። ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች በውስጥ አባላቶቻቸው መሀከል መተማመን የሌላቸው ሲሆንና ህወሃትም የድርጅቶቹ አመራሮችን በቀጥታ የሚቆጣጠራቸውና የሚሰልላቸው ናቸው። ስለኦህዲድና ብአዲን አመራሮች ሁኔታ የየድርጅቶቹ አመራሮች ስለ ድርጅታቸው አባላቶች ተግባርና ባሕሪ ከሚያውቁት በላይ ህወሃት ይበልጥ ያውቃል።
ሁለተኛው በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ አባላቶች በምዝበራና በዋልጌነት እንዲጠመዱ ማድረግ ነው። ብልሹ አስተዳደር ዋልጌነትና ምዝበራ ዋንኛው የህወሃትን የበላይነት ማስጠበቂያ መሣሪያዎች ናቸው። ጥሩ አስተዳደር ከተመሰረተ የክልሉ አስተዳደር ከህዝብ ጋር ፍቅር ይመሠርታል። ይህ ደግም ለህወሃት አደጋ ነው። ምክንያቱም የክልል አመራሮች የህዝብ ድጋፍና የህዝብ ፍቅር ካላቸው የህወሃት ታዛዥና ሎሌ ሊሆኑ አይፈልጉም። ስለዚህ ህወሃት መልካም አስተዳደር እንዲመሰረት የሚፈልግ ድርጅት ሊሆን አይችልም። በየክልሎቹ መልካም አስተዳደር ከሰፈነ የህወሃት የበላይነት ያከትማል ማለት ነው። ይህ ከህወሃት የቅርብም ሆነ የሩቅ ግብ ጋር ይፋለሳል። ስለዚህ ህወሃት የሚፈልገው በብልሹ አስተዳደር የሚጨማለቁና የህዝብ ፍቅርና አመኔታ የሌላቸው ከህወሃት ማፍንገጥ የማይችሉና በሚፈልገው ጊዜ በሌላ መሰል ግለሰቦች የሚተካቸው የክልል አመራሮች ነው። የክልል አመራር ሆነው በሥራቸው ምክንያት በህዝብ የሚወደዱ አመራሮች ዋንኛ የህወሃት ጠላቶች ስለሆኑ በአመራር ቦታቸው ብዙም አይቆዩም። በኦሮሚያና በአማራ ክልል የህወሃት ዋና ዓላማ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ሳይሆን፤ ብልሹ አስተዳደር እንዲሰፍን በማበረታት በህዝብና በአመራሮች መሀከል ጥላቻን በማጠናከር አመራሮቹ ከህዝብ ይልቅ በህወሃት እንዲመኩ በማድረግና አመራሮቹን መቆጣጠርና የህወሃት የብዝበዛ መሣሪያ ማድረግ ነው። በማይፈልጋቸው ጊዜም ያለ ችግር በሌሎች አዳዲስ አገልጋዮች መተካት ነው። ስለዚህ በህወሃት ስሌት ብአዲንና ኦህዲድ የህወሃት መገልገያዎች ናቸው። በአሁኑ ወቅት ዋና መገልገያ በመሆን ላይ የሚገኙት የህወሃት ተንበርካኪ ጥቂት የኦህዲድና የብአዲን አመራሮች ናቸው።
ሦስተኛ ህወሃት በኢህአዲግ ውስጥ የበላይነቱን ይዞ ሊቀጥል የቻለው በብአዲንና በኦህዲድ መሀከል ጥላቻንና ፍጥጫን በማራገብና በማስፋፋት ነው፡፡ ህወሃት ኢትዮጵያን በበላይነት ለመግዛት የቻለው ኦሮሞውንና አማራውን በማናከስ ነው። በኢህአዲግ ውስጥም የሚከተለው ይህንን የተንኮልና የክፋት መንገድ ነው። ብአዲንን አጋር እያደረገ ኦህዲድን መምታት ወይም ኦህዲድን አጋር በማድረግ ብአዲንን መምታት ህወሃት የተካነበት መንገድ ነው። የሚተገበሩት የኢኮኖሚም ልማቶችም ሆነ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ሆን ተብለው ኦህዲድንና ብአዲንን የሚያፎካክሩና የሚያቃርኑ ናቸው። በአማራውና በኦሮሞው መሀክል የጠላትነት ስሜት እንዲሰርፅ ማድረግ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በኦሮማውና በአማራው መሀከል የመደጋገፍና የመናበብ ሁኔታ የተፈጠረ በመሆኑ ይህንን የመተጋግዝ ሁኔታ በአጭሩ ለመቅጨት ህወሃት ከፍተኛ ተንኮልና ሸር እያዘጋጀ ለመሆኑ ምንም የሚካድ አይሆንም። በኢትዮጵያ ውስጥ የህወሃት የበላይነት ሊያጠፋ የሚችል ዋናው መንገድ ቢኖር የአማራውና የኦሮሞው መተባበርና መደጋገፍ ብቻ ይሆናል። ስለዚህ ለራሳችሁና ለሕዝባችሁ ነፃነት ስትሉ በጥንካሬ መተባበርና መናበብ ይኖርባቹኃል። ያለበለዚያ በየተራ በህወሃት እየተበላችሁ ለራሳችሁም ሆነ ለሕዝቡ ጠቃሚ ተግባር ሳትሰሩ ተዋርዶ ማለፍ ነው። እናንተም የህወሃት ተንበርካኪ ጥቂት የብአዲንና የኦህዲድ አመራሮች ልትገነዘቡት የሚገባው፤ ትልቁ ውድቀት ስህተት መስራት ሳይሆን የሰሩትን ስህተት ተገንዝቦና ከስህተት ተምሮ ስህተቱን አለመድገም ይሆናል። የሚያድናችሁ ከሕዝብ ጎን መሆን እንጂ በህወሃት ጉያ ውስጥ መደበቅ አያዛልቅም። በዚህ አንገብጋቢ ወቅት ሕዝብን በመክዳት ከህወሃት ጎን መለጠፍ ይቅር ሊያሰኝ የማይገባ ትልቅ በደል ነው። የህወሃት አገልጋይና ባሪያ ሆኖ የተቀረውን ኢትዮጵያ ወደ መከራና ወደ ብጥብጥ መውሰድ ነው። እንግዲህ ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው የትኛውን መምረጥ እንደሚገባው የታወቀ ነው። እስከ መቼ ነው ለግል ምቾታችሁ ብቻ በማሰብ ሕዝብ ወደ መከራ የምታስገቡት። እስከ መቼ ነው እንደዚህ መቀጠል የምትፈልጉት? ሰዎች አይደላችሁም እንዴ? እንደ ሰው የሚያስብ አእምሮ አይደል ያላችሁ? እስከ መቼ ለህዝባቹ ስቃይና ጭቆና መሣሪያ ትሆናላችሁ?
የአማራና የኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት ዓላማም በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጎጂ ንትርክ ሳይሆን ጤናማ ውይይትና ትብብር የሚጎለብትበትን መንገድ የሚያበረታቱ ሀሳቦችን በማፈላለግና በማሰራጨት፤ በአማራና በኦሮሞ ልዒቃን መሀከል የሚደረገው የታሪክ ንትርክን በተመለከት የታሪክ ባለሙያዎች በሰለጠነ መንገድ በመከባበር እንዲወያዩበት የሚገባ መሆኑን እያበረታታ። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ ግን የአማራና የኦሮም የፓለቲካ ልዒቃን የታሪክ ንትርኩን ለታሪክ ባለሙያዎች በመተው በአንገብጋቢው የወቅቱ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በማተኮር የህወሃትን አገርንና ሕዝብን የሚያጠፋ ድርጊት ለመቋቋም የሚችሉበትን የትብብር ጉዳዮች ላይ ጥረት ማድረግ ነው። በሚቀጥለው ፅሁፋችን ለኦሮሞና ለአማራ የመተባበር ዋና እንቅፋቶች ላይ እናተኩራለን።
ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት
AOCPP (Amhara and Oromo Cooperation Promotion Project)
Contact: aocpp2016@gmail.com