spot_img
Saturday, May 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትለፓርላማው አባላት፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን የለውም። (ከአማራና ኦሮሞ ትብብር...

ለፓርላማው አባላት፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን የለውም። (ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት -አኦትይፕ)

ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት -አኦትይፕ
ታህሳስ 18 ፤ 2010 ዓ ም
በፒዲኤፍ ፎርማት ለማንበብ ይሄንን ይጫኑ

በጀርመን ድምፅ የአማርኛ ሥርጭት በዶይቼ ቬለ ላይ በዲሴምበር 25፣ 2017 ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማው ዝግ ስብሰባ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ከኦሮምያ ክልል ጉጂ ዞን የቡሌ ሆራ ተወካይ አቶ ቦነያ ኡዴሳ የራሳቸውን ፓርላማ ሕገ መንግስታው ሥልጣን ያወቁት አይመስልም። አቶ ቦነያ እንዳሉት ”በአሁኑ ሰዓት እየተሰራ ያለውን፣ እየተጣስ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሊያስቆም የሚችለው ወይም የማስቆምም ግዴታ በሕገ መንግስቱ የተሰጠው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ነው” በማለት ከአንድ የፓርላማ አባል የማይጠበቅ በጣም የተሳሰተ አስተያየት አቅርበዋል። ይህ እንግዲህ በሚያስገርም ሆኔታ የፓርላማው አባላቶች እንኳን አሁን የሚሰሩበትን ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነትና ስልጣን አለመረዳታቸው ነው። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም ሆነ የየትኛውም ድርጅት ስራ አስፈፃሚ አሁን ባለው ሕገ መንግስት የተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት የለም። ኢህአዲግ ሕገ መንግስታዊ ስልጣን የሚኖረው ፓርላማው ውስጥ ብቻ በሚደረግ ውሳኔና በፓርላማው በሚገኙ አባላቶች ድምፅ በፓርላማው ውስጥ ውሳኔ ሲተላለፍ ብቻ ነው። ከፓርላማው ውጪ ኢህአዲግ የሚያስተላልፈው ውሳኔ የጉልበት እንጂ በአገሪቷ ላይ ሕገ መንግስታዊ ስልጣን የለውም። ህወሃት አገሪቷን በበላይነት በመግዛት ላይ የሚገኘው ይህን ሕገ መንገስታዊ ስልጣን የሌለውን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ እየተጠቀመ ነው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ማለት ህወሃት ሕገ መንግስቱ ያልሰጠውን የበላይነቱን የሚያስጠብቅበት በእነ መለሰ ዜናዊ የተንኮል ጭንቅላት የተመሰረት ፀረ – ዴሞክራሲ የሆነ አናሳው ህወሃት አብዛኛውን ኦህዴድን፣ ብአዴንና ደኢሕዴድን በበላይነት የሚገዛበት መሳሪያ ነው።

በኢህአዲግ ስራ አስፈፃም አራቱም ድርጅቶች እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ዘጠኝ ተወካይ ያላቸው ሲሆን ውሳኔ የሚተላለፈው በአባላቶች የድምፅ ብልጫ እንጂ በድርጅቶች ድምፅ ስላልሆነ ሁልጊዜም የሚወሰነው በህወሃት የሚቀነቀን ሀሳብ ነው። ምክንያቱም ህወሃቶች የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ አንድ ስለሆኑና በሌሎች ድርጅቶች ደግሞ በጥቅም የተገዙ የህወሃት ታማኞች ስለሚገኙ በኢህአዲግ ስብሰባ ላይ ህወሃት በድምፅ ብልጫ ተሸንፎ አያውቅም፣ ሊሸነፍም አይችልም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢህአዲግ ስብሰባ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስ የረባ ውሳኔ መጠበቅ ሞኝነት ነው። ምክንያቱም ኢህአዲግ ስራ አስፈፃሚ ማለት ፀረ ዲምክራሲያዊ የሆነ የህወሃት የበላይነት ማስጠበቂያ መሣረያ ነው። አብላጫው የኢህአዲግ ስራ አስፈፃም አባላት ለህወሃት ባደሩ፣ በሥልጣንና በጥቅም በተገዙ ግለሰቦች የተሞላ ነው። የህወሃት የበላይነት እንዲያከትም የሚፈልጉት የኦህዲድና የብአዲን አመራር በኢህአዲግ ስራ አስፈፃም ውስጥ አሸንፈው ሊወጡ አይችሉም። ምክንያቱም ኢህአዲግ ዲዛይን የተደረገው አናሳው ህውሃት የሚፈልገውን በበላይነት እያስወሰነ በአብዮታው ዴምክራሲ አስመስሎ የራሱን ሕገ መንግስት በመናድ አግሪቷን በበላይነት የሚገዛበት ዘዴ ነው። ስለዚህ ኢህአዲግ መፍረስ እንጂ የሚሻሻል ድርጅት አይደለም። እያንዳንዱ አባል ድርጅቶች በተለይም ኦህዴድና ብአዴን ከኢህአዲግ መውጣት ይበጃቸዋል። ሁለቱም ድርጅቶች ከሚፈልጉት ሌሎች ድርጅት ጋር መጣመር የሚችሉበትን በሕዝብ በተመረጡ የፓርላማ አባላቶቻቸው ማስወሰን ይገባቸዋል። ለኦህዴድና ለብአዴን ኢህአዲግ ውስጥ በመቆየት የሚያተርፋት በሕዝባቸው መተፋትና በመጨረሻም በህወሃት መበላት ነው። ወቅቱ አሁን ነው ሕዝቡም ሆነ የፓርላማ አባላቶቻቸው ከጎናቸው ቆመዋል።

ለኦህዴድና ለብአዴን ትልቁ ኃይል መሆን የሚገባቸው ሕዝቡና የፓርላማው አባላቶቻቸው መሆን ይገባቸዋል። ምክንያቱም በሕገ መንግስቱ ፓርላማው ተጠሪነቱም ሆነ ታዛዥነቱ ለመረጠው ሕዝብና የአገሪቷም መንግስት የበላይ የሥልጣን አካል ነው ይላል። በሕገ መንግስቱ መሰረት ፓርላማው በጠቅላይ ሚኒስቴሩም ሆነ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የሚታዘዝ አካል አይደለም። በተቃራኒው ፓርላማው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆነ ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የበላይ የስልጣን አካል ነው። የፓርላማው አባላቶች ፓርላማውና አባላቶቹ ያላቸውን ሕገ መንገስታው ስልጣን በሚገባ መረዳት ይኖርባቸዋል። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 54 ቁጥር 4 መሰረት የፓርላማው አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው። ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግስቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው ብቻ ይሆናል። ማንኛውም የፓርላማ አባል በፓርላማ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም። አስተዳደራዊ እርምጃ አይወሰድበትም ይላል። በአንቀፅ 59 ስለፓርላማው ውሳኔ አሰጣጥና የሥነ ሥነ ሥርዓት ደንቦችን በተመለከተ ማናቸውም ውሳኔዎች በፓርላማው የሚተላለፉት በፓርላማው አባላት የአብላጫ ድምፅ ነው ይላል።

በህጋዊና በዴምክራሲያው መንገድ የህወሃትን የበላይነት ማስወገጃ መንገድ ፓርላማው ብቻ ነው። ህወሃት እራሱ በወጣው ሕገ መንግስት የማይገዛ ከሆነ ያላችሁ የመጨረሻ አማራጭ ከሕዝብ ትግል ጎን በመቆም የህወሃትን የበላይነት ማስወገድ ነው። ከዚህ ውጭ ግን ኢህአዴግን ተጠቅመን ህወሃትን እናሸንፋለን ማለት የዋህነትና ዘበት ነው። ኢህአዴግ የህወሃት መሳሪያ ስለሆነ ቢሻሻልም እንኳን ሊሆን የሚችለው ህወሃት እንዴት በተሻሻለና በተደበቀ መልኩ የበላይነቱን የሚቀጥልበትን ዘዴ ማረጋገጥ ብቻ ይሆናል። ኢህአዴግ ኦህዴድና ብአዴን ማኮላሻና ማንበርከኪያ መሳሪያ ነው። ለሁለቱ ድርጅቶች በኢህአዴግ ውስጥ በመቆየት ያላቸው ምርጫ ሁለት ነው። አንዱም የህወሃት ታዛዝ ሆኖ መቆየት አለበለዚያም በህወሃት ተበልቶ መክሰም ነው። የህወሃት የሁልጊዜ ባህሪው ይህው ነው። የተጠቀመበትን ድርጅት መልሶ ማጥቃትና ማጥፋት ነው። ህወሃት ውለታ አያውቅም። ህወሃት የሚያውቀው ጥቅም ብቻ ነው። መለስ ዜናው እንዳለው ጥቅም ካለው ህወሃት ከሰይጣንም ጋርም ቢሆን አብሮ ይሰራል። ህወሃት ማለት ይህው ነው። የየዋህነት ጉዞ ማብቃት አለበት።

የአማራና የኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት ዓላማም በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጎጂ ንትርክ ሳይሆን ጤናማ ውይይትና ትብብር የሚጎለብትበትን መንገድ የሚያበረታቱ ሀሳቦችን በማፈላለግና በማሰራጨት፤ በአማራና በኦሮሞ ልዒቃን መሀከል የሚደረገው የታሪክ ንትርክን በተመለከት የታሪክ ባለሙያዎች በሰለጠነ መንገድ በመከባበር እንዲወያዩበት የሚገባ መሆኑን እያበረታታ። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ ግን የአማራና የኦሮም የፓለቲካ ልዒቃን የታሪክ ንትርኩን ለታሪክ ባለሙያዎች በመተው በአንገብጋቢው የወቅቱ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በማተኮር የህወሃትን አገርንና ሕዝብን የሚያጠፋ ድርጊት ለመቋቋም የሚችሉበትን የትብብር ጉዳዮች ላይ ጥረት ማድረግ ነው።

ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት

AOCPP (Amhara and Oromo Cooperation Promotion Project)
Contact: aocpp2016@gmail.com

————
ማስታወሻ ፤ በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ አመለካከቶች የጸሃፊውን /ዋን እንጂ የድረ ገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ለማጋራት ወይንም ሃሳብ በሚከተለው አድራሻ መላክ ይቻላል፤ editor@borkena.com

ወቅታዊ መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ማድረግ አይርሱ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here