ቦርከና
ታህሳስ 17 ፤ 2010
ከቀናት በፊት በፌደራል ፖርላማ ያሉ የኦህዴድ እና የብአዴን የህዝብ እንደራሴዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በፖርላማ ቀርበው እየተከሰተ ስላለው የዘር ግጭት እና በአጠቃላይ በሃገሪቱ ስላለው ቀውስ ካላናገሩን በመደበኛ የስራ ገበታችን ላይ አንገኝም በማለት አድማ መምታታቸው ይታወቃል።
ይሄንኑ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰኞ ዕለት እየተካሄደ ያለውን የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ በማቋረጥ አድማ ከመቱት የህዝብ እንደራሴዎች ጋር በፖርላማ ለመሰብሰብ ተገደዋል።
ሆኖም ስብሰባው ያልተለመደ ነገር ተስተውሎበታል። የፖርላማ አባሎች ስልክ እና መሰል የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን ይዘው እንዳይገቡ ጥብቅ ቁጥጥር ተደርጓል። ለገዥው ፖርቲ ቅርበት አላቸው የሚባሉ መገናኛ ብዙሃን እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ካዜጠኞች ወደ ስብሰባው እንዳይገቡ በመከልከል በዝግ እንዲከናወን ተደርጓል። የፓርላማ ሰራተኞችም ለቀረጻ እና ለሎጂስቲክ አቅርቦት ስራ እንዳይገቡ ተደርጓል። ስለ ስብሰባው አጀንዳዎች የታወቀ ዝርዝር የለም።
ህወሓት የስራ አስፈጻሚ ስብሰባውን በመቀሌ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ “በእህት ድርጂቶች መካከል መጠራጠር ተፈጥሯል” ማለቱ የሚታወስ ነው ፤ ጉዳዮን በዝርዝር ባያብራራውም። በተመሳሳይ እየተካሄደ ባለው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ መግለጫ የወጣ ሲሆን ፤ እንደ ህወሓት መግለጫ ሁሉ ኢህአዴግ በድርጂቱ ውስጥ “መጠራጠር” እና “ክፍፍል” ነገሷል ማለቱ ይታወቃል።
ከአባል ድርጂቶች ውስጥ ብአዴን እና ኦህዴድ ከዚህ በኋላ በድርጂቱ ውስጥ የህወሓት የበላይነት የሚታሰብ ነገር አይደለም የሚል አቋም እንደያዙ በሰፊው እየተወራ ሲሆን ፤ የድርጂቱ የኢህአዴግ ህልውና ራሱ ያከትማል እስከማለት የሚደርሱ ተንታኞችም አሉ።
የህወሓት ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል አፍቃሪ ህወሓት ከሚባለው ፋና ብሮድካስቲንግ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የህወሓት የበላይነት አለ የሚባለው ነገር “የጠላት ወሬ” ነው በማለት ለማጣጣል ሞክረው ፤ የትግራይም ህዝብ የተለየ ከስርዓቱ የተጠቀመው ነገር የለም፤ “አዲስ የወጣ መረጃ” አለ ብለዋል ።
———
ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ