spot_img
Sunday, July 21, 2024
Homeነፃ አስተያየትኦህዴድና ብአዴን ኢህአዴግን በመልቀቅ አዲስ መንግስት መመስረት ሕገ መንግስቱ ይፈቅድላቸዋል

ኦህዴድና ብአዴን ኢህአዴግን በመልቀቅ አዲስ መንግስት መመስረት ሕገ መንግስቱ ይፈቅድላቸዋል

Amhara-Oromo Unity
የፋሲል ከነማ ናዝሬት ሲገባ የተደረገለት አቀባበል ገጽታ በከፊል

(ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት – አኦትይፕ)
ታህሳስ 22 ፤ 2010 ዓ ም

ህወሃት የኢህአዴግን ሥራ አስፈፃሚ በመጠቀም በቅርብ ያወጣው ፀረ – ሕዝብ መግለጫ ሕገ መንግሥቱን በግልፅ የጣሰና የኢትዮጵያን ሕዝብ የናቀ የዕብሪት መግለጫ ነው። መግለጫው የህወሃትን ማንነት በድጋሚ ያሳየበት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ህወሃት ከታሪክ የማይማር፣ የወቅቱን ሁኔታ ማገናዘብ የተሳነው በዕብሪት የተሞላ የዘራፊውች ቡድን መሆኑን በድጋሚ ያረጋገጠበት መግለጫ ነው። በተለይም ይህን ዓይነት ሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነት መፍጠርና መቀራረብ ወንጀል ነው የሚል መግለጫ በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውስጥ ተሰምቶም የማይታወቅ ነው። በህወሃት የዕብሪት አስተሳሰብ መሰረት የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ መቀራረብ መርዕ አልባ ሲሆን፤ ነገር ግን ኦሮሞና አማራ በጠላትነት መተያየት መርህን የተከተለ ነው። በህወሃት መርህ መሰረት የአማራና የኦሮሞ ጠላትነት ተገቢ ነው፤ ፍቅር ደግሞ መጥፎ ነው። ይህ እንግዲህ ህወሃት የሚመራበት ሰይጣናዊ መርህ ነው። ህወሃት የኦሮሞና የአማራን መናቆርና መቃረን ዘላለማዊ ነው ብሎ ያመነ ስለነበረ፤ ይህ አሁን ህወሃት ባልጠበቀውና ባልተዘጋጀበት ወቅት ሲፈረካከስ፤ ህወሃት ሁኔታውን ለመረዳት ባለመቻሉ የኢህአዴግን ሥራ አስፈፃሚ በመጠቀም የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነትን በማውገዝ የእብደት መግለጫ ሊያወጣ ተገዷል። እንደዚህ ያለ የሕዝብ ጠላት የሆነ አገዛዝ በኢትዮጵያ የመንግስት ታሪክ ውስጥ ስልጣን ይዞ በፍፁም አያውቅም።

በመግለጫው ህወሃት የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ምን መስማት እንደሚገባቸውም የምወስነው እኔ ነኝ እያለ ነው። ብአዴንና ኦህዴድን በመስተዳድራቸው የሚገኙትን መንግስታዊ ራድዮ፣ ቴሌቪዥንና ጋዜጦች ማንንም ሳይፈሩ በነፃነት የሕዝቡን የልማት፣ የፖለቲካና ሌሎችም ተገቢ ጥያቄዎች በግልፅ ዴምክራሴያዊ በሆነ መንገድ እንዲያፀባርቁት ለማድረግ ተግባራዊ እርምጃ እየወሰዱ ሲሆን፤ ሕዝብን በማፈንና በማወናበድ በኃይል መግዛት ለሚፈልገው ህወሃት ይህ የነፃነትና የግልፅነት መንገድ አደገኛ ስለሆነበት ኦህዴድና ብአዴን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በመግለጫው መመሪያ ሰጥቷል። ከዚህም በተጨማሪ ብአዴንና ኦህዴድ እንወክለዎለን ለሚሉት ሕዝብ ሰብዓዊና ሕገ መንግስታዊ መብት መቆም የተወገዘ ህዝባዊነት በማለት ተኮንኗል። በህወሃት አስተሳሰብ ትክክለኛ ሕዝባዊነት የሚባለው ወርቅ ለሆነው ሕዝብ ብቻ ሲሆን ነው። የህወሃት ከፍተኛ አመራሮች ህወሃት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ማለት ህወሃት ማለት ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ወርቅ ነው፤ የትግራይ ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የበለጠ ነው፤ እንደ ሕዝብ ኮምፓራቲቭ አድቫንቴጅ አለው ብለው በግልፅና በሚዲያ ዘረኛ አስተያየት እያቀረቡ በግልፅ እየተሰማ፤ ብአዴንና ኦህዴድን ግን እንወክለዋለን ስለሚሉት ሕዝብ ሰብዓዊና ሕገ መንግስታዊ መብት መጠየቅ እንድማይገባቸው ህወሃት በመግለጫው መመሪያ ሰጥቷል። ታዲያ እንደዚ በግልፅ ዘረኛ፣ ዕኩይና ሰይጣናዊ ከሆነ ዕብሪተኛ ቡድን ጋር አብሮ መቀጠል ትርጉሙ ምንድነው። ስለዚህ አሁን በሚሰራበት ሕገ መንግስትና የአገሪቱ መከላከያና የፀጥታ ኃይል ሕገ መንግስቱን እንዲያስጠብቅ በማድረግ ህወሃትን አሁኑኑ ከጫንቃቸው ላይ ማሽቀንጠር ለህልውናቸም ቢሆን አማራጭ የሌለው ነው። ያለበለዚያ ግን ህወሃት በቅርብ እንደሚያጠፋቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እየተመራችበት ነው በተባለው ሕገ መንግስት በአንቀፅ 60 ቁጥር 2 በተደነገገው መሠረት በጣምራ የመንግስት ሥልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክር ቤቱ የነበራቸው አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተበትኖ በሕዝብ ተወካዮች ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ ጣምራ መንግስት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሊመሰረት ይቻላል። የፓለቲካ ድርጅቶቹ አዲስ መንግስት ለመፍጠር ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻሉ ምክር ቤት ተበትኖ አዲስ ምርጫ የደረጋል ይላል። እንግዲህ ይህ ማለት ብአዴንና ኦህዴድ ከኢህአዲግ ከወጡ ኢህአዴግ በፓርላማዋ ውስጥ ያለው ድምፅ ከግማሽ በታች ይሆናል። ኢህአዴግ የጣምራ ፓርቲ እንጂ አንድ ፓርቲ አይደለም። ጣምራውን የመሰረቱት ድርጅቶች ካልተስማማቸው በቀጥታ በሕዝብ የተመረጡ አባላቶቻቸውንና አብዛኛው አባላትን በመጠቀም ከጣምራነቱ መውጣት ይችላሉ። ይህ በአገሪቷ ሕገ መንግስት አንቀፅ 60 ቁጥር 2 የተፈቀደ ነው። ስለዚህ የኢህአዴግ የመንግስት ሥልጣን በሕገ መንግስቱ መሠረት ሊወድቅ ይችላል ማለት ነው። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከሥልጣን ይለቃል፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይበተናል። ነገር ግን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ኦህዴድና ብአዴን በፓርላማው ውስጥ ባላቸው አብላጫ ድምፅ አዲስ ጣምራ በመፍጠር መንግስት ማቋቋም ይችላሉ። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ፓርላማ ያለው አባላት 547 ሲሆኑ፤ 180 አባላት ከኦህዴድ፣ 139 አባላት ከአማራ፣ 123 አባላት ከደቡብ፣ 38 አባላት ከህወሃትና የተቀሩት አባላት ከተለያዮ የኢህአዴግ አጋር ድርጆቶች ናቸው። በዚህም መሰረት የኦህዴድና የብአዴን የጋራ የፓርላማው መቀመጫ 319 ሲሆን፣ ይህም በሕግ መንግስት በተደነገገው መሰረት መንግስት ለመመስረት ከሚያስፈልገው ከአምሳ ፐርሰንት የአብላጫ ድምፅ እጅግ የበለጠና ወደ ስልሳ ፐርሰንት ይደርሳል።

በሕገ መንግስቱ ፓርላማው ተጠሪነቱም ሆነ ታዛዥነቱ ለመረጠው ሕዝብና የአገሪቷም መንግስት የበላይ የሥልጣን አካል ነው ይላል። በሕገ መንግስቱ መሰረት ፓርላማው በጠቅላይ ሚኒስቴሩም ሆነ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የሚታዘዝ አካል አይደለም። በተቃራኒው ፓርላማው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆነ ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የበላይ የስልጣን አካል ነው። የፓርላማው አባላቶች ፓርላማውና አባላቶቹ ያላቸውን ሕገ መንገስታው ስልጣን በሚገባ መረዳት ይኖርባቸዋል። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 54 ቁጥር 4 መሰረት የፓርላማው አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው። ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግስቱ፣ ለሕዝቡና ለሕሊናቸው ብቻ ይሆናል። ማንኛውም የፓርላማ አባል በፓርላማ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት አይከሰስም። አስተዳደራዊ እርምጃ አይወሰድበትም ይላል። በአንቀፅ 59 ስለፓርላማው ውሳኔ አሰጣጥና የሥነ ሥነ ሥርዓት ደንቦችን በተመለከተ ማናቸውም ውሳኔዎች በፓርላማው የሚተላለፉት በፓርላማው አባላት የአብላጫ ድምፅ ነው ይላል። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚም ሆነ የየትኛውም ድርጅት ስራ አስፈፃሚ አሁን ባለው ሕገ መንግስት የተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት የለም። ኢህአዲግ ሕገ መንግስታዊ ስልጣን የሚኖረው ፓርላማው ውስጥ ብቻ በሚደረግ ውሳኔና በፓርላማው በሚገኙ አባላቶች ድምፅ በፓርላማው ውስጥ ውሳኔ ሲተላለፍ ብቻ ነው። ከፓርላማው ውጪ ኢህአዲግ የሚያስተላልፈው ውሳኔ የጉልበት እንጂ በአገሪቷ ላይ ሕገ መንግስታዊ ስልጣን የለውም። ህወሃት አገሪቷን በበላይነት በመግዛት ላይ የሚገኘው ይህን ሕገ መንገስታዊ ስልጣን የሌለውን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ እየተጠቀመ ነው። የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ማለት ህወሃት ሕገ መንግስቱ ያልሰጠውን የበላይነቱን የሚያስጠብቅበት በእነ መለሰ ዜናዊ የተንኮል ጭንቅላት የተመሰረት ፀረ – ዴሞክራሲ የሆነ አናሳው ህወሃት አብዛኛውን ኦህዴድን፣ ብአዴንና ደኢሕዴድን በበላይነት የሚገዛበት መሳሪያ ነው።

ጣምራ መፍጠርም ሆነ ከጣምራ መውጣት በሕገ መንግስቱ የተፈቀደና የሚቻል ነው። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 73 ቁጥር 2 መሰረት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ያገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች በመጣመር የመንግሥት ሥልጣን ይረከባል/ይረከባሉ ይላል። ስለዚህ ብአዴንና ኦህዴድ ያላቸው ትልቁ መሳሪያ ሕገ መንግስቱ፤ ሕገ መንግስታዊ መብትና ስልጣን ያላቸው የፓርላማ አባላቶቻቸው፣ የክልላቸውና የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ የሕገ መንግስቱ ጠባቂ የተባለው አብዛኛው የአገሪቷ መከላከያና የፖሊስ ኃይል ናቸው። የአገሪቷ የመከላከያና የፀጥታ ኃይል ሕገ መንግስቱን መጠበቅ እንዳለበት በሕግ የተደነገገና በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 55 ቁጥር 7 መሰረት ተጠሪነቱ በሕዝብ ለተመረጠው ፓርላማ መሆኑ ተደንገጓል። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 55 ቁጥር 7 መሰረት ፓርላማው የፌደራል መንግስት የሀገርና የሕዝብ መከላከያ፣ የደህንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀትን ይወስናል። በሥራ አፈፃፀማቸው ረገድ የሚታዩ መሠረታዊ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶችንና የሀገርን ደህንነት የሚነኩ ጉዳዮች ሲከሰቱ ያጣራል፣ አስፈላጊ እርማጃዎች እንዲወሰዱ ያደርጋል ይላል። ስለዚህ ይህንን ሕገ መንግስታዊ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ በመጠቀም አገሪቷ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ማስወገድ ይችላሉ። ሕገ መንግስታው መብት ከማንኛውም ድርጅትም ሆነ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ የበላይ ነው። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 9 ቁጥር 1 መሰረት ሕገ መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው። ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳው አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረም ይላል። እንዲህም አንቀፅ 9 ቁጥር 1 መሰረት ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፓለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው ሕገ መንግስቱን የማስከበርና ተገዢ የመሆነ ኃላፊነት አለባቸው ይላል። ህወሃት ከሕገ መንግስቱ በላይ ነው የሚል አንቀፅ የለም። የአገር መከላከያና የፀጥታ ኃይልም ቢሆን የጥቂት የህወሃት ጀነራሎች ንብረት ሳይሆን ተጠሪነቱ ለፓርላማውና ለሕገ መንግስቱ ነው። አብዛኛው የመከላከያውና የፀጥታ ኃይል አባላቶች የመጡት ከአማራና ከኦሮሞ ሕዝብ ነው።

ይህ መንገድ ህጋዊ፣ ሕገ መንግስታዊና ሰላሚዊ የሆነ የመንግስት ለውጥ ይሆናል። ይህ መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት በሰፊው እየጠየቀ ለሚገኘው የዴሞክራሲያዊና ሕዝብን በቀጥታ የሚውክል መንግስት ለመመስረት ለሚደረገው ጉዞ ጥሩ መንገድ የሚሆን ይሆናል። ኦህዴድና ብአዴንም ለተጫወቱት ሚና የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ክበር ሊሰጣቸውና በሚቀጥለው የዴምክራሲያዊ ሽግግር በሕዝብ የተወደዱና የተከበሩ ድርጅቶች ሆነው ሊቀጥሉ ይችላሉ። ለታሪክማ ሆነ ለትውልድ ለሚተላለፍ መልካም ተገባር ምሳሌ ሊሆኑ ይችላል። እንታገልለታለን የሚሉትን ሕዝብ ከጭቆናና ከባርነት ማውጣት ከሁሉም በላይ የሚበልጥ ትልቅ ተግባር በመሆኑ፣ ያለፉትን ስህተቶታቸውን በዚህ ትልቅ ተግባር እንደሚዋጥ ምንም ጥርጥር የለውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ይቅር ባይ ሕዝብ ነው። በታሪኩ ብዙ ታላላቅ የይቅር ባይ ተግባራትን ሲያድርግ የኖረ ሕዝብ ነው። በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሁኔታ ለለውጥ እጅግ ተስማሚ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችሁ ተሰልፎል፤ ፓርላማው ከጎናችሁ ነው፤ ሕግ መንግስቱ ይፈቅድላችኃል፤ የህወሃት የበላይነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከዳር አንገሽግሿታል፤ የአገሪቷ ሁኔታ እጅግ መከራ ውስጥ ወድቋል፤ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከከፍተኛ የጦሩ አመራሮች በስተቀር አብዛኛው ወታደር አማራና ኦሮሞ ነው፤ የክልላችሁ የፓሊስና የፀጥታ ኃይሎች ከሕዝባቸው ጎን የቆሙ ናቸው። በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ መካከል ጥሩ መቀራረብና መናበብ የተፈጠረበት በጣም ጥሩ ወቅት ነው። ታዲያ ከዚህ የተሻለ ጊዜ መቼ ልታገኙ ነው። ህወሃት የሕገ ወጥነቱን መንገድ እንድማያዋጣውና ጊዜ የከዳው መሆኑን ተረድቷል፣ ነገር ግን ይህን አስቸጋሪ ወቅትን በዘዴ፣ በማታለልና በማስፈራራት ለማለፍ እየሞከረ ነው። ህወሃት ጊዜ መግዛት ይፈልጋል። የሚቀጥለውን የጭካኔ ተግባሩን የሚፈፅምበትና በአሸናፊ ሊወጣ የሚችልበት ዕቅድ እየወጠነ መሆኑን ለአፍታ እንኳን መዘንጋት አይገባችሁም። ካሁን በኃላ ወደ ኃላ መመለስ ማለት በጅብ መበላት ብቻ ነው የሚሆነው። የህወሃትን የበላይነት አሁን በሕግና በግልፅ ሕዝቡ እያወቀ ከሕዝብ ጋር ሆናችሁ ካላስወገዳችሁት ለናንተም ሆነ ለአገሪቷ ሕልውና የሚበጅ አይሆንም። የሕዝቡ ብሶት ሞልቶ እየፈሰሰ ስለሆነ ሕዝቡ ወደኃላ የሚመለስበት ሁኔታ የለም። ሕዝቡ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ለመቀነስ ያለው አማራጭ ይህ ብቻ ነው።

ይህ ወቅት ህወሃት በፍፁም ያልተዘጋጀበት ወቅት ነው። ህወሃት የከበርቴ መደብ እስኪሆን ድረስ አምሳ ሃመት የመግዛት ህልም ውስጥ ነው የነበረው። በአሁኑ ወቅት ህወሃት ኦህዴድንና ብአዴንን ሳይጠቀም አገሪቷን በጠቅላላ የሚገዛበትም ሆነ የሚያተራምስበት ኃይል የለውም። የመከላከያ ሰራዊቱ አሁን ባለው የሰው ኃይል ይዘት የህወሃትን እኩይ አገር የሚያጠፋ ተግባር የሚፈፅም ሳይሆን፣ የብአዴንና ኦህዴድ ሕገ መንግስታው መንገድ በመከተል የአገርን ህልውናና ሕገ መንግስቱን እንደሚጠብቅ መዘንጋት የለባችሁም። ይህ የአሁኑ ወቅት ህወሃት በፍፁም ያልተዘጋጀበት ወቅት ነው። አማራና ኦሮሞ ተባብረው እንደዚህ በአንድነት በአጭር ጊዜ ውስጥ አብረው ይቆማል ብሎ ህወሃት አላሰበም፣ ከዚህ በፊት የኦሮሞና የአማራው በመከላከያ ውስጥ መብዛት ህወሃት እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ጥቅም ነበር ያየው። ምክንያቱም በመከላከያ ውስጥ አማራና ኦሮሞን እያመጣጠነና እያቃረነ ታዛዥ ማድረግ እንደሚቻል በፅኑ ያመነበት የማካቬሊያን የአስራ አምስተኛው የጨለማ ዘመን አስተሳሰብ ነው። በህወሃት የደደቢት ስሌት መሰረት አማራና ኦሮሞ ለሁልጊዜ ጠላት ሆነው የሚኖሩ ማህበረሰቦች ናቸው። በህወሃት የደደቢት ስሌት መሰረት አማራዎች ስለበደኖ ብቻ እያሰቡ፤ ኦርሞዎች ደግሞ ስለ አኖሌ ብቻ እያሰቡ ሁልጊዜም በለቅሶ፣ በጠላትነትና በበቀል የሚኖሩ ፅናት የሌላቸው ሞኝ ማኅበረሰቦች ናቸው። ስለዚህ ይህን ቅራኔ በማራገብና በማስፋፋት ብዙ ጊዜ ለመግዛት እችላለሁ የሚል መሰሪ እምነት ነበረው። አሁን ይህ መሰሪ አላማ ህወሃት ባልጠበቀው ሁኔታ በቅፅበት ተፈረካከሰ፤ ህወሃት ሌላ መተኪያ ሳይፈጥርለት ዋናው የተንኮል መንገዱ በፍጥነት ተፈረካክሷል። ለህወሃት ጊዜ መስጠት ማለት ሌላ የተንኮል ዘዴ እንዲፈጥር እድል መስጠት ማለት ነው። ህወሃት ካሁን በኃላ አንድ ዓመት እንኳን ቢቆይ የመከላከያ ሰራዊቱን የሰው ኃይል ስብጥር በሌላ ታዛዥ ሆነው ብዙ ይቆያሉ ብሎ በሚያስበው የሰው ኃይል በማጨቅ ሕዝቡን እየጨፈጨፈ ለመግዛት እንደሚሞክር የታወቀ ነው። ስለዚህ ይህን የመሰለ ብዙ ሁኔታዎች የተመቻቹበት ዓይነት ጊዜ ብአዴንና ኦህዴድ እንደገና ሊያገኙ አይችሉም። ይህን የመሰለ ዕድል በከንቱ መባከን የለበትም። በከፍተኛ መስዎዕትነትም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነት ቀን አይቀሬ ነው።

የአማራና የኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት ዓላማው በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጎጂ ንትርክ ሳይሆን ጤናማ ውይይትና ትብብር የሚጎለብትበትን መንገድ የሚያበረታቱ ሀሳቦችን በማፈላለግና በማሰራጨት፤ በአማራና በኦሮሞ ልዒቃን መሀከል የሚደረገው የታሪክ ንትርክን በተመለከት የታሪክ ባለሙያዎች በሰለጠነ መንገድ በመከባበር እንዲወያዩበት የሚገባ መሆኑን እያበረታታ። በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢው ጉዳይ ግን የአማራና የኦሮም የፓለቲካ ልዒቃን የታሪክ ንትርኩን ለታሪክ ባለሙያዎች በመተው በአንገብጋቢው የወቅቱ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በማተኮር የህወሃትን አገርንና ሕዝብን የሚያጠፋ ድርጊት ለመቋቋም የሚችሉበትን የትብብር ጉዳዮች ላይ ጥረት ማድረግ ነው።

ከአማራና ኦሮሞ ትብብር ይለምልም ፕሮጀክት
AOCPP (Amhara and Oromo Cooperation Promotion Project)
Contact: aocpp2016@gmail.com
___
ማስታወሻ ፤ በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ አመለካከቶች የጸሃፊውን /ዋን እንጂ የድረ ገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ለማጋራት ወይንም ሃሳብ በሚከተለው አድራሻ መላክ ይቻላል፤ editor@borkena.com

ወቅታዊ መረጃዎችን እና ትንታኔዎችን ለማግኘት ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ማድረግ አይርሱ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here