spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትግልጥ ደብዳቤ ለ“ኢሕአዲግ መራሹ” መንግስት፤ በብሔራዊ ዕርቅ ሃገራችንን እናድን!(በጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ)

ግልጥ ደብዳቤ ለ“ኢሕአዲግ መራሹ” መንግስት፤ በብሔራዊ ዕርቅ ሃገራችንን እናድን!(በጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ)

በጥበበ ሣሙኤል ፈረንጅ
ታህሳስ 27 ፤ 2010 ዓ ም

ፀሃፊውና ሙዚቀኛው ኦስካር አሊክ-አይስ “የፈለገው ዓይነት ጥላቻ ቢኖር፤ ሰላም ሊኖር ይችላል ብለህ ጠብቅ፤ ሁልጊዜም ለይቅርታ ቦታ ይኑርህ” ይላል በግርድፉ ሲተረጎም። ዛሬ በግፍ በእስር ላይ የሚገኘው ወጣቱ አንዱአለም አራጌ፤ “ያለተሄደበት መንገድ” በሚል ርዕስ ከእስር ቤት ሆኖ በፃፈው፤ ማንዴላዊ ይዘት ባለው መጽሐፉ፤ ሃገራችንን ከገባችበት ከባድ አደጋ ልናድናት የምንችለው በብሔራዊ ዕርቅ ብቻ መሆኑን በማያወላዳ ሁኔታ አስቀምጦታል።

የብሔራዊ ዕርቅ አጀንዳ፤ ሲነገር ይኽው 27ኛ ዓመቱን ይዟል። የወታደራዊው መንግስት ከመውደቁ ከጥቂት ወራት በፊት፤ በሃገራችን ብሔራዊ ዕርቅ እንዲኖር በርካታ ሰዎች ጽፈዋል፤ ተናግረዋል፤ ታግለዋል፤ የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል። ሆኖም ባለመታደል፤ ጠብመንጃ የያዘው “አሸናፊ ቡድን” ለብሔራዊ ዕርቅ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ፤ አደገኛና አገር አፍራሽ ፖሊሲ በመከተሉ፤ ዛሬ ፈጦ የምናየው አደጋ ላይ ደርሰናል። የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ፤ ታላቁ ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ውቅት ያሉት፤ ዛሬ ለሃገራችን ለኢትዮጵያ ጥሩ መስተዋት ሆኖ ያገለግላል ብዬ አምናለሁ።

“ደቡብ አፍሪካ አንድነቷ እንዲረጋገጥ፤ የእርቅ መንፈስ እንዲጠነክር፤ እንዲሁም በተቻለ ፍጥነት ሃገራችን የእድገት ጎዳና እንድትይዝ፤ ጥሩ (መልካም) ወንድና ሴቶችን ማንቀሳቀስ (ማስተባበር) ይቻላል” ኔልሰን ማንዴላ (ድምቀት የተጨመረ)።

የ2018 የምዕራባውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ፤ ፌስ ቡክ ግድግዳዬ ላይ ስጽፍ፤ አንዱ ምኞቴ ቸሩ እግዚአብሔር “ለገዥዎቻችን” የማስተዋልን ጥበበ ሰጥቷቸው፤ የያዙትን የጥፋት ጎዳና በማስተካከል የፖለቲካ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ነበር። የእኔና በሚሊዮን የሚቆጠረው ኢትዮጵያዊም ምኞትና ሕልም እውን ሊሆን መንገድ የያዘ ይመስላል። በታህሳስ 25 ቀን 2010 (01/03/2018) በገዥው ፓርቲ የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለብዙዎቻችን እውነተኛ ዜና እንዳልምሰለን፤ ማህበራዊ ሚድያዎችን ማየት ብቻ በቂ ነው። ይህ ገዥው ፓርቲ በምንም መልኩ ያደርገዋል ተብሎ ያልተጠበቀ መልካም ዜና ነው። ምንም እንኳን መግለጫው እርስ በእርሱ የሚጋጭ ይዘት ያለ ነገር ቢኖርበትም፤ ሲተገበር እየተስተካከለ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ። ብዙ ኢትዮጵያውያን በመግለጫው ቢደሰቱም፤ መግለጫውን በጥርጣሬ ለማየት ተገደዋል። ይህም ያለምክንያት አይደለም። ላለፉት 26 ከተኩል አመታት፤ ገዥው ፓርቲ “እታደሳለሁ” በሚል ዜማ ሕዝቡን ያደነቆረው በመሆኑና፤ ሕዝቡ በገዥው ፓርቲ ላይ ፍጹም እምነት ስለሌለው ነው። ለዓመታት እራሱን ሲሽነግል እና ሕዝቡን ሲዋሽ የነበረው ፓርቲ፤ በተደረገበት የሕዝብ ግፊት፤ በተደረገው ታላቅ ተጋድሎና፤ ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነት፤ መራራውን እውነት ለማየት እና፤ “ብሔራዊ የመግባባት” አጀንዳ ላይ እሰራለሁ ለማለት ተገዷል። በዚህ መግለጫውም፤ የፖለቲካ እሰረኞችን በተመለከተ ድፍን ያለ ነገር ከመግለጹም በላይ፤ የፖለቲካ እሰረኞቹን “ወንጀለኞች” የሚል ታርጋ መለጠፉ በዙዎቻችንንም አስደምሞናል።

ይህችን ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ የፈለግኩት፤ የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት እንዳለባቸው ለማሳሰብና ቀጣዩ እርምጃ ምን መሆን እንዳለበት የሚሰማኝን ለመጠቆም ነው። ገዥው ፓርቲ መሳሳቱን ብቻ ሳይሆን፤ ለሃገሪቱ “ነቀርሳ” ሆኖ መቆየቱን በማያሻማ ሁኔታ ገልጿል። ከገዥው ፓርቲ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ዜጎች አማራጭ በማሳጣቱም ምክንያት፤ አንዳንዶቹ ወደ አመጽ ለመሄድ መገደዳቸውን በመግለጫው ላይ ጠቁሟል። በሌላ አነጋገር፤ “ፖለቲካ እስረኞቻችን”፤ ገዥው ፓርቲ ላለፉት 26 ከተኩል ዓመታት የተሳሳተና አደገኛ የፖለቲካ አቅጣጫ ሲከተል፤ “ተው፤ ተሳስታችኋል፤ ሃገራችንን አደጋ ላይ እየጣላችሁ ነው” ብለው በተለያየ መንገድ ለገዥው ፓርቲ የጠቆሙ፤ አቅጣጫውን እንዲያስተካክል የታገሉ፤ ሙስናንና መጥፎ አስተዳደርን የተቃወሙ፤ በዲሞክራሲ ስም የተሰራውን ሽፍጥ ያጋለጡ፤ በሃገሪቱ ባለስልጣናትና የጸጥታ ሃይሉ ያለአግባብ ዜጎች ሲታሰሩ፤ ሲገደሉ፤ ሲጉላሉና ሲበደሉ፤ ግፉን ያጋለጡና የተሟገቱ ብርቅዬ ዜጎች ናቸው። ገዥው ፓርቲ፤ ሃገሪቱ ውስጥ በርካታ በደሎች መፈጸማቸውን ሲያምን፤ የአንድ ፓርቲ እና የጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ብቻ የነገሰበት አገዛዝ እንደሆን ሲቀበል፤ የ “ፍትሕ አስተዳደሩ” የተበላሸ መሆኑን መቀበል ይኖርበታል። ዳኞቹ፤ አቃቤ ሕጉ፤ የጸጥታ ሃይሉ፤ ከዚህ ግፍና በደል ያልጠሩ መሆናቸውንም መቀበል ይኖርበታል፤ አለዛ የመግለጫው ጋጋታ ጉንጭ አልፋ ከመሆን አያልፍም። አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ፤ ዛሬ በእስር ላይ የሚገኙት ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች፤ የታሰሩት በገዥው ፓርቲ ስህተት ነው፤ ፍርድ ቤት የቀረቡት በተጭበረበረ ክስ ነው፤ የፈረዱባቸው ዳኞች ፍርድ የሰጡት በፖለቲካ ተጽእኖ ነው፤ ከገዥው ፓርቲ ነጻ የሆነና ፍትሃዊ ፍርድ ቤት የለም። ስለዚህ፤ እነዚህን ለውድ ሕይወታቸ ሳይሳሱ፤ ገዥውን ፓርቲ ተሳስተሃል፤ የያዝከው አቅጣጫ አደገኛ ነው፤ አገር አጥፊ ነው፤ ሕዝብን እርስ በእርሱ የሚያፋጅ ነው ብለው በሚችሉት መንገድና ባላቸው አቅም ሁሉ በመግለጣቸው፤ እንዴት ወንጀለኛ ሊባሉ ይችላሉ?

እነዚህ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጆች፤ ዛሬ ገዥው ፓርቲ “የተናዘዘውን” ቀድመው የተነበዩ ባለራእይ ዜጎች ናቸው። ፍላጎታቸውና የታገሉለት ዓላማ፤ በሃገራችን አንድነት እንዲኖር፤ ዲሞክራሲ እንዲጎለብት፤ የሰብአዊ መብት እንዲከበር፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ገዥው ፓርቲ የሚከተለው የዘር ፖለቲካ ሕዝብን በሕዝብ ላይ የሚያነሳሳ አደገኛ መሆኑን ለሕዝቡም ለገዥውም ፓርቲ ለማሳየት ነው። የፖለቲካ እስረኞቻችን የሃገር ባለውለታ እንጂ ወንጀለኞች አይደሉም። እንደገባኝ ከሆነ፤ የገዥው ፓርቲ ትልቁና ዋናው ስህተቱ የሕዝብን መብት ማፈኑ ነው። እነዚህ ብርቅዬ ዜጎችም የዚህ አፈና ሰለባ ናቸው፤ ይህ በጣም ግልጽ መሆን አለበት።

ገዥው ፓርቲ በጣም ቢዘገይም፤ ለመለወጥ ያሳየው ፍላጎት የሚደገፍ ነው። በመግለጫው ላይ ግን፤ አባላቱን፤ ወይም ደግሞ ዛሬም ሃገሪቱን በጠብመንጃና በስለላ መረብ የሚቆጣጠረውን ቡድን “ላለማስቀየም” በሚመስል መልኩ፤ የፖለቲካ እስረኞችን ፍትሃዊ በሆን ፍርድ ቤት፤ “በሰሩት ወንጀል” እንደተፈረደባቸው አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩ ግን፤ ገዥው ፓርቲ፤ ግማሽ መንገድ ለመሄድ መዘጋጀቱን የሚጠቁም ነው። ገዥው ፓርቲ ባጠፋው ጥፋት፤ በጣሰው ሕግ፤ በፈጸመው አፈና፤ ግድያና ግፍ፤ ዝም አንልም ብለው በገሃድ የተጋፈጡ ብርቅዬ ዜጎችን ወንጀለኛ ማድረግ፤ እራሱን የቻለ ወንጀል መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። እዚህ ላይ፤ ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ፤ “የሰላምና ዕርቅ ትርጉምና መንገዶች በሚለው መጽሃፋቸው በገጽ 105 ላይ ያስፈሩትን መጥቀስ ለሁላችንም ልንከተለው ለሚግባ አቅጣጫ አመላካች ይሆናል፤ “ስሕተትና መከራ ታላቅ አስተማሪዎች ናቸው። በጥበብ ከመረመርናቸው ማንም ታላቅ መምህር ሊያስተምረን የማይችለውን ትምህርት ሊያስተምሩን ይችላሉ።ትክክለኛውን ትምህርት ከቀሰምን ያለፍንበት መከራ በእሳት እንደ ተፈተነ ወርቅ ሰብአዊነታችንን ያነጥረዋል ወደ ከፍተኛ ደረጃ ያሸጋግረዋል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የመከራው ትርጉሙና ትምህርቱ ምንድነው ብሎ ከመጠየቅ፤ ከመማርና ከመሻሻል ይልቅ መከራው ባስከተለው ክፋት፤ቁጣ፤ ፍርሀት፤ ጥርጣሬና በቀል በመነዳት ያንኑ መከራ የሚደግሙ ተግባሮችን እንፈጽማለን” (ሰረዝና ድምቀት የተጨመረ)። ይህ ታሪካዊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል፤ የገዥው ፓርቲ በሃገርና በሕዝብ ላይ የፈጸመውን በደል ተረድቶ፤ ወደ ብሔራዊ መግባባት ለመሄድ የተጀመረ ጉዞ፤ በተለይም ላለፉት 44 ዓመታት በሃገራችንና በሕዝባችን ላይ የተፈጸመው ግፍ እንዳይደገም፤ ወደ ብሔራዊ መግባባትና እርቅም እንድንሄድ፤ ገዥው ፓርቲ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ፤ በግፍ የታሰሩት፤ የተሰደዱት፤ የቆሰሉት፤ የተገደሉት፤ እንዲሁም በሰላማዊም ሆነ፤ በአመጽና በትጥቅ ትግል ለመሳተፍ የተገደዱት ብርቅዬ ዜጎች፤ ወንጀለኞች እንዳልሆኑ መቀበል ቀጣይ እርምጃው መሆን አለበት። ገዥው ፓርቲ ሕግ በመጣሱ፤ አፋኝ በመሆኑ፤ ኢዲሞክራሲያዊ በመሆኑና ሞልቶ በፈሰሰው ግፍ ምክንያት፤ ተቃውሞዋቸውን ለማሰማት የበኩላቸውን ያደረጉ ዜጎች ወንጀለኞች አለመሆናቸው እውቅና ሊያገኝ ይገባዋል።

ይህ ታሪካዊ ክስተት ገዥው ፓርቲ ወዶና ፈልጎ ለሕዝብ የሰጠው ስጦታ ሣይሆን፤ ግፉዓን በፈጠሩት ግፊትና በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከሰተ መሆኑም ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባዋል። እንደ አቶ ለማ መገርሣ ያሉ የገዥው ፓርቲ አካላት፤ የሕዝቡን የበደል ጩኽት ሰምተው በማስተጋባታቸውና፤ ፈጦ የመጣው አደጋ ስለታያቸው ነው፤ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ የደረስነው። ይህ ለማንም ግልጽ ሊሆን ይገባዋል። “ወሬ ቢበዛ በአህያ አይጫንም እንዲሉ ነውና” የገዥው ፓርቲ የመጀመርያ እርምጃ መሆን ያለበት፤ ከሕግ ውጪ ያሰራቸውን፤ ፍትሃዊና ነጻ ባልሆነ ፍርድ ቤቱ ያስፈረደባቸውን ብርቅዬ ዜጎች በአስቸኳይ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት ነው። ይህ ሳይሆን፤ ወደ ብሔራዊ እርቅ ሊኬድ የሚቻልበት መንገድ የለም። የፖለቲካ እስረኞች ከተፈቱ በኋላም፤ ገዥው ፓርቲ፤ ጊዜ ሳይፈጅ፤ ከሃገሪቱ ሽማግሌዎች፤ ከተለያዩ የእምነት ተቋማት አባቶች፤ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ከሃገሪቱ ምሁራን፤ ከወጣቶች፤ ከሙያና፤ ሕዝባዊ ማህበራት፤ ከመገናኛ ብዙሃን፤ እንዲሁም በሃገራችን ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ግለሰቦችና ተቋማት ከተውጣጡ ዜጎች፤ አንድ ኮምሽን በማቋቋም፤ ኮምሽኑ የሃገሪቱን የብሔራዊ ዕርቅ አጀንዳ መቀመር ይኖርበታል። ይህም እስኪሆን ድረስ፤ በጸጥታ ሃይሉ፤ የሚደረግ ሕገ ወጥ እስራትም ሆነ ግድያ በአስቸጓይ እንዲቆም፤ በማያወላዳ ሁኔታ ትዕዛዝ መተላለፍ አለበት። የቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዝዳንትና፤ አንዱ የአሜሪካ ሕገ መንግስት አርቃቂ የነበሩት ቶማስ ጃፈርሰን እንዳሉት፤ “ካለፈው ታሪክ የበለጠ የወደፊቱን ሕልም እወደዋለሁ”። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊባል በሚችልበት መልኩ፤ በዚህ ታሪካዊ ጅማሮ ከፍተኛ ተስፋ ጥሏል። ይህን ጅማሮ፤ በፍጥነት መተግበር ደግሞ የገዥው ፓርቲ ሃላፊነትና ግዴታ ቢሆንም፤ እንደዜጋ፤ እያንዳንዳችን የምንጫወተው በጎ ሚና አለ። ይህ ጅማሮ ስኬታማ እንዲሆን፤ ሁላችንም፤ ሳንዘናጋ እድል ልንሰጠው ይገባል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብርቅዬ ዜጎቻችን፤ ሏዓላዊነቷና አንድነቷ የተጠበቀ፤ ዲሞክራሲያዊትና የሕግ የበላይነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ለመገንባት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ ይህ እውን እንዲሆን ለሃገራችንና ለዚህ ታላቅ ሕዝብ ዘብ የመቆም ታሪካዊ ግዴታ አለብን። ቸሩ እግዚአብሔር ሃገራችንና ሕዝባችንን ይጠብቅ።

ጸሃፊውን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል : tibebesamuel@yahoo.com

___
ማስታወሻ : በዚህ ጽሁፍ ላይ የተነጸባረቁ ሃሳቦች የጸሃፊውን ሃሳብ ያንጸባርቃሉ። በዚህ ድረ ገጽ ነጻ አስተያየት ወይ ሃሳብ ለማካፈል ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here