spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትኢህአዴግ ምን እያለ ነው?! (በመስከረም አበራ)

ኢህአዴግ ምን እያለ ነው?! (በመስከረም አበራ)

(በመስከረም አበራ)
ታህሳስ 30 2010

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ
የኢትዮጵያ ህዝብ በከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ውስጥ መሆኑ ያፈጠጠ ሃቅ ነው፡፡ የለውጥ አምሮቱ የሚንጠው የሃገራችን ፖለቲካ ከዲሞክራሲ ባነሰ ነገር እንደ ማይረጋጋ ሸርተት የማይል ሃቅ ሆኖ ሳለ ይለወጥ ዘንድ የተፈለገውን ስርዓት የሚጋልበው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ፣ከቅን ልቦና የመነጨ ለውጥ ለማምጣት ተፈጥሮውም፣አቅሙም፣ ፍላጎቱም፣ጆሮውም አለው ወይ የሚለው ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ህወሃት የቤቱን ራስ አቶ መለስን ካጣ በኋላ እንደተዳከመ እሙን ቢሆንም ከማንም በላይ የሃገራችንን የወደፊት እጣፋንታ በመወሰኑ በኩል አሁንም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ እሙን ነው፡፡ በሃገራችን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ውትርናም መስክ ክቡድ ህልውና ያለው ህወሃት ከስልጣኑ አሻግሮ የሃገርን እጣፋንታ በጎ የማድረጊያውን የተሻለ መንገድ የማየት አርቆ አሳቢነት እንዳለው የሚያሳይ ሪኮርድ የለውም፡፡ይልቅስ በማንኛውም መስዕዋትነት ስልጣኑን ማዳን፣በየትኛውም ኪሳራ የበላይነቱን ማረጋገጥ፣ እንደምንም ብሎ የጎሳውን ዘመን ተሻጋሪ ገዥ/ነጅነት ለማረጋገጥ በመፋተር ነው የምናውቀው፡፡

ንፁሃንን ከእስር መፍታት ግዴታ ነው ደግነት?!

ኢህአዴግ ከሰሞኑ ለሃገራዊ መግባባት ስል የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር የሆኑ እስረኞችን ሁሉ እፈታለሁ እያለ ነው፡፡ይህ ውሳኔው በጣም የሚያስደስት ቢሆንም ቅንነት አጥብቆ ከራቀው ህወሃት መራሹ ግንባር የወጣ ነውና ልናየው ሚገባው በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ እስረኞቹ እስርቤት የሚማቅቁት ቀለላል የሆነውን ለራስ የኖር ዘይቤ ንቀው ብፁዕ እና ከባድ የሆነውን ለሌሎች የመኖርን መልካም ዕጣ ስለመረጡ ነው፡፡ኢህአዴግ አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ ፀረ-ሰላም እያለ እንደ ተራ ወንበዴ የሚያበሻቅጣቸው ሰዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከተዘፈቀበት መከራ መውጫ የተስፋ ጭላንጭል አድርጎ የሚያስባቸው ባለብሩህ አዕምሮዎች ናቸውና እስራቸው እስሩ ነው፡፡በበኩሌ እነዚህን የፖለቲካ እስረኞች ባሰብኩ ቁጥር ከባድ የባለ ዕዳነት ስሜት ይሰማኛል፡፡

ኢህአዴግ እነዚህን ሰዎች ሲያስር ሚሊዮኖችን አብሮ እንዳሰረ፣በሚሊኖች ልብ ውስጥ ክፉ ጥላቻን እየተጠላ እንደሆነ የሚያስብ አይመስለኝም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ጉብዝናውን የሚለካው አስሮ በገረፈው ሰው ብዛት ይመስላል፡፡ ደደቢት በረሃ ኖሮ፣ጉና ተራራ ሰንብቶ የመጣ፣ጉብዝናውን በጣለው የወንድሙ ሬሳ ብዛት የሚመዝን፣ጀግንነቱን ባጠነው የባሩድ ሽታ የሚወስን እግረኛ ቀን ቀንቶት ስልጣን ላይ ሲወጣ ያንኑ የጦር ሜዳ የቆረጣ ስነልቦናውን ሊተው አይችልምና በየእስርቤቶቹ የሚያደርገው አውሬያዊ ባህሪ ከለመደው ግዳይ መጣል ጋር ያመሳስለዋል፡፡እናም የቀን ጎዶሎ በክፉ እጁ ላይ የጣላቸውን የህሊና እስረኞች በማይሞላው እስርቤቱ አጉሮ አሳር መከራ ያሳያል፡፡ ማሰባቸው ብቻ ወንጀል ሆኖባቸው የሲኦል ኑሮ መኖራቸው ሳያንስ በደጋፊዎቻቸው እንኳን እንዳይጠየቁ፣ታመው እንዳይታከሙ አድርጎ ‘ጎበዝነቱን’ በክፉነቱ ሲለካ ኖሯል፡፡ እድሜ እየተለመነላቸው ለሃገራቸው ሊሰሩ የሚገባቸውን ሰዎች እስርቤት አጉሮ ምጡቅ አዕምሯቸውን ቦአዝኖ፣ኩሩ ማንነታቸውን አሸማቆ፣ቅስማቸውን ሰብሮ፣ከሰውነት ጎዳና አውጥቶ በምትኩ ሃገርን ለጥራዝ ነጠቅ ካድሬ አስረክቦ ማላገጫ ማድረጉ ለይቅርታ የሚያዳግት የህወሃት/ኢህአዴግ ከተራራ የገዘፈ ጥፋት ነው፡፡

ይህ የሃገርን እርምጃ የማዘግየት ትልቅ ውድመት ድሮም መታሰር የሌለባቸውን ሰዎች በመፍታት ብቻ የሚስተሰረይ ሃጥያት ነው ብሎ ማሰብ የሞኝ ብልጠት ነው፡፡ ንፁሃንን ማሰሩ ራሱ ወንጀል መሆኑ የማያጠያይቅ ስለሆነ እስረኞቹን ከማይገባቸው የሲኦል ኑሮ መፍታቱ በትክክለኛው የፍትህ መንገድ ከታሰበ የመንግስት ግዴታ እንጅ እጅግም አጀብ የሚያስብል የደግነት መገለጫ አይደለም፡፡ማንም የማይጠይቀው አፄ በጉልበቱ ሆኖ ከመኖሩ የተነሳ ሳያጠፉ የታሰሩ የሃገር ሃብቶችን በእስርቤት ሲያሰቃይ ከርሞ ሲፈታልንም ስንደሰት ኖረናልና የዛሬው የእስረኛ እፈታለሁ የኢህአዴግ አዋጅ ከደስታ በላይ እንደሚያስደስተን የታወቀ ነው፡፡

ሆኖም ከደስታችን ስሜታዊነት ስንመለስ እነዚህ ሰዎች በእስር ያጡትን ነገር ከእስር መፈታት ብቻ እንደማይመልስላቸው እርግጥ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡በእስርቤት የባከነን የጉብዝና ወራት የሚመልሰው ማን ነው? ከገራፊ እጅ ከሚወርደው የዱላ መዓት እኩል ካልተገራ አፍ የሚዘንበውን ቅስም ሰባሪ ስድብ ከዕለታት አንድ ቀን ከእስር መፈታት ይክሰዋል?የልጅን ናፍቆት የቤተሰብን ርሃብ መካሻው ምንድን ነው? ይህ ሁሉ መከራ ሲወርድበት የኖረ ሰው ሃገሩን ሲወድ ከነበረው ውድ እጥፍ ጥላቻ ጠልቶ ከእስር ቢወጣ የሚጠቀመው ማን ነው? ለዚህ ሁሉ መንስዔ የሆነው አስሮ የማይጠግበው መንግስት ታዲያ እስረኛ ስለፈታሁ ይህ ለመለወጤ ምልክት ይሁናችሁና ተነስታችሁ አመስግኑኝ እያለ ነው፡፡ ለዚሁም ማን ተፈትቶ ማን ይቅር የሚለው ገና ጌቶችን እያወዛገበ እንደሆነ ነው የሚወራው፡፡

የመብት ተሟጋቾችን አስሮ ማሰቃየቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዴግ ላይ ካቄመባቸው ብዙ ጥፋቶቹ አንዱ እና ዋነኛው ነው እንጅ ብቸኛው አይደለም፡፡ ስለዚህ እስረኞችን እፈታለሁ ማለቱ አንድ በጎ ነገር ሆኖ ይወሰድ ይሆናል እንጅ የሥራ ሁሉ ፍፃሜ ነው ማለት አይደለም፡፡ኢህአዴግ ሲያጠፋ የኖረው ብዙ ስለሆነ ያለጥፋታቸው የታሰሩ እስረኞችን ከመልቀቁ ባሻገር ሊያርመው የሚገባው የትየለሌ ስህተት አለው፡፡

በሽፍታ ጭካኔ እንጅ በመንግስት ርህራሄ እና ምህረት የማናውቀው ኢህአዴግ ብድግ ብሎ እስረኛ እፈታለሁ ያለበት አካሄድ አላማ ግብ ራሱ በጥልቅ መጤን አለበት፡፡ በሃገራችን የፖለቲካ እስረኛ የለም ሲል የኖረው ገዥው ግንባር ዛሬ ብድግ ብሎ እፈታቸዋለሁ ያላቸውን የፖለቲካ እስረኞች የሚጠራበት ስም አጥቶ “የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች” ይል ይዟል፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሚል ስም የተሰጣቸው ሰዎች ከፖለቲካ በቀር የምን እስረኞች ሊባሉ ነው?ደግሞስ መንግስት ሃሳባቸው ከሃሳቡ ጋር ስላልገጠመ ብቻ ያሰራቸው የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ብቻ ነው?ከሆነ እስክንድር ነጋ የየትኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ተብሎ ነው የታሰረው? ይሄ ሁሉ መንተፋተፍ ቀድሞ የፖለቲካ እስረኞች በግዛቴ የሉም ሲባል የተኖረውን ለማስተባበል ታስቦ ነው፡፡ነገሩ ግን ከንቱ ድካም ነው፡፡የሚያመላክተውም የኢህአዴግን ከአፈርኩ አይመልሰኝ ገታራነት ዳርቻ፣ስህተቱን ከሚያምን ፍርጥ ብሎ መሞትን የሚመርጥ፣በመለወጡ ተስፋ የማያደርጉበት ድርጅት መሆኑን ነው፡፡ ይህ እና ሌሎች በኢህአዴግ አባል ፓርቲ ሊቀመንበሮች በተሰጠው መግለጫ ላይ የተሰገሰጉ የማድበስበስ፣ማስቀየስ፣መካድ እና ሃቅን የመሸሽ ሁኔታዎችን ስናስተውል ፓርቲው እስረኞችን እፈታለሁ የማለቱ እርምጃ ራሱ ኢህአዴግ እንደሚያወራው ለሃገራዊ መግባባት ሲል ያደረገው ከራሱ የመነጨ፣የፍፁም መለወጡ ምልክት ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል፡፡

መግለጫው ሲገለጥ

ኢህአዴግ የቀድሞው ተሃድሶየ ጥልቀት ስለጎደለው ተመሼ ወደ አዘቅት ወርጃለሁና ሌላ ግምገማ ያስፈልገኛል ብሎ ለሃያ የተጠጋ ቀን እንደ ኑዛዜ የሚቃጣው ግምገማ አድርጓ ተመልሷል፡፡ ግንባሩን ለአስቸኳይ ሂስ ቀመስ ስብሰባ ያበቃው በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ያለችበት አስፈሪ ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ይህ ቀውስ የታየው ደግሞ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች ብቻ አይደለም፡፡እንደውም ከፍተኛ ቀውስ ላስከተለው የኦሮሞ ህዝቦች ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መፈናቀል ስረ-ምክንያቱ አጋር ፓርቲ በሆነው ኢሶህዴፓ አስተደደር ነው፡፡ነገር ግን ኢሶህዴፓ በሰሞኑ የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አልተካፈለም፤ለማብራሪያም አልተገኘም፡፡ በተመሳሳይ አማሮች በገጀራ እየተመተሩ የተጣሉበትን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሚያስተዳድረው ቤጉዴፓም የስብሰባውም ሆነ የመግለጫው አካል አይደሉም፡፡ይህ ከኢህአዴግ የአባል እና አጋር ድርጅቶች ሚስጥራዊ ተፈጥሮ እና ግንኙነት የሚመነጭ እንቆቅልሻዊነት አጋር ድርጅቶች ምን አይነት አካላት እንደሆኑ ይበልጥ እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንዲፈናቀል፣ክቡር የሰውልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ በገጀራ እንዲመተር ያደረገን አመራር የግምገማው አካል ያላደረገ የተለውጠናል አዋጅ ለማን ትርጉም ይሰጣል ተብሎ እንደሚወራ ግራ ነው፡፡

እንዲህ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የተሰየመው ስብሰባ እንደ ተቋጨ ለየት ያለ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ የተላለፈበት እንደሆነ ኢህአዴግ በፀሃፊው በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ በኩል አስነገረ፡፡ይህም መግለጫው በጉጉት እንዲጠበቅ አደረገ፡፡ ከዚሁ ግምገማ መልስ ረዘም ያለ መግለጫ ማውጣቱ የማይበቃ ሆኖ የግንባሩ እህት ድርጅቶች ከረዥሙ መግለጫ የረዘመ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ሆኖም የግምገማው መግለጫም ሆነ የእህት ድርጅቶ ማብራሪያ የተጠበቀውን ያህል የኢህአዴግን መለወጥ የሚያመልክት ሆኖ አልተገኘም፡፡ይልቅስ የተለመደው ማድበስበስ፣ አድማጭን ቂል አድርጎ የማየት የሞኝ ብልጠት እና ጭልጥ ያለ ክህደት የታየበት ነው፡፡

ማስቀየስ

በመግለጫውም ሆነ የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች ነን ብለው በቀረቡት የፓርቲ ሊቀመንበሮች የተሰጠው ማብራሪያ የችግርን አናት ከመምታት ይልቅ ማድበስበስ እና ማስቀየስ የበዛበት ነበር፡፡ ኳስ ሜዳ ሳይቀር በዘር የሚጋደሉበት መድረክ የሆነው በጎሳ ፌደራሊዝሙ ሳይሆን በአፈፃፀሙ የተነሳ ነው ይላሉ የተሻለ የተናገሩ የመሰላቸው ኢህአዴጎች፡፡ዘራቸውን መቁጠራቸው ብቻ ባለስልጣን ያደረጋቸው ካድሬዎች የስልጣን ህልውናቸው የሆነውን የጎሳ ፌደራሊዝም በክፉ ባያነሱ አይገርምም፡፡የሚገርመው የሚወቅሱት የጎሳ ፌደራሊዝሙ አፈፃፀምም ቢሆን ከራሳቸው ውጭ ባለቤት እንደሌለው አለማወቃቸው ነው! አፈፃፀሙ አላማረም የሚሉት የጎሳ ፌደራሊዝም በማን እጅ ሆኖ ነው ያላማረው? የአፈፃፀም እንከኑ በስልጣን ላይ ቂጥጥ ካሉት ከእነሱ አላዋቂነት ሌላ በማን ሊመካኝ ነው? ሃያ ምናምን አመት ሙሉ አፈፃፀም አልቻልኩም የሚል አስፈፃሚ ምን ሊያደርግ ስልጣን ላይ ይቀመጣል?

እውን ችግሩ ከጎሳ ፌደራሊዝሙ ሳይሆን ከአፈፃፀሙ ቢሆን ኖሮ በካቢኔ ለውጥ፣በሹም ሽር የሚፈታ ቀላል ነገር ነበር፡፡ ኢህአዴግም በየጊዜው ሹም ሽር ሲያደርግ ኖሮ ጭራሽ የዶክተሮች ካቢኔ አመጣሁ ባለ ማግስት አፈፃፀምን እንደ ብርቱ ችግር እያወራ ነው፡፡ይህ የሚያሳየው የሃገሪቱ የፖለቲካ ችግር ሁሉ የሚቀዳው ከራሱ ከግንባሩ ማንነት እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የሃገር ችግር እንዲፈታ ራሱ ግንባሩ ከነእህትም ሆነ አክስት ድርጅቶቹ ከህዝብ ጫንቃ ላይ ሲወርድ ነው፡፡ የህዝብ ጥያቄም ያረጀ ያፈጀው ግንባር ከስልጣን ገለል እንዲል እንጅ ለማያርመው ጥፋቱ የተለያየ ስም እያወጣ ሁሌ ማሩኝ እንዲል አይደለም፡፡

መግለጫውም ሆነ የባለስልጣናቱ ማብራሪያ ያስቀመጠው ሌላው ጉዳይ የሃገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች እየተዳደሩ ያሉት በራሳቸው ልጆች ነው የሚለው ባለ መንታ ገፅ ማስቀየሻ ነው፡፡ የዚህ አባባል አንዱ መልዕክት ለሃገሪቱ ችግር ሁሉ ህወሃትን ተቀዳሚ ተወቃሽ አታድርጉ፣ችግር ካለም ችግሩን የፈጠሩት በየክልላችሁ የሚያስተዳሯችሁ የጎሳችሁ ሰዎች ናቸው የሚል ነው:: ይህ በዋነኝነት የሚያነጣጥረው በትግራይ እና በሌሎች ክልሎች መሃከል ፍትሃዊ ያልሆነ እድገት አለ በሚል ጎላ ብሎ በሚነሳው እና ህዝዊ እንቅስቃሴውን በዋናነት ባጎነው ጉዳይ ላይ ነው፡፡
በአይን የሚታየውን የኢፈርትን መንሰራፋት ተጠቅሶ ለሚቀርበው ክርክር ህወሃት መልስ ማድረግ የፈለገው ኢፈርትን ያመጣው የህወሃት አመራሮች ጠንካራነት እንጅ ሌላ እንዳልሆነ፣በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ የፋብሪካዎች መዋለድ እንዲታይ ያላደረገው የእህት ፓርቲዎች መሪዎች ድክመት ስለሆነ እዛው የራሳችሁን መሪዎች ውቀሱ እና ተቻቻሉ እንጅ ነገሩን የህወሃት የበላይነት ያመጣው አድርጋችሁ አትውሰዱ ለማለት ነው፡፡ ይህ ማድበስበስ የማይመልሰው አብይ ጥያቄ ግን ክልሎች ራሳቸውን እያስተዳደሩ ከሆነ በቅርቡ በኦሮሚያ፣በአማራ እና በደቡብ ክልሎች በሚደረጉ የህባዊ አመፆች ላይ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ሰልፈኞች የሚያስተዳድሯቸውን ፓርቲ ማለትም ኦህዴድ ወይም ብአዴን ወይም ደኢህዴን ይውረድ ከማለት ይልቅ “ዳውን ዳውን ወያኔ” ሲሉ አሻግረው የህወሃትን ፍፃሜ የሚናፍቁት ለምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡

የዚህ ማስቀየሻ ሌላው መልዕክት የጎሳ ፌደራሊዝሙን የማሞካሼቱ ቅጥያ ነው፡፡የትግራይ ህዝብ በየቤቱ ልጅ አዋጥቶ ለድል ያበቃው ህወሃት የፈጠረው የጎሳ ፌደራሊዝም ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ያደረገ፣የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ፈቅደው የመሰረቱት ብቸኛ እፁብ መንገድ ነው ባይ ነው ህወሃት/ኢህአዴግ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረው የጎሳ ግጭትም የአፈፀፀም እንጅ የሌላ ችግር ስላልሆነ ህወሃት አምጦ የወለደውን፣ዘላለም የበላይ ሆኖ በስልጣን የመኖሩ መሰረት የሆነውን የጎሳ ፌደራሊዝም በዜግነት ፖለቲካ በተቃኜ ሌላ አይነት ፌደራሊዝም ለመቀየር የምታስቡ አደብ ግዙ የሚል ነው፡፡ ይህን አጥብቆ መናገር ስላስፈለገ ከመሄዳቸው መምጣታቸው የቀደመው አቶ በረከት ስምኦንም በየደረሱበት ሲያወሩት ሰንብተዋል፡፡ ይህን ማስረገጥ ያስፈለገው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሃት አጥብቆ በሚፈልገው የጎሳ ፌደራሊዝሙ ላይ ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያዎች በህዝቡ ዘንድ ስለታዩ ነው፡፡

ማድበስበስ

የእህት ፓርቲ አመራር ነን ብለው የቀረቡት አራት አመራሮች አብዝተው ያድበሰበሱት የህወሃት የበላይነት ጉዳይ ከህወሃት በቀር ሶስቱ ፓርቲዎች ያሉበትን የአሽከርነት ደረጃ ያሳያል፡፡ አቶ ለማ እና አቶ ደመቀ የማይጋረደውን የህወሃት ጌትነት ለመጋረድ የሚያደርጉት መቁነጥነጥ፣የሚናገሩት ሞልቶ ተርፎ በጌታ ምሳር ላለመከተፍ ሲሉ ብቻ ሃቅን ከአፋቸው ለመመለስ የሚታገሉት ትግል፣ቁና ቁና የሚያስተነፍሳቸው የፍርሃት ሰራዊት እነሱን ሳታደርግ ግደለኝ ያስብላል፡፡

የገዥዎች እንጅ የአንድ ብሄር የበላይነት ዛሬም ድሮም እንደሌለ ለማስገንዘብ ታሪክን አጣቅሰው ያስረዱት አቶ ለማ መገርሳ ይህ ማለት እበልጣለሁ ባይ የለም ማለት አይደለም፣በፌደራል መስሪያ ቤቶች የአንድ ወገን ህልውና ጎልቶ አይታይም ማለት አይደለም ሲሉ የጌታን ስም ሳይጠሩ ዳርዳር ብለዋል፡፡የህወሃት አድራጊ ፈጣሪነት የፈጠረባቸው ብሶት ከፊታቸው የሚነበበው አቶ ለማ መገርሳ ህወሃት ከራሱ ፓርቲ አልፎ በእሳቸው ፓርቲ ውስጥ ቡድንተኞችን እያሰለፈ እንደሚያምሳቸው፣የሚሰራ በማይሰራ ተጠልፎ እንዲወድቅ እያደረገ ፈተና እንደሆነባቸው በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች እህት ፓርቲዎች ድንበር አልፈው በሌላ ፓርቲ ውስጥ ገብቶ በመፈትፈት አልተወቀሱም፡፡ ይህ ራሱ የህወሃትን የበላይነት የማይመሰክረው እንዴት እንደሆነ እህትማማች ነን ባዮቹ ራሳቸው ያውቃሉ!

አቶ ኃ/ማርያም በበኩላቸው የትግራይ የበላይነት ቢኖር ኖሮ ትግረኛ ተናገሩ ተብለን መቸገር ነበረብን፣የትግሬ ባህል እላያችን ላይ ይጫን ነበር ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የአንድ ብሄር የበላይነት አለማለት አንችልም ሲሉ የፖለቲካ ግንዛቤያቸውን ያህል ሲናገሩ በአቶ መለስ አእምሮ ለምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ያሳጫቸውን ምስጢር ገለፁ፡፡ አቶ መለስ ያደረጉት እንዳይቀርባቸው “አንድ አሰፋ የሚባል ሰው ከእናቱ ጋር ሲኖር ሲኖር…” ብለው ለሶስተኛ ክፍል ተማሪዎች እንኳን በሚያዛጋ ተረት አዘል ማብራሪያ የጀመሩት አቶ ኃ/ማርያም ይህን ሲሉ ማንኛውም ካድሬ አፉን የሚፈታበትን የአማራን ጨቋኝነት እና የህወሃትን ከዚህ ጭቆና አውጭ ቤዛነት ማስረገጣቸው ነው፡፡ እግረ መገዳቸውንም እሳቸውን የመሰለ ሰው ጠ/ሚኒስትር ያደረገውን “ድንቅ” ሥርዓት ለመመስረት የትግራይ ህዝብ ከአንድ ቤት ስድስት ሰባት ሰው በመገበር የከፈለውን መስዕዋትነት ገልፀው ከዛው ብሄር የወጡ ግን ደግሞ ለትግሉ ልጅ ያላዋጡ ኪራይ ሰብሳብዎች እንዴት በትግራይ ህዝብ ስም እየነገዱ እንደሆነ ገልፀው አሳርገዋል፡፡በእሳቸው ቤት ኪራይ ሰብሳቢ የተባሉት ትግሬዎች ኪራይ የሚሰበስቡት ከላይ አይዞህ ባይ ጌታ ሳያስቀምጡ እንዲሁ በአየር ላይ ነው፡፡ሰውየው አቶ ኃ/ማርያም ናቸውና ከዚህ በላይ አይጠበቅባቸውም፤የአንድ ወገን የበላይነት የሚገለፅበትን ፈርጄ ብዙ ማመሳከሪያ አገናዝበው እንዲናገሩ መጠበቅ ከእሳቸው መባስ ነው፡፡

መናገሩም መተውም የከበዳቸው የሚመስሉት አቶ ደመቀ ፈራ ተባ እያሉ የህወሃት የበላይነት አለ የሚባለው እንዲሁ ሳይሆን መንጠላጠያዎች ስላሉ ነው ቢሉም መንጠላጠያዎቹ ምን እንደሆኑ ሳያስረዱ አድበስብሰው ትተውት ለህወሃት ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ቤተኛ ነኝ ባይ ትግሬዎች የትግራይ የበላይነት ያለ የሚያስመስሉ ስለሆኑ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጠቁመው አለፉት፡፡የአቶ ደመቀ ንግግር ሲጠቃለል የህወሃት የበላይነት ያለ ይመስላል እንጅ የለም፡፡ ያለ የመሰለው ደግሞ አንዳንድ መንጠላጠያዎች ስላሉ ስለሆነ እነዚህን መንጠላጠያዎች ለማስወገድ ኢህአዴግ በመወሰኑ ችግሩ ይቀረፋል ሲሉ ሌላው ቢቀር አራቱ ሰዎች በተቀመጡት መድረክ ላይ የሶስቱ ፓርቲዎች መሪዎች ስለ ህወሃት የበላይነት ለመናገርም ለመተውም በሚያዩት አሳር መከራ ሳይቀር የሚገለፀውን የህወሃት የበላይነት አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡ አቶ ኃ/ማርያም የህወሃት የበላይነት እንደሌለ የደሰኮሩትን ነገር የማይዋጥለት ብዙ እንደሆነ ጠቆም ማድረጋቸው የሚናገሩት ነገር እውነት ሃሰትነት ለራሳቸውም እንደማይጠፋቸው ያሳብቃል፡፡የህወሃቱ ዶ/ር ደብረፅዮን የህወሃት የበላይነት የሚለወን ነገር ያስጀመረባቸው ደርግ እንደሆነ፣ ያኔ በድርድሩ ወቅትም ከህወሃት እንጅ ከኢህዴን ጋር አልደራደርም ሲል እንደነበረ ይህ ነገር አሁንም የቀጠለው የተመሰረተው ስርዓት የሁሉም እንዳልሆነ ለማስመሰል በሚደረግ ተንኮል እንጅ ሌላ የሚጨበጥ ምክንያት እንደሌለው ሰሚ ካገኙ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ሌላው አናዳጅ ማድበስበስ የኢህአዴግ መንግስት የሰብዓዊ መብት አያዝን በተመለከተ የተነገረው ይሉኝታ ቢስነትን የጨመረ ሹፈት ነወ፡፡በዚህ ረገድ አራቱም መሪዎች አላግጠዋል፣የምናውቀውን እንደማናውቅ ሊያሞኙን ሞክረዋል፡፡የመንግስታቸው አውሬያዊ አረመኔነት የሚገለፅበትን የህሊና እስረኞች አያያዝ በተመለከተ ያለውን ያፈጠጠ ሃቅ ሊክዱ ከንቱ ደክመዋል፡፡ በፍርድ ቤት ችሎት የተገኘ ሁሉ የሚያነባበትን በተለይ በፖለቲካ እስረኞች ላይ ስለሚፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት ትንፍሽ ሳይሉ ‘እንደተጠበቀው አይደለንም እንጅ ምንም አንልም’ ሲሉ አላገጡ! ማዕከላዊ የሚባለው የሲኦል ቅርንጫፍም የሚዘጋው በደርግ ዘመን የነበረው የስቅይት ቆሌ እየመጣ እያስደነገጠ ስለሆነ እንጅ ዛሬ ግፍ ስለሚሰራበት አይደለም ባይ ናቸው በደህና ቀን ይሉኝታቸውን የጣሉት ጠ/ሚኒስትር ተብየው ሰውየ! አቶ ለማ መገርሳም እስረኞች በምርመራ ጊዜ የሚደረገውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በለሆሳስ አልፈው በፍርድ ስርዓቱ ሂደት እና መዛባት ላይ ማተኮርን መርጠዋል፡፡

ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ደርግ ሰዎችን ሲያሰቃይበት የነበረውን ማዕከላዊ የተባለውን ማጎሪያ ሙዚየም ልናደርገው ነው ሲሉ ማዕከላዊን የሲኦል ቅርንጫፍ በማድረጉ በኩል እሳቸው አቤት ወዴት የሚሉለት ስርዓት የባሰው እንደሆነ እኛ ቂልነታችን የተረጋገጠ ህዝቦች አናውቅም፡፡ ለመሆኑ በዚች ሃገር ሰው የሚሰቃየው ማዕከላዊ ብቻ ነው?የነገሩ ስር ያለውስ በማዕከላዊ ሙዚየም መሆን አለመሆን ነው በስርዓቱ ኢሰብዓዊ ጨካኝ ተፈጥሮ?በደብረዘይት፣ በሸዋሮቢት፣ በቂሊንጦ፣ በዝዋይ ቀርቶ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሳይቀር ሰው እየታሰረ ቁም ስቅል እንደሚያይ የአይን ምስክሮች አልገለፁም? ጠላቱን በማሰቃየት የሚደሰት ሥርዓት ማዕከላዊ ስለተዘጋ የማሰቃያ መቼት አጥቶ ያነደደውን የበቀል እሳት ሊያጠፋ መሆኑ ነው? ማዕከላዊን ለግፍ ይጠቀምበት የነበረው ደርግ ብቻ ከሆነ ለምን እስካሬ አልዘጉትም? ከሃያ ስድስት አመት በኋላ ምን መጣ? ዛሬ ተቀይረው ነው ብለን በቅንነት እንዳንቀበል እልፍ ማድበስበሳቸው፣ሽህ ማስመሰላቸው ያለመቀየራቸው ምስክር ነው! እንዲህ ባለው ማድበስበስ እና ጨፍኑ ላሙኛችሁ ውስጥ ሃገራዊ መግባባት ቀርቶ ግለሰባዊ መደማመጥ ሊመጣ አይችልም፡፡መለወጥ ከመፀፀት ይጀምራል፡፡ መፀፀት ደግሞ ስህተትን ጠብሰቅ ረገጥ አድርጎ ማመንን ይጠይቃል ፡፡

አቶ ኃ/ማርያም ምናልባት ደርግ ከወደቀ በኋላ ማዕከላዊ ውስጥ የሚመረመር ሰው ለስላሳ ሙዚቃ ተከፍቶለት ነው ተብለው ይህንንም አምነው ይሆናል፡፡ እኛ ግን ስለማዕከላዊ በእዛው የግፍ ጊቢ ውስጥ ፍዳ መከራቸውን ከቆጠሩ፣ዘራቸውን መተካት ቀርቶ ሱሪ መታጠቅ እንዳይችሉ ተደርገው ግልድም አገልድመው ፍርድቤት የቀረቡ፣የበደላቸው ብዛት ሃፍረታቸውን አስረስቷቸው ልብሳቸውን አውልቀው በወንድነታቸው ላይ የደረሰውን በደል ለህዝብ ሲሳዩ አይተን ሰምተናልና በኃ/ማርያም ቀልድ የምንስቅበት ጥርስ የለንም! ማዕከላዊን ለሰይጣናዊ ጭካኔው የሚጠቀምበት ደርግ ብቻ ከሆነ ዛሬ የእነ ንግስት ይርጋን አስር የእግር ጥፍር ነቅሎ በፌስታል እነሆ የሚለው ማነው ነው? ማዕከላዊ ሰው በእግሩ ገብቶ በቃሬዛ የሚወጣበት፣መነኩሴ ቆቡ ወልቆ ቱታ እንዲለብስ የሚገደድበት፣የሰው ልጅ እንደ ክርስቶስ የሚሰቀልበት የዝነኛ አረመኔዎች አምባ መሆኑን አላውቅም የሚል ካለ ሆዱ እና ጭንቅላቱ የተቀያየረበት የስልጣን አምላኪ ብቻ ነው! ይህን ለማድበስበስ መሞከር በራስ ላይ እሳት ማንደድ ነው! ስህተትን ማድበስበስ እና ማስቀየስ ሳይታረሙ የመሞት ምልክቶች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የማንን መጨረሻ እንደሚያከፋ ይታያል፡፡

ሌላው ግልፅ ማድበስበስ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ለዓመታት ከኖረበት ቀየው በማንነቱ ብቻ ተፈናቅሎ ሜዳላይ የተሰጣበትን ወንጀል ሃላፊነት የሚወስድ ማን እንደሆነ የተቀመጠበት መንገድ ነው፡፡ የዚህን ትልቅ ወንጀል ሃላፊነት የሚወስዱት መናፍስት ይሁኑ ሰው ማይታወቁ ኪራይ ሰብሳቢዎች እና ኮንትሮባንዲስቶች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ይህን የሚሉት ለህዝብ አሳቢ ተደርገው ድቤ እየተመታላቸው ያሉት አቶ ለማ መገርሳ መሆናቸው ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የወልቃይት ጉዳይ በዝምታ መታለፉ ደግሞ የብአዴንን የቁም ሞት ብቻ ሳይሆን የህወሃትን የልቡን ሳይሰራ የማይተኛ፣የሁልጊዜ አሸናፊነት ያስገነዝባል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚመጣውን መዘዝ መመለሱ አድበስብሶ እንደማለፉ የሚቀል ከሆነ የምናየው ይሆናል፡፡

ኢህአዴግ በማብራሪያው የተቃውሞ ፖለቲካውን ስላሽመደመደበት እኩይ ስራው ያስቀመጠው ማብራሪያ ከማድበስበስም በላይ ነው፡፡ የተቃውሞ ጎራውን እግር በእግር እየተከታለ ቋንጃውን ሲቆርጥ የኖረው ባለጠመንጃው ኢህአዴግ ‘ለተቃውሞ ፖለቲካው ድጋፍ ባለማድረጌ ፀፅቶኛል፤ ይህንንም ያለ ሃፍረት መክሬበታለሁ’ ሲል የሰራው ስራ አሳፋሪ መሆኑን ልቦናው እንዳወቀ ያሳብቃል፡፡ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች እግር ሲያወጡ ጠብቄ እግር እቆርጣለሁ ከማለት በገንዘባቸው የሆቴል አዳራሽ ተከራይተው እንኳን እንዳይመክሩ እስከማድረግ የደረሰ፣ በመጨረሻም ለመደራደር ስምንት ወር የሚደራደሩ ምንደኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አዝሎ የቀረ እኩያ አልቦ አምባገነን ፓርቲ እንደሆነ ቤት ቀርቶ ጎረቤት ያወቀው ሃቅ ነው፡፡

የተቃውሞውን ጎራ በጠመንጃ እና በእስርቤት ታግዞ ፀጥ ካደረገ በኋላ አውራ ፓርቲ ነኝ ሲል የኖረው ኢህአዴግ ዛሬ ብድግ ብሎ የተቃውሞ ፖለቲካውን ባለማገዜ አዝናለሁ ማለቱ ቀልድ ይሁን ቁምነገር ውሎ አድሮ ይለያል፡፡ ያለምንም ይሉኝታ ምርጫ ቦርድን ሳይቀር ተጠቅሞ፣ፍርድቤቶችን አስከትሎ፣ወታደሩን አሰማርቶ፣ይሁዳዎች አስርጎ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዳልነበረ ማድረግ የተቃውሞ ፖለቲካውን ማውደም ሳይሆን አለማገዝ ብቻ ሆኖ የቀረበበት መንገድ ለነገሩ ቀልድነት ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡

መካድ

ከግምገማው መልስ ሃገራችን የምትገኝበት ችግር ሁሉ መንስኤ በፓርቲችን አባል ፓርቲዎች መሃከል የሚደረገው መርህ አልቦ ግንኑነት ነው እንጅ አስተዳደራችን ለእኩልነት የተመቼ የማንም የበላይነት የሌለው ነው ይላሉ ክህደት መድህን የሚመስላቸው የኢህአዴግ መሪዎች፡፡ የባሰውን ያመጡት አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ “የኢትዮጵያ ህዝብ እያለ ያለው ተስተካከሉና እናንተው አስተዳድሩን ነው” ሲሉ ወፍራም ክህደት ይክዳሉ፡፡“ዳውን ዳውን ወያኔ!” የሚለው በየሰላማዊ ሰልፉ የማይጠፋው ጥያቄ እንዴት ሆኖ ተስተካክላችሁ ግዙን ተብሎ እንደተተረጎመ ካድሬ ያልሆነ ሰው ሊገባው አይችልም፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ ወገብ ያጎበጠው የዲሞክራሲ እጦት፣የእኩልነት ጥማት፣ የመተንፈሻ መድረክ ማጣት ቀንበር፣የድህነት መንሰራፋት፣የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የሙሰኛ ባለስልጣናት በስልጣን መባለግ፣ የፍርሃት ቆፈን ሁሉ ወደጎን ተጣለና ዋኛው የሃገሪቱ ችግር የኢህአዴግ አባል ፓርቲ የላይኛው አመራር ከቀድሞ አሽከርነቱ መጉደሉ ተደርጎ ቀረበ፡፡ ይህ የሚያሳየው ህወሃት ኢህአዴግን ችግር መስሎ የሚታየው የራሱን ስልጣን ሊያሳጣ የሚችል ችግር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እንደ ጉድ የተወራው የግንባሩ አባል ፓርቲዎች የጎንዮሽ ልፊያ ፈፅሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር አይደለም፡፡ችግር ከሆነ ችግር የሚሆነው በአሽከር ካድሬዎች አድሮ ኢትዮጵያን ሲዘውር ለኖረው እና ታማኝ አሽከሮቹ ቀን አይተው ላንጓጠጡት ህወሃት ብቻ ነው፡፡በዚህ ከቀጠልን በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በሌላም መታኮሳችን አይቀርም የሚለው የዶ/ር ደብረፂዮን ንግግር የዚህ ምስክር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የስርዓት ለውጥ፤የእኩልነት ጥማት፣የሃገር ባለቤትነት፣የሰብዓዊ ክብር አምሮት ነው እንጅ የህወሃት በኦህዴድ ላይ መግነን ወይም የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የቀድሞ ግርማ መሸራረፍ አይደለም፡፡በነዚህ እውነተኛ የህዝብ ጥያቄዎች ዙሪያ ያላጠነጠነ የክህደት መንገድ ለራስ እንጅ ለህዝብ ጥያቄ መልስ አይሆንም!

የመግለጫ/ማብራሪያው አያዎ

ኢህአዴግ ታላላቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አስተላለፍኩበት ሲል ብዙ ያለለት መግለጫም ሆነ ማብራሪያ ልብ ላለው በተቃርኖዎች የተሞላ ነው፡፡ የተቃርኖውን አሃዱ ሲል ኢህአዴግ የመሰረተው ስርዓት ማንንም የበላይ ማንንም የበታች የማያደርግ የእኩልነት ዓለም እንደሆነ በመግለጫው የወተወተው ተረስቶ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ አፈና በመኖሩ የተለየ ሃሳብ ማንፀባረቅ ስላልተቻለ በፓርቲው ውስጥ ዲሞክራሲ ሊቀጭጭ ቻለ ሚል ነገር በአራቱም አመራሮች አብዝቶ ተነገረ፡፡ያለ ፍርሃት መናገር ባለመቻሉ ደግሞ በእህት ፓርቲዎች ውስጥ አለመተማመን እና ጥርጣሬ ነገሰ፤የሰፈነው አለመተማመን እና ጥርጣሬ ደግሞ እስከመታኮስ ሊያደርስ እንደሚችል ነው የተብራራው፡፡እንደተባለው ፓርቲው የበላይ እና የበታች የሌለው የእኩልነት ቤት ከሆነ የተለየ ሃሳብ እንዳይነገር የሚያፍነው ማን ነው? አፈና እና አፋኝ ካለ አፋኙ የበላይ ታፋኙ የበታች መሆኑ ያነጋግራል? አፈና ባለበት እኩልነት ከወዴት ይመጣል?የበላይ የበታች ካልኖረ ማን ማንን ነው የሚፈራው? ምን እንዳይመጣ ነው ጥርጣሬው?

ሌላው አያዎ በአቶ ለማ መገርሳ ተነገረው የኢትዮጵያዊነት ጭነት ጉዳይ ነው፡፡ አባይን ተሻግረው “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው” ሲሉ የባጁት ኦቦ ለማ ከዶ/ር ደብረፅዮን ጋር በተሰየሙበት መድረክ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በብሄር ብሄረሰቦች ላይ የተጫነ ጭነት በመሆኑ በጎሳ ፌደራሊዝሙ በኩል ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን ያስተዳድሩ ዘንድ ግድ እንደሆነ ፈርጠም ብለው ይገልፃሉ፡፡ ወዲያው ደግሞ ማንኛውም የግንባራቸው እርምጃ ሃገራዊ አንድነትን ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ፣የሃገርን ህልውና ያስቀደመ መሆን እንደሚገባው ጠንከር አድርገው ይናገራሉ፡፡ በግድ የተጫነ ላሉት ኢትዮጵያዊነት ህልውና ይህን ያህል ማሳሰቢያ ማብዛታቸው ግራ ነው፡፡

ሌላው የአቶ ለማ ግራ አጋቢ ንግግር በስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ውጤት መርካታቸውን የገለፁበት ነገር ነው፡፡በአራቱ ድርጅቶች መግለጫ ላይ በተሻለ ድፍረት እውነትን ለመግለፅ ሲጣጣሩ የዋሉት አቶ ለማ ብዙ ጭጋግ በወረሰው የግንባራቸውን የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ውጤት ለመርካት መቸኮላቸው የውድ ይሁን የግድ ራሳቸው ያውቃሉ፡፡አቶ ደመቀ መኮንን ስለ ህወሃት የበላይነት አለመኖር እየተናገሩ ይህን የሚያስጠረጥሩ አንዳንድ መንጠላጠያዎች ግን መኖራቸውን የደሰኮሩት የአሽከርነት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነገር ቢሆንም ምንም በሌለበት መንጠላጠያ ከየት መጣ ማስባሉ አይቀርም፡፡ አቶ ደመቀ አንዳንድ መንጠላጠያዎች ሲሉ ሊያሳንሱት የሞከሩት በውትድርናው፣በደህንነቱ፣በውጭግንኙነቱ፣በውጭ ንግዱ፣በኢፈርት ግዝፈት፣በየፌደራል መስሪያቤቱ የአድራጊ ፈጣሪ ስብጥር፣በአዲስ አበባ ሁለመና የሚገለፀውን ለአደግዳጊ ብቻ የማይከሰተውን የገዘፈሃቅ ነው፡፡በዚህ ረገድ አይናቸውን በጨው አጥበው ከተናገሩት አቶ ደመቀ ይልቅ “ህወሃት የበላይ አይደለም የምንለውን ሁሉም ሰሚ እንደማያምነን እናውቃለን” ያሉት አቶ ኃ/ማርያም ይሻላሉ፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በእህት ድርጅቶቹ በኩል ያለውን ችግር በመፍታቱ ለሁሉ መፍትሄ ያመጣ፣በውስጠፓርቲው ቀርቶ ለተቃዋሚዎ ፓርቲዎች የመጫወቻ ሜዳውን በመክፈት ዲሞክራሲን የማስፋት ስራ እንዲሰራና ሃገራዊ መግባባት እንዲመጣ በማድረግ ሃገራችን ላለችበት ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄን የሚያመጣ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ይህ በሚነገርበት ወቅት ግን ከፖለቲካዊ መፍትሄ ጋር ግንኙነት በሌለው ሁኔታ መለዮለባሾችን ያጨቀ በአቶ ሲራጅ ፈጌሳ እና በአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የሚመራ፣በክልል ፕሬዚደንቶች የታጀበ የብሄራዊ ፀጥታ ምክርቤት ስብሰባ ይከወናል፡፡ ይህ የፀጥታ ምክርቤት ፋኖ በየክልሉ አሰማርቶ የሃገሪቱን ፀጥታ በክላሽ በታጀበ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ግብረሃይል ነው፡፡ ይህ ግብረሃይል ከተዋቀረ አንድ ወር አስቆጥሯል፤ከሰሞኑም የየክልል ፕሬዚደንቶችን ጨምሮ ለስብሰባ ተሰይሟል፡፡በዚህ ውስጥ ጉልበት እንጅ ፖለቲካዊ መፍትሄ አይታይም፡፡ እውን ኢህአዴግ ለሃገራችን ወቅታዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ቢሰጥ ኖሮ የክልሎችን ፀጥታ ለማስጠበቅ የክልል ፖሊስ በቂ ነበር፡፡

ብሄራዊ የፀጥታ ምክርቤቱ ፀጥ የማድረግ ስራውን ለመከወን ወደ ክልሎች ሲወርድ የክልሎች የሲቪል አስተዳደር ተሸመድምዶ ለዚሁ ወታደራዊ ጫማ እጅ አለመስጠቱን፣ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር በሃገሪቱ ስለአለመስፈኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ሃገርን የማረጋጋቱ ስራ በወታደራዊ ጡንቻ ታገዘ ማለት የደህንነት እና ወታደራዊ ክንፉን የሚዘውረው ህወሃት የተለመደ ግዝፍናውን አገኘ ማለት ነው፡፡ይህ ማለት ደግሞ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ምክርቤት ስብሰባ ብዙ የተወራለት የግንባሩ እህት ድርጅቶች ነፃነት፣ራስን በራስ የማስተዳደር ነገር ውሃ በላው ማለት ነው፡፡

“ወደህ በገባህ አትከራከር!”

አስራሰባት አመት መታገሉን የጌትነቱ ሰገነት ያደረገው ህወሃት በኢህአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ አጋርም ሆነ አባል ብሎ የሰየማቸው ፓርቲዎች ውልደት እድገታቸው ህወሃት በደሙ በላቡ በፃፈው “ደማቅ ታሪክ” እንደሆነ አምነው የተጠመቁ፣ይህንኑ የቤቱን ህግ አክብረው ሊኖሩ ወደው የገቡ የድሮ የጠመንጃ ገድል ምርኮኞች ናቸው፡፡ ይህን በተግባርም በቃልም ከማስገንዘብ የማይቦዝነው ህወሃት ከአንድ ትግሬ አባወራ ቤት ስንት ሰው ሞቶ በአጠቃላይ ስልሳ ሽህ ትግሬ ተሰውቶ አዲስ አበባ እንደ ተደረሰ ለወዶ ገቦቹም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለመተረክ ደክሞት አይውቅም፡፡ ህወሃት ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ስልሳ ሽህ ምክንያት እንዳለው በቅርቡ በትግራይ ኦንላይን ላይ ተፅፎ አንብበናል፡፡
በኢህአዴግ ቤት ተቀምጦ የህወሃት እበልጣለሁባይት አስቸገረኝ፣ቡድንተኞች አሰማራብኝ፣ዘመዶቹ ይበልጥ ቤተኛ ነን አሉኝ፣ እኔ ሳላውቅ በክልሌ ወታደር ልከው አስተኮሱብኝ የሚለውን ክስ የሚያቀርብ ባለሟል ይሳቅበት ይሆናል እንጅ አይታዘንለትም፡፡የተለመደውን፣ወደው የገቡበትን፣የቤቱን ዋነኛ ደንብ ዛሬ ከሰማይ ዱብ ያለ በደል አድርጎ ማውራት ትርጉም የለውም፡፡

ጥያቄያቸው እና ጥያቄያችን ….

ኢህአዴግ ብዙ ችግሬን አየሁበት መፍትሄም አስቀመጥኩበት ባለበት የሰሞኑ የስራ አሰፈፃሚ ስብሰባው አንገብጋቢ አድርጎ ያነሳው ጉዳይ ሲጠቃለል ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በግንባሩ ውስጥ የቀድሞ ሞገሱን ማጣቱ፣የአባል ፓርቲዎች ቋንቋ መደበላለቅ፣ከቀድሞ አቤት ወዴት ባይነታቸው መጉደል፣የውሰጠ ፓርቲ ደሞክራሲአለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ የራሱን የቤት ጣጣ ነው እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ችግር ተደርጎ የቀረበው የግንባሩ ፓርቲዎች የቋንቋ መደበላለቅ፣ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ክንድ መዛል ለኢትዮጵያ ህዝብ ደስታ እንጅ ሃዘን አይደለም፡፡
የኢትየጵያ ህዝብ የሚፈልገው ዲሞክራሲ እነ አቶ ለማ/ደመቀ የሚናፍቁት ከኢህአዴግ ውስጠ ፓርቲ ተነስቶ፣በሊጎች እና ክንፎች ዞሮ ህዝብ ጋ የሚደርስ፣ በዲሚክራሲያዊ ማዕከላዊነት የተቀፈደደ አይነት ዲሞክራሲ አይደለም፡፡ስለሆነም ኢትየጵያህዝም ጥያቄ ከኦህዴድም ሆነ ከብአዴን ጥያቄ ጋር አይገጥምም፡፡ኢህአዴግ የሚወተውተው የተለውጫለሁ ጋጋታም ከሚፈለገው ለውጥ ርቆ የቆመ ማስመሰሉ የበዛ፣ ይጨብጡት ዘንድ ህልውና የሌለው፣እስረኛ እፈታለሁ ከሚለው በስተቀር ሌላ የሚጨበጥ ቁምነገር የሌለው ነገር ነው፡፡ እስረኛ እፈታለሁ የሚለውም የባቡር ሃዲድ ስለሰራሁ፣አባይን ስለገደብኩ ስልጣ ላይ ልቀመጥ የሚለው የተለመደ ስልጣን ላይ ለመሰንበት የሚጠየቅ የዋስትና ማረጋገጫ ከመሆን አይዘልም፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

___
በዚህ ድረ ገጽ ነጻ አስተያየት ወይ ሃሳብ ለማካፈል ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here